Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ ተቋማት ዘንድሮ በሚያካሂዱት ጠቅላላ ጉባዔ ካፒታላቸውን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ለምን ፈለጉ?

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ዘንድሮ በሚያካሂዱት ጠቅላላ ጉባዔያቸው ላይ አብዛኞቹ በሚባል ደረጃ አንድ ተመሳሳይ የውይይት አጀንዳ ይዘዋል። 

ከሞላ ጎደል ሁሉም የግል ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከዚህ ወር ጀምሮ በተከታታይ በሚያካሂዱት ጠቅላላ ጉባዔዎቻቸው ላይ ካፒታላቸውን ለማሳደግ አጀንዳ ይዘው የባለአክስዮኖች ስብሰባ እየጠሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

አብዛኞቹ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ ካፒታላቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ የተነሱበትን ምክንያት በተለመለከተ ሪፖርተር ያነጋገርናቸው ጉምቱው የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ሲናገሩ፣ ‹‹ጊዜው ካፒታላቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ግድ ስለሚላቸው ነው፤›› ይላሉ፡፡ 

ይህም ከውጭ ባንኮች መግባትና ኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ የተወሰነው ውሳኔ ካፒታላቸውን ለማሳደግ ከወዲሁ መዘጋጀት ስላለባቸው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን አምስት ቢሊዮን ብር ማድረስ እንዳለባቸው፣ የአምስት ዓመት ጊዜ ገደብ ያስቀመጠ ቢሆንም፣ የካፒታል መጠናቸው ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ያደረጉትም ሆነ በዚህ ዝቅተኛ የካፒታል መጠን ላይ ያልደረሱት ባንኮች ካፒታላቸውን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የተለየ ዕቅድ ይዘው ለውሳኔ መዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡ 

ካፒታላቸውን የማሳደግ አጀንዳ ይዘው ባለአክሲዮኖቻቸውን ለጠቅላላ ጉባዔ እየጠሩ ከሚገኙት መካከል አንዱና በአሁኑ ወቅት ከፍተኛውን የካፒታል መጠን ከያዙ የግል ባንኮች መካከል ግንባር ቀደም የሆነው አዋሽ ባንክ ይገኝበታል። አዋሽ ባንክ በቅርቡ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባዔ እንደገና ካፒታሉን ለማሳደግ ለባለአክሲዮኖች ጥያቄውን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

አዋሽ ባንክ የተቋቋመበትን ካፒታል ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ካደረሰ ከሦስት ዓመት በላይ ያስቆጠረና ከግል ባንኮች ትልቅ ካፒታል የያዘ ቢሆንም፣ ይህንን የካፒታል መጠን ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሰሞኑን በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተጨማሪ ካፒታል እንዲጨምር የባንክ ቦርድ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ ይህንኑ ውሳኔውን ለጠቅላላ ጉበዔ በማቅረብ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከአዋሽ ባንክ በተጨማሪ፣ ኅብረት ባንክም በዘንድሮ ጠቅላላ ጉባዔው አሁን ያለውን የባንኩን ካፒታል በ11 ቢሊዮን ብር በማሳደግ፣ 16 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ስለመወጠኑ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ 

ከፋይናንስ ተቋማት ሰሞኑን ቀድሞ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አኃዱ ባንክም፣ 770 ሚሊዮን ብር በላይ የነበረውን የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ በጠቅላላ ጉባዔ አስወስኗል፡፡ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን ተጨማሪ ካፒታልም በሦስት ዓመታት ውስጥ ለመሙላት ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ ይህንን ውሳኔ ቦርዱ እንዲያስፈጽም ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ 

ከእነዚህ ባንኮች ሌላ ካፒታላቸውን ለማሳደግ እየተዘጋጁና ለጠቅላላ ጉባዔያቸውን ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ካሳወቁት ውስጥ ዓባይ ባንክ፣ ዳሸን ባንክና ንብ ባንክ ይገኙበታል፡፡ 

የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም የካፒታላቸውን ለማሳደግ እየተዘጋጁ ሲሆን፣ ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዘንድሮው ጠቅላላ ጉባዔቸው ላይ ካፒታላቸውን ለማሳደግ የሚያስችላቸውን ጥያቄ ለጠቅላላ ጉባዔ አቅርበው ያፀድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እስካሁንም ይፋዊ በሆነ መንገድ ካፒታላቸውን ለማሳደግ ካስታወቁት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ኅብረት ኢንሹራንስ፣ ዘመን ኢንሹራንስና ናይስ ኢንሹራንስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ የግል ኢንሹራስ ኩባንያዎች ከፍተኛ ካፒታል ያለው አዋሽ ኢንሹራንስም በዘንድሮው ጠቅላላ ጉባዔ ካፒታሉን ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አዋሽ ኢንሹራንስ አሁን ያስመዘገበው ካፒታል 1.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህንን የካፒታል መጠን ከዕጥፍ በላይ እንደሚያሳድግ ይጠበቃል፡፡ 

የአገሪቱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ዘንድሮ በሚያካሂዱት ጠቅላላ ጉባዔ ካፒታላቸውን ለማሳደግ የተዘጋጁበት ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ባፀደቀው መመርያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ዝቀተኛ የካፒታል መጠን ከፍ ከማድረጉ ጋር ይያያዛል። 

በአጠቃላይ ሁሉም የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ካፒታላቸውን ከማሳደግ ውጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ የላቸውም የሚሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የመግባታቸው ጉዳይ እርግጥ እየሆነ መምጣቱ ደግሞ፣ ባንኮች የግድ ካፒታላቸውንና አቅማቸውን አሳድገው መጠበቅ የግድ ይሆንባቸዋል ሲሉ አስረድተዋል።

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚፈቀድበት አራት ዓይነት ሥልቶች ይኖራሉ ተብሎ የሚታሰብ መሆኑን የገለጹት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ በተለይም አገር ውስጥ ከሚገኙ ባንኮች ጋር በሽርክና አብሮ መሥራት አንደኛው መንገድ እንደሚሆን ጠቁመዋል። ይህ ከሆነ ደግሞ የአገር ውስጥ ባንኮች ካፒታላቸውን በማሳደግ ዝግጁ ሆነው መጠበቅ የግድ እንደሚላቸው ጠቁመዋል። 

ከአንድ ወር በፊት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባፀደቀው አዲስ የፋይናንስ ፖሊሲ ለውጭ ዜጎችና የውጭ ባንኮች ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ለውጭ ባንኮችና የውጭ ዜጎች ዝግ ሆኖ የቆየው የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ደረጃ በደረጃ እንዲከፈት የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፖሊሲ ማዕቀፍ ማፅደቁ ይታወሳል። ሪፖርተር የተመለከተው ይህ የፖሊሲ ሰነድ የውጭ ባንኮችና የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ ባንኮች ላይ የተወሰነ ድርሻ ይዘው እንዲገቡ የሚፈቅድ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ባንኮች ከ30 በመቶ እስከ 40 በመቶ ድርሻ እንዲሸጡም ይፈቅዳል። 

በመሆኑም የአገር ውስጥ ባንኮች ካፒታላቸውን የማሳደግ ግዴታ ሳይጣልባቸው፣ በዘንድሮ ጠቅላላ ጉባዔዎቻቸው ካፒታል የማሳደግ አጀንዳ መቅረፃቸው፣ ነገሩ የሞት ወይም የሽረት ሁኔታ ውስጥ ስለሚከታቸው እንደሆነ አቶ ኢየሱስወርቅ ይገልጻሉ።

አዲሱ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩ የውጭ ባንኮች በቅድሚያ ምርጫቸው የሚያደርጉት ጠንካራ የካፒታል መሠረት ያለውን የኢትዮጵያ ባንክ በመሆኑ፣ ሁሉም የአገር ውስጥ ባንኮች ለዚያ የሚያበቃ ዝግጅት ማድረጋቸው ጤናማ መሆኑን ያስረዳሉ። 

‹‹የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የካፒታል ማሳደግ እንቅስቃሴ እስካሁን ከውጭ ኢንሹራስ መግባት ጋር የተያያዘ ነገር የለውም፤›› የሚሉት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ ምክንያቱም የውጭ ኢንሹራስ ኩባንያዎችን መግባት በተመለከተ፣ የተወሰነ ውሳኔ ስለሌለ አሁን የሚያደርጉት የካፒታል ማሳደግ ውሳኔያቸው በቀጥታ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የካፒታል መጠናቸውን 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ አለባቸው ከሚለው ጋር የተያዘ ነው የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ወደ ሰባት የሚሆኑት በቅርቡ የተወሰነውን 500 ሚሊዮን ብር ዝቅተኛ ካፒታል ማሟላታቸውን የጠቆሙት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ ገንዘብ የመግዛት አቅም እየተዳከመ በመምጣቱ አሁንም ካፒታላቸውን ማሳደግ ግድ እንዳላቸው አስረድተዋል።

 

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች