ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ቀዳሚ ከሚባሉ አገሮች የምትመደብ ቢሆንም፣ ከዘርፉ ብዙም ተጠቃሚ አይደለችም፡፡ በእንስሳት ጤና፣ አመጋገብ፣ አያያዝ እንዲሁም በገበያ ትስስርና የእሴት ሰንሰለት ዙሪያ ችግሮች እንዳሉ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡
መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የአሥር ዓመታት ስትራቴጂ ነድፎ እየሠራ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎንም በዘርፉ ሊሰማሩ የሚችሉ ባለሀብቶች የሚሳተፉባቸው ዓውደ ርዕዮች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህም መካከል በእንስሳት ሀብት ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያስችላል የተባለውና ከጥቅምት 17 እስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በስካይላይት ሆቴል የተካሄደው ዓውደ ርዕይ ይገኝበታል፡፡
በፕራና ኢቨንትስና መቀመጫውን ሱዳን ባደረገው አጋሩ ኤክስፖ ቲም ትብብር የተዘጋጀው የዶሮና የእንስሳት ሀብት የቴክኖሎጂና የግብዓት ዓውደ ርዕይ፣ የዘርፉን ተግዳሮቶች ለመቀነስ ዕድል ይፈጥራልም ተብሏል፡፡
ለሦስት ቀናት የዘለቀውን ዓውደ ርዕይና ጉባዔ ከአጋሩ ጋር በመሆን ያዘጋጀው የፕራና ኢቨንትስ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ እንዳሉት፣ ዓውደ ርዕዩ የዶሮና የሥጋ እሴት ሰንሰለቶች ልማት ላይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ፣ የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማመቻቸትና መንግሥት የዘርፉን ተግዳሮቶች ለመፍታት የጀመረውን ሥራ ለማገዝ ያስችላል፡፡
ከ11 አገሮች የተውጣጡ ከ70 በላይ ኩባንያዎች በተሳተፉበት ዓውደ ርዕይ፣ በኢትዮጵያ በዘርፉ ላይ ዕድገት እየታየ ቢሆንም፣ በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮችም ሆነ ባለሀብቶች በተለይ የውኃ አቅርቦት ችግር እንዳለ ተገልጿል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የመኖ፣ የቴክኖሎጂ ግብዓት፣ የገበያ ትስስር ዘርፉን የሚገዳደሩ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
እንደ ዓለም ምግብ ድርጅት፣ የእንስሳት ሀብት ባደጉት አገሮች 40 በመቶ የሚጠጋውን በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ደግሞ 20 በመቶውን የግብርና ምርት ይሸፍናል፡፡ በዚህም በዓለም ዙሪያ ቢያንስ 1.3 ቢሊዮን ሕዝቦች ኑሯቸውን ይደግፉበታል፡፡
በአፍሪካም በሕዝብ ቁጥር ማደግ፣ በተጠቃሚዎች የመግዛት አቅም መጨመርና በከተሞች መስፋፋት ምክንያት የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ፍላጎት በፍጥነት እያደገ ይገኛል፡፡
ይህም አምራቾችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በእንስሳት ዕርባታ ሥርዓትና የእሴት ሰንሰለት ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንዲያደርጉ የሚጋብዝ በመሆኑ፣ የአፍሪካን የእንስሳት ሀብት ልማት በአኅጉሪቱ ዕድገት ላይ ጉልህና ዘላቂ ተፅዕኖ እንዲኖረው በጠንካራ መሠረት ላይ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የ2020/21 ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በ42.9 ሚሊዮን በጎች፣ 52.5 ሚሊዮን ፍየሎች፣ 70.2 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶችና 8.1 ሚሊዮን ግመሎች ያሏት ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ቀዳሚ የእንስሳት ሀብት ባለቤት ነች፡፡
በ2014 በጀት ዓመትም አገሪቱ ወደ ውጭ ከላከችው 22,689 ቶን ሥጋና ተረፈ ምርቶች 121 ሚሊዮን ዶላር ያገኘች ሲሆን፣ ይህም ከ2013 ዓ.ም. አፈጻጸም ሲነጻጸር ዕድገት አሳይቷል፡፡
ከፍተኛ የመኖ ዋጋ፣ የመሬት እጥረትና የቦታ ውስንነት፣ የመኖ ጥራት፣ አቅርቦትና የዋጋ ችግሮች እንዲሁም የእንስሳት ሕክምና አገልግሎት በበቂ ሁኔታ አለመኖሩ ዋና ዋናዎቹ የወተት ዘርፉ ተግዳሮቶች ቢሆኑም፣ ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም. ወደ አምስት ቢሊዮን ሊትር የሚጠጋ የላም ወተት ማምረቷንም የማዕከላዊ ስታትስቲክ ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የ9.86 ዓመታዊ ጥቅል ዕድገት መኖሩን ያሳያል፡፡
በኢትዮጵያ የዶሮ ብዛት 57 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 34.26 በመቶ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች ሲሆኑ፣ 32.86 በመቶ ጫጬቶች እንዲሁም 6.47 በመቶ የቄብ ዶሮዎች እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡
ዝርያን በተመለከተ፣ 78.85 በመቶ፣ 12.02 በመቶ፣ እና 9.11 በመቶው የዶሮ ዕርባታ አገር በቀል፣ ድብልቅ እና የውጭ ናቸው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ በነፍስ ወከፍ የዶሮና የዶሮ ምርት ፍጆታ በዓለም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በ2012 ዓ.ም. ከዶሮ ዕርባታ ዘርፍ 88.572 ዶላር የሚያወጣ 35 ቶን የዶሮ ምርት ወደ ሶማሊያ ቢላክም፣ አገሪቱ አሁንም የተጣራ የዶሮ ምርቶችን አስመጪ ነች፡፡
በ2050 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ወደ 200 ማሊዮን ገደማ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአገር ውስጥ ምርት የነፍስ ወከፍ ገቢ በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት 700 ዶላር በታች ገቢ በ2042 ዓ.ም. 5500 ዶላር በላይ ያድጋል ተብሎም ይገመታል፡፡
እያደገ የመጣው የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት አርብቶ አደሮች የእንስሳት ሀብታቸውን እንዲያሳድጉ፣ ምርታማነትን እንዲያሳድጉና ከእንስሶቻቸውም ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመላክታል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ የአገር ውስጥ አምራቾች አቅም እያደገ ቢሆንም፣ የውጭ ኩባንያዎችም ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡
በዓውደ ርዕዩ ላይ እንደተመለከተውም፣ በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ከውጭ ካሉ ጋር በመሥራት በዘርፉ ያላቸውን ድርሻ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡
መንግሥት በአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱ የወተት ምርትን ወደ 11.8 ቢሊዮን ሊትር፣ የሥጋ ምርትን ወደ 1.7 ሚሊዮን ቶን፣ እንቁላል 5.5 ቢሊዮን እንዲሁም የዶሮ ሥጋ ምርትን 106 ሺሕ ቶን ለማድረስ ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡