Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየዓለም ምግብ ዋስትና ላይ ሥጋት የጣለው የጥቁር ባህር ዳግም መዘጋት

የዓለም ምግብ ዋስትና ላይ ሥጋት የጣለው የጥቁር ባህር ዳግም መዘጋት

ቀን:

የምግብ እህል በጥቁር ባህር እንዲያልፍ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ያደረገችውን ስምምነት ሻረች፡፡ በጥቁር ባህር ላይ ከዩክሬን እህል ተጭኖ እንዳይወጣም አግዳለች፡፡

ዓመት ሊሞላው አራት ወራት ያህል የቀረው የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት፣ ዓለምን በተለይም በማደግ ላይ ያሉትንና አብዛኛውን የስንዴ፣ የበቆሎና የቅባት እህል የፍላጎታቸውን ከሁለቱ አገሮች ለሚያስገቡ አገሮች ፈተና ሆኗል፡፡ የጦርነቱ መዘዝ አሜሪካን፣ አውሮፓንም ሆነ አፍሪካን በምግብ ዋጋ ንረት ፈትኗል፡፡

ጦርነቱ ከሁለቱ አገሮች አልፎ የሌሎችም የምግብ ዋስትና እንቅፋት ሆኗል፡፡ አገሮች ብቻ ሳይሆኑ የሰብል ምርት ከዩክሬን ገዝተው በድርቅና በረሃብ ለተጎዱ ሕዝቦች ዕርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶችም መቸገራችን ሲገልጹም ከርመዋል፡፡

በዩክሬን የተከማቹና በጦርነቱ ምክንያት መውጣት ያልቻሉ የሰብል ምርቶች በጥቁር ባህር እንዲጓጓዙ ለማስቻልና በዓለም ላይ የተከሰተውን የምግብ እጥረት ለመቀልበስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የግብርና ውጤቶች፣  ቱርክና አሸማጋይነት ሩሲያ የጥቁር ባህር ኮሪደርን ለዩክሬን የሰብል ምርት ክፍት እንድታደርግ ከስምምነት ተደርሶም ነበር፡፡

በተመድና በቱርክ አግባቢነት በሐምሌ 2014 ዓ.ም. የተደረሰው ስምምነት፣ ዩክሬን በጥቁር ባህር የግብርና ምርቶቿን ለዓለም ገበያ እንድትልክ አስችሎ የነበረ ቢሆንም፣ ቅዳሜ ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ሩሲያ በጥቁር ባህር የሚላኩ የዩክሬን የግብርና ምርቶች እንዳያልፉ አግዳለች፣ ከተደረሰው ስምምነት መውጣቷንም አስታውቃለች፡፡

ቢቢሲ እንደሚለው፣ ‹‹ሩሲያ ከስምምነቱ የወጣችው ዩክሬን ክፍት የሆነውን የጥቁር ባህር ኮሪደር ተጠቅማ መርከቦቼ ላይ ጥቃት ፈጽማለች›› በሚል ነው፡፡

ዩክሬን ለጥቃቱ ኃላፊነት አልወሰደችም፡፡ ተመድ ግን በበኩሉ፣ ‹‹በወቅቱ በጥቁር ባህር የዩክሬን ምርት መተላለፊያ ኮሪደር ላይ ምንም ዓይነት መርከብ አልነበረም›› ሲል ገልጿል፡፡

ሰብልን ጨምሮ 354,500 ቶን የግብርና ምርቶችን የያዙ 12 መርከቦች ከዩክሬን ጥቁር ባህር ወደቦች የተነሱት ከሳምንት በፊት እንደነበር የዩክሬን መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ይህ ስምምነቱ ከተደረገ በኋላ ጥልቅ መጠን ያለው የግብርና ምርት ነበር፡፡

በሩሲያና በዩክሬን መካከል በየካቲት 2014 ዓ.ም. ጦርነት በመጀመሩ የዩክሬን ጥቁር ባህር ወደቦች ከተዘጉ በኋላ፣ የሱፍ ዘይት፣ የበቆሎና የሰብል ምርቶችን ጨምሮ 20 ሚሊዮን ቶን ያህል ምግብ ወደ ውጭ መላክ አልተቻለም ነበር፡፡

ሆኖም ሐምሌ 2014 ዓ.ም. ላይ ሩሲያና ዩክሬን በቱርክና በተመድ አወያይነት በጥቁር ባህር ወደብ የግብርና ምርቶች እንዲያልፉ በመስማማታቸው፣ የዕርዳታ ድርጅቶችም ሆኑ አገሮች ምርቶችን ማግኘት ችለው ነበር፡፡

ከቀናት በፊት ደግሞ ዕገዳውን የጣሉት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንደሚደሉት፣ በክራይሚያ በሚገኙ የሩሲያ መርከቦች ላይ በርካታ የድሮን ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዩክሬን ኃላፊነቱን ትወስዳለች፡፡

የባህር ላይ ደኅንነቱ ባልተከበረበት ሁኔታ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ መላኩም አደጋ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ሩሲያ ከስምምነቱ ራሷን ማውጣቷን ተከትሎ ከአሜሪካ ‹‹ምግብን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም›› የሚል ውግዘት ቢገጥማትም፣ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ሩሲያ ውሳኔዋን እንድትቀለብስ ጠይቀዋል፡፡

‹‹የሰብልና የማዳበሪያ አቅርቦትን ማገድ የዓለም የምግብ ቀውስን ያባብሰዋል›› ም ብለዋል፡፡

ሩሲያና ዩክሬን በሐምሌ 2014 ዓ.ም. የደረሱበት ስምምነት ጭነት በሚጓጓዝበት ወቅት ሩሲያ ወደቦችን ዒላማ እንዳታደርግ፣ ቱርክ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ እየተደረገላት ሩሲያ ሥጋት ብላ ያነሳችውን የጦር መሣሪያ ዝውውር ለማስወገድ በመርከቦች ላይ ፍተሻና ቁጥጥር ታደርጋለች እንዲሁም ሩሲያ በጥቁር ባህር በኩል እህልና ማዳበሪያ ወደ ውጭ እንድትልክ ይመቻቻል የሚሉ ነጥቦች ይገኙበት ነበር።

ዩክሬን ዋና የሆኑ የምግብ ምርቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ የምትታወቅ ሲሆን፣ በ2019 ብቻ በዓለም ገበያ የነበራት ድርሻ የሱፍ ዘይት 42 በመቶ፣ በቆሎ 16 በመቶ፣ ገብስ 10 በመቶ እንዲሁም ስንዴ ዘጠኝ በመቶ መሆኑን የተመድ የምግብና የግብርና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...