በገነት ዓለሙ
ማክሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. የጀመረው የሳምንቱ ከፍ ያለ፣ ከፍተኛ ዜና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንደሚካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የሰላም ንግግር ነው፡፡ ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጀትና በመጻፍ ላይ እያለሁ የኢትዮጵያ መንግሥትም፣ ሕወሓትም የሰላም ንግግሩ ተሳታፊዎች ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ መግባታቸውን፣ እሑድ ይጀመራል የተባለውን ንግግርም ወደ ማክሰኞ መሻገሩን፣ እንደተባለውም ማክሰኞ ዕለት መጀመሩን፣ እስከ እሑድ ጥቅምት 20 ድረስ እንደሚቆይ መነገሩን እየሰማን ነው፡፡ ከሰላም ንግግሩ የመጀመር ዜና ጋር የሰላም ንግግር ስላስፈለገው፣ ሰላማዊ ዕልባትና መቋጫ የግድ ስለሚያስፈልገው ከሁለት ዓመት በፊት ጥቅምት 23/24 ቀን 2013 ዓ.ም. ስለተነሳው ጦርነትም የሚባለውን እየሰማን ነው፡፡ ከምንሰማቸው ነገሮች መካከል ለምሳሌ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. (ቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉት) ፀሎት ነው፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ኢትዮጵያን ያስታወሱበት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የጠየቁበት፣ በሕዝብ ላይ የሚደርሰው ስቃይ እንዲያበቃ፣ በአገሪቱ ዘለቂ ሰላም እንዲወርድ የፖለቲካ መሪዎች ፍትሐዊ መፍትሔዎችን እንዲያገኙ ጥሪ ያደረጉበት ይህ ፀሎት ራሱም ዜና ሲሆንና ዜናዎችንም ሲያጅብ ሰምተናል፡፡
በዚህ የፀሎት ዜና ከታጀቡት ዜናዎች መካከል አንዱ ለምሳሌ የፍራንስ 24 የጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት ዜና ነው፡፡ የዚህ ቴሌቪዥን በመደበኛ የምሽቱ ዜናው ያሰማንን እንዳለ እጠቅሳለሁ፡፡
‹‹Tigray has been decimated by the war which broke out in late 2020. At the time leaders of the regional dominant party, TPLF grew critical of the government for attempting to centralize power; a peace deal struck with neighboring Eritrea over disputed territory was also met with disdain. In September that year Tigray held its own regional election, an act Addis Ababa declared illegal; and fighting erupted two months later when Prime Minister Abiy Ahmed ordered an offensive accusing TPLF forces of attacking government army camp…››
ይህ በሮማው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፀሎት ዜና የታጀበውና ዓለም የሰላም ንግግሩን እየተመለከተው ነው ያለው፣ የጳጳሱንም ፀሎት ለዚህ አብነት አድርጎ በዋነኛነት የገለጸው ዜና ግን የሚገባውን ያህል የሰላም ንግግሩን የሚረዳ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እንዳነሳበት አድርጎኛል፡፡ የአንድ ጋዜጣ፣ ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን ወይም የማናቸውም ሚዲያ ተግባር የትኛውንም የጦርነትም ሆነ የሰላም ርብርብ ማገዝ ምንትስ የሚባል ነገር አይደለም የሚል መከራከሪያ እንደሚያቀርብም አውቃለሁ፡፡ እንዲህ ያለ መከራከሪያ ያነገበ ሚዲያም ቢሆን ‹‹እውነት የመናገር›› ሚናውን፣ ግዴታውንና አደራውን፣ ከዚያም የበለጠ ደግሞ ግዳጁን እርግፍ አድርጎ መተውም ሆነ፣ ‹‹አንዳንዴም በዋልድባም ይዘፈናል›› ብሎ ውሸት የመናገር ፈቃድ የሚያገኝበት ምንም ዓይነት ማመካኛ የለውም፡፡
የጥቅምት 23/24ቱ ጦርነት እንዴት ተነሳ? መላው ኮርፖሬት ሚዲያ የሚሰጠው መልስ ከሞላ ጎደል አንድ ዓይነት ነው፡፡ ልክ ይህ የፍራንስ 24 የጠቀስኩት ዜና እንደሚለው ያለ ነው፡፡
‹‹Fighting erupted… when P.M Abiy Ahmed ordered an offensive accusing TPLF forces of attacking government army camps.›› ማለትም ጦርነቱን ያፈነዳው ዓብይ አህመድ የሕወሓት ኃይሎች የጦር ሠራዊት ካምፕን (ለዚያውም የጦር ሠራዊት ካምፕ) አጥቅተውብኛል ብለው የማጥቃት ዕርምጃ እንዲወሰድ ሲያዙ ነው ይላል፡፡
ይህ በዚህ ሳምንት የሰላም ንግግሩ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ መጀመሩን መነሻ በማድረግ የምንሰማው የፍራንስ 24 ዜና፣ ወይም የዜና የጀርባ ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ ዘንድሮ መቶኛ ዓመቱን የሚያከብረው፣ በመላው ዓለም ዝናው የተናኘ ነው የሚባለው፣ የአገራችን የመንግሥት ሚዲያዎች ጭምር በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹ሙያ››ና ወግ አድርገው ‹‹ዘገባው የቢቢሲ ነው›› (ቢቢሲን ምንጭ ማድረግ አይደለም) እያሉ ‹‹ዋስ›› አድርገው የሚቆጥሩትና የሚጠሩት ቢቢሲ የ29 ጁን 2021 ዜና፣ ‹‹የኢትዮጵያ ትግራይ ጦርነት አጭር፣ መካለኛና ረዥም ታሪክ›› የሚል ርዕስ ሰጥቶ የሠራው ዜና እንዲህ ያለ፣ የጠቀስነውን የመሰለ እንደ ከብት ዕውር ድንበሩን የሚከተለው ‹‹አማኝ››፣ ‹‹ቢቢሲ እኮ ነው ይህን ያለው›› ብሎ የሚምልና የሚገዘት ተከታይ ‹‹ሠራዊት›› እንዳለው በደንብ አውቃለሁ የሚል ይመስላል ታሪኩን በአንድ መቶ፣ በሦስት መቶ፣ እንዲሁም በአምስት መቶ ቃላት ‹‹ፈትፍቶ›› እንደ አቅማችንና ችሎታችን ሲቀርብልን፡፡ በዚህ ፍትፍት ዜና መሠረት፣
‹‹The conflict started on 4 November, when the Ethiopian Prime Minister Abiy Ahmed ordered a military offensive against regional forces in Tigray. He said he did so in response to an attack on a military base housing government troops.›› መቶ ዓመት ሲከበርም ዜና የሚሠራው፣ የታሪክ የመጀመርያ ረቂቅ የሚጻፈው በዚህ ዓይነት ነው፡፡ ሁለት ዓመታት ሙሉ አልጄዚራን የመሰለ ሳይቀር (አልጄዚራ የምለው ይህንን አርማለሁ ብሎ የመጣ ሚዲያ ስለሆነ/ስለሚል ነው) ‹‹መላው ዓለም››፣ ‹‹ዘፈን›› እና ዜና ይህን የመሰለ ነው፣ የዚህ ፎቶኮፒ ነው፣ የመረጥኩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ፍራንስ 24 ይህንን ‹‹ነጠላ ዜማ›› ጉዳዩ በተነሳ ቁጥር የሚያሰማንና የሚያቀርብልን ሚዲያዎች የሚሉት እውነት ነው? አይደለም? ወደ የሚለው የገዛ ራሴ፣ የገዛ ራሳችን መልስ ሳልሄድ በፊት እነዚህ ሚዲያዎች ዝም ብለው፣ ዘለው እንዲህ ዓይነት ‹‹ዘፈን ምርጫ›› ገብተው ስሙልን ወይም ስሙን ከማለታቸው በፊት ማረጋገጥ ያለባቸውን ጉዳይ አረጋግጠዋል ወይ? የሚል ተራና ቀላል ጥያቄ አቀርባለሁ፡፡ ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን፣ ሁለት ዓመታት የሞላውን፣ ርዕስ ሊቃነ ጳጳሱ የፀለዩለትን ይህንን ጦርነት ምን ቀሰቀሰው? እንዴት ተጀመረ? ማን ጀመረው? የ‹‹ዓለም›› ሚዲያ አብሮና ተባብሮ ‹‹ሴራ መትቶ›› የሚነግረን፣ ጦርነቱን የጀመሩት ዓብይ አህመድ ናቸው፡፡ ጦርነቱ የተጫረው ዓብይ አህመድ ሠራዊታቸውን ‹‹ቀጥል››፣ ‹‹ግፋ›› ብለው ስላዘዙት፣ ሲያዙት ነው ይሉናል፡፡ ዓብይ አህመድ ዝም ብለው ከመሬት ተነስተው ሠራዊቱን አዘዙ? ጥያቄ ነው፡፡ የለም ሠራዊቱን ያዘዙት ከመሬት ተነስተውስ አይደለም፣ የሰሜን ዕዝ ተጠቃ ብለው ነው ይላል መልሱ፡፡
ይህንን መልስ፣ መልሱ ውስጥ ያለውንና ያሰመርኩበትን ብለው የሚለውን ቃል ልብ ይሏል፡፡ በዚህ መልስ ውስጥ በዚህ ‹‹የሰሜን ዕዝ ተጠቃ ብለው ነው›› በሚለው አባባል ወይም ‹‹ስቴትመንት›› ውስጥ ብለው ማለት በሌላ አነጋር የሚል ምክንያት ሰጥተው ነው ማለት ነው፡፡ የሰሜን ዕዝ ተጠቃ የሚል ምክንያት፣ ሰበብ/ማመካኛ ሰጥተው ነው ማለትም ነው፡፡ ጋዜጣ፣ ጋዜጠኛ፣ ሚዲያና የሚዲያ ባለሙያ ይህንን ለምን አያጣራም? ወይም አጣርቶ እውነት ወይም ውሸት አይልም፣ ወይም የሰሜን ዕዝ ተጠቃ የሚል የውሸት ምክንያት ሰጥተው ነው ብሎ፣ አጣርቶ፣ እውነቱን ፍርጥ አድርጎ አይናገርም? አለዚያም ዝም ብሎ አድበስብሶ ጋዜጣው ወይም ሚዲያው ውስጥ የሚተናነቀውን አድሏዊነት፣ ወገንተኛነት አያጋልጥም? ሲሆን የምናየው ግን የኋላኛው/ሁለተኛው ነው፡፡
እውነቱ፣ እርግጡ ግን ምንድነው? ዓብይ አህመድ የሰሜን ዕዝ ሳይጠቃ ተጠቃ አላሉም፡፡ መጠቃቱም አፀፋዊ ዕርምጃ የግድና በውጤትነት የሚያስከትል ነበር፡፡ ይህ የእኔ ተራ ቃል ወይም ‹‹ምስክርነት›› አይደለም፡፡ ‹‹UNDP›› (ዩኤንዲፒ) የካቲት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. (16 ፌብሩዋሪ 2020) ለተመድ ዋና ጸሐፊ በላከው ማስታወሻ የተገለጸ ምስክርነት ነው፡፡ ይህ ሚሞ በተመድ ሥርዓት የውስጥ አሠራር መሠረት የሚመሰክረው የኢትዮጵያን መንግሥት የማጥቃት ዕርምጃ ‹‹ፕሮቮክ›› ያደረገው፣ ትግራይ ውስጥ የሚገኘውን የኢትዮጵያን የሰሜን ዕዝ ዋና መምርያ በማጥቃቱና በቁጥጥር ሥር በማድረጉ በማለት ነው፡፡ የ‹‹UNDP›› (ዩኤንዲፒ) ማስታወሻ ከዚያም በላይ ይህንን ድርጊት፣ ‹‹Act of war everywhere in the world and one that typically triggers military response in defense of any nation.›› ይለዋል፡፡ ይህ የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት ድርጅት ዋና ኃላፊ፣ ይህንን ምስክርነት ከሰጡ በኋላም እንደገና በኃላፊነት የተመረጡት ባለሥልጣንና የተቋማቸው የ‹‹UNDP›› (ዩኤንዲፒ) ምስክርነት ነው፡፡ ሌላው እማኝ ቲቦር ናዥ ናቸው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስና ምናልባትም ‹‹ምስክርነታቸውን›› ሲሰጡም የአሜሪካ በአፍሪካ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (ሴክሬተሪ ኦፍ ስቴት) ነበሩ፡፡ ‹‹Tigrayan forces started the conflict with a premeditated attack on the Ethiopian army’s northern command. (The scenario was very similar to the confederacy’s attack on Fort Sumter that started the American Civil War)›› ማለት ድረስ ማን ተራማጅ፣ ማን አድሃሪ፣ ማን ግራ፣ ማን ቀኝ፣ ማን ለነፃነት፣ ማን ለባርነት እንደቆመ ሁሉ ይናገራሉ፡፡ የቲቦር ናዥ ይህ ምስክርነትና ቃል ከተነገረባቸው የተለያዩ መድረኮች መካከልም አንዱ ፍራንስ 24 እንደነበር፣ ይህንንም የዛሬ ዓመት ኅዳር 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በዚህ ጋዜጣ በዚህ ዓምድ መጻፌን አስታውሳለሁ፡፡
እና ጦርነቱ ወይም ግጭቱ የተጀመረው ዓብይ አህመድ ለዚያውም ተራ የወታደር ካምፕ ተጠቃብኝ የሚል ክስ፣ ያልተረጋገጠ ስሞታ፣ ወይም ሰበብና ማመካኛ አቅርበው ሳይሆን፣ የሰሜን ዕዝ ከእነ ሁለመናው ስለተጠቃ ነው፡፡ ላጣራ ላለ፣ እውነቱ ላይ ልድረስ ላለ፣ ሁሉንም እውነት መናገርን ‹‹ሙያ››ውና ‹‹እንጀራው›› ላደረገ ደግሞ፣ ዓብይ አህመድ የጥምቅት 23/24ቱን የእኩለ ሌሊት ዕርምጃ የወሰዱት አገር ከውስጥ ስለተወረረ ነው፡፡ በዩኤንዲፒ ቋንቋና ምስክርነት ደግሞ ‹‹An Act of War›› ስለታወጀበት ነው፡፡
እውነቱ መነገር ያለበት፣ ይህ የሚዲያው ዋነኛ ሥራና ተግባር ስለሆነም፣ የሰላም ንግግሩንም በእጅጉ ስለሚያግዝ ነው፡፡ የሰላም ስምምነቱን ለማገዝ እውነትን ማውጣትና መናገር ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ደግሞ ‹‹በዓለም ማኅበር›› ሥርዓት ውስጥ ሆኖ፣ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ስለተጠያቂነትና ሳይጠየቁ መቅረትን እዋጋለሁ፣ እታገላለሁ እያሉ ጥፋቶችንና ተጠያቂነትን አድበስብሶ ማሳለፍ፣ ‹‹ዋሽቶ ማስታረቅ›› ችግር ማቃለያ ዘዴ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ ሚዲያው የገለልተኛነትን ኃላፊነት አሽቀንጥሮ እየጣለ፣ ወይም እንዲህ ያለ ኃላፊነት የጎደለው ድጥ ውስጥ ሸርተቴ እየተጫወተ፣ ሚዛናዊና እውነታዊ ዕውቀት እንዴት አድርጎ ሊይዝና ‹‹ሊያሳውቅስ›› ይችላል? የሰላሙ ንግግር መካሄድ የጀመረው ከሌሎች መካከል ይህን በመለሰለ አንጓ ላይ፣ አድሎኛና በየቦታውና በየፊናው አንዱን ጠቅሞ አንዱን በሚጎዳ ውዥንብር ውስጥ ነው፡፡
የሰላሙ ውይይት እውነትን፣ እውነት መናገርን፣ እውነት ላይ መመሥረትን የሚፈልገውን ያህል የሚመራበትም ሕግና የሕግ ማዕቀፍ ይጠይቃል፡፡ ይህ ሕግ ደግሞ ተወያይም ሆነ ተዋዋይ ወገኖች የሚነድፉትን የበላ ልበልሃ ሕግ (Rules of Engagement) ጨምሮ፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና ከሕገ መንግሥቱ የተቀዱና ከእሱ የሚጣጣሙ ሕጎች መሆን አለበት፡፡ በተወያይ ወገኖች ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጪ ያለው የኢትዮጰያ ሕዝብ፣ ማኅበረሰብ ወይም አካል በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ‹‹ሕገ መንግሥቱን አልወደውም›› የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ አሁን ጥያቄው እንኳንስ በዚህ በሰላም ውይይት ውስጥ ሕገ መንግሥቱን ራሱን እናሻሽል ብለን በምንነሳበትና ይህንንም በምንፈጽምበት ጊዜም ቢሆን፣ ሕገ መንግሥቱን ማክበር ያለብን መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻልም፣ እንዳለ ለመለወጥም ይህንን የበላይ ሕግ ማክበር አለብን፡፡ በዚህ ምክንያት የሰላም ውይይቱ የሚመራው በዚህ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ በሉዓላዊት ኢትዮጵያ አድማስ ውስጥ ነው፡፡ እንኳንስ ውይይቱ ውስጥ የሚነሱ ጭብጦች ስለውይይቱም ወሬ አወራለሁ፣ አስተያየት እሰጣለሁ የሚል ሰው በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ መታጠርና መቀንበብ አለበት፡፡ ይህ ማለት አንድ ጉዳይ የሰላም ውይይቱ ርዕሰ ጉዳይ ይሆናል ወይ? መወያያና መነጋገሪያስ ሆኖ በዚህ ውይይት ውስጥ ይወሰናል ወይ? ለማለት ይህን ሕገ መንግሥቱ ይፈቅዳልን? ብሎ መጀመርያ ይህንን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጋር ሁልጊዜ ማስታወስ ያለብንና ብዙ ጊዜም፣ ምናልባትም እንዲህ ያለ ጉዳይ ሲያጋጥም ሁልጊዜ የምንረሳው ሕገ መንግሥቱን ያወጣው የመንግሥት የሥልጣን አካል ከፌዴራሉም፣ ከክልሎችም መንግሥት የበለጠ ሥልጣን የተሰጠው አካል መሆኑን ነው፡፡ ለዚህም ነው ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል (በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105 እንደተደነገገው) በየትኛውም ደረጃ በሚገኝ መንግሥት (የፌዴራልም ሆነ የክልል) ተራ ሕግ የማውጣት ያህል ቀላል ያልሆነው፣ ወይም አስቸጋሪ የሆነው፡፡ የምናገረው በመርህና በሕግ ደረጃ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ‹‹ማሻሻል›› ምን ያህል ቀላልና ጨዋታ እንደነበረማ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 (5) ሲሻሻል ወይም ተሻሻለ ሲባል ዓይተናል፡፡
በነገራችን ላይ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ድንጋጌ አንቀጽ 103 (5) የሕዝብ ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ ይካሄዳል ብሎ ይጀምራል፡፡ በ1996/7 ዓ.ም. በተደረገው ወይም ተደረገ በተባለው ማሻሻያ፣ ‹‹ሆኖም ቆጠራውን ለማካሄድ ከአቅም በላይ ችግር ስለመኖሩ የተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ ካረጋገጡ የቆጠራው ዘመን እንደ ሁኔታው ሊራዘም ይችላል›› ተባለ፡፡ ይህንን ማሻሻያ የሕግ አወጣጥ ሥርዓት እንደሚደነግገውና እንደሚጠይቀው አትሞ የሚያወጣ (ፐብሊሽ የሚደርግ) ግን ጠፋ፡፡
ሕግን መጣስ፣ ይህን ያህል ስፍኖ በኖረበት አገር፣ በየትኛውም ደረጃ ከሚገኝ ሕግ በላይ መሆንና የተቃዋሚ ማጥቂያ አድርጎ የመጠቀም ልማድ ገንግኖ በኖረበት አገር፣ ሕግ መከበር አለበት የምለው ይህንንም ጭምር ከቁጥር በማስገባ ነው፡፡
እናም የሰላም ውይይቱ ውስጥ ይህ ‹‹መሬት›› የማነው የሚል ጥያቄ ቢነሳ፣ ይህማ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊ ሥልጣን ነው፣ ደቡብ አፍሪካ የተሰየመ ተዋዋይ የሚወስነው ነገር አይደለም መባል አለበት፡፡
ይህንን እንደ ምሳሌ የተጠቀሰ፣ ነገር ግን እጅግ በጣም ከፍተኛ ጉዳይ ይበልጥ አጉልቶና ፋይዳውንም ለማሳየት ከውጭ ግንኙነት አንፃር እንየው፡፡ ይህ የሰላም ውይይት የሚደረገው ከሌላ ሉዓላዊ አገር ጋር ቢሆንስ? ይህ ‹‹መሬት›› የእኔ ነው፣ የለም የአንተ አይደለም የሚለው ክርክር ከሌላ የውጭ አገር ጋር ቢሆንስ ከሚለው ጥያቄ እንነሳ፡፡ በዚህም አማካይት የውጭ ግንኙነት የመንግሥት ሥልጣን ልዩ ልዩነትና ክፍፍልና ድልድልን እንመልከት፡፡ ከውጭ አገር ጋር የሚደረገውን ግንኙነት የበላይ ሆኖ የሚመራው በአጠቃላይ የማዕከላዊው መንግሥት ከፍተኛው አስፈጻሚና አስተዳደራዊ አካል ነው፡፡ በዚህ አጠቃላይ ማዕቀፍ ውስጥ ከውጭ መንግሥት ጋር ያለውን ክርክር ሕጋዊ በሆኑና በሰላማዊ መንገድ የመወሰን፣ እንዲሁም ፀጥታና የጋራ መከላከያ በሚጠበቅበት ረገድ ከውጭ አገር መንግሥታት ጋር ተባብሮ መሥራትም የዚሁ አስፈጻሚ አካል መብትና ሥልጣን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ስም ውሎችንና ሌሎችንም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የማፅደቅ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ይፈጸሙ ዘንድ ግዴታ ከመሆናቸው አስቀድሞ የትኞቹ ውሎችና ስምምነቶች በየትኛው የሥልጣን አካልና እንዴት መፅደቅ እንደሚገባቸው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ይወስናል፡፡
በዚህ አጠላቃይ መርህና ማዕቀፍ ውስጥ ደግሞ የሰላም ውሎች ሁሉ፣ የኢትዮጵያ የግዛት አገርን፣ ወይም ከግዛቱ ማናቸውንም ክፍል ወይም ገዥነትን ወይም የዳኝነትን ሥልጣን የሚያሻሽሉ ወይም በአገሪቱ ዜጎች ላይ ጉዳትን የሚያመጡ ወይም ፀንቶ የቆመውን ሕግ የሚያሻሽሉ፣ ማሻሻልን አስፈላጊ የሚያደርጉ ወይም የመንግሥት ገንዘብ ወጪ እንዲሆንባቸው የሚጠይቁ ወይም ብድሮች፣ ሞኖፖል ያለባቸው ውሎችና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ለፓርላማ መቅረብ ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያትና በዚህ አጠቃይ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ ከውጭ መንግሥት ጋር ያለውን መሬት ወይም ግዛት የሚመለከት ክርክር ሕጋዊ በሆነና በሰላማዊ መንገድ ለመወሰን፣ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያም ሆነ አልጀርስ አልጀሪያ ላይ መነጋገር፣ መፈራረም ኋላም ፓርማ ቀርቦ እንዲፀድቅ ማድረግ ይቻላል፡፡
አገሪቱን ክልል አንድ (ትግራይ)፣ ክልል ሁለት (አፋር)፣ ክልል ሦስት (አማራ)፣ ወዘተ. ብሎ ‹‹ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማው ያደረገ›› (አንቀጽ 52/2ሀ) ግብ ይዞ ኢትዮጵያን የሸነሸነው አሠራር ግን የውጭ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከአገር የሚወጣ፣ ከውጭ አገር ጋር የሚደረግ ግንኙነትን በሚመራ ሕግ የሚሸፈን አይደለም፡፡
ይህ ለምሳሌ የተጠቀሰ እንጂ ብቸኛው ጉዳይ አይደለም፡፡ የሰላም ውይይቱ እውነትም ‹‹አፍሪካ መር›› በኢትዮጵያ ባለቤነት (ኢትዮጵያን ኦውንድ) ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ለዚህም አገርና ሕዝብ መረባረብ አለበት፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡