የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ሰኞ ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ስለኢትዮጵያ ተጠይቀው ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን በአገራቸውና በተለያዩ የዓለም ከተሞች ሰላማዊ ሠልፍ በመውጣት የአሜሪካን ጣልቃ ገብነትን አውግዘዋል የሚል ጥያቄ ነበር የቀረበላቸው፡፡ ‹‹ይቅርታ የጥያቄው የመጀመርያ ክፍል አልተሰማኝም፤›› ሲሉ መስፍን ብሎ ራሱን ያስተዋወቀውን ጠያቂ መልሰው ጠየቁ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን አሜሪካ ሉዓላዊነታችንን ታክብር ሲሉ ጠይቀዋል፣ ምን መልስ አላችሁ?›› ሲል ጠያቂው ደገመላቸው፡፡
‹‹መልሳችን የሚቀርብብን ክስ ትክክለኛ ያልሆነ ነው የሚል ነው፡፡ የአሜሪካ ፍላጎት እኮ የኢትዮጵያውያንም ፍላጎት ነው፡፡ ሰላም በኢትዮጵያ እንዲመለስ ነው የምንፈልገው፡፡ ግጭቱ ቆሞ ሉዓላዊነቷና ሰላሟ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ማየት እንፈልጋለን፡፡ ለዚያም ነው የአፍሪካ ኅብረትን የሰላም ጥረት የምንደግፈው፤›› በማለት ነበር ኔድ ፕራይስ የአሜሪካ ፍላጎት ያሉትን ያስረዱት፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አባል የሆኑት ሦስት የአፍሪካ አገሮች (A3) የጠሩት ነው በተባለው የምክር ቤቱ ስብሰባ ወቅት፣ የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድም ቢሆኑ ከኔድ ፕራይስ የተለየ አልተናገሩም፡፡ ሦስቱ የአፍሪካ አገሮችና የአፍሪካ ኅብረት ለሰላም ጥረቱ መጀመር ያደረጉት መነሳሳት በጣም ጥሩ እንደሆነ የተናገሩት ግሪንፊልድ፣ በኢትዮጵያ ላይ ምክር ቤቱ ጠንካራ ውሳኔ አለማሳለፉ እንዳበሳጫቸው ገልጸዋል፣ ‹‹ለግጭቱ ጦርነት መፍትሔ አይሆንም፡፡ ሁሉም ኃይሎች ጦር መሣሪያቸውን አስቀምጠው ወደ ድርድሩ ይምጡ፤›› በማለት ነበር የአሜሪካን አቋም የተናገሩት፡፡
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን እንፈልጋለን ይላሉ፡፡ አገራቸው የኢትዮጵያን ጉዳይ በሚዛናዊነት እንደማትዳኝ ሲነገራቸው የእኛ ፍላጎት ሰላም ነው ይላሉ፡፡ አሜሪካኖቹ በአንድ ጎን ሰላም እያሉ በሌላ ጎን ደግሞ በማዕቀብና በዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ማስፈራራታቸውን ቀጥለዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ዓርብ ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የተጀመረውና ሰኞ በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የሰላም ሒደት ትልቅ ዕርምጃ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ ምክር ቤቱ በመግለጫው በተፋላሚ ኃይሎች መካከል በጠላትነት መተያየትና ግጭት መቀጠሉ እንዳሳሰበው አስታውቆ ነበር፡፡
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ ፅኑ ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ ግጭቱ በአስቸኳይ ቆሞ ለሰላም ሒደቱ ቅድሚያ እንዲሰጥ በመጠየቅ ነው መግለጫውን የቋጨው፡፡
ይህን መግለጫ ተከትሎ በነበሩ ቀናት የተደራዳሪዎቹ ልዑካን የደቡብ አፍሪካ ጉዞ ነበር ዋነኛ የትኩረት ጉዳይ ሆኖ የከረመው፡፡ የሕወሓት ተደራዳሪዎች እሑድ ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪካ የመግባታቸው ዜና የተሰማ ሲሆን፣ በማግሥቱ ሰኞ ደግሞ የኢትዮጵያን መንግሥት ወክሎ የሚደራደረው ቡድን አባላት ወደ ጆሀንስበርግ ማቅናታቸው ተነግሯል፡፡ ማክሰኞ ደግሞ ሁለቱ ወገኖች የገጽ ለገጽ ግንኙነት የማድረጋቸው ዜና ዋነኛ ትኩረት ሳቢ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ግን የሰላም ሒደቱ በምን መንገድ ይካሄድ የሚለው ጥያቄ ጎልቶ እየተነሳ የሚገኝ ሲሆን፣ ሁለቱ ወገኖች በምን ጉዳዮች ላይ አተኩረው ይነጋገራሉ የሚለው ተጠባቂ ዜና ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የተደራዳሪ ልዑኩ ወደ ደቡብ አፍሪካ ባመራበት ወቅት፣ ንግግሩ ግጭቱን ለማስቆምና መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ለማሻሻል ዕድል እንደሚፈጥር ገልጾ ነበር፡፡
የሕወሓት ቃል አቀባይ ክንደያ ገብረ ሕይወት (ዶ/ር) ተደራዳሪዎቻቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ መግባታቸውን ተከትሎ በሰጡት የትዊተር መግለጫ ደግሞ ንግግሩ በጠላትነት መተያየትን የሚያስቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ረድኤት አቅርቦት የሚያስጀምር፣ እንዲሁም የኤርትራን ጦር ከትግራይ እንዲወጣ የሚያደርግ መሆን እንደሚኖርበት ገልጸው ነበር፡፡
በደቡብ አፍሪካ ለሚካሄደው የሰላም ንግግር አሜሪካና ደቡብ አፍሪካ ለሕወሓት ተደራዳሪዎች የደኅንነት ዋስትና መስጠታቸው ንግግሩ እንዲጀመር ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ዘ ኢስት አፍሪካን ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ እንደዘገበው የአሜሪካና የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ለሕወሓት ሰዎች የደኅንነት ጥያቄ ዋስትና በመስጠታቸው፣ ንግግሩ ከተጠበቀው ጊዜ ቀድሞ ሊጀመር መቻሉን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመርን ጨምሮ የሕወሓት ተደራዳሪዎችን የያዘ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ከመቀሌ በመነሳት ወደ ደቡብ አፍሪካ መብረሩን ይኸው ዘገባ ያወሳል፡፡
ማክሰኞ ከቀትር በኋላ የተሰማው ሌላ ዜና ደግሞ ንግግሩ በይፋ መጀመሩን ያረጋገጠ ሲሆን፣ እስከ እሑድ ድረስ እንደሚቀጥል ነው የተነገረው፡፡
ኅትመት እስከገባንበት በነበሩ ሰዓታት የሰላም ንግግሩን በተመለከተ የተብራራ መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ንግግሩ በምን ነጥቦች ላይ እንዳተኮረም ሆነ ሒደቱ አያስገኘው ያለውን ውጤት ለመናገር አሁን ላይ ጊዜው ገና ይመስላል፡፡
ማክሰኞ አመሻሽ ላይ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ቃል አቀባይ ቪንሰንት ማግዌንያ በሰጡት መግለጫ፣ ከንግግር ሒደቱ የሰላም ውጤት ይገኛል የሚል ተስፋ ደቡብ አፍሪካ እንዳላት ተናግረዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ይህን ንግግር ማስተናገዷም ከውጭ ግንኙነት መርህ ጋር የሚጣጣም ነው ብለዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር መጀመር ሁለተኛ ዓመቱን ለመድፈን ጥቂት ቀናት የቀረውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለማስቆም በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ተስፋ እያሳደረ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምሥረታ ቀን ሲታሰብ ድርጅቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለዓለም ሰላም መስፈን የሚያስፈልግበት ጊዜ እንደሆነ የተናገሩት ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬስ፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ግጭት በሰፋባቸው አገሮች ሰላም ለማስፈን የተመድ መመሥረቻ ቻርተር እሴቶችና መርሆዎችን መተግበር እንደሚያዋጣ ተናግረዋል፡፡
የቫቲካን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ በበኩላቸው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለምዕመናን በሰጡት ቡራኬ፣ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን እንደሚፀልዩ ተናግረው ነበር፡፡
የናይጄሪያው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ፉምዚሌ ምላምቦ ንጉካ ይመሩታል የተባለው የሰላም ንግግር፣ የኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
ይሁን እንጂ ከሰላም ንግግሩ ጎን ለጎን በትግራይ ክልል የሚደረገው ጦርነት አለመገባደዱ እየተነገረ ነው፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል እያካሄደ ባለው ዘመቻ አዳዲስ አካባቢዎችን ከሕወሓት ቁጥጥር ማስለቀቁ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በመቀሌ አቅራቢያ ወደሚገኘው ኩያ አካባቢ መከላከያ መግባቱም እየተሰማ ነው፡፡
የሕወሓት መሪ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ሰኞ ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ደግሞ፣ ትግራይ የወራሪዎች መቀበሪያ ትሆናለች ማለታቸው ተነግሯል፡፡ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በዚህ መግለጫቸው አሁንም ቢሆን የትግራይ ኃይሎች ጠላትን የመመከት አቅም እንዳላቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የሰላም ንግግሩ መጀመር ዋና ዓላማ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት የሆነውን ሕወሓት ከመደምሰስ ለመታደግ ታስቦ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ምዕራባውያኑ የሕወሓትን ዕድሜ ለማራዘም በሚል የንግግሩን ጉዳይ አጥብቀው እየገፉት እንደሆነ የሚገምቱ በርካቶች ናቸው፡፡ ሆኖም ከንግግሩ መጀመር እኩል ሕወሓቶች አቅማችን ገና ነው ራሳችንን መከላከል እንችላለን ብለው መናገራቸው፣ አሁንም ቢሆን ከሰላም ሒደቱ ጎን የጦርነት ጉዳይም ከአጀንዳ ዝርዝር ውስጥ አለመፋቁን አመላካች መሆኑን ብዙዎችን ያስማማል፡፡
በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን በጎ ምኞታቸውንና ተስፋቸውን የሚገልጹ በበዙበት በዚህ ወቅት፣ ለግጭቱ መቆምም ሆነ ለሰላም ጥረቱ ስኬት በጎ ሚና የሚወጡ ጥቂት ናቸው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የምዕራባውያን ባለሥልጣናት ሰላም ይስፈን የሚለው ውትወታቸው ቢበረታም፣ በአውሮፓ ኅብረትና በአሜሪካ ምክር ቤቶች ኢትዮጵያን ለመቅጣት የማዕቀብ ዝግጅቶች መኖራቸው ይሰማል፡፡ ግጭቱ በሰላም ብቻ ነው የሚቆመው የሚል አቋም የሚያራምዱት ምዕራባውያኑ፣ ወደ ማዕቀብና ጫና መግባታቸው ለሰላም ሒደቱ እንደማይበጅ የሚናገሩ በርካታ ናቸው፡፡
የሰላም ሒደቱን እንደሚደግፉ ሲናገሩ የተደመጡት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ፣ የኢትዮጵያ ጦር፣ በጦርነቱ እያሸነፈ ስለመምጣቱ ሲጠየቁ የመለሱት ይህን የሚያጠናክር ነበር፡፡ ‹‹ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እንፈልጋለን፡፡ የኤርትራ ጦርም በአስቸኳይ እንዲወጣ እንፈልጋለን፤›› ብለው ይህ ካልሆነ ግን አገራቸው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደሯን እንደምትቀጥል በሚጠቁም መንገድ ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡
በቅርቡ ከአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት በወጣ አንድ ሪፖርት አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰላም ሒደቱ ላይ የሚኖራቸውን ሚና አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ አቅርቦ ነበር፡፡ ሦስቱ ወገኖች ከአፍሪካ ኅብረት ጎን የድርድሩን ስትራቴጂካዊ ማዕቀፎች በማዘጋጀት ሚና እንደሚኖራቸው ሰነዱ አረጋግጧል፡፡
የደቡብ አፍሪካው የሰላም ሒደት የአፍሪካ ኅብረት በዋናነት የሚመራው ነው ቢባልም፣ በተለይ የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ በሒደቱ ያላቸው ሚና ቀላል እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ሁለቱ አካላት ደግሞ በኢትዮጵያ ጉዳይ በተለይ በጦርነቱ ላይ የሚያራምዱት አቋም ሚዛናዊ አለመሆኑ ሲተች የቆየ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ይህንን በተደጋጋሚ ስትቃወም ነበር፡፡ በዚህ ከባቢ አየር ውስጥ ሆኖ ከተጀመረው የሰላም ንግግር ምን ውጤት ይገኛል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡