Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአማራ ክልል የተሟላ የከተማ ካርታ የሌላቸውን ይዞታዎች ሕጋዊ ሊያደርግ ነው

የአማራ ክልል የተሟላ የከተማ ካርታ የሌላቸውን ይዞታዎች ሕጋዊ ሊያደርግ ነው

ቀን:

የአማራ ክልል የከተሞችና መሠረተ ልማት ቢሮ፣ በክልሉ የተሟላ የከተማ ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሌላቸው ይዞታዎችን ሕጋዊ የሚያደርግበት አዲስ አሠራር ዘረጋ፡፡

በክልሉ ከተሞች በሥራ ላይ የነበሩት የተሟላ ሰነድ የሌላቸውና ሰነድ አልባ ይዞታዎች ሰነድ አሰጣጥ መመርያ ቁጥር 2/2005፣ 8/2007፣ እንዲሁም መመርያ 2/2011 በባህላዊ ግዥና በስጦታ የከተማ ቦታ የሚተላለፍበት መንገድ ለሕገወጥ አሠራር በር መክፈቱ አንዱ በምክንያትነት የተጠቀሰ ጉዳይ ሲሆን፣ ያንን ለማስተካከል የክልሉ የከተሞችና መሠረተ ልማት ቢሮ የተሻሻለ የአፈጻጸም መመርያ ማዘጋጀቱ ታውቋል፡፡

የተሻሻለው መመርያ በከተማ አስተዳደሮች (ሪጂዮፖሊታን፣ የከተማ አስተዳደር፣ ፈርጅ አንድ የከተማ አስተዳደር፣ ፈርጅ ሁለት የከተማ አስተዳደር) እንዲሁም በማዘጋጃ ቤት ከተሞች ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል፡፡

የከተሞችና መሠረተ ልማት ቢሮ እንዳስታወቀው፣ በአማራ ክልል በሥራ ላይ የነበረው የሰነድ አልባና ያልተሟላ ሰነድ አጣርቶ ማስተናገድ አገልግሎት በመቆሙ፣ ሕጋዊ የሆነ ከፊል የሰነድ ማስረጃ ያላቸው ባለ ይዞታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሳይስተናገዱ ቆይተዋል፡፡ ነዋሪዎች የከተማ ቦታ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዲሰጣቸው የሚያቀርቡት ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እነዚህ ተገልጋዮች ባለመስተናገዳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመፈጠሩ መመርያውን ማሻሻል አስፈላጊነቱን ገልጿል፡፡

በተሻሻለው መመርያ መሠረት በሕጋዊ መንገድ የተያዘ ይዞታ ስለመሆኑ የሚያስረዳ አግባብ ካለው አካል የተሰጠ የምሪት ካርኒ ወይም የግንባታ ፕላን፣ በሕጋዊ መንገድ (በምሪት) የተላለፈ ስለመሆኑ የተረጋገጠ የከተማ ቦታ የግብር ካርኒ ማቅረብ ከተቻለ ካርታ ማግኘት ይችላል፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተሰጠ ካርታ ያለው ሆኖ በማዘጋጃ ቤት በኩል በደብዳቤ ተጠይቆ በአዋጅ ቁጥር 47/67 ያልተወረሰ ስለመሆኑ፣ ከዞን መምርያ ማስረጃ ሲቀርብ እንዲሁ ካርታ የሚሰጥ ይሆናል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም በደርግ ዘመነ መንግሥት በምሪት የተገኘ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ወይም የቤት ባለቤትነት ደብተር ካለው፣ ከላይ ከተጠቀሱት የሰነድ ማስረጃዎች አንዱን የሚያቀርብ፣ ይገባኛል ክርክር የሌለበትና ለዚህም ከከተማ ማዘጋጃ ቤት ወይም አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ማስረጃ የሚያቀርብ ባለይዞታ ሆኖ ለሦስተኛ ወገን የተላለፈና የባህላዊ ግዥ ወይም ስጦታ ውል ማስረጃ ማቅረብ የሚችልና ቤት የተሠራበት ይዞታ፣ ካርታ ለመስጠት ሊሟሉ የሚገባቸው አስፈላጊ ሰነዶች መሆናቸውን መመርያው ያትታል፡፡

በምሪት ለተጠቃሚ የተላለፉ የመኖሪያ ወይም ደርጅት ይዞታዎች የቦታ መጠን የሚወሰነው በምሪት ካርኒው ወይም ካርታ ላይ በተገለጸው የቦታ መጠን መሠረት ሲሆን፣ ካርኒው ወይም ካርታው ላይ የቦታ መጠኑ ካልተገለጸ በብሎኩ ውስጥ ባሉት አዋሳኞች የቦታ ሽንሻኖ መጠን መሠረት የሚፀድላቸው ይሆናል ተብሏል፡፡

መመርያው እንዳስቀመጠው በባህላዊ ስጦታ ወይም ሽያጭ ወደ ሦስተኛ ወገን የተላለፈ ይዞታ፣ ስጦታው ወይም ሽያጩ በተላለፈበት ወቅት በነበረው የሊዝ መነሻ ዋጋ መሠረት ወደ ሊዝ ሥርዓት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የይዞታ ማረጋጋጫ ካርታ ወደ ሊዝ ሥርዓት በገቡ ከተሞች ወደ ሦስተኛ ወገን ከተላለፉ ይዞታዎች በስተቀር በነባር ይዞታ ሥሪት የሚስተናገድ ሲሆን፣ ወደ ሊዝ ሥርዓት ባልገቡ ከተሞች ደግሞ ሁሉም ይዞታዎች በነባር ሥሪት አግባብ ተዘጋጅተው የሚሰጡ መሆኑን መመርያው ያስረዳል፡፡

በከተማ ፕላን ምደባ መሠረት ለጋራ አገልግሎት (ለስታዲየም፣ ለስፖርት ማዘውተሪያ፣ ለአረንጓዴ ቦታ፣ ለደን፣ ለገበያ፣ ለመንገድ፣ ለአምልኮ፣ ለማኅበራዊ አገልግሎት) በተመደበ ቦታ ላይ ተነሺ የሆኑ ሕጋዊ የይዞታ ባለቤቶች ከቦታ ተነሺ በሚሆኑበት ጊዜ፣ በካሳ ሕግ መሠረት መብታቸው የሚከበርላቸው ይሆናል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ከተማው የከተማነት ዕውቅና ካገኘ በኋላ የተያዙና በተሻሻለው መመርያ መሥፈርቱን አሟልተው የቀረቡ ይዞታዎች እየተጣሩ እንዲፀድቁ የሚደረግ ሲሆን፣ ይዞታውን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ውዝፍ የከተማ ቦታ ኪራይ ክፍያ እንዲከፍሉ ተደርጎ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲያገኙ እንደሚደረግ በመመርያው ተመላክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...