የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ እግር ኳስ ውድድር (ሴካፋ) የዞን ማጣሪያ ውድድር ታንዛንያን ይገጥማል፡፡ ከሳምንታት በፊት ጀምሮ ሲዘጋጅ የነበረው ብሔራዊ ቡድኑ፣ ሱዳን በምታዘጋጀው ውድድር ላይ ለመካፈል ከቀናት በፊት ወደ ሥፍራው ያቀና ሲሆን፣ ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ታንዛንያን ይገጥማል፡፡
በአሠልጣኝ ዕድሉ ደረጀ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ፣ ሰኞ ጥቅምት 21 ቀን የመጀመሪያ ልምምዱ ያደረገ ሲሆን፣ በምድብ ሁለት ከዑጋንዳና ከታንዛንያ ጋር ተደልድሏል፡፡ በምድብ አንድ ብሩንዲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ጂቡቲ ተደልድለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የተደለደሉት ዑጋንዳና ታንዛንያ ባደረጉት የምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ዑጋንዳ 2 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል፡፡
ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር ለ14ኛ ጊዜ የሚከናወነው ከጥቅምት 18 ቀን እስከ ኅዳር 2 ቀን ድረስ ነው፡፡ ውድድሩን በበላይነት ከየምድባቸው አንደኛና ሁለተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ አገሮች እ.ኤ.አ. በ2023 በግብፅ ለሚከናወነው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ይሳተፋሉ፡፡
ኢትዮጵያ የምድቧን ሁለተኛ ጨዋታ እሑድ ጥቅምት 27 ቀን ከዑጋንዳ ጋር ታደርጋለች፡፡ አሠልጣኝ ዕድሉ ደረጀን በአሠልጣኝነት ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 43 ተጫዋቾችን መርጦ ለሳምንታት ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2020 የሴካፋ ውድድር ከኬንያና ከሱዳን ጋር ተደልድላ የነበረ ሲሆን፣ ሱዳንን 3 ለ 2 ብትረታም በኬንያ 3 ለ 0 በመሸነፏ ከምድቧ ማለፍ አልቻለችም ነበር፡፡