ፀጉሩን አንጨብርሮ፣ ፂሙን አሳጥሮ
ጥግ ተቀምጦ ለሚታየኝ ወጣት
ሒድና ታዘዘው ስጠው አንድ ድራፍት
ቅዳላት ደብል ጂን ሒሳቡን ይርሳበት
በፂሙ መጎፈር፣ በፀጉሩ መንጨብረር
ቁጥር ፈታ በሚል በግንባሩ መስመር
ይታየኛል ቋንቋ ይታየኛል ነገር፡፡
እዛም ከጨለማው፣ ብቸኝነት ውጧት፣
ሲጋራዋን ይዛ፣ ለቆመችው ወጣት
ሒድና ታዘዛት፣ የሚጠጣ ስጣት
ምጋ በተፋችው በግጭሶች መሀል
ሴትነት ሲበደል፣ እህትነት ሲጣል
እናትነት ሲጎል
ይታየኛል ቋንቋ ይታየኛል ፊደል
ገጣሚ ኤፍሬም ሥዩም