Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይቀርብ የነበረ ዕርዳታ በመንግሥት ሊመራ ነው

በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይቀርብ የነበረ ዕርዳታ በመንግሥት ሊመራ ነው

ቀን:

የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል በተቆጣጠራቸው ቦታዎች ላይ የዕርዳታ ሥርጭትን እንደሚቆጣጠር አስታወቀ፡፡

ሰኔ 2013 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል የሚገቡ ዕርዳታዎች ሲሠራጩ የነበሩት በክልሉ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ነበር፡፡ በክልሉ ውስጥ ዕርዳታውን ሲያቀርቡ የነበሩት እንደ የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) እና የአሜሪካ የልማትና ተራድኦ ድርጅት (USAID) ያሉ ‹‹ጥቂት›› ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንደሆኑ የተናገሩት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አይደሩስ ሀሰን፣ አሁን ዕርዳታው የሚመራው በፌዴራል መንግሥት መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት የሽሬ፣ ኮረምና አላማጣ ከተሞችን መቆጣጠሩን ካስታወቀ በኋላ፣ በሰሜን ጎንደር ወደ ሽሬ የሚወስደው መንገድና ከኮምቦልቻ ተነስቶ በደሴ-ወልድያ-ቆቦ ወደ አላማጣ የሚያደርሰውን መንገድ እንደሚከፍት አስታውቋል፡፡ ይኼም ከዚህ ቀደም  በምድር ብቸኛ የነበረውን የአፋር የዕርዳታ መስመር ወደ ሦስት ያሳድገዋል፡፡

- Advertisement -

በተጨማሪም መንግሥት የሽሬ አውሮፕላን ማረፊያን በመጠቀምም ዕርዳታ እንደሚያቀርብ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር፡፡

የአገልገሎቱ ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታም ሆነ ጥበቃ ለድርድር አይቀርብም›› ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የመንግሥትን አቋም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ‹‹የሰብዓዊ ዕርዳታ›› ለማቅረብና ‹‹የመሠረታዊ የአገልግሎት አቅርቦት›› ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑንና በተለይም ‹‹በአስቻጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሁሉ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማፋጠን›› ያለውን አቋም አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹በተረጂዎች ስም የሚመጣ የዕርዳታ እህልና መድኃኒት በየትኛውም የሽብር ቡድን እንዲዘረፍ መንግሥት አይፈቅድም›› ያሉ ሲሆን መንግሥት የዕርዳታ ሥርጭቱን እንደሚቆጣጠር ገልጸዋል፡፡

የዕርዳታውን ሥርጭት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆኑ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ›› እንደሆነና ተግባራዊነቱም በሁሉም አገሪቱ ክፍሎች መሆኑን አስፍረዋል፡፡

ሪፖርተር በዕርዳታ ሥርጭቱ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽ አገልግሎትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች አልተሳኩም፡፡

በትግራይ ክልል ዕርዳታ እያቀረቡ የነበሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጦርነቱ በድጋሚ ካገረሸ በኋላ ሥራቸውን ለማከናወን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳጋጠማቸው በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይም በፀጥታ ሥጋት ምክንያት በሽሬ የሚገኙ የዕርዳታ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ማቆማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር አስታውቆ ነበር፡፡

ጦርነቱ በድጋሚ ከማገርሸቱ በፊት በነበሩት ወራት ውስጥ 21 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሰብዓዊ ዕርዳታና 360 ሺሕ ጋሎን ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ወደ ክልል ዕርዳታ ለማቅረብ የሚደረጉ የመኪናና የአውሮፕላን ጉዞዎች ቆመዋል፡፡

ዩኤስኤ አይዲ ከአንድ ወር በፊት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ጦርነቱ በድጋሚ ከጀመረ በኋላ 300 ሺሕ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...