አሁን ካለንበት እውነታ አንፃር ዓለማችን በአብላጫው የምትመራው ዕውቀትንና ክህሎትን መሠረት ባደረጉ አሠራሮች መሆኑ ይታወቃል፡፡ እየመጣ ያለው አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮትም ዕውቀትንና ክህሎትን መሠረት በማድረግ በሚፈጠሩ ቴክኖሎጂዎች ምክንያት የሕዝቦችን አኗኗርና አሠራር እንዲሁም የአገሮችን ተወዳዳሪነት ወሳኝ በሆነ መልኩ እንደሚወስን ይጠበቃል፡፡ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዚህ አዲስ የአኗኗርና የውድድር ዘመን ውጤታማና ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው ሰፊ መሠረት ያለው ቴክኖሎጂዎችን የሚፈጥር፣ አሠራሮችን የሚያዘምንና መጪውን ጊዜ ታሳቢ በማድረግ መምራት የሚችል የሰው ሀብት ማልማት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የ‹ታለንት› ልማት ለመንግሥት ወይም ለተወሰኑ ድርጅቶች የሚተው ጉዳይ ሳይሆን የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጠንካራ ተሳትፎ ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ‹‹አሶሴሽን ፎር ታለንት ዴቨሎፕመንት በኢትዮጵያ›› ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር) የአሶሴሽኑ ቦርድ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ በታለንት ልማት፣ በአሶሴሽኑና ተጓዳኝ በሆኑ ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ሰብሳቢውን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡– አሶሴሽኑ ታለንትን እንዴት ነው የሚረዳው?
ዶ/ር ገመቹ፡- ታለንት አሁን ባለው አጠቃቀምና እኛ በምናስበው መልኩ ልግለጸው፡፡ በአንድ አገር ሕዝብ ይኖራል፡፡ ሁሉም ሕዝብ ግን ምርታማ ወይም አምራች፣ ለውጥ አምጪና አገሪቱን ወደ ዕድገት ያሻግራል ማለት አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ታለንት የሚለውን ባጠቃቀም ደረጃ ካየነው ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ድርጅቶችን ወደ ውጤታማነት የሚያደርሱ፣ አገርን መቀየር፣ መምራትና ወደፊት ማምጣት የሚችሉ ማለት ነው፡፡ ታለንት በአጠቃላይ የሰው ሀብትን ነው የሚመለከተው፡፡ በዚህች አገር ተፅዕኖ የሚፈጥሩ፣ ለውጥ የሚያመጡ፣ አገርንም ተቋማትንም ወደሚፈለገው ደረጃ ማድረስ የሚችሉትን ታለንት ብለን ልንወስዳቸው እንችላለን፡፡ ከዚህም ሌላ የሰው ሀብት ወይም አቅም ያለውና ብቁ የሆነ የሰው ሀብት ተብሎ ቢወሰድም ስህተት አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡– ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ሥራ እየፈለጉ ነገር ግን ያላገኙ ብዙ ሰዎች እያሉ፣ ድርጅቶች ወይም ተቋማት ገበያ ውስጥ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል እያገኘን አይደለም ይላሉ፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?
ዶ/ር ገመቹ፡- በአገራችን ብሎም በዓለማችን ላይ ምን እየተካሄደ ነው? የሚለው ሲታይ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ኃይል ብዛት ችግር የለብንም፡፡ እስከ 120 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ አለን፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሁሉም የአገሪቱን አቅም መቀየር የሚችል አቅም አለው ለማለት አይቻልም፡፡ በገበያ ውስጥም የተጠቀሰውን አቅም ያላቸው ሰዎችም ብዙ አይደሉም፡፡ ይህ በምን ይገለጻል ቢባል የባንክን ወይም የፋይናንስ ዘርፍ ብቻ ብንመለከት አቅም ያላቸውን ባለሙያዎችን የመነጣጠቅ ሁኔታ ይታይበታል፡፡ ይህም የሆነው ሠራተኛ ስለጠፋ ሳይሆን ብቃት ያለው ሠራተኛ በብዛት ከማጣት የተነሳ ነው፡፡ ብቃት ያለው ባለሙያ ከገበያ ወስጥ ከሌለ ታለንት ወደ መነጣጠቅ እየገባን ነው፡፡ ምክንያቱም አዲስ የሚቋቋሙት ባንኮች በዋናነት ተማምነው የሚመሠርቱት አዲስ የሚያለሙትን የሰው ኃይል በመያዝ ሳይሆን አሁን በሥራ ላይ ያሉትን ነው የሚቀሙት፡፡ በሥራ ላይ ያሉት እየተናጠቁ የሚወስዱ ከሆነ ሌላው ድርጅት ያለማውን የሰው ኃይል ወደ መቀማማት ነው የሚተኮረው፡፡
ሪፖርተር፡– በገበያ ውስጥ ጥሩ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስፈልጉ መሠረቶችን በተመለከተ ዘርዘር አድርገው ቢገልጹልንና እግረ መንገድዎትንም ለአሶሴሽኑ መቋቋም ያነሳሳችሁ ምክንያትን ጭምር ቢያብራሩልን?
ዶ/ር ገመቹ፡- የአሶሴሽኑ መቋቋም ለምን አስፈለገ የሚለውን ከመመለሴ በፊት ታለንት የመወዳደሪያ ቁልፍ የሆነ ሚና እንዳለው ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ በመሠረቱ ዓለማችን የሚመራው በውድድር ነው፡፡ ለውድድሩ ደግሞ በርካታ መሠረቶች እንደሚያስፈልጉት መገንዘብ ይገባል፡፡ ከሚያስፈልጉትም መሠረቶች መካከል ፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂና የሰው ሀብት የመሳሰሉ ይገኙበታል፡፡ ቴክኖሎጂ ግን በአሁኑ ጊዜ ፋይናንስ ያለው ማንም ሰው የሚገዛው ሆኗል፡፡ ይህም ማለት አንደኛው ተቋም የገዛውን ቴክኖሎጂ ሌላኛውም መግዛት ይችላል፡፡ በዚህም የተነሳ መወዳደሪያዬን ልዩ የሚያደርገው ምናምን ማለት ይከብዳል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ብዙ የፋይናንስ አቅም ኖሯቸው የሚሠሩትን በአግባቡ የማያከናውኑና መወዳደርም ያቃታቸው ብዙ ድርጅቶች እንዳሉ፣ በአንፃሩ ደግሞ መፍጠርና መምራት የሚችል አቅም ያላቸው ድርጅቶች አሸናፊ እየሆኑ እንደመጡ እናውቃለን፡፡ ከዚህም መረዳት የሚቻለው ነገር ቢኖር ታለንት የመወዳደሪያ ቁልፍ የሆነ ሚና መጫወቱን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሁሉም ድርጅቶች የተሻለ የሰው ኃይል መፈለግ ግድ ሆነባቸው፡፡ የተሻለ የሰው ሀብት ሲባልም በተሻለ ሁኔታ መምራት የሚችል፣ አካባቢውንና ወደፊት የሚመጣውን የሚረዳ፣ አዳዲስ የአሠራር አገልግሎቶችን የሚያመጣ፣ የተገኘውን ቴክኖሎጂ በደንብ አድርጎ መጠቀም የሚችል ማለት ነው፡፡ ተቋማቱም በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀሱን ተያያዙት፡፡ ይህ ዓይነቱም እንቅስቃሴ የሠለጠነ የሰው ኃይልን ወደ መሻማት ያተኮረ በር ከፋች ሆነ፡፡ ይህም ሁኔታ የአሶሴሽን ታለንት ፎር ዴቨሎፕመንት ኢን ኢትዮጵያ›› ለመመሥረት መንስዔ ሆነ፡፡
ሪፖርተር፡– ታለንት በኢትዮጵያ ውስጥ ያስከተለውን መልካም አጋጣሚና ሥጋት እንዴት ይገመግሙታል?
ዶ/ር ገመቹ፡- ታለንት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሀብት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ቁጭ ብሎ ለአሜሪካ ካምፓኒ መቀጠር ይችላል፡፡ ከዚህም ሌላ የመካከለኛው ምሥራቅ የሥራ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ የተማረ፣ ብቃትና አቅም ያለው ሠራተኛ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ጀርመን ወዘተ ሊቀጠር ይችላል፡፡ እነዚህ አገሮች ጥሩ ጥሩ ሰዎችን እይሰበሰቡና ዴሞግራፊያቸው እየተቀየረ ነው፡፡ ይህም ብዙ የሰው ሀብት እንዲፈልጉ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም በዓለም የታለንት ጦርነት እየተከሰተ ነው (ግሎባል ታለንት ዎር ኢን ኤ ሜኪንግ)፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ በኢትዮጵያ ሁለት ነገሮች እንዲታዩ ያደርጋል፡፡ አንደኛው መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ታለንትን ለሌሎች አገሮች በማቅረብ ገቢ የማግኘት ዕድል፣ ሁለተኛው ደግሞ ይኼንን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም ካልቻልን ‹‹ብሬንድሬን›› ወደሚለው ጽንሰ ሐሳብ ይወስደናል፡፡ ወይም መልካም አጋጣሚ መሆኑ ይቀርና ጥፋትም ሥጋትም ይሆንብናል፡፡ ምክንያቱም በቂ የፍላጎት አቅርቦት ስለሌለ ካለው ላይ ነው የሚወስዱብን፡፡ ከዚህ አንፃር ታለንትን በስፋት ካለምነው ሊያስጨንቀን አይችልም፡፡
ሪፖርተር፡– መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2030 20 ሚሊዮን ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይናገራል፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
ዶ/ር ገመቹ፡- ችግሩ ሥራ መፍጠር ሳይሆን ሥራን በአግባቡ መከወን የሚችሉ አልምተናል ወይ? የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ሥራው ተፈጥሮ ኢኮኖሚው ላይ ወይም አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት (ጂዲፒ) ላይ አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ ለሌሎችም ብዙ ሥራ መፍጠርና ደንበኞችን በደንብ ማስተናገድ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ ብዙ አገሮች ሰው ላይ ሠርተው ነው ለውጥ ያመጡት፡፡ ከዚህ አኳያ በእኛም አገር በዚህ መልክ መሠራት ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ‹‹ናሽናል ስኪል ፕላንኒነግ›› የሚል ጥናት ከሥራ ዕድልና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር አዘጋጅተን ብዙ ውጤትም ተገኝቶበታል፡፡ ውጤቱም በየጊዜው እየተተገበረ ይሄዳል ብለን እናምናለን፡፡ በዚህም ጥናት ላይ ሌላ ያየነው ነገር ቢኖር ታለንት ገበያ ውስጥ ጤናማ የሆነ ፍላጎትን የሚመራ መሆኑ ነው፡፡ አቅርቦት የሚወስነው ዓለም አቀፉ ገበያ ምን ይፈልጋል? ከሚል ጥያቄ በመነሳት ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ከኢትዮጵያ አኳኋን ሲታይ ግን በግልባጭ ነው፡፡ ይህም ማለት ሌበር በፍላጎት ሳይሆን እየተመራ ያለው በአቅርቦት ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የሌበር ማርኬት (የሰው ኃይል ገበያ) አመራር በፍላጎት መመራት ሲገባው በአቅርቦት ነው አየተመራ ያለው፡፡ ፍላጎት እስካልመራው ድረስ አይስተካከልም፡፡ ይህንንም ማድረግ የሚችል ሲስተም፣ ፖሊሲና አሠራር መተግበር አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል፡፡