የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታን ለማንፀባረቅ እንዲሁም የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላት መንግሥት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ ቢሆንም፣ ዘርፉ ላይ አሁንም ክፍተት አለ፡፡ በተለይም የመንገድና ሌሎች ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፐሮጀክቶችን ዕውን ከማድረግ አኳያ በርካታ ተግዳሮቶች ታይተዋል፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህን ሁሉ ተግዳሮች ለመቀልበስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዓምና ብቻ ከ33 በላይ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን አስታውቋል፡፡
ዘንድሮም ይህንኑ አሠራር በመከተል የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው በቅርቡ አገልግሎት የሚሰጡ ስድስት ፕሮጀክቶችን ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች አስጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሜጋ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋና ሥራ አስኪያጅ ደቦ ቱንካ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ የከተማዋን ውበት ለማበልፀግና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ ቢቻልም፣ በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ በጥሬ ዕቃ (ማቴሪያል) ውድነትም ሆነ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የመጓተት ሁኔታ ታይቷል ብለዋል፡፡
በተለይም በጥሬ ዕቃ ውድነት፣ በሰሜኑ ኢትዮጵያ በኩል በተከፈተው ጦርነትና በማኔጅመንት ችግር የተነሳ አብዛኛው ፕሮጀክቶች በተባለላቸው ጊዜ ሳይጠናቀቁ መቅረታቸው ችግሩን ይበልጥ እንዳጎላው ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
እንደ አጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ በኩል እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን በተፈለገው ጊዜ አጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ እየሠራ መሆኑን፣ ከዚህ ቀደምም ለአብነት ያህል መስቀል አደባባይና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማደረጉን ጠቁመዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እስካሁን አስገንብቶ ያጠናቀቃቸውን ፕሮጀክቶች ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ ወጪ መደረጉን፣ ይህንንም አጠናክሮ በመቀጠል በቀጣይ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት መንግሥት የተለያዩ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡም ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ተጠናቆ አገልግሎት የሚሰጠው ግራንድ የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክት በ1.17 ቢሊዮን ብር ፈሰስ እንደተደረገበት ደቦ (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለቤትነት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን በተባለላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ተቋሙ እየሠራ መሆኑን፣ የከተማ አስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ጠይባ ሎና ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ዕውን ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት፣ ይሁን እንጂ ተግዳሮቶቹን በማለፍና በዘርፉ ላይ የነበሩ ችግሮችን በማስወገድ ውጤታማ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ አክለዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት አነስተኛና መካከለኛ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን መደረጉን፣ ይህንንም ዘላቂነት ባለው መልኩ ለማስኬድ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
ግራንድ የመኪና ማቆሚያ
ግራንድ የመኪና ማቆሚያ ዓለም አቀፍ የግንባታ ጥራቱን ጠብቆ የተገነባ ሲሆን፣ በቀን 1,000 የሚሆኑ ተሽከርካሪዎችን የመያዝ አቅም አለው፡፡ ሕንፃው ወደ ታች አራት የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች የያዘ ሲሆን፣ 9,000 ካሬ ሜርት ላይ አርፏል፡፡
ማዕከሉ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ሦስት ዓመት ያህል ጊዜ የፈጀ ሲሆን፣ ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ፈሰስ ተደርጎበታል፡፡ ከተሽከርካሪዎች በተጨማሪ የአንበሳና የሸገር ባስ ማቆሚያ ቦታ ያለው ሲሆን፣ በውስጡም የተለያዩ ሱቆች፣ አምፊ ቴአትር ቤትና ቢሮዎችን አካቶ ይዟል፡፡
ዘመናዊነትን የተላበሰና ከታች ግራውንድ እስከ ላይ ድረስ የሚያወጣ የራሱ የሆነ የመኪና ማጓጓዣ አሳንሰር አለው፡፡ በሌላ በኩል ከዩኒቲ ፓርክ ጋር ቀጥታ የሚያገናኝ ዋሻ በማዕከሉ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የማዕከሉ ግንባታ የተጠናቀቀ መሆኑን፣ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
ትራፊክ ማኔጅመንት ማዕከል
የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 አካባቢ በመገንባት ላይ ያለ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ሕንፃውም 7,507,175 ካሬ ሜትር ላይ አርፏል፡፡ ግንባታውም ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ 831,842,924.43 ብር ፈሰስ የተደረገበት መሆኑን፣ በሕንፃው የመጀመርያ ወለል ላይ የደኅንነት መጠበቂያ ክፍል፣ ፓርኪንግ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የፋይናስ ክፍል፣ የእንግዳ መቀበያ ክፍል፣ የአደጋ መውጫና ሌሎች ክፍሎችን አካቶ ይዟል፡፡ በሁለተኛ፣ በሦስተኛና በአራተኛ ወለል ላይም የተለያዩ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ዕውን ሲሆን፣ ዘመናዊና ቴክኖሎጂን የተላበሰ የትራፊክ አገልግሎትን የሚሰጥ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል፡፡
ሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር
በፍላሚንጎ አካባቢ የሚገኘው የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ግንባታ፣ ከዛሬ አምስት ዓመታት በፊት የተጀመረና ረዥም ዓመታት የፈጀ ሲሆን፣ ከብዙ ተግዳሮቶች በኋላ ፕሮጀክቱ በቅርቡ ዕውን እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
የቴአትር ቤቱ ሕንፃ 4,500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈና 483,187,018.31 ብር ወጪ የወጣበት መሆኑም ተነግሯል፡፡ ሕንፃው በአሁኑ ወቅት 95 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው 180 እና 220 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶች አሉት፡፡ ሕንፃው ባለ 11 ወለል ሲሆን ከ1,200 ሰዎች በላይ የመያዝ አቅም ያለው ዘመናዊ ቴአትር ቤትና የመሰብሰቢያ አዳራሽ አለው፡፡ በማዕከሉም በአንድ ጊዜ ከ180 በላይ ማስተናገድ የሚያስችል ተሽከርካሪዎች ማቆሚያ ያለው ሲሆን፣ ምቹና ዘመናዊ የሆነ የሕፃናትና የወጣቶች ቤተ መጻሕፍትንም ይዟል፡፡
የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት
የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ኮዬ ፈቼ ኮንዶሚኒየም አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹ 14 ሔክታር መሬት ላይ አርፏል፡፡ ፕሮጀክቱ እስካሁን 811,683,914,94 ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ከ91 በመቶ በላይ ተጠናቋል፡፡ ፕሮጀክቱም በልማት ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑበት የታለመ ሲሆን፣ በውስጡም 300 ሜትር ኪዩብ ውኃ የመያዝ አቅም ያለው ማጠራቂሚያ አለው፡፡ በተጨማሪም አሥር ብሎኮች ለወተት ላሞች ዕርባታ፣ አሥር ብሎኮች ለሥጋ ከብቶች ማደለቢያ፣ 32 ሼዶች ለምርት መሸጫና ማሳያ፣ አንድ የከብቶች መኖ ማከማቻ መጋዘን፣ አንድ የዶሮ መኖ ማከማቻና ሌሎች መዳረሻ ቦታዎችን አካቶ መያዙ በወቅቱ ተገልጿል፡፡
ከዚህ ቀደም ተጀምረው ያላለቁ ፕሮጀክቶች
በአዲስ አበባ ከተማ በ11 ክፍለ ከተሞች ውስጥ ተጀምረው ያላለቁ ፕሮጀክቶች ቁጥር የትየለሌ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም ጊዜና ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ያላለቁ ፕሮጀክቶች ሥፍር ቁጥር እንደሌላቸው ይታመናል፡፡ ለአብነት ያህል የቃሊቲ፣ የኮተቤ መንገድና በመገናኛ አካባቢ የሚገኝ የመኪና ማቆሚያና ሌሎች ፕሮጀክቶች እስካሁን አለመጠናቀቃቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ ጥያቄን ፈጥሯል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በከተማዋም በአጠቃላይ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች ከግብ ለማድረስ የከተማ አስተዳደሩ ዘርፈ ብዙ ሚናዎችን እያተጫወተ መሆኑ ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ተገልጿል፡፡