Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየአዲስ አበባ አዲሱ መለያ ‹‹አፍሪቃዊቷ መልኅቅ››

የአዲስ አበባ አዲሱ መለያ ‹‹አፍሪቃዊቷ መልኅቅ››

ቀን:

‹‹በአዲስ አበባ ከተማ የትኛውም አቅጣጫ ቢጓዙ ፓርኮችን ወይም የመንገድ ላይ ማረፊያዎችን ማየት ቅንጦት እየሆነ መጥቷል፡፡ በየንጋቱ እየበቀሉ የሚያድሩት ልዩ ልዩ ግንባታዎችም መናፈሻ የሌላቸው፣ ለፓርኪንግ ያልታደሉ፣ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ትኩረት የሌላቸው ናቸው፡፡

‹‹ነፃ የሕዝብ ቦታዎችን ማዘጋጀት የመንግሥት ግዴታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የሚሰበሰበውን የግብር እና የታክስ ገቢ ለዚህም ተግባር ቢያውል ባስመሰገነው፡፡ ከተማን ከተማ ከሚያስብሉት ያውም ደግሞ አዲስ አበባን የመሰለ የአፍሪካውያን መናኸርያ ቅጥ ባጡ የሕንፃ ጋጋታ መጣበብ የመጥቀሙን ያህል ለሕዝብ የሚመች ነፃ ሥፍራና አረንጓዴነትን የተላበሱ መናፈሻዎች ካልተቸሩት፣ ውሎ ሲያድር አያምር እንዳይሆን ትኩረት ሊቸረው የሚገባ ነው፡፡

ደግሞስ በየሳምንቱ የዕረፍት ቀናት የከተማዪቱ አንዳንድ አደባባዮች የውኃ ፏፏቴዎችን እየከፈቱ፣ እውነትም የዕረፍት፣ የመናፈሻ ቀን ቢያደርጉት ምን ይጎዳቸው ኖሯል? ይህንን የሚያወጉን ከተማውን የሚታዘቡ አዛውንቶች ሳይወዱ በግድ የካፍቴሪያና የግሮሰሪ ጓዳ ጥገኛ እንዲሆኑ መገደዳቸውን በመግለጽ ነው፡፡››

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር እነዚህን ከመናፈሻዎች ጋር የተያያዙ ዐበይት ነጥቦችን ከዐሥር ዓመታት በፊት ‹‹መናፈሻዎች የሚናፍቋት አዲስ አበባ›› በሚል ርዕስ ባወጣው ልዩ ዘገባው ላይ ያሠፈራቸው ናቸው፡፡

ያኔ አዲስ አበባውያን ለከተማው አስተዳደር ያቀርቧቸው ከነበሩት ጥያቄዎች አንዱ የመናፈሻ ዐፀድ አስፈላጊነትን ያነገበው ነበር፡፡

‹‹አፍሪቃዊቷ መልኅቅ›› የተሰኘው የአዲስ አበባ መለያ

ይህ የዓመታት ጥያቄ የነበረውና በአየር መለወጫ በመናፈሻ ሥፍራ ዕጦት ተቸግራ የነበረችው አዲስ አበባ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዚህ ረገድ በውላጤ (ትራንስፎርሜሸን) ውስጥ ትገኛለች፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ከሚገኘው የአንድነት ፓርክ እስከ ወዳጅነት ፓርክ፣ ከእንጦጦ ፓርክ እስከ ቸርችል ጎዳና፣ መስቀል አደባባይን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች አረንጓዴ አፀዶች ተመሥርተው ይታያሉ፡፡ ከሕንፃ እስከ አዋቂ የሚስተናገዱበት፣ ዘና የሚሉበት መሆኑም እየተስተዋለ ነው፡፡

አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ የማደርጉ ተግባር በቀጠለበት ተግባር ጎን ለጎንም አኅጉራዊ መዲናና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባ በቱሪዝሙ መስክም ተመራጭና ተደራሽ ለማድረግ በቅርቡ መለያ ተፈጥሮላታል፡፡ የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከሰሞኑ የከተማን መለያ (ብራንድ) ይፋ አድርጓል፡፡

ቢሮው የዘንድሮውን የዓለም ቱሪዝም ቀንን ‹‹አዲስ እሳቤ ለቱሪዝም›› በሚል መሪ ቃል በከተማ ደረጃ ሲያከብር የአዲስ አበባን የቱሪዝም ብራንድና ሎጎንም አስተዋውቋል፡፡ መለያው ‹‹አፍሪቃዊቷ መልኅቅ (The Vibrant Hub of Africa) እንደሚሰኝ ቢሮው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ገልጾታል፡፡

በክብረ ቀኑ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር ዓባይ፣ አስተዳደሩ ለቱሪዝም ዘርፉ ዕድገት በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፣ አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ለውጥ ላይ እንደምትገኝና ይህም ለከተማው የቱሪዝም ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት በከተማዋ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች የሚሆኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመሥራት የሚያስመሠግን ሥራ መሥራቱን የጠቆሙት የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ ዘርፉን ከዚህ በበለጠ ለከተማዋ ሀብት ማስገኛ ለማደረግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ መለያና ትርጉሙ

አዲሱን የአዲስ አበባ መለያ (ብራንድ) በአምስት ወራት ውስጥ የነደፉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበብና የንድፍ የግራፊክስ ዲዛይን መምህራን ኦስማን ሀሰን፣ አገኘሁ አዳነና ልዑል ሳህለ ማርያም ሲሆኑ፣ የጽሑፉ ሐሳብ መነሻን ያዘጋጁት ሠዓሊና ደራሲ አገኘሁ አዳነ ናቸው፡፡

በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ የንድፈ እሳቤ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

(ሀ) የአፍሪካ ቅርፅ:-

 የአፍሪካ ቅርፅ በብሩሽ የተሠራ ነው የሚመስለው። ብሩሹ እንቅስቃሴን ያሳየናል። በብሩሹ የተሣለው የአፍሪካ ምስል ተንቀሳቅሶ አዲስ አበባ ላይ ይገባል። ይህም ንድፍ አዲስ አበባ የአፍሪካ እምብርት መሆኗን ያመለክታል።

 (ለ) አበባው፡-

አበባው ስምንት ቅጠል ያለው አገር በቀሉ አደይ አበባ ሲሆን፣ ቅጠሎቹ አዲስ አበባን ማዕከል አድርገው ወደ ሁሉም ቦታ አቅጣጫን ያመለክታሉ፡፡ በሁሉም አቅጣጫዎች ከተማይቱ ወደ አፍሪካ ትገናኛለች ማለት ነው። አበባውም አፍሪካም ጋደድ የተደረጉት የዕይታ እንቅስቃሴን ለማመልከት ነው። በፍጥነት እየተለወጠና እየተንቀሳቀሰ ያለውን አኅጉር ያመለክቱናል። አበባው እንደ ኃይል ማመንጫ ተርባይንም ዕይታዊ እሽክርክሪት አለው። የምስሎቹ እንቅስቃሴ ዲፕሎማሲን ጨምሮ የተለያዩ ከተማችንን የሚገልጹ እንቅስቃሴዎችን የሚያመለክት ሲሆን፣ ከተማይቷ የአፍሪካ የንቃት መናኸርያና እምብርት መሆኗንም ጭምር ያሳስበናል።

(ሐ) የቀለም ምርጫ፡-

አረንጓዴ

አረንጓዴ ሰላምን ልምላሜን እርጋታን የሚያመለክት በቶሎ የምንወዳጀው ቀለም ነው። በዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ ውስጥ ሰላምን ያሳያል። እንቅስቃሴውን በእርጋታ ሚዛን ላይ ያስቀምጥልናል።

ቢጫ

ቢጫ ቀለም አብርሆት፣ ጥበብና ተስፋን ይወክላል።

የቢጫና አረንጓዴ ቀለማት የአፍሪካ አቀፍ (ፓን አፍሪካን) ቀለም ናቸው። በኢትዮጵያም ሆነ በአያሌ የአፍሪካ አገሮች ሰንደቅ ዓላማዎች ላይ ይገኛሉ። በዚህም ንድፉ ከተማችን የኛ ከተማ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካውያንም ከተማ ነች እያለ ነው።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...