Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየወንጀል ሕጉ ወሲባዊ ጥቃቶችን በጦር ወንጀልነት አካቶ እንዲሻሻል ኢሰመኮ ጠየቀ

የወንጀል ሕጉ ወሲባዊ ጥቃቶችን በጦር ወንጀልነት አካቶ እንዲሻሻል ኢሰመኮ ጠየቀ

ቀን:

ከ19 ዓመታት በፊት የተሻሻለው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዓውድ ውስጥ የተፈጸሙትንና እስከ “የጦር ወንጀልነት” እንደሚደርሱ የሚገለጹትን የወሲብ ጥቃቶች በሚያካትት መልኩ እንዲሻሻል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ፡፡

በወንጀል ሕጉ ውስጥ በጦር ወንጀልነት ተፈርጀው የተቀመጡት ጉዳዮች፣ በጦርነቱ ውስጥ ‹‹ታቅደው የጦርነት ዓላማን ለማስፈጸም የተደረጉ ድርጊቶችን›› ጨምሮ ሌሎች ወሲባዊ ጥቃቶችን እንዳላካተተ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ይህም የተጠቂዎችን ፍትሕ የማግኘት መብት እንደሚያጓድል አሳስቧል፡፡

በወንጀል ሕጉ ላይ ከፆታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ የተጠቀሱ የጦር ወንጀሎች “ጥቅል” እንደሆኑ ለሪፖርተር የተናገሩት የኢሰመኮ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ ውስጥ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዓውድ ውስጥ እንደተፈጸሙ የተረጋገጡ ወሲባዊ ጥቃቶች በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሚሸፈኑ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡

የሕጉ አለመስተካከል ‹‹በተለይ ሕግ ለሚተረጉምበት ፍርድ ቤት ሲቀርብ ጉዳዩን አስቸጋሪ ያደርገዋል፤›› ሲሉ የኮሚሽኑን ሥጋት ገልጸዋል፡፡

ኢሰመኮ ይህንን ምክረ ሐሳብ ያቀረበው ‹‹የኢትዮጵያ የሴቶችና ሕፃናት የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ›› ላይ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ነው፡፡ ኮሚሽኑ በዚህ ሪፖርቱ ከመስከረም 2014 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች በሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ላይ ያሉ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ክፍተቶችን፣ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የሴቶችና የሕፃናት አያያዝ፣ ከጥቃትና ብዝበዛ መጠበቅ ጋር በተያያዘ መብትንና ተያያዥ ጉዳዮችን ዳሷል፡፡ ባለ 36 ገጹ ሪፖርት የተዘጋጀው ካካሄዳቸው ክትትሎች፣ ምርመራዎችና የመስክ ምልከታዎች፣ ባስተናገዳቸው የግለሰቦች አቤቱታዎች፣ የሕግና የፖሊሲ ግምገማዎች፣ ጥናቶችና ምክክሮች እንዲሁም ሌሎች ጠቋሚዎች በመነሳት መሆኑን በሪፖርቱ ላይ ሠፍሯል፡፡

በሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ክፍተቶች ሥር በግጭት ዓውድ የሚፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን የተመለከተው ሪፖርቱ፣ ኢሰመኮ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ በትግራይ፣ አፋርና በአማራ ክልሎች “በርካታ” ሴቶችና ሕፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ያስታውሳል፡፡ እነዚህ ጥቃቶች ‹‹መጠነ ሰፊ እንዲሁም ሥልታዊ በሆነ መልኩ በግፍና በጭካኔም ጭምር የተፈጸሙ፤›› ስለመሆናቸው ኢሰመኮ በምርመራዎቹ ማረጋገጡም ተገልጿል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተካሄደባቸው ትግራይ፣ የአፋርና የአማራ ክልሎች ውስጥ የተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶችና የማሰቃየት ድርጊቶች ‹‹በሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግፍና ጭካኔ የተሞላባቸው፤›› መሆናቸው በሪፖርቱ ላይ ተጠሰቅሷል፡፡ ‹‹የተናጠልና የቡድን አስገድዶ የመድፈር ጥቃት፣ አስገድዶ የመድፈር ሙከራ፣ ባዕድ ነገር ወደ ማህፀን የመክተት ድርጊት፣ አካላዊ ጥቃቶች፣ ግድያና የማሰቃየት ድርጊቶች፤›› ጦርነቱ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ የተፈጸሙ ድርጊቶች ስለመሆናቸው ኢሰመኮ አስረድቷል፡፡

በጦርነቱ ዓውድ ውስጥ በሦስቱ ክልሎች በሴቶች ላይ በተለይም ወሲባዊ ጥቃቶች ሲፈጸሙ፣ ድርጊቱን ‹‹እንደ አንድ የጦር ሥልት የመጠቀም አዝማሚያም›› መታየቱ መሆኑን አሳሳቢ እንደሚያደርገው የሚጠቅሰው ኮሚሽኑ፣ እነዚህ ድርጊቶች “የጦር ወንጀል” ሊሆኑ የሚችሉ መሆናቸውን በሪፖርቱ ላይ አስቀምጧል፡፡

ይሁንና የአገሪቱ የወንጀል ሕግ በጦር ወንጀልነት ሊፈረጁ የሚችሉ በሚል የዘረዘራቸው ፆታን መሠረት ያደረጉ የጥቃት ዓይነቶች በማስገደድ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መሆኑን ኢሰመኮ ያስረዳል፡

በ1996 ዓ.ም. የተሻሻለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 270 ‹‹በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሚፈጸም የጦርነት ወንጀል›› በሚለው ድንጋጌ (ረ)፣ ሥር ከፆታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ የጦርነት ወንጀሎች እንደሆነ የተጠቀሱት ‹‹የዝሙት አዳሪነት፣ የብልግና ድርጊት ወይም የግብረ ሥጋ ድፍረት ተግባር እንዲፈጸም ያስገደደ እንደሆነ፤›› የሚሉ ናቸው፡፡

በሕጉ ላይ የተዘረዘሩት ፆታዊ ወንጀሎች ውስንና ጥቅል መሆናቸውን የሚገልጸው የኢሰመኮ ሪፖርት፣ ‹‹በወንጀል ሕጉ የጦር ወንጀል ተብለው የተቀመጡ ድርጊቶች ውስን በመሆናቸው፣ በተለየ የሐሳብ ክፍልና የጭካኔ ደረጃ የተፈጸሙ ጥቃቶች በተገቢው የወንጀል ደረጃ የሚዳኙበት የሕግ ማዕቀፍ የለም፤›› ሲል ሐሳቡን አብራርቷል፡፡

እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ፣ ከዓለም አቀፍ ሕግጋት አኳያ የጦር ወንጀል ሊሆኑ የሚችሉት ታቅደው የጦርነት ዓላማን ለማስፈጸም የተደረጉ ድርጊቶችን፣ እንዲሁም የጭካኔ ደረጃቸው ከፍ ያሉ ጥቃቶች በሕጉ ውስጥ አልተካተቱም፡፡ በቡድን አስገድዶ መድፈር፣ ባዕድ ነገር ማህፀን ውስጥ መክተት፣ የግዳጅ ጋብቻና የወሲብ ባርነት በሕጉ ውስጥ ካልተካተቱት ፆታዊ ጥቃቶች መካከል መሆናቸው ተጠቅሰዋል፡፡

የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነሯ መስከረም ገስጥ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተፈጸሙት ወሲባዊ ወንጀሎች ‹‹በሕጉ ውስጥ›› በጦር ወንጀልነት አለመጠቀሳቸው ከዓለም አቀፍ አሠራር ጋር የማይስማማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹[ወሲባዊ ወንጀሎቹን] በሌላ ተመሳሳይ የሆኑ የወንጀል ሕግ አንቀጾችን ጠቅሶ እያጠጋጉ ለማድረግ የሚቻልበት አጋጣሚና ወይም አማራጭ ቢኖርም፣ ወንጀሉ በተፈጸመበት ልክና በዓለም አቀፍ ሕጎች በተሰጠው ደረጃ የጦር ወይም በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ለማለት አስቸጋሪ ያደርገዋል፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን አብራርተዋል፡፡

‹‹የጦርነት ወንጀል ሊሆኑ ይችላሉ›› የተባሉት እነዚህን ወንጀሎች በሕጉ ላይ በጦር ወንጀልነት አለመካተታቸው የተጎጂዎችን ፍትሕ የማግኘት መብት “የሚያጓድል” መሆኑንና ጥቃት ፈጻሚ ግለሰቦችና ቡድኖች በድርጊቱ መጠን ሊኖራቸው የሚገባውን የወንጀል ተጠያቂነት የሚቀንስ መሆኑን ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ አሥፍራል፡፡

ኮሚሽኑ በምክረ ሐሳቡ፣ ‹‹በግጭትና በድኅረ-ግጭት የሚፈጸሙ ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን በበቂ ጥልቀትና ዝርዝር በማካተት፣ የተፈጸሙበትን የሐሳብ ክፍልና የአፈጻጸም ሁኔታ በሚመጥን መልኩ የወንጀል ሕጉ እንዲሻሻል፤›› ሲል ጠይቋል፡፡

ኮሚሽነር መስከረም፣ የተጠቀሱት ድርጊቶች በጦር ወንጀልነት የሚካተቱበት መንገድ “የሕግ አውጪው አካል የሚወስነው” እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ ተጨማሪ የጦር ወንጀሎችን የሚዘረዝር ሕግ ማውጣት እንዱ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...