ዘንድሮ ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት በዓለም ስሟን የሚያስጠራ ትልቅ ተግባር እያከናወነች ነው፡፡ ከስንዴ ልማቱ በተጨማሪ በሌሎች የምግብና ምግብ ነክ ምርቶች በሰፊው ተሰማርቶ ከድህነት ለመገላገል፣ እንደ ሰማይ የራቀውን ሰላም መልሶ ማምጣት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ነው፡፡ በልማቱም ሆነ በሌሎች መሠረታዊ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት በመፍጠር ማደግ የሚቻለው፣ ከምንም ነገር በላይ ሰላም ሰፍኖ በነፃነትና በእኩልነት የሚኖርባት አገር ለመገንባት ስምምነት ሲኖር ነው፡፡ ለዘመናት የአገር መቅሰፍት ከሆኑት ጥላቻ፣ መናናቅ፣ መተናነቅና ዓይንህን ለአፈር ከሚያስብለው የተበላሸ ፖለቲካ መላቀቅ የግድ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የጥቂቶች ሳትሆን የ120 ሚሊዮን ልጆቿ አገር መሆኗን በመተማመን፣ ከዕብሪትና ከጥጋብ አስተሳሰብ በመላቀቅ ለብሔራዊ ጥቅሞቿና ደኅንነቷ በጋራ መቆም መለመድ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የሚያምርባት ለዘመናት ያልታረሱ ድንግል መሬቶቿ ታርሰው የተትረፈረፈ ምግብ ሲሰጡ፣ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ማዕድናቷ ወጥተው ገቢ ሲያመነጩ፣ መልከ ብዙዎቹ የቱሪዝም መስህቦቿ የዓለም ቱሪስቶችን በብዛት ሲስቡና ወጣት የሰው ኃይሏ በመደበኛው ትምህርትና በዘመን አፈራሹ ቴክኖሎጂ ሲራቀቅ እንጂ እርስ በርሱ ሲባላ አይደለም፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች ተስፋ ሰጪ ሆኖ የተጀመረው የስንዴ ልማት የበለጠ ጎምርቶ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲስፋፋ፣ እንደ መልከዓ ምድሩ አቀማመጥና የአየር ፀባይ ሌሎች ምርቶችም በብዛት እንዲመረቱ፣ ለዘመናት ያለ ከልካይ ሲፈሱ የኖሩ ወንዞች በስፋት ለልማት እንዲውሉና በሥራ አጥነት ተስፋ የቆረጡ ወጣቶች ሕይወት እንዲያብብ ሰላም አስፈላጊ ነው፡፡ ሰላም በቤተሰብ ውስጥ፣ በጓደኞች፣ በሥራና በመኖሪያ አካባቢ፣ በሕዝብና በመንግሥት፣ በፖለቲከኞችና በመላው ሕዝባችን መካከል ሊሰፍን የሚችለው እርስ በርስ መከባበር ሲኖር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጨዋነት ባህል ሲሆን ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ራስንና ቡድንን ከአገርና ከሕዝብ ማስቀደም ነውር ይሆናል፡፡ ሌብነትና ሥነ ምግባር አልባነት የተናቁ ይሆናሉ፡፡ ለሥልጣንና ጥቅም ለማግበስበስ ሲባል የሚፈጸሙ ብልግናዎች ይቆማሉ፡፡ አድሎአዊነትና አግላይነት የኋላቀርነት መገለጫ ይደረጋሉ፡፡ ችግር ሲያጋጥም ዱላ ከመማዘዝ ይልቅ ንግግር ይቀድማል፡፡ ጉልበት ሳይሆን ሐሳብ ገዥ ስለሚሆን ጉልበተኞች ለሕግ ይገዛሉ፡፡
በዚህ ዘመን በተለይ ወጣቶችና ታዳጊዎች ከመንደር አስተሳሰብ ወጥተው ዓለምን አሸጋግረው ማየት አለባቸው፡፡ ያለንበት ዘመን በቴክኖሎጂ መስክ አስደማሚ ነገሮችን እያሳየ ነው፡፡ የሰው ልጅ ምድርን ለቆ በአየር መንሳፈፍና በባህር ላይ መቅዘፍ ከጀመረ አንስቶ፣ በዓለም ላይ በየዘመኑ ከታዩት ቴክኖሎጂዎች እጅግ የላቁት አሁን በመፈልሰፍ ላይ ያሉት ናቸው፡፡ ቀደም ሲል አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ብቻቸውን የተቆጣጠሩት ቴክኖሎጂ፣ አሁን የእያንዳንዱን ሰው በራፍ እያንኳኳ ነው፡፡ በእጅ ከሚያዘው ስልክ ጀምሮ በተለያዩ መስኮች እየተሠራጨ ያለው የቴክኖሎጂ በረከት ብዙዎችን ሀብታም እያደረገ ባለበት ጊዜ፣ በማይረቡ ምክንያቶች ማንነትንና እምነትን እየታከኩ እርስ በርስ መገዳደል አሳፋሪ ነው፡፡ ወጣቶችን ለማይረባ ዓላማ ጠመንጃ አስታጥቆ እሳት ውስጥ መክተትም ሆነ፣ ጊዜ ባለፈባቸው ትርክቶች አደናቁሮ ከዕውቀት ማዕድ እንዳይቋደሱ ማድረግ ትውልድ ገዳይነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከስንዴም ሆነ ከሌሎች ምርቶች በላይ በወጣቶቿ አዕምሮ ብትጠቀም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሠለጠኑት አገሮች ተርታ የመሠለፍ ዕምቅ አቅም አላት፡፡ ወጣቱ በአገሩ በነፃነት እየተማረ እንዲዘጋጅ መብትና ግዴታውን ማሳወቅ፣ ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ እንዲያድግ አርዓያ መሆንና ራስንም ከአላስፈላጊ ድርጊቶች መግታት የመንግሥትና የማኅበረሰቡ ኃላፊነት ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ምሁራንና ልሂቃን ራሳችሁን መፈተሽ አለባችሁ፡፡ የትምህርት ተቋማት በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈቺ ትውልድ ለመፍጠር ምን እየሠሩ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ያሉ ምሁራን ምን ያህል ለወጣቱ ትውልድ ዕድገት እየጣሩ እንደሆነ የሚታይ ነገር የለም፡፡ ምናልባት ጥቂት የሚፍጨረጨሩ ቢኖሩም እነሱን ከማገዝ ይልቅ ለማንጓጠጥ የሚበረታው ይበዛል፡፡ ብዙዎቹ ምሁራን ለዘመኑ በማይመጥን የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ተሸጉጠው፣ ወይም ራሳቸውን የዳር ተመልካች አድርገው አገር ስትጎዳ ምንም እንዳልተፈጠረ ታዛቢ ሆነዋል፡፡ የብሔር ፖለቲካው ፈር ስቶ አገር የሚያፈርሱ ትርክቶች በበዙበት በዚህ ጊዜ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አይሆንም ብለው የሚታገሉት ጥቂቶች ለመሆናቸው በተለይ በመደበኛው ሚዲያም ሆነ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ያለውን ተሳትፎ መመልከት ይበቃል፡፡ ሰላም አደፍራሾች ከአገርና ከሕዝብ ደኅንነት በላይ የቡድን ፍላጎትን አስቀድመው ትርምስ ሲፈጥሩ፣ የብዙኃኑ ምሁራንና ልሂቃን የምን ቸገረኝ ድብርት ከመጠን በላይ ያሳስባል፡፡ የእነዚህ አልበቃ ብሎ በምስኪኑ ሕዝብ ገንዘብ የሚበለፅጉ አልጠግብ ባይ ነጋዴዎችና ቢጤዎቻቸው፣ አገሪቱን ከማራቆት አልፈው ወጣቱን ትውልድ ሌብነት እያስተማሩት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ምንም ሳይጎድልባት በልጆቿ ስምምነት ማጣት ምክንያት መከራዋን ስታይ የኖረች ምስኪን አገር ናት፡፡ በፖለቲካ አለመግባባት ምክንያት አገርን ከፅኑ ችግር መታደግ የሚችሉ ምሁራንና ልሂቃን ተገድለውባታል፣ ብዙዎችም ተሰደው የባዕዳን አገልጋይ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት መገርሰስ በኋላ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ በማስተናገድ አገርን ማሻገር አቅቶ፣ አንድ ትውልድ በቀይና በነጭ ሽብር ከማለቁም በላይ በአስከፊ ጦርነቶች ብዙዎች አልቀዋል፡፡ ከግድያና ከእስራት የሸሹት ደግሞ ለስደት ተዳርገው ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡ በተከታታይ ሥልጣን የያዙ ፖለቲከኞች አንዳቸው ከሌላው ስህተት መማር አቅቷቸው፣ ከግጭትና ከአውዳሚ ጦርነት መገላገል አልተቻለም፡፡ ከእርስ በርስ ጭቅጭቁና መተናነቁ በተጨማሪ ሌብነትና ኢሞራላዊ ድርጊቶች በጣም እየበዙ ነው፡፡ ሠርቶ አርዓያ ከመሆን ይልቅ ሰርቆ መዘባነን አላሳፍር እያለ ነው፡፡ በብሔር፣ በእምነትና በጥቅም ትስስር እየተቧደኑ አገርን መዝረፍ ሙያ ያደረጉ ሲበዙ፣ ለምድራዊም ሆነ ለሰማያዊው ሕግ ቁብ የማይሰጡ በየቦታው ሲንጎማለሉ የአገር ዕጣ ፈንታ ያስፈራል፡፡ አገራዊ ምክክሩ መካሄድ ሲጀምር ለእንዲህ ዓይነቱ አስፈሪ ጉዳይ ቦታ መስጠት የግድ መሆን አለበት፡፡
ኢትዮጵያ በልማት ወደፊት መገስገስ የምትችለው ለአገራቸው የሚያስቡ ሲበዙ ነው፡፡ ለአገር ማሰብ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሚረዱ ሐሳቦችን ከማዋጣት ይጀምራል፡፡ አገርንና ሕዝብን ከሚጎዱ ማናቸውም አደገኛ ድርጊቶች መታቀብንም ይጨምራል፡፡ አገርና ሕዝብ ሲጎዱ ለምን ብሎ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መሟገትም አስፈላጊ ነው፡፡ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት የሚንሰራፉት ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ግድ የለሽ ሲሆኑ ነው፡፡ አሁንም የስንዴውም ሆነ የሌሎች ልማት እንቅስቃሴ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ መሆን፣ ከሚያስገኘው ጥቅም በተጨማሪ መብትና ግዴታን በአግባቡ ለመወጣት ያገለግላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከብሔር፣ ከእምነትና ከመሳሰሉት ልዩነቶች ይልቅ የሚያስተሳስሯቸው በርካታ ዕድሜ ጠገብ ዘመን ተሻጋሪ ማኅበራዊ እሴቶች ስላሏቸው፣ በአገራቸው ብሔራዊ ጉዳዮች እኩል ተሳታፊ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እኩል ባለቤትነት እንዳላቸው ለማረጋገጥ፣ በቅንነትና በኃላፊነት መንፈስ ማኅበራዊ መስተጋብሮቻቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል፡፡ በስማቸው እየነገዱ ሊያጣሏቸው ወይም ሊያጋድሏቸው የሚያደቡ መሰሪዎችን ማጋለጥ የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አገር ስለሆነች፣ የልማቱም ሆነ የሰላሙ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ ይታወቅ!