- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድርጅቶች ኅብረት (ኢሰመድኅ) ዋና ዳይሬክተር አቶ መስዑድ ገበየሁ
ከአሥር ዓመታት በፊት በማዕድን ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ማዕድን ኢንዱስትሪ ግልፅነት ኢንሼቲቭ ጽሕፈት ቤት መዘጋት ክፍተት እየፈጠረ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኅብረት (ኢሰመድኅ) አስታወቀ፡፡ ጽሕፈት ቤቱ የማዕድን ሚኒስቴር በአዲሱ ካቢኔ እንደ አዲስ መዋቀሩን ተከትሎ ከባለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ የተዘጋ ሲሆን፣ ኢሰመድሕ ጽሕፈት ቤቱ እንዲከፈት ጠይቋል፡፡
ኅብረቱ የማዕድን ቁፋሮና ማውጣት ዘርፍ ላይ ባደረገው ጥናት መሠረት በማዕድን ሚኒስቴር ሥር የነበረው በድጋሚ እንዲደራጅ ጠይቋል፡፡
በአዲሱ የማዕድን ሚኒስቴር የካቤኔ አወቃቀር ከነሐሴ ወር ጀምሮ አዲስ የሰው ኃይል ድልድል ምክንያት ጽሕፈት ቤቱ መፍረሱንና በዚህ ጽሕፈት ቤት ይሠሩ የነበሩት ባለሙያዎችም ወደተለያየ ዲፓርትመንት መመደባቸውን የኅብረቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስዑድ ገበየሁ ገልጸዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪዎች ግልጽነት ኢኒሼቲቭ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ፣ ጋዝና ማዕድን ሀብት መልካም አስተዳደርን የሚያሰፍን እንዲሁም በዘርፉ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚንቀሳቀስ ኢኒሼቲቭ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን ኢኒሼቲቭ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ አብራ በመሆን የተቀላቀለች ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ያለውን ብሔራዊ ኢንሺቴቭ ጽሕፈት ቤት የማዕድን አውጪዎችን ተጠያቂነት በማስፈን፣ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ፣ የማዕድን ሚኒስቴር የኢኒሼቲቩን የማረጋገጫ ሪፖርት የሚያዘጋጅ፣ የባለድርሻ አካላት ውይይትና መረጃ የማሠራጨት ሥራዎችን ይሠራ ነበር፡፡
ብሔራዊ ጽሕፈት ቤቱ አሥራ አምስት ቡድን፣ አምስት የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች፣ አምስት የግሉ ዘርፍ ተወካዮችና ቀሪዎቹ አምስት የመንግሥት ተወካዮችን ያቀፈ ነበር።
በኢትዮጵያ ከሚገኙት 2,971 የተመዘገቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያሉ ቢሆንም፣ ከእነዚህ ውስጥ ጥቂት የሲቪል ማኅበራት ብቻ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ይሠሩ እንደነበርና ይህንን አሠራር የሚያስተባብረው የማዕድን ሚኒስቴር የሥራ ክፍል የነበረው ጽሕፈት ቤቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሥራውን ማቆሙን ጥናቱ አመላክቷል፡፡
መንግሥት ይህንን ጽሕፈት ቤት በድጋሚ እንዲያደራጅ እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት ተሳትፎ እንዲጨምር ማድረግ እንደሚገባው ኅብረቱ ይፋ ባደረገው ጥናት ተገልጿል፡፡
ኅብረቱ ጥቅምት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ከተለያየ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች የተወጣጡና በርካታ ዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ሁለት ጥናቶች ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የሁለቱም ጥናት ትንተና በየዘርፎቹ ያሉት የሲቪክ ምኅዳሩ ምን እንደሚመስል የተመለከተ ነው፡፡
በመጀመሪያ የቀረበው ጥናት ማዕድን ማውጣት ዘርፍ ላይ ያለው ግልፀኝነት ምን እንደሚመስል፣ በዘርፉ ያለውን የሲቪክ ምኅዳር ምን እንደሚመስል፣ ዘርፉ በበርካታ ጉዳዮች ችግር የሚገጥሙት እንደመሆኑ መጠን በርካታ ማኅበረሰብን እንዴት ማሳተፍ ይቻላል የሚለውን ይዘት የያዘ ነው፡፡
የዚህ ጥናት ዓላማ በመንግሥት ተቋማት ትኩረት በማግኘት የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለመፍጠር ሲሆን፣ ጉዳዩ የተመረጠበት ዋነኛ ዓላማ እ.ኤ.አ. ጥር 2023 ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ የምትገመገም በመሆኑ፣ የአገሪቷን ገጽታ ለመገንባትና መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች እንዲሻሻሉ ለማድረግ ኅብረቱ ያስጠናውን ሰነድ እንደማመሳከሪያ ለኤክስትራክቲቭ ኢንዱስትሪስ ትራንስፓረንሲ ኢኒሼቲቭ ጽሕፈት ቤት የሚያስገባ መሆኑን አቶ መስዑድ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በጥናቱ ላይ በኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ያለው የሲቪክ ምኅዳር ትንተና ጫና ውስጥ መሆኑን አሳይቷል፡፡
በጥናቱ ላይ እንደተመላከተው፣ የሲቪክ ምኅዳር መስፋት ማለት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ተቋማዊ አሠራር ሥርዓት ሆኖ አንድ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ሊፈጥር የሚገባና የዜጎችን የነቃና ትርጉም ያለው ተሳትፎ በተለያየ ጉዳዮች ላይ የሚያሳይ ነው፡፡
በዚህም መሠረት በማዕድን ዘርፍ በኢትዮጵያ ያለውን የሲቪክ ምኅዳር ትንተና በሚታይበት ወቅት፣ የሲቪክ ምኅዳሩ ጫና ውስጥ መሆኑን የኅብረቱ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መስዑድ ገበየሁ ገልጸዋል፡፡
በአብዛኛው የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ያልተዳሰሰ ዘርፍ በመሆኑ፣ የማዕድን ዘርፉ ጤናማ፣ አሳታፊ፣ ግልጽ አሠራር እንዲኖርና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ጥናት መካሄዱን አቶ መስዑድ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በዘርፉ ተደራጅተው የሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰቦች ቁጥር አናሳ ከመሆኑም ባሻገር የተጠያቂነት አሳታፊነቱ አነስተኛ መሆኑን አቶ መስዑድ ገልጸዋል፡፡
ኅብረቱ ባደረገው ጥናት መሠረት የሲቪል ማኅበረሰቡን በማዕድን ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ በጣም አነስተኛ ከሆነበት ምክንያቶች አንዱ፣ ማዕድናት የሚወጡበት አካባቢዎች ከከተማ የራቁ በመሆናቸውና የተቀመጠው ሕግ ማኅበረሰብን ተንተርሰው የተቋቋሙ ተቋማት የሚያካትትና የሚያሳትፍ አለመሆኑ ነው ሲሉ አቶ መስዑድ አብራርተዋል፡፡
በሁለተኛው ጥናት ደግሞ የሕፃናት መብት አያያዝን የሚመለት ሲሆን፣ ከሕፃናት አድን ድርጅት (Save the Children) ጋር በጋራ የሚሠራ ፕሮጀክት ውስጥ የተካተተ ጥናት ነው፡፡
ኅብረቱ ከሕፃናት አድን ድርጅት ጋር ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ስምምነት ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የሕፃናት መብት አስተዳደር ማሻሻያ ጥናት አድርጓል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት በሕፃናት መብት አስተዳደር ላይ ያለውን የሲቪክ ምኅዳሩን ማየት ሲሆን፣ ለዚህም የአምስት ዓመታት ፕሮጀክት መነሻ ጥናት (Baseline Assessment) ቀርቧል፡፡
ጥናቱ በሕፃናት ላይ የሚሠሩ ሲቪል ማኅበራት ያለባቸው ክልከላ ምንድነው፣ የመደራጀት መብት፣ የሕፃናት ፓርላማና የሕፃናትን መብትን የሚያቀነቅንና ጠበቃ የሚሆን የመንግሥት ተቋም፣ ጠንካራ የሲቪል ማኅበራት እንደሚያስፈልጉ የሚገልጽ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኅብረት (ኢሰመድኅ) በ2010 የተቋቋመ ሲሆን በሰብዓዊ መብት፣ ዴሞክራሲና የሰላም እሴት ግንባታ ላይ ይሠራል፡፡
ኅብረቱ ሲቋቋም አምስት አባላት የነበሩት ሲሆን፣ አሁን ላይ 17 አባላት ያሉት እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን አቅም በማጎልበት የሚሠራ ተቋም ነው፡፡