Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዓይን መንሸዋረር ችግር ያለባቸውን ለመታደግ

የዓይን መንሸዋረር ችግር ያለባቸውን ለመታደግ

ቀን:

ኦርቢስ የዓይን መንሸዋረር ላለባቸው ሕፃናት ሕክምና ለዓይን ሐኪሞች ደግሞ ሥልጠና ሲሰጥ

ገሊላ አዳሙ ትባላለች፡፡ 14 ዓመቷ ነው። ቤተሰቦቿ የሚኖሩት በአርባ ምንጭ ከተማ ዙሪያ ሰላም በር እየተባለ በሚጠራ የገጠር ቀበሌ ነው። ገሊላን ያገኘኋት ከእናቷ ጋር በሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡ ለቤተሰቦቿ 7ኛ ልጅ ስትሆን የ5ኛ ክፍል ተማሪ ናት። እዚህ ሆስፒታል ከእናቷ ጋር የመገኘቷ ምክንያት ደግሞ ከልጅነቷ ጀምሮ የተከሰተባትን የዓይን መንሸዋረር ለመታከም ነበር።

ሕመሙ ሲጀምራት ምንም ትኩረት አልሰጡትም ነበር፡፡ የት መሄድ እንዳለባቸው ባለማወቃቸው ሕመሙ ሊብስባት እንደቻለ እናቷ ይናገራሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ሕመሙ ዓይኗን እያሳከካት፣ እያቀላውና እየባሰባት በመምጣቱ ወደ ወላይታ ሶዶ ሆስፒታል ወስደዋት ነበር፡፡ በሕክምናው ማሳከክ መቅላቱ ቢያቆምም ሸውራራነቱን ማስተካከል አልተቻለም፡፡

ይህም በትምህርት ቤትና በሰፈሯ አካባቢ ‹‹ሸውራራዋ ልጅ›› የሚል ቅፅል እንዲሰጣት አድርጓል፡፡ በዚህም ከፍተኛ የሥነ ልቦና ችግር ውስጥ በመግባቷ ትምህርት ቤት ከመሄድና ውጭ ከመውጣት በመቆጠብ ስታለቅስ በመዋሏ ሕመሙ ሊብስባት መቻሉን ጠቅስው ፀባይዋንም ሕመሙ ስለሚቀየረው ሁሌም ፀብ እንደነበርና በዚህም ቤተሰብም ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ያክላሉ፡፡

ዶክተር ሳምሶን ተስፋዬ ይባላሉ፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት በዓይን ሕክምና በተሰማራው ግብረ ሰናይ ድርጅት ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ውስጥ ከፍተኛ የፕሮግራም ኃላፊ፣ የአቅም ግንባታ፣ የሥልጠናና የምርምር ፕሮግራም ኃላፊ ናቸው፡፡

ድርጅታቸውም ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያም ከዛሬ 25 ዓመት በፊት የገባና ሕጋዊ ሰውነትንም በማግኘት ትኩረቱን በዓይን ሕክምና ላይ ብቻ በማድረግ ሥራ መጀመሩን አስታውሰዋል።

ሥራውን ሲያከናውን ከተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከክልል ጤና ተቋማት ጋር በመተባበር እንደሆነ ይገልጻሉ።

ድርጅቱ ከሚሠራቸው ሥራዎች አንዱና ዋነኛው በዓይን ሕክምና ሰብ እስፔሻሊስት መፍጠር በመሆኑ በዓይን ሕክምና ዙሪያ ያሉትን ባለሙያዎች ውጭ በመላክ፣ በማስተማርና አገር ውስጥ በሚመጡ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ባገኙ በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞች ሥልጠና በመስጠት ላይ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ከሚሠሩባቸው አምስት የሪፈራል ሆስፒታሎች ውስጥ አንዱ በሆነው በሐዋሳ ሆስፒታል የሚሰጠው ሥልጠናም፣ በሕፃናት ላይ የሚከሰተውን የዓይን መንሸዋረር ሕመም እንዴት በቀዶ ጥገና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማከም ይቻላል በሚለው ዙሪያ ነበር፡፡

ሥልጠናው የተሰጠውም ሆስፒታሉ ያስፈልጉኛል ባላቸው የሕክምና ሥራዎች ዓይነት ሲሆን፣ የሕክምና ባለሙያዎቹም ሥልጠናውን ያገኙት ዋናው ቢሮ መልምሎ ባዘጋጀው መሠረት ነው፡፡

ለሕክምናው እንዲሁም ድጋፍ ለሚደረግላቸው ታማሚዎች የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ከውጭ የመጡ ሐኪሞች ያመጡ ሲሆን፣ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ሦስት ሠልጣኞችም በዓይን መንሸዋረር ዙሪያ እያንዳንዷን ሒደት በቀጥታ በመከታተል ልምድና ትምህርት ወስደዋል።

ለተከታታይ አምስት ቀናት የቆየው ሥልጠና ለሕክምና ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ሊያስቀር እንደቻለ ዶ/ር ሳምሶን ገልጸዋል።

ሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል በኢትዮጵያ ካሉ አምስት ሪፈራል ሆስፒታሎች ውስጥ አንዱ ሲሆን ለሲዳማ፣ ደቡብ ክልል እንዲሁም ለአጎራባች ክልሎች ብቸኛው የሕፃናት የዓይን ሕክምና የሚሰጥ ማዕከል አለው። ከእነዚህ ሁሉ ሪፈር የሚደረግለትን በሺሕ የሚቆጠሩ ሕፃናትን በተመላላሽ ቀዶ ሕክምና የሚያደርግና ሕክምናና ትምህርት የሚሰጥ ዘመናዊ ሆስፒታል እንደሆነ የሆስፒታሉ የዓይን ሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር አርጋው አበራ ይገልጻሉ፡፡

የልጆቻቸውን ሕክምና በተስፋና በጉጉት ከሚጠባበቁት መካከል ለአሥር ዓመታት ሕክምና ፍለጋ ሲንከራተቱ እንደነበር የሚያነሱም አሉ፡፡ ከሩቅ የመጡ አልጋ ይዘው ሕክምናቸውን የሚጠባበቁ እንዳሉ ተመልክተናል፡፡

የሕክምና ጥሪውን ከቤተሰብ፣ ከዘመድ አዝማድ በመስማት መምጣታቸውን አንዳንዶችም ሕመሙ ከእግዚአብሔር የመጣ ነው በማለት ለመቅረት የወሰኑ እንደነበሩ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

በቅርቡ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው ጥናት በኢትዮጵያ ከአንድ መቶ ሰዎች 1.6 የሚሆኑት ዓይነ ሥውር እንደሆኑና 3.7 የሚሆኑት ደግሞ ዝቅተኛ የማየት ችግር እንዳለባቸው ይጠቁማል።

በኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት ወዳጄ እንደሚሉት፣ ድርጅታቸው በዓይን ሕክምና ዙሪያ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት ከጠብታ ጀምሮ የሕክምና ቁሳቁሶችን በማቅረብ ብቁ ባለሙያ እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ ሕክምና እንዲኖር ሠርቷል፡፡ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም አገልግሎቱን ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...