ብርሃን ባንክ ከአንድ ዓመት በፊት ያጋጠመውን ከፍተኛ የተበላሸ ብር መጠን በማሻሻል ባለፈው ዓመት ቅናሽ የታየበትን የትርፍ ምጣኔ በ2014 የሒሳብ ዓመት የተሻለ በ72.5 በመቶ ማድረግ መቻሉን አስታወቀ፡፡
ባንኩ የ2014 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት ጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንዳስታወቀው በ2014 የሒሳብ ዓመት ታክስ በፊት 583.4 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡
ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት ባጋጠመው ከፍተኛ የሚባል የተበላሸ ብድር መጠን ክምችት ምክንያት 337.7 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር ያተረፈው፡፡ በ2014 የሒሳብ ዓመት ግን 583.4 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ72.5 በመቶ ብልጫ ያሳየ መሆኑን የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጉማቸው ኩሴ ለጠቅላላ ጉባዔው ገልጸዋል፡፡ ባንኩ አጋጠመው የተባለው የተበላሸ የብድር መጠን ባለፈው ዓመት ከመገለጹ ቀደም ብሎ ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔው 708 ሚሊዮን ብር ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የባንኩ የተከታታይ ዓመታትን አፈጻጸም የሚያሳየው መረጃ በ2010 የሒሳብ ዓመት 580 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ደግሞ ከታክስ በፊት አስመዝግቦ የነበረው 708 ሚሊዮን ብር መሆኑን የባንኩ መረጃ ያስረዳል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ግን ይህ የትርፍ ምጣኔው ወደ 338 ሊወርድ መቻሉ አይዘነጋም፡፡
ባንኩ የ2014 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን በተመለከተ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጉማቸው፣ በሒሳብ ዓመቱ የተበላሹ የብድር ክምችት ለመቀነስ የተሠራው ሥራ እንዲሁም ትርፋማነትን ለማሻሻል በተሠራው ሥራ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ የተሻለ ትርፍ መገኘቱን አመልክተዋል፡፡
በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ፍተሻዎችን ስለማካሄዱ የጠቀሱት የቦርድ ሊቀመንበሩ ባንኩ የተለያዩ ለውጦችን በማድረጉ ከነበረበት ፈተና በመውጣት አሁን ወዳለበት ደረጃ ለመድረስ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
የባንኩን አቋም ለማስተካከል በበትጀት ዓመቱ በርካታ ውሳኔዎች መወሰናቸውንና በሦስተኛው ሩብ ዓመት ላይም ለባንኩ አዲስ ፕሬዚዳንት እንዲሾም መደረጉ ዋነኛ ጉዳይ ነበር ብለዋል፡፡ ባንኩ አዲሱን ፕሬዚዳንት ከመሾሙ በፊት ለሦስት ወራት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት በመሰየም ሲሠራ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ባንኩ ከነበረበት ችግር ወጥቶ ነገሮችን በማስተካከል የተሻለ ትርፍ ቢያስመዘግብም በጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተገኙ አስተያየት ለመስጠት ዕድል ያገኙ ባለአክሲዮኖች ግን ባንኩ ከሌሎች አቻ ባንኮች ጋር ሲወዳደር ያገኘው ትርፍ ዝቅተኛ ነው በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
አንዳንድ ባለአክሲዮኖች ደግሞ ከዓምና አንፃር ዘንድሮ ለውጥ ቢኖርም ባንኩን ማሳደግ በሚቻልበት ደረጃ አላሳደጋችሁትም ብለው የቦርዱንና ማኔጅመንቱን ሲወቅሱ ተደምጠዋል፡፡
ስለዚህ ባንኩን ችግር ውስጥ ከቶ የቆየው የተበላሸ ብድር ክምችት መንስዔ ግልጽ እንዲሆንላቸው ከመጠየቃቸውም በላይ በለጠ እንዲሠራ ጠንካራ አመራር ያሻናል በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹አዲስ ፕሬዚዳንት ሆኜ የተሾምኩ እንደመሆኑ ባንኩን ካለበት ሁኔታ ለማውጣትና ለመቀየር የተራው የጋራ ሥራ የሚያበረታታ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤›› ያሉት አዲሱ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ግሩም ፀጋዬ ከፋይናንስ አፈጻጸም አንፃር በመጀመርያው ሩብ ዓመት ሽግግር ላይ የነበረበት ወቅት ቢሆንም የሚያበረታታ ውጤት መመዝገቡን በዓመታዊ ሪፖርታቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ የሒሳብ ዓመቱ የባንኩ የብድር ክምችት በ24.4 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ በሒሳብ ዓመቱ ለአንድ ሩብ ዓመት ባንኮች ብድር እንዳይሰጡ በመገደቡ ምክንያት ነው እንጂ የባንኩ የብድር ክምችት ከዚህም በላይ ይሆን ነበር ብለዋል፡፡ እሳቸው ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ በኋላ የተለያዩ ለውጦች መደረጋቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ በሒሳብ ዓመቱ ለተገኘው የተሻለ ውጤትና አፈጻጸም ሁሉም የባንኩ ቤተሰቦች ባደረጉት ጥረት ጭምር መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡
የባንኩ የ2014 የሒሳብ ዓመት ሪፖርት እንደሚያሳየው የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ19.9 በመቶ በማሳደግ 26 ቢሊዮን ማድረስ ችሏል፡፡ የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞቹን ቁጥር ደግሞ በ39.7 በማሳደግ 1.6 ሚሊዮን ማድረሱን የሚያመለክተው የባንኩ ሪፖርት የብድር ክምችት መጠኑ 22.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
በ2014 የሒሳብ ዓመት 4.4 ቢሊዮን ብር ብድር የሰጠ ሲሆን፣ ይህ የብድር መጠን ከቀዳሚው ዓመት 24.4 በመቶ ብልጫ እንዳለው ታውቋል፡፡ ባንኩ ባለፈው ዓመት (2013) የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው የተበላሸ የብድር መጠን 9.8 በመቶ ሲሆን፣ ይህም የብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት በመቶ ጣሪያ እጅግ ከፍ ያለ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ባንኩ በዘንድሮ ሪፖርቱ እንደገለጸው ደግሞ 9.8 በመቶ ደርሶ የነበረው የተበላሸ የብድር መጠን ወደ 8.5 በመቶ ማውረድ መቻሉን ነው፡፡
ብርሃን ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ ገቢን በ22 በመቶ በማሳደግ 3.4 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ የሀብት መጠን 26.9 ቢሊዮን ብር መድረሱን የሚጠቁመው የባንኩ መረጃ የባንኩ ጠቅላላ ካፒታል 4.46 ቢሊዮን ብር፣ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 3.15 ቢሊዮን ብር ነው፡፡
በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 65 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 326 አድርሷል፡፡ ባንኩ 6,278 ሠራተኞች አሉት፡፡