Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየነዳጅ ድጎማው አስተዋጽኦ

የነዳጅ ድጎማው አስተዋጽኦ

ቀን:

የኑሮ ውድነትን ከሚያባብሱ ነገሮች መካከል የነዳጅ ዋጋ ከፍ ማለት ከግንባር ቀደሞቹ ይመደባል፡፡ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩም የሸቀጣ ሸቀጦችና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች ዋጋ ከፍ እንዲል ማድረጉ አልቀረም፡፡

በኢትዮጵያ የ2014 ዓ.ም. በሚያዝያ ወር የነዳጅ ዋጋ ነጭ ናፍጣ በሊትር 35 ብር ከ43 ሳንቲም፣ ቤንዚን ደግሞ 36 ብር ከ87 ሳንቲም እንዲሸጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡

በኋላም በሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ነጭ ናፍጣ 49 ብር፣ ቤንዚን 47.83 ሳንቲም ተደርጓል፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአንድ ሊትር ነጭ ናፍጣ 59. ብር ከ90 ሳንቲም፣ ቤንዚን በሊትር 57 ብር ከ05 ሳንቲም እንዲሸጥ የወሰነውም  መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ነው፡፡ በ2014 ዓ.ም. ሚያዝያ ወርና በመስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም. መካከል የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ሲሰላም የ24 ብር ከ47 ሳንቲም ልዩነት አሳይቷል፡፡

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ የሚመጣ የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ መንግሥት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎችን በመለየት  የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆኑም አድርጓል፡፡

ከድጎማው ተጠቃሚ ከሆኑት አንዱ ወጣት አብዲ ከማል ነው፡፡ የሹፍርና ሥራ ከጀመረ መሰንበቱን ይገልጻል፡፡ ወጣት አብዲ 12 ተሳፋሪዎችን የሚይዘው ሚኒባስ ሾፌር መሆኑንና ከመጀመርያዎቹ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ተርታ መሠለፉን ያስረዳል፡፡

በቀን 25 ሊትር ነዳጅ በ41 ብር 26 ሳንቲም እንደሚገዛ የገለጸው ወጣቱ፣ በቀን እንዳሠራውና መንገዱ ከ25 ሊትር እስከ 30 ሊትር ነዳጅ እንደሚጠቀም ይገልጻል፡፡

25 ሊትር ነዳጅ የሚቀዳ ከሆነም 1,031 ብር ከአምስት ሳንቲም እንደሚያወጣ ገልጿል፡፡

ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ያልሆኑት 25 ሊትር ነዳጅ የሚቀዱ ከሆነ 1,497 ብር ከአምስት ሳንቲም እንደሚገዙና የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑት በ25 ሊትር 466 ብር እንደሚቀንስላቸው ወይም የሚጨምርባቸውን ገንዘብ መንግሥት እንደሚሸፍንላቸው ተናግሯል፡፡

እንደ ወጣት አብዲ፣ የነዳጅ ድጎማው በትክክልና በአግባቡ ለተጠቀመበት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ መንገዶች በትራፊክ መጨናነቅ የነዳጅ ፍጆታቸውን በቀን ከ25 ሊትር በላይ እንደሚያደርገው ይጠቁማል፡፡

ባለሦስት እግር (ባጃጅ) አሽከርካሪው አቶ ፈጠነ ንጉሡ በበኩሉ፣ በቀን ሰባት ሊትር ነዳጅ እንደሚደጎም፣ በቀን ሰባት ሊትር በ40 ብር ሒሳብ ሲሰላ 288 ብር መሆኑን፣ የድጎማው ተጠቃሚ ያልሆኑት ደግሞ በ402 ብር ከ99 ሳንቲም እንደሚቀዱ ገልጿል፡፡

የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ የባለሦስት እግር አሽከርካሪዎች በመንግሥት 114 ብር ከ17 ሳንቲም ድጎማ እንደሚደረግላቸው አክሏል፡፡

አገር አቋራጭ ለሚሠሩ የሚኒባስ ተሽከርካሪዎችም የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ በቀን እስከ 65 ሊትር የነዳጅ ድጎማ ያገኛሉ፡፡

አገር አቋራጭ ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች በቀን የ65 ሊትር ድጎማ የሚያገኙ ሲሆን፣ ይህ ከድጎማ ውጭ ሲሰላ 3,893 ብር ከአምስት ሳንቲም ይሆናል፡፡

የድጎማ ተጠቃሚ የሆኑት ደግሞ 65 ሊትር ነዳጅ በ41 ብር 26 ሳንቲም ሲሰላላቸው 2,681 ብር ከዘጠኝ ሳንቲም ሲሆን፣ የድጎማ ተጠቃሚ ለሆኑት ከአንድ ሺሕ ብር በላይ መንግሥት ይሸፍንላቸዋል፡፡

አቶ ደመቀ ጌጡ ብራስ አካባቢ በሚገኝ አንድ ነዳጅ ማደያ ውስጥ ለስምንት ዓመታት ሠርቷል፡፡ አቶ ደመቀ ስለነዳጅ ድጎማው ለሪፖርተር እንደተናገረው፣ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው፡፡ በነዳጅ ማደያው በርካታ የድጋፍ ሰጪ ባሶች፣ ሚኒባሶች፣ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) እና አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ያመጣሉ፡፡

በቀን ውስጥ በሊትር እስከ 20 ብር ድረስ መንግሥት ድጎማ የሚያደርግላቸው መኖራቸውን፣ ከሰባት እስከ 102 ሊትር ድረስ የነዳጅ ኮታ የሚጠቀሙ እንዳሉ መሆኑን ገልጿል፡፡

በገንዘብ ሲሰላ ከ114 ብር ከ17 ሳንቲም እስከ 1,901 ብር ከ28 ሳንቲም ድረስ መንግሥት ድጎማ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

በምሳሌነትም ሰባት ሊትር ድጎማ የሚደረግላቸው የባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ ከአንድ መቶ ብር በላይ ድጎማ እንደሚደረግላቸው ጠቁሟል፡፡

ከዚህ ባለፈ የ95 ሊትር ነዳጅ ድጎማ ለሚደረግላቸው ድጋፍ ሰጪ ባሶች መንግሥት እስከ 1,770 ብር ድረስ ወጪያቸውን ይሸፍናል፡፡

ለቤንዚል ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ሲሆን ደግሞ፣ በሊትር በ40 ብር ሒሳብ እንደሚሰላላቸው፣ በዚህም መሠረት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች በሊትር ከ18 እስከ 20 ብር ድረስ ድጎማ እንደሚያገኙ፣ በአንድ ነዳጅ ማደያ በቀን የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች እስከ 130 ሺሕ ሊትር እንደሚቀዱ ገልጸዋል፡፡

በአንድ የነዳጅ ማደያ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ለሆኑት ብቻ አገልግሎት ቢሰጥ፣ እስከ 5,363,800 ብር በቴሌ ብር አማካይነት ይዘዋወራል፡፡

መንግሥትም ከአንድ ነዳጅ ማደያ ብቻ ለሚቀዱ ተጠቃሚዎች እስከ 2,423,200 ብር ለነዳጅ ድጎማ ያደርጋል፡፡

የነዳጅ ኮታው ተጠቃሚዎች ነዳጅ መቅዳት የሚችሉት አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፣ ከተሰጣቸው ኮታ በላይ ከሆነ የሚከፍሉት ከኪሳቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

የሕዝብ ትራንስፖርት የድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች 15 በመቶ በመንግሥት ሲደጉሙ ቀሪውን አሥር በመቶ ራሳቸው ይከፍላሉ፡፡ ድጎማ መጠኑንም በቴሌ ብር አማካይነት ተመላሽ እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡

ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ኢትዮ ቴሌኮም እንዳስታወቀውም፣ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ 146,000 ተሽከርካሪዎች ያሉ ሲሆን፣ በቴሌ ብር አማካይነት ከ4.1 ቢሊዮን ብር በላይ ክፍያ ተፈጽሟል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በትግራይ ተቋርጦ የነበረው የምግብ ዕርዳታ እንዲጀምር አቶ ጌታቸው ጥያቄ አቀረቡ

የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት...

ኢዜማ ከለቀቁ አባላት ግማሽ ያህሉ የዲሲፒሊን ችግር የነበረባቸው ናቸው አለ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በቅርቡ ከፓርቲው አባልነት ለቀናል...

የአዲስ አበበ መምህራን ማኅበር የደመወዝ ጥያቄው ምላሽ ካላገኘ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ለረጅም ዓመት ያገለገሉ መምህራን ደመወዝና...

ኢሰመኮ በዩኒቨርሲቲዎች የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ጉዳይ የሚመራበት የጽሑፍ ፖሊሲ አለመኖሩን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች...