Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፖለቲካ ፓርቲዎች በመተዳደሪያ ደንቦቻቸውና በጠቅላላ ጉባዔ ወቅት የሚፈጽሟቸው ግድፈቶች ይፋ ተደረጉ

የፖለቲካ ፓርቲዎች በመተዳደሪያ ደንቦቻቸውና በጠቅላላ ጉባዔ ወቅት የሚፈጽሟቸው ግድፈቶች ይፋ ተደረጉ

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመተዳደሪያ ደንቦቻቸውና በጠቅላላ ጉባዔያቸው የሚፈጽሟቸውን የሕግና የአሠራር ግድፈቶች ይፋ አደረገ፡፡

ቦርዱ ዓርብ ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባካሄደው ውይይት፣ ከፓርቲዎች አሠራር ጋር ተያይዞ ስለሚታዩ ግድፈቶችና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሲካሄድ የነበረውን ምክክር እንደገና ለማስቀጠል የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን በተመለከተ ተነጋግሯል፡፡

በምክክሩ የፓርቲዎቹን አሠራር በተመለከተ ጽሑፍ ያቀረቡት የቦርዱ የሕግ ክፍል ባልደረባ ወ/ሮ ቀነኒ እንሰሙ የፓርቲ አመራሮችና በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎች ምርጫው ግልጽ፣ ነፃና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አለመከናወኑን መወሳቱን፣ በተጨማሪም የተለያዩ የፓርቲ የውስጥ አደረጃጀቶችን ሥልጣንና ተግባር፣ እንዲሁም አወቃቀር በመተዳዳሪያ ደንብ በግልጽ አለመደንገግና የአንዱ ሥልጣን ከሌላው ሥልጣን ጋር የሚጣረስ አሠራር መስተዋሉን አስረድተዋል፡፡

በፓርቲዎች መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ለአገር አቀፍና በየደረጃው ላሉ አገራዊ ምርጫዎች የሚታጩበት ሥርዓት በደንባቸው ውስጥ አለመካተት፣ በአባላት ላይ ስለሚወሰድ የሥነ ሥርዓትና የሥነ ምግባር ዕርምጃ በደንብ ውስጥ አለመሥፈርና በፓርቲ የውስጥ አለመግባባት ሲያጋጥም የአፈታት ሥርዓት አለመቀመጡን ወ/ሮ ቀነኒ አክለው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ በተለያዩ ደረጃ ያሉ ኃላፊዎችና አመራሮች ምርጫ በአብዛኛው በእጅ ማውጣት መከናወኑን፣ በውድድር ወቅት በቂ ዕጩ ላለማቅረብ የተጋለጡ መሆናቸውን፣ ግልጽነት የጎደለው የድምፅ ቆጠራ ሒደትና የዕጩ አቀራረብ ስለመስተዋላቸው አክለው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በጉባዔ በተመረጡ አባላትና ለቦርዱ በቀረቡ አባላት ዝርዝር ላይ ልዩነት መፈጠር የሚሉት ግድፈቶችን አብራርተዋል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔን በጊዜው ጠብቆ በሕግና ሥርዓት መሠረት ከማድረግ አኳያ በሚጠብቀው ደረጃ ያለ መፈጸም ክፍተትና ችግር እንደሚታይ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የገለጹ ሲሆን፣ ለአብነት እንኳ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹የለየለት›› የሚባል ስህተትና የሕግ ጥሰት መፍጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በሰጡት መረጃ ስለጠቅላላ ጉባዔ የተሳሳተ መረጃ ለማቅረብ መሞከራቸውን አስረድተዋል፡፡

ፓርቲዎቹ በምርጫ መመረጥ የነበረባቸውን ኃላፊዎች ምርጫ ሳያካሂዱ ሰይመው በመገኘታቸው እንደገና እንዲደግሙ መደረጉን በመግለጽ፣ የሚጠበቀው የፖለቲካ ልምምድ እንዲመጣ ፓርቲዎች ሥራቸውን ሕጉ በሚፈቅደውና በሚጠበቅባቸው ልክ እንዲሠሩ ሰብሳቢዋ ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔ በድጋሚ እንዲያካሂዱ የተጠየቁት ፓርቲዎች በድጋሚ አካሂደው የሚጠበቅባቸውን መረጃ ካላመጡ የመሰረዝ ዕድል ሊያጋጥማቸው እንደሚችል፣ እንዲሁም በሕገወጥ ድርጊት ተሰማርተው የተገኙት ራሳቸውን ተከላከሉ ተብለው ዕድል የተሰጣቸው በመሆኑ፣ የሚደረገው ክርክር ታይቶ የፈጸሙት ጥፋት ‹‹የለየለት ወንጀል›› በመሆኑ፣ የመሰረዝ ዕድል ሊገጥማቸው እንደሚችል አክለው ተናግረዋል፡፡

ቦርዱ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጠ የገንዘብ ድጋፍን አስመልክቶ፣ የድጋፍ ገንዘቡ በፓርቲዎቹ የባንክ ሒሳብ መግባቱን የሚያሳይ ደረሰኝና የኦዲት ሪፖርት ያቀረቡና ያላቀረቡ ፓርቲዎችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህ መሠረት የ2014 ዓ.ም. የገንዘብ ድጋፉን አስመልክቶ የኦዲት ሪፖርትም ሆነ ገንዘቡ ገቢ የተደረገበትን ደረሰኝ ካላቀረቡ 24 ፓርቲዎች መካከል ለአብነት ያህል ብልፅግና ፓርቲ፣ አብን፣ ኅብር ኢትዮጵያ ፓርቲ፣ ኢሕአፓ፣ እናት ፓርቲ፣ ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪ በ2013 ዓ.ም. የተደረገውን የገንዘብ ድጋፍ አስመልክቶ የኦዲት ሪፖርትም ሆነ ገንዘቡ ገቢ የተደረገበት ደረሰኝ ያላቀረቡ ስድስት ፓርቲዎች ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር፣ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄና የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ናቸው፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰጡት አስተያየት፣ የፖለቲካ ሥራቸውን እንዳያዳብሩ፣ በገዥው ፓርቲ አማካይነት የሚደርስ ግድያ፣ እንግልት፣ እስር፣ እንዲሁም የመሰብሰቢያ አዳራሽ ክልከላና የመሳሰሉ ችግሮች በማቅረብ ለቦርዱ አቤቱታ አሰምተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...