Thursday, November 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ዘጠና በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሸቀጣ ሸቀጥ ስለሚያጓጉዘው ግድ መርከብ ምን እናውቃለን? (ክፍል ሁለት)

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ማስታወሻ ውድ አንባቢያን፣ በክፍል አንድ መርከብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ የመርከብ ታሪክ መቼና በምን ምክንያት እንደሚጀምር፣ ጥንታዊት ኢትዮጵያ የነበራት የባህር መስመር በሚመለከት በሰፊው መቅረቡ ይታወሳል፡፡ ጽሑፉን ምናልባት ካላነበቡት መርከቦች ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ እንደ ሰማይ በጠለቁ፣ ከከርሰ ምድር በላይ በሰፉ ውቅያኖሶችና በባህሮች ተለያይተው የነበሩ የዓለም ሕዝቦችን ያገናኙ፣ ባህልን ከባህል፣ ማኅበራዊ ኑሮን ከማኅበራዊ ኑሮ፣ ፍልስፍናን ከፍልስፍና ያገናኙና ያዋሃዱ፣ የሰው ልጅ አካባቢውን ለመቆጣጥር ወይም የሚገጥመውን ፈተና ድል ለማድረግ ታጥቆ የሚሠራ መሆኑን ያስገነዝቡ የየዘመኑ ቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ውጤቶች መሆናቸውን ከዳሰስን በኋላ የመርከብ አመጣጥ ታሪክ፣ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ታሪክና ስለዘመናዊ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ታሪክ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ደግሞ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ምሥረታ የንጉሠ ነገሥቱና የባለሥልጣኖቻቸው ሚና ምን እንደነበር እናያለን፡፡

  1. ኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ታሪክ የንጉሠ ነገሥቱና የባለሥልጣኖቻቸው ሚና

በ1940ዎቹና በ1950ዎቹ የንግድ መርከብ አስፈላጊነት ከምንጊዜም ጎልቶ እየታየ የመጣበት ሁኔታ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ ስለዚህም ጉዳይ የባህር ክፍል ረዳት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጌታቸው በቀለ በዩጎዝላቪያ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክተው ጥቅምት 12 ቀን 1953 ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፣  

«… ያለውን ችግር ለማስወገድና የአገራችንን ሀብት ለማልማት በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ከቀረው ዓለም ጋር ልትወዳደር እምትችልበት ደረጃ ለመድረስ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አንድ ግብ እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ይኸውም ሰው አላፊ መሆኑና የሰው ህያውነት ለአገሬ ብሎ አስቦ በሚሠራው ሥራ ለትውልድ እየተላለፈ፣ ለተተኪው ትውልድ መኩሪያና መደሰቻ ሆኖ እየቀጠለ እንደሚሄድ፣ በአንፃሩም ለግሌ ብሎ የሚሠራው ሰው ሁሉ ሳይሞት የሞተ ሥራው በአጭሩ ተቀጭቶ የሚቀር ውጥን መሆኑን ሕዝቡም ባለሥልጣኖቹም እንዲረዱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ለአገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት የንግድ መርከብ በግርማዊነትዎ መልካም ፈቃድ ማቋቋም አስፈላጊ ነው፡፡ የግርማዊነትዎ መልካም ፈቃድ የቢሆን የዩጎዝላቭ መንግሥት በዚህ ሥራ ችሎታ ያላቸው አንድ ሁለት ሰዎች እንዲያውሱን ቢጠየቁ፣ እንዲሁም የተወሰኑ ሰዎች ወደ አገራቸው ሄደው በመርከብ ኩባንያዎቻቸው በሥራ እንዲሠለጥኑ ቢደረግ፣ ይህ ኩባንያ እንዲዳብርና ማንኛውንም የመጫንና የማራገፍ ሥራ ጠቅልሎ እንዲይዝ…ማድረግ ይቻላል፡፡

«ይህን የመሰለ ኩባንያ ለማቋቋም ለመጀመሪያው ዓመት አንድ መቶ ሺሕ ብር መጠባበቂያ ከተገኘ በሦስተኛው ዓመት ብድሩን ለመክፈል ይጀምራል፡፡ በአምስተኛው ዓመት ትርፉን ሊሰጥ ይችላል፤» ብለዋል፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም፣ «ኢትዮጵያ ከውጭ አገሮች ጋር ያላት ንግድ ሳይቋረጥ እንዲያድግ መንገድ መክፈታችን የመላውን ኢትዮጵያን ሀብት ለተወዳጁ ሕዝባችን አሟላንለት ማለት ነው፤» ብለዋል (ሰንደቅ ዓላማችን 195ዐ፣ 18ተኛ ዓመት ቁጥር 4፣ገጽ 2)፡፡

አጥቢያ ኮከብ የተባለችው መርከብና አራቱ ታግ ቦቶች ተገዝተው ከመጡ፣ እንዲሁም የአሰብ ወደብ በዘመናዊ መንገድ ከተሠራ በኋላ በ1950-51 ዓ.ም. የወጪና ገቢ ዕቃው መጠን ከፍ እያለ በመሄዱ የንግድ መርከብ አስፈላጊነት እየጎላ መጣ፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አክስዮን ማኀበርን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት አመነበት፡፡ ጥናቱም ተካሄደ፡፡ በተካሄደው ጥናት መሠረትም  የንግድ መርከብ ማኅበር ማቋቋም ኢትዮጵያን ያዋጣት እንደሆነ ሲጠና ኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገር የምትልከው የንግድ ሸቀጥ ማኅበሩ ከመቋቋሙ 15 ዓመት በፊት ጀምሮ እያደገ መምጣቱን አመለከተ፡፡ በዚህም የሚከተለው ማስረጃ ከሰባተኛው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መጽሔት የተወሰደው ማስረጃ እንደሚያመለክተውም፣ የንግድ መርከብ ማኅበር ማቋቋም ኢትዮጵያን ያዋጣት እንደሆነ ሲጠና ኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገር የምትልከው የንግድ ሸቀጥ ማኅበሩ ከመቋቋሙ 15 ዓመት በፊት ጀምሮ እያደገ መምጣቱን ጠቆመ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ቦርድን ማቋቋም አስፈላጊነቱ ስለታመነበት ይህንን አካል የሚያቋቁም አካል ተመሠረተ፡፡ አካሉም የሥራ መመርያ በማውጣት ቦርዱን አቋቋመ፡፡ ቦርዱ ልዩ ልዩ ስብሰባዎች ካካሄደ በኋላ የሚከተለውን ማስታወሻ ግንቦት 17 ቀን 1956 ዓ.ም. ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቀረበ፡፡ የማስታወሻውም ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ማኀበር አቋቁሞ ለመሥራት ተዘጋጅቶ የነበረው የኢኮኖሚ ጥናት ሥራው በብዙ መንገድ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን ለማሳየት ችሎ ነበር፡፡

በዚህም ሥራ ማከናወኛ የሚያስፈልገው ገንዘብ በሙሉ ከአገር ውስጥ ለማግኘት የሚያዳግት በመሆኑና ሥራውንም ቢሆን ራሳችን ልንሠራው የማንችል ስለሆነ፣ በገንዘብ መዋጮ ሆነ በማኀበሩ ሥራ አመራር ከውጭ አገር ሰዎች ጋር መተባበር በማስፈለጉ፣ ባለፈው ኀዳር ወር (1956 ዓ.ም.) «ቬርሎሜ ዩናይትድ ሺፕ ያርድስ» የተባለው የሆላንድ የመርከብ ሥራ ማኀበር የእሱ ተባባሪ ከሆኑት ከፋይናንስ ሰዎች ጋር በዚሁ ሥራ በሙሉ የሚተባበር መሆኑን በመግለጽ ደብዳቤ ጻፈ፡፡ ከዚሁ ጋር አከታትሎ ቶርስ የተባለው የአሜርካ ኩባንያ እስከ 49 በመቶ ኢኩቲ ካፒታል የሚያወጣ መሆኑን ገለጸ፡፡

በሰሜን አውሮፓ ከሜድትራንያን አገሮች ጋር ያለን የንግድ ልውውጥ በሁለቱም በኩል ተመዛዛኝ በመሆኑ፣ ሁለት አነስተኛ መርከቦች አሠርተን በዚህ መስመር ቢሠሩ ትርፍ የሚያስገኝ መሆኑን በቀድሞው ጥናታችን ደርሰንበታል፡፡ በመሀሉም የአሰብ ዘይት ማጣሪያ እንዲሠራ በወሰኑ፣ ድፍድፍ የሚመጣው ከውጭ አገር ስለሆነ የማጣሪያው ማኀበር ለማስጫኛ የሚከፍለው ገንዘብ ወደውጭ ከሚሄደው እኛው ዘንድ እንዲቀር ለማድረግ አንድ የዘይት ማስጫኛ መርከብ መግዛትና ይህን ሥራ መውሰድ የንግድ መርከብ ማኀበር ለማቋቋም ያለንን ሐሳብ በተጨማሪ የሚደግፍ ሆነ፡፡ አሰብ ላይ የሚቋቋመው የዘይት ማጣሪያ በመጀመርያው ዓመት 5ዐዐ‚ዐዐዐ ቶንስ ድፍድፍ ከውጭ ማምጣት አለበት፡፡

ለዚሁ የኢትዮጵያ 4,267,500 ዶላር የመርከብ ኪራይ ይከፍላል፡፡ በተደረገው ጥናት የምናሠራው 33‚000 ቶንስ የዘይት መጫኛ መርከብ በዓመት 260,000 ቶንስ ዘይት ለሌላ ሥፍራም ስለሚጭን፣ ጠቅላላ የዓመት ገቢ የኢት ዶላር 6,197,200 ነው፡፡  የሥራ ማስኬጃና ሌላው ወጭ ተቀንሶ፣ በጠቅላላው በዓመት የኢት ዶላር 3,281,100 ለማትረፍ የሚቻል መሆኑ ታውቋል፡፡ ሌላውን ወጪ አሁን በትክክል ለማወቅ ስለማይቻል፣ የተጣራው ትርፍ ከዚህ ያነሰ መሆን አለበት፡፡

የተዘጋጀው ጥናት ለቬርሎሜ ማኀበር ተሰጥቶ አጥንተው አስተያየታቸውን እንዲያቀርቡ ተጠየቁ፡፡ እነሱም በበኩላቸው አጥንተው በኢትዮጵያ፣ በሰሜን አውሮፓና በሜድትራንያን አገሮች መካከል ያለው ንግድ በገቢና በወጪ ዕቃ መጠን የተስተካከለና ብዙም የማይለያይ ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ የንግድ ዕቃ 30 በመቶ በኢትዮጵያ መርከቦች ቢጭን እንኳን፣ ይህን ዕቃ ለማመላለስ ሁለት እያንዳንዳቸው ስድስት ሺሕ ቶንስ ክብደት ያላቸው መርከቦች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህም መርከቦች በዓመት ዘጠኝ ጊዜ መመላለስ አለባቸው፡፡ በዚሁ የሚገኘው ጠቅላላ ገቢ የኢት ዶላር 5,500,000 ስለሚሆን፣ ሥራ ማስኬጃውንና ሌላውንም ወጭ ሁሉ ችሎ በዓመት የኢት ዶላር 75ዐ,ዐዐዐ የተጣራ ትርፍ ማግኘት የሚቻል መሆኑን ደርሰውበታል፡፡ በጠቅላላው ይህ ሥራ 7.5 በመቶ የተጣራ ትርፍ የሚያስገኝ መሆኑን ታውቋል፡፡

የእህል ጐተራም አሰብና ምፅዋ ላይ ተሠርቶ እህል እያከማቹ ወደ ሚያስፈልግበት ሥፍራ መሸጥም ለመርከቦች ሥራ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ ትርፍ ያለው መሆኑ ታውቋል፡፡ የመርከብ ማኀበር ተቋቁሞ እንዲሠራ እንዲፈቀድ ጉዳዩ ለኘላኒንግ ቦርድ ቀርቦ ለጊዜው በኢት ዶላር 50,000 ካፒታል ኩባንያው እንዲቋቋምና፣ ከቬርሎሜ የቀረበውን የመርከብ ዋጋ፣ የክሬዲት ሁናቴና የሥራ አመራር መርምሮ የሚያዋጣ ከሆነ፣ ኩባንያው እንዲስፋፋ ይደረጋል ተብሎ የተሰጠው ውሳኔና በባህር ክፍል መሥሪያ ቤት፣ «ቶሮስ ኢንቨስትመንት ኢንኮርፖሬትድ» እየተባለ በሚጠራው የአሜሪካ ኩባንያና «ቬርሎሜ ዩናይትድ ሺፕ ያርድስ» በተባለው የሆላንድ የመርከብ ሥራ ኩባንያ መካከል በተደረገው መሠረታዊ ስምምነት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ከተመከረበት በኋላ ውሳኔ ተሰጠ፡፡

«ቶሮስ ኢንቨስትመንት ኢንኮርፖሬትድ» የተባለው የአሜሪካ ኩባንያና «ቬርሎሜ ዩናይትድ ሺፕ ያርድስ ኤንድ ኢንጂነሪንግ ካምፓኒ» ከተባለው የሆላንድ ኩባንያ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ማኀበር እንዲቋቋም ባለአክሲዮኖቹ ተሰብስበው የቦርድ አባሎች መርጠው ቦርዱም ሰብሳቢ መርጦ ሥራውን ጀመረ፡፡ ቦርዱ በመጀመሪያው ስብሰባ የተነጋገረበት ጉዳይ ከቬርሎሜ ቀርቦ ስለነበረው የመርከቦች ዋጋ፣ የክሬዲት ሁናቴና የሥራ አመራር ሐሳብ ነበር፡፡ ሁለቱን የጭነት መርከቦች እያንዳንዳቸውን በኢት ዶላር 5,875,000 የዘይቱን መርከብ በኢት ዶላር 11,625,000 ለመሥራት 61/2 በመቶ  ወለድ ጋር በዘጠኝ ዓመት የሚከፈል ለዚሁ ሥራ የሚውል ክሬዲት ለማስገኘት፣ የማኀበሩን ሥራ ለመምራት፣ ኢትዮጵያዊ ሠራተኛ ለማሠልጠንና አክሲዮን በመግዛት ከማኀበሩ ሀብት ተካፋይ ለመሆን ሐሳብ ቀረበ፡፡

እንደዚህ ያለ የተሟላ መተባበር የሚያዳግት መሆኑ ቢታወቅም፣ ሌሎችም መርከብ ሠሪዎች ሳንጠይቅ ያቀረበውን ሐሳብ መቀበልም ቅር የሚያሰኝ በመሆኑ፣ ኢኩቲውን የሚያዋጡት የኢትዮጵያ መንግሥትና የቶሮስ ሰዎች ያሉበት ኮሚቴ ተሹሞ፣ አውሮፓ ሄደው አማካሪ ቀጥረው የመርከብ ዋጋና ሌላውንም ሁናቴ እንዲያጣሩ ቦርዱ ወስኖ፣ መሐንዲስና አንድ የማሪን ኤክስፐርት ከባህር ክፍል፣ ሁለት ሰዎች ከቶሮስ ተመርጠው ወደ አውሮፓ ሄደው አማካሪ መሐንዲስ ቀጥረው በአማካሪው አማካይነት ለአሥራ ስድስት መርከብ ሠሪዎች፣ ለሚፈለጉ መርከቦች ዋጋ እንዲያቀርቡ፣ ክሬዲትም ለማስገኘት የሚችሉ፣ የመርከቡን ኩባንያ ሥራም ለመሥራት የሚችሉ መሆናቸውንና የሚጠየቁትስ ግዴታ ምን አንደሆነ እንዲያስታውቁ ጥያቄ ተልኮ ስድስት ያህል መልስ ሰጥተው ነበር፡፡

ውጤቱ ሲመረመር ቬርሎሜ አቅርቦት በነበረው የመርከቦች ጠቅላላ ዋጋና ተጠይቆ በቀረበው አነስተኛ ዋጋ መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት የኢት ብር 1,062,500 ነበር፡፡ ከዚህ ሌላ በክሬዲትና በማኀበሩ ሥራ አመራር በኩል ቬርሎሜ አቅርቦት ከነበረው ሁናቴ የተሻለ ለማግኘት አልተቻለም፡፡ የኢኮኖሚውንም ጥናት አማካሪው እንደገና አጥንቶ አጥጋቢ መሆኑን አረጋገጠ፡፡

ቬርሎሜ ዩናይትድ ሺፕ ያርድስ አቅርቦት የነበረው ዋጋ አነስተኛ ሆኖ ከተገኘ በኋላ እንደገና የኢት ዶላር 250,000 ከጠቅላላው ዋጋ ቅናሽ አደረገ፡፡ የቬርሎሜን ዋጋና ሌላውንም የሥራ መተባበር ሐሳብ እንዲቀበሉና እንዲስማሙ ለሰብሳቢውና ለምክትል ሰብሳቢው ቦርዱ ሥልጣን ሰጣቸው፡፡ በዚሁ መሠረት ከ6.5 በመቶ ወለድ ጋር በዘጠኝ ዓመት የሚከፈል ክሬዲት የሚከፈል ከሆላንድ ንግድ ባንክ ለመውሰድ፣ ከፍ ብሎ በተዘረዘረው ዋጋ መሠረት መርከቦች ለማሠራት፣ የማኀበሩን የንግድ ሥራ ቬርሎሜ እንዲሠራ ለማድረግ፣ ኢትዮጵያን ሠራተኞች ለማሠልጠንና የኢትዮጵያ መንግሥትና ቶሮስ መርከቦቹን በማስያዝ ከሚሰጠው የክሬዲት ገንዘብ ዋስትና ውጪ ለሚተርፈው በየበኩላቸው ተጨማሪ ዋስትና እንዲሰጡ ውል ተፈረመ፡፡ ይህ ስምምነት ለቦርዱ ቀርቦ ሁለቱ ወገኖች የቀረባቸውን የካፒታል ወጪ (በኢትዮጵያ በኩል ሊከፈል የሚገባው የገንዘብ መዋጮ የኢት ዶላር 1,813,000 እንዲከፍሉና ማኀበሩ ሥራውን አስፋፍቶ እንዲሠራ ተስማምቶበት ጉዳዩ ለባለአክሲዮኖቹ ቀርቦ እንዲፀድቅ ወሰነ፡፡

የመርከቦቹን ዋጋ የኢት ዶላር 23,375,000 ነው፡፡ ለሠራተኞች ማሠልጠኛ፣ ለመለዋለጫ ዕቃ መግዣ፣ መርከቦች ሥራ ሲጀምሩ አስፈላጊውን ዕቃና ስንቅ ማደራጃ ለክሬዲት ለኢንሹራንስ ዋጋና ለድንገኛ ወጭ ጭምር 3ዐ በመቶ ወይም የኢት ዶላር 7,112,500 ተጨማሪ ብድር ያስፈልጋል፡፡ የብድሩ ጠቅላላ ድምር የኢት ዶላር 30,487,000  ይሆናል፡፡ ይህም እንደተገለጸው ሁሉ ከ6.5 በመቶ ወለድ ጋር በዘጠኝ ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ ነው፡፡ ወደ ውጭ በክሬዲት ለሚሸጥ ዕቃ ሁሉ የፖለቲካ ሪስክ ኢንሹራንስ ያስፈልገዋል፡፡ ይህንን የሚከፍለው ገዥው ነው፡፡ ለክሬዲት ኢንሹራንስና ለብድር ወጭ የሚከፈለው 3.25 በመቶ ነው፡፡ ይህም 30 በመቶ ለሪዘርቭ ከተያዘው ይከፈላል፡፡ ከሆላንድ የክሬዲት ኢንሹራንስ ባንክ ባለሥልጣኖች ጋር በተነጋገርኩ ጊዜ የኢንሹራንስ ዋጋ 3.25 በመቶ የሆነው የኢትዮጵያ ባላንስ ኦፍ ፔይሜንት መልካም ስለሆነና የኢኮኖሚ ዕድገትዋም እየተራመደ በመሄዱ ነው ክፍያው እስከዚህ ያነሰው እንጂ፣ ከዚህ የሚበልጥ የሚያስከፍሉ መሆኑን ገልጸውልኛል፡፡

መርከከቦቹ ሁለቱ በአንድ ዓመት ከሁለት ወር፣ አንድ የዘይት መጫኛ መርከብ በዓመት ከስምንት ወር ተሠርተው እንዲያልቁ ይዘጋጃሉ፡፡ ጠቅላላውን የክሬዲት፣ የሥራ አመራር፣ የመርከብ ሥራ ስምምነት፣ ለእያንዳንዱ መርከብ የተፈጸመውን የሥራ ስምምነት፣ ለማሠልጠኛና ለሪዘርቭ ተብሎ የነበረው ከ2.5 በመቶ አምስት በመቶ (5 በመቶ) እንዲሆን የተስማማበትን፣ ተቀጥሮ የነበረው አማካሪያችን በቴክኒክና በኢኮኖሚ ረገድ ፕሮጄውን በመደገፍ ያዘጋጀውን ጥናትና የቦርዱ ሰብሳቢ ምክትል ሰብሳቢ ለቦርዱ አቅርበው የፀደቀውን ሪፖርት ግልባጭ አያይዤ አቅርቤያለሁ፡፡  በስምምነቱ በኩል መርከቦቹ በተባለው ጊዜ ሳይሠሩ ቢቀሩ ወይም ከተስማማንበት የአሠራር ዝርዝር ውጭ ተሠርተው ቢገኙና እንደዚሁም፣ ደግሞ መርከቡን የሚሠራው ማኀበር የገባውን ግዴታ ሁሉ ሳይፈጽም ቢቀር መቀጫ እንዲከፍል ሆኖ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ማኀበርም በበኩሉ ለሠሪው የገባው ግዴታ ሳይፈጸም ቢቀር አስፈላጊው ቅጣት እንዲወሰንበት በስምምነቱ ተገልጿል፡፡ ሌላው ዝርዝር ሁሉ በኮንትራት አሠራር እንደተለመደው ተጠናቆ የተሠራ ነው፡፡

በመንግሥት ከመንግሥት ሲበደር ወለድና ሌላውም የብድር ወጭ ያነሰ ሆኖ የክፍያውም ጊዜ ስለሚረዝም የኢትዮጵያ መንግሥት ከሆላንድ መንግሥት ተነጋግሮ ብድር ቢያገኝ የሚሻል ነው፡፡ እስከዚያው በዚሁ ሥራውን መጀመሩ ጠቃሚ ነው፡፡  ከሆላንድ ባንክ ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግሬ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲጠይቅ ብድር ሊገኝ የሚቻል መሆኑንና የንግድን ባንክ ብድር በመንግሥት ብድር ለመለወጥ የሚቻል መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ እስከዚያው መርከቦች መያዣ ተሰጥተው ለሚተርፈው የኢትዮጵያ ድርሻ ብቻ መንግሥት ዋስትና መስጠት አለበት፡፡ መንግሥት ዋስትና የሚሰጠው ለጥቂት ገንዘብ ስለሚሆን ከባድ ኃላፊነት የለበትም፡፡

በዚህም ሥራ የሚተባበሩት የአሜሪካንና የሆላንድ ዜጎች ወደፊት በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ሁሉ በመርከብ ኩባንያ በኩል ስለሚያሰማሩ ሐሳቡ የሚደገፍ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሥራዎች ለመጀመር ከሚስተር ፖል ገቲ የሚፈለገው መተባበር ተስፋ ያለው ነው፡፡ የመርከብ ማደሻም ለመሥራት ጉዳዩ በጥናት ላይ ይገኛል፡፡ አሁን በቅርቡ በመስኩቦች 400 መርከቦች ለማሠራት ስለወሰኑ የመርከብ ዋጋ አሁኑኑ ከፍ ማለት ስለጀመረ፣ ከዚህ ጊዜ ቀደም ብለን ይህን ስምምነት ከሆላንድ ሰዎች ጋር መፈጸማችን ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ሳይወሰን ውሉ ያደረ እንደሆነ ሆላንዶች በምክንያት ስምምነቱን ከማፍረስ አይመለሱም፡፡ ይህንኑ የመስኰቦቹን መርከብ ለማሠራት መሽቀዳደም ተመልክተን፣ በተጨማሪ አንድ መርከብ በስድስት ወር ውስጥ በአሁኑ ዋጋ ለማዘዝ ውለታ አስፈርመናቸዋል፡፡  ካልፈለግን ግዴታ የለብንም፡፡

እንደሌላው ኢንዱስትሪ ሁሉ የንግድ መርከብ ሥራም እስኪቋቋምና እስኪደራጅ ድረስ መጠበቅን ይፈልጋል፡፡ በሌሎችም አገሮች መንግሥት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በናሽናል ባንክ በኩል ነጋዴዎች ሁሉ ከአሥር እስከ አሥራ አምስት (10 -15 በመቶ) ዕቃዎች በአገር መርከቦች እንዲጭኑ ያደርጋሉ፡፡ ይህ የሚሆነው በአዋጅ ሳይሆን በተቃዋሚ ትዕዛዝ ነው፡፡ ለአንድ መንግሥት ይህ አድራጎት ሕጋዊ መብቱ ነው፡፡

ይህ ስምምነት አሁኑኑ ፀድቆ በኢትዮጵያ በኩል የቀረው የካፒታል መዋጮ ተከፍሎ ማኀበሩ ሥራውን እንዲቀጥል እንዲወስን አሳስባለሁ፡፡ ከተማ አበበ፣ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ማኅበር ፕሬዚዳንት በዚህም መሠረት የኢ.ን.ነ.መ እና ቶሮስ ኢንቨስትመንት ኢንኮርፖሬትድ የተባለው ኩባንያ ቀደም ሲል በተጠቀሰው ፍሬ ሐሳብ መሠረት መጋቢት 1 ቀን 1956 የሁለቱም ተወካዮች ባሉበት ስምምነቱን አፀደቁ፡፡ ስምምነቱን ካፀደቀ በኋላም በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ የሚከተለው ትዕዛዝ እንዲፈጸም ለገንዘብ ሚኒስቴር የሚከተለውን ደብዳቤ ግንቦት 22 ቀን 1956 ዓ.ምም ጽፈዋል፡፡ ሙሉ ትዕዛዙ የሚከተለው ነበር፡፡

ለክቡር አቶ ይልማ ዳሬሳ

የገንዘብ ሚኒስትር

አዲስ አበባ

ስለኢትዮጵያ ንግድ መርከብ መቋቋም ከኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ማኀበር ቦርድ ሰብሳቢ ከክቡር አቶ ከተማ አበበ ግንቦት 17 ቀን 1956 ዓ.ም. የተጻፈው ማስታወሻ ግንቦት 18 ቀን 1956 ዓ.ም. በተደረገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ቀርቦ ንግግር ከተደረገበት በኋላ፡-

  1. በባህር ክፍል፣ በቴክኒክ ኤጀንሲና በፕላኒንግ ቦርድ ኮሚቴ ተጠንቶ በቀረበው ሐሳብ መሠረት የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ማኀበር መቋቋም የሚጠቅም መሆኑን በመረዳት ቶርስ ኢንቨስትመንት ኢንኮርፖሬትድ ከተባለው የአሜሪካ ኩባንያና ቬርሎሜ ድናይትድ ያርድስ ኤንድ ኢንጂነሪንግ ካምፓኒ ከተባለው የሆላንድ ኩባንያ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ድርሻ ካፒታል (49 በመቶ) ሆኖ፣ የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ማኀበር እንዲቋቋም በመጋቢት 8 ቀን 1956 ዓ.ም. በተደረገው ስብሰባ የተወሰነ ስለሆነ፣
  2. ቬርሎሜ ከተባለው ኩባንያ የቀረበው የመርከቦች ዋጋ፣ የክሬዲት ሁኔታና የሥራ አመራር ስምምነትና የኢኮኖሚውም ሁኔታ ለሥራ መጀመር ያህል በአነስተኛ ካፒታል በሚቋቋመው ማኀበር ተጠንቶ፣ የመጨረሻው ስምምነት ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ጉዳዩ በተቋቋመው ማኀበር የዳይሬክተሮች ቦርድና በዚሁ ሥራ ችሎታ ባለው የአሜሪካ ድርጅትና በባህር ክፍል ኤክስፐርቶችም የተጠና በመሆኑ፣
  3. በኢኮኖሚክስ በኩል ደግሞ ከሆላንድ የንግድ በአንድ በጠቅላላው ማኀበሩ የሚያበድረውን የኢት ዶላር 30,487,000 ብድር በመቶ ስድስት ተኩል (5) ወለድ ጋር በዘጠኝ ዓመት ለመክፈል የሚቻል ከመሆኑም በላይ በመቶ ሰባት ተኩል (ከ7.5) ሒሳብ በዓመት የተጣራ ትርፍ ለማግኘት የሚቻል ስለመሆኑ ከቦርዱ ማረጋገጫ ስለቀረበ፣

4  በስምምነቱ መሠረት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሊያዋጣ ከሚገባው ካፒታል ቀሪው የኢት ዶላር 1,813,000 (አንድ ሚሊዮን ስምንት መቶ አሥራ ሦስት ሺሕ የኢት ብር) እንዲከፍል ስላስፈለገ፣

  1. የተደረገው ጥናት ስምምነት ጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱ ስምምነቱ ፀድቆ ከሆላንድ የንግድ ባንክ በተገኘው ዶላር 30,487,000 (ሰላሳ ሚሊዮን አራት መቶ ሰማንያ ሰባት ሺሕ የኢት ብር) የመርከቦች ሥራ እንዲቀጥል ሆኖ የወለዱን መጠን ለመቀነስ የመክፈያውንም ጊዜ ለማራዘም ይቻል የሚል ነበር፡፡

መጋቢት 30 ቀን 1956 ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዩጵያ የንግድ ማኀበር ስለማቋቋም ለገንዘብ ሚኒስትር የተጻፈው ደብዳቤም የሚከተለው ነበር፡፡

ለክቡር አቶ ይልማ ዳሬሳ

የገንዘብ ሚኒስትር

አዲስ አበባ

የኢትዩጵያ የንግድ ማኅበር ስለማቋቋም ከባህር ክፍል የቀረበው የስምምነት ሐሳብ መጋቢት 8 ቀን 1995 ዓ.ም. በነበረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ቀርቦ ንግግር ከተደረገበት በኋላ፣

  1. የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ማቋቋም ማስፈለጉን በመገንዘብ፣
  2. የዚህም ማኀበር መቋቋም ጠቃሚነት በባህር ክፍል፣ በቴክኒካል ኤጀንሲና በኘላኒንግ ቦርድ ኮሚቴ ተጠንቶ የተደገፈ መሆኑን በመረዳት፣
  3. ኩባንያው ተቋቁሞ መርከብ በመግዛት የንግድ ሥራ ቢጀምር ከኢትዮጵያ ወደ ኢሮፕ ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ለመርከብ ጭነት የሚበቃ ሸቀጥ ስለሚገኝ የሚገዙት መርከቦች ሊሠማሩ የሚችሉበት መስመር ስለመኖሩ የታሰበውን ማረጋገጫ በመቀበል፣
  4. ኩባንያው የሚቋቋመው ዶላር 50,000 የኢት ብር ካፒታል ሆኖ ከዚሁ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በመቶ አርባ ዘጠኝ (49 በመቶ) ሒሳብ በቅድሚያ የሚያወጣው ዶላር 6,250 የኢት ብር መሆኑንና ማኀበሩ በመጠኑ ካፒታል ተቋቁሞ ሥራ ከጀመረ በኋላ የማኀበሩን ሥራ ማስፋፋት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ የማኀበሩ ሙሉ ካፒታል ዶላር 3,750,000 የኢት ብር በሙሉ እንዲወጣ ቢያስፈልግ በመንግሥት ድርሻው ዶላር 1,837,500 የኢት ብር ማዋጣት የሚኖርበት መሆኑን በማወቅ፣
  5. በንግድ መርከብ ሥራ አመራር ልምድ ካላቸውና ካፒታልም ከሚያዋጡ የውጭ አገር ኩባንያዎች ጋር በመተባበር በሥርዓቱ የሚጠቅም መሆኑን በመረዳት፣

ቶሮስ ኢንቨስትመንት ኢንኮርፖሬትድ የተባለው የአሜሪካን ኩባንያና ቬርሎሜ ዩናይትድ ሺፕ ያርድስ ኤንድ ኢንጂነሪንግ ካምፓኒ ከተባለው የሆላንድ ኩባንያ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ማኀበር እንዲቋቋም ሲል ጉባዔው የተስማማበት ሐሳብ ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀርቦ፣ በዚሁ በቀረበው ሐሳብ መሠረት እንዲፈጸም ለመፈቀዱ መጋቢት 23 ቀን 1956 ዓ.ም. በቁጥር አ/226 ስለተጻፈልኝ፣ ከዚህ በላይ እንደተመለከተው እንዲፈጸም ይደረግ ዘንድ በማክበር አስታውሳለሁ፡፡

ከማክበር ሰላምታ ጋር፣ ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ

ቀጥሎም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ለገንዘብ ሚኒስቴር የሚከተለውን ደብዳቤ አከታትሎ ጻፈ፡፡ ፍሬ ሐሳቡም የሚከተለው ነበር፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ብድሩ በሆላንድ መንግሥት ብድር ሊለወጥ ስለሚቻልበት ሁኔታ ከሆላንድ መንግሥት ጋር ንግግር እንዲቀጥልና የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሊያዋጣ ከሚገባው ካፒታል ቀሪው ኢት ዶላር 1,813,000 (አንድ ሚሊዮን ስምንት መቶ አሥራ ሦስት ሺሕ) የኢት ብር እንዲከፈል ጉባዔው የተስማማበት ሐሳብ ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀርቦ፣ በዚሁ መሠረት እንዲፈጸም ለመፈቀዱ በቁጥር 2142/23/56 ስለፈጻመልን፣ ከዚህ በላይ በተመለከተው መሠረት እንዲፈጸም ያደርጉ ዘንድ በማክበር አስታውቃለሁ፡፡

ከማክበር ሰላምታ ጋር፣ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር

በአንድ በኩል ውይይቱ፣ የግዥ ሥራና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራት እየተከናወኑ በሌላ በኩል ደግሞ የንግድ መርከብ ሥራ ሕጋዊ ለማድረግ ዝግጅት ማድረግ ተጀመረ፡፡  የንግድ መርከብ ጉዳይን ሕጋዊነት ለመስጠት ይቻል ዘንድም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኘላኒንግ ቦርድ ኮሚቴ በ27/6/56 ስብሰባ አካሄደ፡፡ ቃለ ጉባዔውም እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

«የፕላኒንግ ቦርድ ኮሚቴ 27/6/56 በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የስብሰባ አዳራሽ ከእኩለ ቀን በላይ ስብሰባ ተደርጓል፡፡ በዚህም ስብሰባ ክቡር ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ክቡር አቶ ይልማ ደሬሳ፣ ክቡር ባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ ክቡር ብላታ ግርማቸው ተክለ ሃዋርያት፣ ክቡር አቶ ጌታሁን ተሰማ፣ ክቡር አቶ ገብረ መስቀል ክፍለ እግዚ፣ ክቡር አቶ ምናሴ ለማ፣ ክቡር አቶ ከተማ አበበ፣ ከባህር ክፍል መሥሪያ ቤት አቶ ወርቁ ሀብተወልድ፣ አቶ ሀብተአብ ባይፈሩ ተገኝተው ነበር፡፡

የቦርዱ ኮሚቴ በ26/6/56 ባደረገው ስብሰባ ስለመርከብ ንግድ ጉዳይ በአስቸኳይ የሕጋዊ መልክ ማስያዝ ማስፈለጉና  የሁለተኛው አምስት ዓመት ፕላን ይህን የመርከብ ሥር ጥቅም በመረዳት ዓይነተኛ ሥራ ሊሰጠው ወዲያውኑ ለሥራው አጀማመር ዕርምጃ መውሰድ ይገባ እንደነበር፡፡ ክቡር አቶ ይልማ ደሬሳ ለካምፓኒው ማቋቋሚያ 50‚000 ብር ውስጥ 1/4 በማስቀመጥ የመርከቡ ንግድ ሥራ ስምምነት መሠረታዊ ዕርምጃ ቢወሰድም እስከ 30 ቀን ድረስ የመጨረሻ ስምምነት ወይም አለመስጠት መግለጽ እንደሚያስፈልግ፣ መርከቦችን ያለጨረታ ወይም በጨረታ ለመወሰን ቢያስቸግርም የውጭ ድርጅቶች ድርሻ 51 በመቶ በመሆኑ ለራሳቸው ጥቅምና ትርፍ ሲሉ የተቃና አመራር በይበልጥ የሚስቡበት ስለሆነ ይህ ሁኔታ ራሱ እንደ ጋራንቲ ሊገመት ስለሚችል ሐሳቡ ተቀባይነት አገኘ፡፡

በዚህም መሠረት መጋቢት 18 ቀን 1956 በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መዝገብ ቁጥር 4551/56 ተመዝግቦ ሲቋቋም የነበረው ካፒታል ብር 50,000 ሲሆን፣ በዚህም ይዞታ ውስጥ 49 በመቶ የኢትዮጵያ ድርሻ 51 በመቶ ደግሞ በውጭ አገር ከበርቴዎች የተያዘ ነበር ኮርፖሬሽኑ እንደተቋቋመ ቬርሎሜ ከተባለ የኔዘርላንድ ኩባንያ ጋር የስምምነት ውል ተፈራርሞ ሁለት ደረቅ ዕቃ ጫኝ መርከቦች እያንዳንዳቸው 6‚550 ቶን የመሸከም ችሎታ ያላቸው፣ «የይሁዳ አንበሳ» (በኋላ «የኢትዮጵያ አንበሳ»)፣ «ንግሥት ሳባ» የተባሉት፣ አንድ 34,075 ቶን የመሸከም ችሎታ ያላትና «ላሊበላ» የተለየች ነዳጅ ጫኝ መርከብ በጠቅላላው ሦስት መርከቦች በ31.6 ሚሊዮን ብር እንዲሠሩ ታዘዘ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አክሲዮን ማኅበር በመጋቢት ወር 1958 «የይሁዳ አንበሳ» የተባለች የመጀመርያውን መርከብ ተረክቦ በቀይ ባህርና በሰሜን አውሮፓ መደበኛ ሥራውን ቀጠለ፡፡ በተከታታይ «ንግሥት ሳባ» እና «ላሊበላ» የተባሉትን መርከቦች በሚያዝያና በነሐሴ 1958 አሠማራ፡፡ ነገር ግን የድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴ ሳይጠናከር የስዊዝ ቦይ በመዘጋቱና በሦስት መርከቦች ብቻ ንግዱ ሥራ ሳያቋርጥ መሥራት ባለመቻሉ «አዱሊስ»፣ «ጣና ሐይቅ»፣ «አሸንጌ ሐይቅ»፣ «ዝዋይ ሐይቅ» ይባሉ የነበሩትን ያገለገሉ መርከቦች ገዝቶ አሠማራ፡፡ በዚህ ጊዜም በአንድ አገር የራሱ የሆነ የንግድ መርከብ አገልግሎት መኖር አስፈላጊና አስተማማኝ መሆኑን በተግባር አረጋገጠ፡፡

ግንቦት 20 ቀን 1956 ዓ.ም.

ማስታወሻ

ለክቡር ሌተና ጄኔራል መርዕድ መንገሻ

የመከላከያ ሚኒስትር

አዲስ አበባ

ክቡር ሆይ፣

የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ኩባንያ ስለማቋቋም ጉዳይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መጋቢት 8 ቀን 1956 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ከተነጋገረበት በኋላ ማኀበሩ እንዲቋቋም ወስኖ እንደነበር በማክበር አስታውሳለሁ፡፡

በዚሁ ውሳኔ መሠረት ማኀበሩ መጋቢት 18 ቀን 1956 ዓ.ም. ተቋቋመ፡፡  ለማኀበሩ ሥራ የሚያስፈልጉትን ሦስት መርከቦች ለማሠራት ቀደም ብሎ ቬርሎሜ ከተባለው የሆላንድ ኩባንያ ቀርቦ የነበረውን ዋጋና ሌላም ኮንዲሲዮን መነሻ በማድረግ በማኀበሩ ሥራ ተባባሪ ከሆኑት አሜሪካኖች ጋር አውሮፓ ሄደን የመርከብ ዋጋ፣የክሬዲት ኮንዲሲዮንና ሌላውንም ተያይዞ ያለውን ሁኔታ ሁሉ መርምረን ካጣራን በኋላ ከሆላንድ መርከብ ሠሪ ኩባንያ ቀርቦ የነበረው የመርከብ ዋጋና ሌላውም ኮንዲሲዮን ሁሉ የተሻለ ሆኖ ተገኝቶ ነበር፡፡ ተጨማሪ ካፒታል ተከፍሎ በዚሁ መሠረት የማኀበሩ ሥራ ተስፋፍቶ እንዲሠራ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲስማማ አቅርቤ የነበረውን ራፖርት ከዚህ ጋር አያይዤ ክቡርነትዎ እንዲያውቀው ልኬያለሁ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ክቡርነትዎ በሌሉበት ሐሳቡም በሚኒስሮች ምክር ቤት የፀደቀ መሆኑን በማክበር እገልጻለሁ፡፡   

ከማክበር ሰላምታ ጋር፣ ከተማ አበበ፣ የሥራ አስኪያጅ ቦርድ ሊቀ መንበር

ከዚያስ ምን ሆነ? ምን እንደሆነ በክፍል ሦስት እንመለከታለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles