- ክለቦች ሆቴልና ልምምድ ሥፍራ ዋጋ ጭማሪ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል
የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከመስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ ለአምስት ሳምንታት ሲከናወን ከቆየ በኋላ፣ ባለፈው ቅዳሜ ፋሲል ከነማ ከባህር ዳር ከተማ ባደረጉት የተስተካካይ ጨዋታ ተጠናቋል፡፡ ሁለተኛው የሊጉ ውድድር ከጥቅምት 25 ቀን ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ ይካሄዳል፡፡
ከስድስተኛ ሳምንት እስከ አሥረኛ ሳምንት ለሚከናወነው የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላይ የሚካፈሉ ክለቦች ከባህር ዳር ወደ ድሬዳዋ እየተመሙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ውድድሩን ለሦስተኛ ጊዜ የማሰናዳት ዕድል ያገኘው የድሬዳዋ ከተማ፣ የተለያዩ መሰናዶችን እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ቀደም የስታዲየሙ ዙሪያ ዕድሳትና የማሻሻያ ግንባታዎች ተጠናቀው ለውድድሩ ዝግጁ መሆናቸውን የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ባለሙያ አቶ ጉሌድ መሐመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት ዕድሳት የተደረገባቸው የመጫወቻ ሜዳ፣ የመልበሻ፣ የመፀዳጃና የሚዲያ ክፍሎች ሲሆኑ፣ የቪአይፒ ክፍሎችም ተገንብተው፣ ለውድድሩ ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ጉሌድ አብራርተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በመጫወቻ ሜዳው ጥግ የሚቀመጥ ለውድድሩ አዲስና ዘመናዊ የሆነ የዲጅታል ማስታወቂያ መሣሪያ እንዲሁም የሰዓት መቁጠሪያ ስክሪን እንደ አዲስ መተከላቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህም ቀድሞ በኅትመት ሲቀርቡ የነበሩት ማስታወቂያዎች በዲጂታል መንገድ ብቻ እንደሚቀርቡ አቶ ጉሌድ ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል በከተማዋ በተደራጁ ወጣቶች አማካይነት ስድስት አርቴፊሻል ሜዳዎች የተሰናዱ ሲሆን፣ ክለቦች በክፍያ ልምምድ እንዲያደርጉበት በአማራጭነት ቀርበዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ አየር ኃይል፣ ሳብያን ሜዳ፣ ኤርፖርት (ኮንጎ ሜዳ) እንዲሁም አስታጥቄ ሜዳ ለክለቦች ለልምምድ አማራጭነት መቅረባቸው ተገልጿል፡፡
ክለቦቹ በከተማዋ በሚያደርጉት ቆይታ ለሁለት ሰዓት ልምምድ፣ በተጫዋች 50 ብር ክፍያ እንደሚጠየቁና በቆይታቸው ከፍተኛ ገንዘብ ለማውጣት እንደሚገደዱ ይናገራሉ፡፡ ክፍያው ክለቦችን ለመጉዳት የተተመነ ሳይሆን የጤና ቡድን ማኅበራት በመደበኛውም ጊዜ ለከተማው ነዋሪ የሚሰጥበት ዋጋ እንደሆነ አቶ ጉሌድ ያስረዳሉ፡፡
በሌላ በኩል ክለቦች በከተማዋ አስተዳደር ሥር የሚገኙ የአየር ኃይልን በመሳሰሉ ሜዳዎች ላይ ልምምድ እንዳናደርግ ተከልክለናል የሚል ቅሬታን አንስተው የነበረ ሲሆን፣ ይህም ክለቦች በተቀመጠው መርሐ ግብር መሠረት የልምምድ ቦታው ላይ ተገኝተው አለመሥራታቸው ክፍተት መፍጠሩን አቶ ጉሌድ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡
በተለያዩ ከተሞች መከናወን ከጀመረ ሦስተኛ ዓመቱን የያዘው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን ከፍተኛ ገንዘብ እያስወጣ መሆኑ ይነገራል፡፡ በዚህም ክለቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ የሆቴሎች ክፍያ መናር እንዳሳሰባቸውና ላልተፈለገ ወጪ እየዳረጋቸው መሆኑ ያነሳሉ፡፡
በተለይ ለሆቴል ዋጋ መናር በመሀል የሚገቡት ደላሎች እንደ ምክንያት እንደሚነሱ የክለቡ የቡድን መሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ክለቦች በአንድ ከተማ ለአምስት ሳምንታት ቆይታ ሲያደርጉ ለአንድ ተጫዋች በቀን እስከ አንድ ሺሕ ብር ድረስ ክፍያ ሲጠይቁ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን 2,000 ብር ድረስ እንደሚጠየቁ ክለቦቹ ያስረዳሉ፡፡ ምንም እንኳ የዋጋው መናር ወቅታዊው የዕቃዎች ዋጋ መናር አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ በሆቴሎችና በክለቦች መካከል ጣልቃ የሚገቡት ደላሎች ለዋጋ መጨመር አስተዋጽኦ እንዳለው፣ ስማቸውን እንዳይገለጽ የፈለጉ የቡድን መሪ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የሆቴሎች የዋጋ መናርን ተከትሎም ክለቦች ከውድድር አዘጋጅ ከተሞች አስተዳደር ጋር እየተወያዩ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ዓርብ ጥቅምት 25 ቀን በድሬዳዋ ስታዲየም በሚጀምረው የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ፣ ኢትዮጵያ መድን ከባህር ዳር ከተማ ዘጠኝ ሰዓት እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በ12 ሰዓት ላይ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል፡፡