Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

‹‹የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ›› እየተባለ እንደ ዘበት የሚነገረው ጉዳይ ጥልቅ የሆነ ግንዛቤና ትምህርት ካልተሰጠበት ውጤቱ ‹‹ውኃ ቢወቅጡት እምቦጭ›› ከመሆን እንደማይዘል በእጅጉ እየገባኝ መጥቷል፡፡ ይህንን ገጠመኝ የምጽፈውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በልማዳዊ አኗኗራችን ምክንያት ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር መራመድ ሲያቅተን ምን ያህል እንደምንጎዳ የምናውቀው በቀላሉ ይገባናል፡፡ ብዙ ጊዜ ለለውጥ ዳተኛ ወይም ተፃራሪ የሆኑ ሰዎች ምንም እንኳ በአብዛኛው ካለማወቅ የተነሳ ለውጥን ቢጠሉም፣ መጠነኛ የሆነ ግንዛቤ ካገኙ ግን የተሻለ ሁኔታ እንደሚፈጠርላቸው አልጠራጠርም፡፡ ለውጥን የምንጠላው ከጠቀሜታው ይልቅ ይዞት የሚመጣው ክስተት ስለሚያሳስበን ስለሆነ ትምህርት የግድ ይለናል፡፡ ስለዚህ ችግሮቻችንን እየነቀስን ብንማማርስ?

ትዝ ይለኛል የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ መገናኛ አደባባዩ አጠገብ ካለው መተላለፊያ ላይ አንድ አካል ጉዳተኛ በሰው ተከቦ አያለሁ፡፡ ይህ ሰው እጅ አልባ በመሆኑ እነዚያ አስገራሚ እግሮቹን በመጠቀም የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎችን ሲሠራ፣ ብዙዎች አፋቸውን ከፍተው ያዩታል፡፡ እኔ እዚያ ቦታ ስደርስ በግምት ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ዙሪያውን በስፋት ከበው በአድናቆት ሲመለከቱት፣ ይህ ለሥራ የተፈጠረ አካል ጉዳተኛ ግን በእግሮቹ መጋዝና መዶሻ በቀላሉ እየተጠቀመ ሥራውን በትኩረት ቀጥሏል፡፡ ይህንን አስገራሚ የሥራ ሰውና ሥራ ፈተው የሚመለከቱትን ‹‹አካለ ሙሉ›› ሰዎች በመገረም ሳይ፣ አንድ አዛውንት ቆም ብለው ዙሪያ ገባውን ካዩ በኋላ፣ ‹‹ኧረ ሥራ ፈታችሁ ሰውየውን ሥራ አታስፈቱት…›› ሲሉ አንዳንዶች አፈር፣ ሌሎች ደግሞ ደንገጥ እያሉ ተበተኑ፡፡ ብዙዎቹ ግን እዚያው ቆመዋል፡፡ ከመሀል አንዱ ወደ አዛውንቱ እያንጋጠጠ፣ ‹‹ሥራ በሌለበት ከየት አምጥተን እንሥራ?›› ሲላቸው፣ ‹‹ይኼው የእሱ ረዳት ሆነህ ሚስማርና እንጨት በማቀበል መጀመር ትችል ነበር…›› ሲሉት አካባቢው በሳቅ ተናወጠ፡፡

ይታያችሁ አካል ጉዳተኛው ልመናን ንቆ ራሱን በሥራ ጠምዶ አላፊ አግዳሚውን ሲያስደምም እያየ፣ ስለሥራ ግንዛቤው ያልተፈጠረለት ደግሞ ሥራ ከየት ይምጣ ይላል፡፡ ይህ ሰው አካባቢውን የሚያይበት ግንዛቤ ወይም ንቃት ስላልተፈጠረለት ይሆናል ሥራ የታለ ብሎ የሚጠይቀው፡፡ ዞር ዞር ብለን አካባቢያችንን ስንቃኝ ለሥራ ያልደረሱ ሕፃናት ሳይቀሩ የዕለት እንጀራ ፍለጋ ላይ ታች ሲሉ ይታያሉ፡፡ ሎተሪ ያዞራሉ፣ ጫማ ያሳምራሉ፣ የተለያዩ ሸቀጦችን ያቀርባሉ፣ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ በመጦሪያቸው ዘመን ጉልት የሚቸረችሩ፣ እንጀራ የሚጋግሩ፣ ልብስ የሚያጥቡ፣ ወዘተ ብዙ አሉ፡፡ ለስንት ጉዳይ የሚውል ጉልበት ያላቸው ደግሞ አላፊ አግዳሚውን በልመና ያሰለቻሉ፡፡ ልመና ‹‹ሥራ›› እስኪመስል ድረስ መተዳደሪያ ያደረጉ ሞልተዋል፡፡ በዚህ አሳፋሪ ተግባርም ንብረት ያፈሩ እንደዚሁ፡፡ በመሆኑም የሚሠሩትን የሚደግፍ፣ የማይሠሩትን ወደ ሥራ የሚያስገባ በእውቀት ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ያሻናል፡፡

በሌላ በኩል የአመለካከት ለውጥ ከሚያስፈልጋቸው በርካታ ችግሮቻችን መካከል አንደኛው ፖለቲካው ነው፡፡ ፖለቲካችን በጭፍን ጥላቻና በአሳፋሪ ፍረጃ የተተበተበ በመሆኑ ምክንያት ከኮረንቲ በበለጠ በሰዓት የተሞላ ፈንጂ መስሏል፡፡ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፡፡ የሚነበቡትን ፖለቲካ ነክ መጻሕፍት አንድ በአንድ ስታዳርሱ ውሸት፣ ራስን ከተጠያቂነት ማሸሽ፣ ሌላውን ማብጠልጠል፣ የራስን ማወደስና ማንቆለጳጰስ፣ ታሪክን ማዛባት፣ ወዘተ ነግሠው ይታያሉ፡፡ እጅግ በጣም በጣት ከሚቆጠሩ ትጉሃንና ምስጉኖች በስተቀር የብዙዎቹ ድርጊት ኧረ ወዴት እየሄድን ነው ያሰኛል፡፡ በጣም ጥቂት ከሚባሉት በስተቀር ገበያ ውስጥ ያሉ ፖለቲከኛ ነኝ የሚሉ ግለሰቦችን የጻፉዋቸውን ብዙዎችን መጻሕፍት አንብቡና ምን ያህል የሞራል መላሸቅ እንደተፈጠረ ትረዳላችሁ፡፡ በዓይናችን ያየናቸውን በርካታ እውነታዎች ሽምጥጥ አድርገው ይክዱናል፡፡ የአመለካከት ለውጥ ያልጎበኘው ፖለቲካችን ለመቻቻልና ለድርድር አልመች ያለው ሲንከባለል በመጣው ችግራችን ከሆነ ለምን ለውጥ አያሻንም? በጅምላ እየተፈራረጅንስ እንዴት እንዘልቀዋለን? አንድ ቦታ ላይ እንደ ድንበር ድንጋይ ተገትረን የምንኖረውስ እስከ መቼ ነው? ይህ የሚያሳየን የባህልና የዕውቀት ዘመቻ እንደሚያስፈልገን ነው፡፡

በአመለካከት ለውጥ ላይ ይህን ያህል ከተነጋገርን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰዎች ምን አስተያየት አላቸው የሚለውን ማየት የግድ ይላል፡፡ አብራኝ የምትሠራ የ25 ዓመት ወጣት ለውጥን ለመቀበል ደፋር መሆን ብቻ ሳይሆን ለውጥን ማቀንቀንም ያስፈልጋል አለችኝ፡፡ የ30 ዓመቱ የሥራ ባልደረባዬ ለውጥን ተግባራዊ ለማድረግ መጀመርያ ራስን መፈተሽ ይሻላል አለኝ፡፡ ቡና የሚያስተናግደን የካፌ ወጣት ማንኛውንም ለውጥ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን አስረድቶኝ፣ የበለጠ ትምህርት ቢያገኝ የተሻለ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ የሠፈሬ ግሮሰሪ ባለቤት በለውጥ ሰበብ የሚመጣው ጉዳይ ስለሚያስፈራቸው እዚያው በሩቁ አሉ፡፡ የባለቤቴ አባት ለውጥ የበለጠ ሰቆቃ ይዞ ይመጣል አሉ፡፡ ሥራ የማይወደው ተጧሪ ልጃቸው በለውጥ ምክንያት የትም አይደረስም ብሎ ደመደመ፡፡ በአንድ ወቅት ፖለቲካውን ብሎ ብሎ የሰለቸው የዚያ ትውልድ ሰው የበፊቱን እያስታወሰ ለውጥ በአንገቴ ይውጣ አለ፡፡

በሚዲያው ላይ ከለውጥ ይልቅ መናኛ ነገሮች በዝተዋል፡፡ ብዙዎቹ ወጣቶች ለውጥ ሲሹ ዕድሜያቸው የገፋው ይቃወማሉ፡፡ የፖለቲከኞችን መጽሐፍ አገላብጣችሁ ስትመለከቱ ስለነገው የተሻለ ቀን ሳይሆን፣ ያለፈውን የሰቆቃ ታሪካቸውን አስውበው ሊያቀርቡ ይፈልጋሉ፡፡ ሥራ መሥራት የማይወደውንና ታሪክን ማዛባት የተጠናወተውን ይዘን የት ድረስ እንዘልቃለን? የአመለካከት ለውጥ ግለሰብን ከጭፍን አመለካከትና ከድህነት ሲያወጣ፣ አገርን ደግሞ ለመጪው ትውልድ የተመቻቸ ያደርጋል፡፡ ከለውጥ በተቃራኒ የሚደረግ ጉዞ ግን ከሥልጣኔም ሆነ ከሀብት ያራርቀናል፡፡ በመሆኑም ለውጥን ለመቀበል እስቲ ኅሊናችንን ነፃ እናውጣው፡፡ ነፃ የወጣ ኅሊና ለውጥን ይመራል፡፡ ግጭትና ጦርነት አልላቀቅ ያሉን ለውጥ በመጥላታችን እንደሆነ እንተማመን፡፡

(ዘሪሁን ድጋፌ፣ ከላምበረት) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...