ላለፉት 12 ዓመታት በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ በወርቅ ፍለጋ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው አኮቦ ሚነራልስ፣ በሰገሌ ወርቅ ማዕድን ማውጫ አካባቢ ወርቅ የማውጣት ቁፋሮውን ጀመረ፡፡ ባለፈው ዓመት በተሰጠው የ16 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ ወርቅ ለማውጣትና በየአምስት ዓመታት የሚታደስ ፈቃድ ሲዘጋጅ ቆይቶ፣ ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. የማውጣቱን የመጀመርያ ሥራ በይፋ መጀመሩን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል፡፡
ድርጅቱ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በ182 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ ወርቅ ለመፈለግ ለአሥር ዓመታት የሚቆይ ፈቃድ ካገኘ በኋላም፣ ለመጀመርያ ጊዜ የማውጣት ሥራውን ይጀምራል፡፡ ባለፈው ዓመት የመፈለግ ፈቃዱን ለቀጣይ አሥር ዓመታት እንዳደሰ የገለጹት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጆርገን ኢቭየን፣ አካባቢው ምንም ዓይነት ወርቅ የማውጣት ሥራ ተሠርቶበት ስለማያውቅ ረዥም ጊዜ እንደፈጀባቸውም ተናግረዋል፡፡
‹‹አካባቢው ትልቅ ዕምቅ አቅም ያለውና በወርቅ ማዕድን በጣም ሀብታም ነው፡፡ ምናልባትም በሰፊ ቦታ ላይ ባይሆንም፣ በአንድ ቦታ ተጠቅጥቆ በመያዝ በዓለምም ትልቁ ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በአሁን ጊዜ ወርቁን ለማውጣት ቁፋሮውን የጀመረው አኮቦ ሚነራልስ፣ በቀጣይ ሁለት ዓመታት እስከ ሁለት ቶን ወርቅ እንደ ማስጀመርያ እንደሚያወጣና ይህም በአሁኑ ጊዜ ባለው የገበያ ዋጋ እስከ 115 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጣ እንደሚችል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥር የሚገኘውና በኦሮሚያ ክልል ለገ ደንቢ የሚገኘው የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ማውጫ ድርጅት፣ ላለፉት 25 ዓመታት በብቸኝነት የከፍተኛ ደረጃ ወርቅ አውጪነት ሥራን ሲሠራ ቆይቷል፡፡
አኮቦ ሚነራልስ እስካሁን ጊዜ ድረስ 30 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ላይ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ3,000 በላይ ባለድርሻዎችም እንዳሉት ጀርገን ገልጸዋል፡፡ ወደ 100 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በሥፍራው እየሠሩ እንደሚገኙና በጥቂት ወራትም ወደ 200 ሊጠጉ እንደሚችሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
‹‹ወደ ሌሎች ክልሎችና አካባቢዎች ለማስፋፋት ዕቅድ የያዝንና ፈቃድም የምንጠይቅ ይሆናል፤›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡