Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን መባባስ የሰላም ዕጦት ትልቅ ቦታ አለው!

አገር በምትሻው የዕድገት ጎዳና ለመራመድ ሰላም ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ያለ ሰላም ዕድገትን ማምጣት አይቻልም፡፡ የዜጎችን ሕይወት ለመለወጥና የተሻለ አገር ለመፍጠር ከተፈለገ ሰላም መሠረት ነው፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን አገራችንን ሰላም የነሷት በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመዋታል፡፡ ሰላምን የሚያደፈርሱ ግጭቶች እዚህም፣ እዚያም ይስተዋላሉ፡፡ አንዱ ተቋጨ ሲባል ሌላው ይተካል፡፡ በተለይ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንደ አገር ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ከዚህ የጦርነት አዙሪት እስካሁን አልወጣንም፡፡ እነዚህ ሰላም የነሱን ቀውሶች በርካታ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ካስከተሉት ሰብዓዊ ቀውሶች ባሻገር ኢኮኖሚያችንን በእጅጉ ደቁሶታል፡፡ እያንዳንዷ የሰላም ዕጦት ኢኮኖሚያችን ላይ ያሳረፈው በትር ይደርስበታል ከተባለው ሁለንታናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ጎድቶታል፡፡

ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ሀብት በአብዛኛው እየተካሄደ ባለው ጦርነትና በየጊዜው በየአካባቢው የሚከሰተው ግጭት እየበላው ነው፡፡

እንዲህ ያሉ ቀውሶች ኢኮኖሚውን በእጅጉ አሳምመዋል፣ በማሳመም ብቻ ሳይወሰኑም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ዋነኛ ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ የምጣኔ ባለሙያዎች ትናንትም የሰሜኑ ጦርነት አገርን ኢኮኖሚ ጎድቷል እያሉ ነው፡፡ ትንንሽ የምንላቸው ግጭቶችና ሆን ተብለው በዜጎች ላይ ሲፈጸሙ የነበሩ ጥቃቶች የሰው ሕይወት ከመቅጠፋቸውና ንብረት ከማውደማቸው ባሻገር፣ አጠቃላይ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችን ተጭነዋል፡፡ ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ ፈጥረዋል፡፡ ነገሩን ከፍ አድረገን ስናየውም በአገር ደረጃ ኢኮኖሚያችንን እየጎዳ መጥቶ አስቸጋሪ ከምንለው ደረጃ ላይ አድርሶናል፡፡

ለውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ለዋጋ ንረት መባባስና ለተያያዥ ችግሮች ሁሉ ከዚሁ ሰላም ማጣታችን ጋር የተያያዙ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

ጦርነቱ እያደቀቀ ያለው ኢኮኖሚን ለማከም፣ ተባብሶ የሚታየውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተወሰነ ደረጃም ቢሆንም የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ ለማድረግ፣ በአጠቃላይ የታመመውን የማክሮ ኢኮኖሚ ለማከም ይረዳል የተባሉ በመንግሥት የተለያዩ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡

በተለይ በማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው ከተወሰዱ ዕርምጃዎች አንዱ ይህንን ያህል ጠቀሜታ የላቸውም ወይም አንገብጋቢ አይደሉም የተባሉ 38 ምርቶች ከውጭ እንዳይገቡ ማገድ ነው፡፡

ዕርምጃው የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ሊኖረው ቢችልም፣ ጥቅሙ ይልቃል ተብሎ ታምኖበት፣ ለእነዚህ ምርቶች ሌተር ኦፍ ክሬዲት እንዳይከፈት ውሳኔ ተላልፏል፡፡

ወደ ስድስት ሺሕ የሚገመቱ የተለያዩ ምርቶችን ከውጭ በማስገባት የምትታወቀዋ አገራችን፣ አሁን ክልከላ የተደረገባቸው ምርቶችን ቁጥር ካሠላን እጅግ ኢምንት እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ያላግባብ ይበላሉ የተባሉ ወይም የሚወጣባቸው የውጭ ምንዛሪ ያስቆጫል ብለን የምንጠቅሳቸው ምርቶች ግን አሁን መንግሥት በይፋ ክልከላ ያደረገባቸው ብቻ ናቸው ወይ? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡

የ38ቱ ምርቶች ክልከላ የሚያሳየን ያለንበት ችግር ግዝፈት ማሳያ በመሆኑ ውሳኔው አግባብ አይደለም ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ እንዲህ ባሉ ውሳኔዎች እየደገፉ መጓዝ ግድ ይላል በሚል፣ የተከለከሉ ዕቃዎች ‹መከልከል አልነበረባቸውም› የሚል ሙግት አልተነሳበትም፡፡

በእነዚህ ክልከላ በተደረገባቸው ምርቶች ብቻ ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ ማዳን ይቻል ይሆን? የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከዚህም በኋላ ቢሆን የውጭ ምንዛሪ ችግራችንን የምንወጣበት ጊዜ አጭር አለመሆኑን ተገንዝቦ፣ ሌሎች ተያያዥ ዕርምጃዎች ሊወሰዱ የሚገባ ስለመሆኑ እንድናስብ ያደርገናል፡፡

በሰሞናዊው የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ውሳኔ ሊመጣ የሚችለው ለውጥ በተለይም ኑሮ የከበደውን ሸማች የበለጠ እንዳያከብደው የሚያግዝ ከሆነ እሰየው ነው፡፡ በአንፃሩ ግን አገር በሌለ ሀብት ያለገደብ የውጭ ምንዛሪ የሚረጭባቸው፣ በሌላ አነጋገር አንገብጋቢ የማይባሉ ምርቶች እነዚህ ብቻ አለመሆናቸውን በመገንዘብ፣ የውጭ ምንዛሪ ረሃባችንን ለማስታገስ ሌሎችም ምርቶች መታሰብ አለባቸው፡፡

ከእነዚህ ክልከላ ከተደረገባቸው ምርቶች በላይ በፍፁም መግባት የሌለባቸው ብዙ ምርቶች ከመኖራቸው አንፃር የውሳኔ ጉድለት አለበት ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው ይህንን ታሳቢ ያደረገ ዕርምጃ ቢወስድ ውሳኔው አሁን ላለው ችግራችን ብቻ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው፡፡

ይህንን ሐሳብ በአጭሩ ለመግለጽ እንደ አገር በቀላሉ የምናመርታቸው፣ ነገር ግን ከውጭ የምናስገባቸው ምርቶችን በመለየት ወደ ዕርምጃው መግባት አትራፊ ያደርጋል የሚባለው ከችግር ከወጣን፣ በኋላም ለእነዚያ ምርቶች የውጭ ምንዛሪ እንዳናወጣ የሚያግዝ ይሆናል፡፡ እዚህ መሠራት ወይም መመረት እየቻሉ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን የሚያስገቡ አስመጪዎችን በማገዝ ዘላቂ አምራች መሆን የሚችሉበትን መንገድ እየጠረጉ መሄድንም ያስተምራል፡፡ ስለዚህ ክልከላውን ዜጎች እንደ መልካም አጋጣሚ የሚጠቀሙበት እንዲሆን መደገፍ፣ አምራች ዜጋ ማበራከትና ሁሌም የምንሰቃይበትን የውጭ ምንዛሪ ጫና በተወሰነ ደረጃ ማቃለል ይቻላልና እንዲህ ካሉ ውሳኔዎች ጎን ለጎን ዘላቂ መፍትሔዎች ላይም ጥሩ ፖሊሲ ሊኖረን ይገባል፡፡ ክልከላችን አሁን የገጠመንን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመሻገር ብቻ ከሆነ ግን ትርጉም አይኖረው፡፡ አገር ወደምትፈልገው ዕድገት መራመድ የምትችለውም እንዲህ ያሉ ነገሮችን አስቦ መተግበር ግድ ይለናል፡፡

አጋጣሚውንም እንደ መልካም ዕድል በመውሰድ፣ በተቻለ መጠን የሚከለከሉ ምርቶችን እዚህ ለማምረት ወደሚቻልበት ደረጃ እንዲወስደን አብሮ ማሰቡ ብልህነት ነው፡፡ ሰሞኑን በተደረገ ክልከላ ቼኮሌት የሚያመርቱ አገር በቀል ፋብሪካዎች ድጋፍ ከተደረገልን ከውጭ የሚገባውን መተካት እንችላለን የሚለው አንድ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ክልከላዎቹ የአገር ውስጥ አምራቾችን የሚያበረታታ እንዲሆንም የማስቻሉ ሥራ ጎን ለጎን ሊሄድ ከቻለ፣ አንዳንድ መጥፎ አጋጣሚዎችን ለተሻለ ነገር መጠቀም ያስችለናል፡፡

በጊዜያዊነት እንደ መፍትሔ የተወሰዱ ዕርምጃዎች ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጡ ከታሰበ ከሚወሰዱት ዕርምጃዎች ጎን ለጎን ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጡ መፍትሔዎችን አብሮ ማያያዝ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ምርታማነትን ማሳደግ ዋናው ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡ ተደጋግሞ እንደሚባለው ለችግሩ መፍቻ ሰሞኑን የተወሰዱት ዕርምጃዎች ብቻ በቂ አለመሆናቸውን አውቆ፣ በሌሎች መፍትሔ አምጪ ዕርምጃዎች መታጀብ ካልተቻለ የሚፈለገው ውጤት አይመጣም፡፡ ዋናው ነገር ግን ለኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን መባባስ የሰላም ዕጦት መሆኑን ተገንዝቦ፣ ይህንን ለማምጣት መድከም ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት