Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተጣለው ክልከላ ተፅዕኖና አኮኖሚያዊ ፋይዳ ሲመዘን

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብሔራዊ ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው ከሳምንት በፊት ባሳለፈው ውሳኔ 38 የሚሆኑ ምርቶች ከውጭ እንዳይገቡ ክልከላ ጥሎ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። በዚህም መሠረት የአገሪቱ ባንኮች ካለፈው ሳምንት መጀመርያ አንስቶ ለነዚህ ምርቶች የውጭ ምንዛሪ ከፍያ ሒሳብ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) እንዳይከፈቱ ትዕዛዝ የደረሳቸው ሲሆን ትዕዛዙንም ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል።

ብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው ባሳለፈው በዚህ ውሳኔ ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶች ቢነሱም አብዛኞቹ ግን አገሪቱ ከገጠማት የውጭ ምንዛሪ ቀውስ አንፃር ውሳኔው ተገቢ እንደሆነ ያምናሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ቼፍ ኢኮኖሚስት አቶ ፍቃዱ ደግፌ እንደሚገልጹትም ለብዙኃን ጥቅም ሲባል ቅድሚያ ሊሰጣቸው የማይገቡ ምርቶችን ላልተወሰነ ጊዜ ማገዱ ተገቢ ነው፡፡

በተለይም አሁን ክልከላ የተጣለባቸውን ምርቶች ለማስገባት በሚል ሽፋን የሚፈጸሙ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ የማጭበርበር ተግባራትን ለማስቀረት ውሳኔው ጠቃሚ እንደሆነም ያክላሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ከማበረታታት አንፃርም ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ፈቃዱ፣ መመርያው የተከለከሉ ምርቶችን በአገር ውስጥ የሚያመርቱ ኩባንያዎችን በማበረታታት ረገድ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

ክልከላው ከተጣለባቸው ምርቶች መካከል እንደ ቸኮሌት፣ ማስቲካና ሌሎች ጣፋጭ ምርቶች ይገኙበታል። በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የንብ ጣፋጭ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ተሾመ ውሳኔው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን የሚያበረታታ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ይህ ውሳኔ ዘግይቶ ቢመጣም በጎ ነው የሚሉት አቶ ኤልያስ፣ በኢትዮጵያ ቸኮሌትና ሌሎች የጣፋጭ ምርቶችን የሚያመርቱ አምራቾች በማኅበራቸው በኩል በተደጋጋሚ ጊዜ ለመንግሥት ያቀረቡት የነበረ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይ ከውጭ የሚመጡና አገር ውስጥ የሚመረቱ ተመሳሳይ ምርቶች ላይ አንድ ዓይነት የታክስ መጠን ሊጣልባቸው አይገባም የሚል ሙግት ሲያቀርቡ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን በአገር ውስጥ ለሚመረተውም ከውጭ ለሚገባውም ምርት አንድ ዓይነት ታክስ መጣሉ የጣፋጭ ምግብ አምራቾች ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ግን የተወሰነው ውሳኔ ኢንዱስትሪውን በተወሰነ ደረጃ የሚያነቃቃና በምርቱ ላይ በተጣለ ከፍተኛ ኤሌክሳይስ ታክስ ምክንያት ከገበያ የወጡትን የጣፋጭ ምግብ አምራቾችን ወደ ገበያ ሊመልስ እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስመጣት ለኢትዮጵያ ገበያ እያቀረበ የሚገኘው ግሪን ቴክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርም መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ የኩባንያውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑን አመልክቷል፡፡ 

ኩባንያው ይህ መመርያው ከመውጣቱ በፊትም ቢሆን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በብዛት በማስምጣት ለገበያ እያቀረበ ቢሆንም፣ የመመርያ መውጣት ኩባንያው የተሰማራበትን ዘርፍ በአጠቃላይ የሚበረታታ ሆኖ እንዳገኘው አመልክቷል፡፡ የዚህ መመርያ ጠቀሜታ ለግሪን ቴክና መሰል ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን፣ ለኅብረተሰቡ ከዚያም በላይ ለአገር መሆኑን ከኩባንያው ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም የአካባቢ ብክለትን በመቀነስና አገር ለነዳጅ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በመቆጠብ ጭምር የሚረዳ በመሆኑ ቀድሞ በማሰብ እየሠራ ያለውን ይህንን ሥራ የበለጠ እንዲገፋበት መመርያው እንደሚያበረታታው ገልጿል።

በቅርብ ጊዜ ውስጥም በድሬዳዋ እየገነባ ያለውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የመገጣጠሚያ ፋብሪካ በማጠናቀቅ አገልግሎቱን በማስፋት እንደሚንቀሳቀስ በመግለጽ፣ በዚህ ዕድል ሁሉንም የሚጠቅም ሥራ እንደሚሠራም ኩባንያው አስታውቋል፡፡

ከዚህ መመርያ መተግበር በኋላ ግን በተለይ የተሽከርካሪዎች ገበያ እንቅስቃሴ ቀዝቅዟል፡፡ ብዙዎቹ አውቶሞቢል አስመጪዎች በእጃቸው ያለውን ተሽከርካሪ ከመሸጥ ይልቅ ያዝ ማድረግን የመረጡ ይመስላል፡፡ አንዳንድ የመኪና መሸጫዎችም ዝግ ሆነው ታይተዋል፡፡ እንዳይገቡ የተከለከሉ ሌሎች ላይም የዋጋ ለውጥ እየታየ ስለመሆኑ ረፖርተር ለመታዘብ ችሏል።

ክልከላው ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ ባይሆንም አሁን በመንግሥት የተወሰነው ውሳኔ አግባብነት እንዳለው የሚገልጹት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር)፣ አሁን ክልከላ ከተደረገባቸው ምርቶች በተለይ ተሽከርካሪ ለመግዛት አቅም ያላቸውን መመርያው የሚጫን ቢሆንም ከብዙኃኑ ጥቅም አንፃር ሲታይ ፋይዳው ያመዝናል ይላሉ፡፡

በአንፃሩ እነዚህን ምርቶች የሚያስመጡ ኩባንያዎች ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን አሁን ላይ የተሽከርካሪ አስመጪዎችን መኪና የሚያጓጉዙ የጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ቢዝነሶች ላይ የተወሰነ ጊዜ ጫና ሊያሳድር ይችላል የሚል አስተያየትም ተሰጥቷል፡፡ የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃ አቅራቢዎች ቢዝነስ ላይም የራሱ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል የሚናገሩ አሉ። 

በዚህ መመርያ ቢዝነሳቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርባቸው ከተጠቀሱት ውስጥ የፋይናንስ ተቋማትም ተከታትለዋል፡፡ በተለይ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይገቡ ለነበሩ እያንዳንዱ ተሽከርካሪ የመድን ሽፋን የሚሰጡ በመሆኑ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ባህሪ አንፃር ከ65 በመቶ በላይ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ገቢ የተመሠረተው በተሽከርካሪ የመድን ሽፋን በመሆኑ መመርያው ፀንቶ እስከሚቆይ ጊዜ ድረስ ኩባንያዎቹ ያገኙት የነበረውን የተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን ዓረቦን ሊያሳጣቸው መቻሉ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡  

ባንኮችም ቢሆኑ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ለሚገዙ ብድር በስፋት ማቅረብ በመጀመራቸው ከዚህ ያገኙት የነበረውን ትርፍ የሚሰጣቸው እንደሆነ ያነጋገርናቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጠቁመዋል፡፡ 

ሌሎች የተከለከሉ ምርቶችን የሚያስመጡ ኩባንያዎችም በተለያየ መጠን ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉ የገለጹልን የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ከሁሉም በተለይ ግን መንግሥት ከእነዚህ ምርቶች የሚያገኘውን ከፍተኛ የታክስ ገቢ እንደሚያጣ ጠቁመዋል፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር ከጥቂት ወራት በፊት ባወጣው መመርያ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ 3 በመቶ የማኅበራዊ ዓላማ ቀረጥ መጣሉ የሚታወስ ሲሆን፣  በዚህ መመርያ አማካይነትም በዓመት ከ19 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝ ታሳቢ ተደርጎ ነበር። አብዛኞቹ ክልከላ የተጣለባቸው ምርቶች አዲስ በተጣለው የሦስት በመቶ ቀረጥ ሥር የሚወድቁ በመሆኑ መንግሥት አዲስ በጣለው ቀረጥ አገኛለሁ ብሎ ያሰበውን ገቢ በአመዛኙ ሊያጣ ይችላል።

አቶ ፈቃዱ ግን የመንግሥት ገቢ ላይ ተፅዕኖ ቢያሳርፍም ክልከላው ከሚያስገኘው ጥቅም ጋር ሊነፃፀር እንደማይችል ያመለክታሉ፡፡ በዚሁ ሐሳብ የሚስማሙት ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ ክልከላው በመንግሥት ታክስ ገቢ ላይ የጎላ ተፅዕኖ የሚያመጣ እንዳልሆነ ያመለክታሉ። ነገር ግን እንዲህ ያሉ ክልከላዎች በጊዜያዊነት ሊያስገኙ የሚችሉት ጥቅም እንዳለ ሆኖ፣ ዘለቄታዊ መፍትሔ ማበጀት የተሻለ መሆኑን ይመክራሉ። ክልከላው ከውጭ ምንዛሪ ችግር ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን የገለጹት ቴዎድሮስ፣ የውጭ ምንዛሪ ገበያን በገበያ ዋጋ እንዲመራ ማድረግ ዘላቂ መፍትሔ እንደሆነ ይገልጻሉ። 

ቴዎድሮስ (ዶ/ር) አክለውም ይህንን መመርያ ተከትሎ የኮንትሮባንድ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምር የሚችል በመሆኑ መንግሥት እንዲህ ያለውን ክፍተት ለመድፈን ከወዲሁ መሠራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ይህ መመርያ ተስፋ የሰጣቸው የጣፋጭ አምራቾች ከውጭ የሚገባውን ቼኮሌትና የተለያዩ ጣፋጭ ብስኩቶችን በአገር ውስጥ አምራቾች ለመተካት ግን ዕገዛ የሚያስፈልግ መሆኑን ግን አቶ ኤልያስ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ለምርቶቹ የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎች ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው በአገር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ከውጭ ለሚመጣ ጥሬ ዕቃ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ግን ከባድ ሆኖ ቆይቷል፡፡

አሁን ከውጭ እንዳይገቡ የተከለከሉ ምርቶችን እዚህ ለማምረት የሚቻልበት ዕድል ስላለ ዕገዛው የውጭ ምንዛሪ በመፍቀድና ለሥራ የሚሆን ፋይናንስ ማግኘትም ሥራውን ለማንቀሳቀስ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

ይህ ጉዳይ ቀላል እንዳልሆነ በማመልከትም ተገቢ ዕገዛ ከተደረገ ከውጭ የሚገቡትን በተወሰነ ደረጃ ለመተካት የሚደረገው እንቅስቃሴ ተዘግተው የነበሩትን መቶ የሚሆኑ ፋብሪካዎች ለማንቀሳቀስና ቀጥረው ሲያሠሯቸው የነበሩ ሠራተኞችን ሊመልሱ የሚያስችል ዕድል ሊኖረው እንደሚችል አቶ ኤልያስ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች