Saturday, March 2, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም የሚሰነዘርባትን ጫና እንድትቋቋም የሚያግዙ የዲፕሎማሲ መፍትሔዎች

ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም የሚሰነዘርባትን ጫና እንድትቋቋም የሚያግዙ የዲፕሎማሲ መፍትሔዎች

ቀን:

በሀብታሙ ግርማ ደምሴ

መግቢያ

ምዕራባውያን አገሮች በተለይም አሜሪካ ከቅርብ ወራት ጀምሮ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ጥቅሞች ላይ የተቃጣ ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን በማሳደር ላይ ይገኛሉ፡፡ የምዕራቡ ዓለም ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ እያደረገችው ባለው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ፣ እንዲሁም የደኅንነት አስተዳደርና/ፖለሲ ማሻሻያዎችን ተጠቅመው ድብቅ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ላይ ታች እያሉ ነው፡፡ የምዕራባውያን ድብቅ ፍላጎት የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ከሚመራው ሕዝብ ጥቅም ይልቅ፣ ለእነሱ ጥቅሞች አድልቶ መሥራት አለበት የሚል ነው፡፡ ነገር ግን የለውጡ አመራር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅሞች ወገንተኝነት በማሳየቱ፣ አሜሪካ መራሹ የምዕራቡ አገሮች ስብስብ ኩርፊያውን በተለያዩ መንገዶች እየገለጸ ይገኛል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እንደታየው በትግራይ ክልል ባለው የደኅንነት ሁኔታ ሰበብ አድርገው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ፣ የሚዲያ፣ የዲፕሎማሲና የደኅንነት ጫናዎች የሚያሳድሩ ተግባራትን በተቀናጀ ሁኔታ እየሠሩ ነው፡፡ በዚህ ክፍል ኢትዮጵያ ከምዕራባውን አገሮች ለሚሰነዘር ዘርፈ ብዙ ጫና፣ የዲፕሎማሲ መሣሪያዎችን ተጠቅማ እንዴት መቋቋም እንደምትችል የግል ምልከታዬን ለማጋራት እሞክራለሁ፡፡ በዚህም በሚከተሉት አንኳር ነጥቦች ዙሪያ ዳሰሳ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡

  • ኢትዮጵያ ከአገሮች ጋር (በአጠቃላይ) እና ከምዕራባውያን ጋር (በተለይ) በሚኖራት ግንኙነት መከተል ስለሚገባት መርህ፣
  • የአገሪቱን የመደራደር አቅም መገንባት፣
  • አፍቃሪ ኢትዮጵያ (Pan – Ethiopian) እና አፍቃሪ አፍሪካ (Pan African) ዓለም አቀፍ የዲጂታልና የኅትመት ሚዲያዎችን ማቋቋም፣
  • የዲፕሎማሲ ሥራው በዓለም አቀፋዊነት ሥነ ልቦና የተደገፈ እንዲሆን ማስቻል፡፡
  1. ኢትዮጵያ ከአገሮች ጋር (በአጠቃላይ) ከምዕራባውያ ጋር (በተለይ) በሚኖራት ግንኙነት መከተል ስለሚገባት መርህ

መንግሥት ከምዕራባውያን አገሮች ጋር ስለሚኖረው የወደፊት ግንኙነት ሊከተለው የሚገባውን መርህ ወሳኝ ነው፡፡ በእኔ አመለካከት የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አመራር ለአገር ሉዓላዊነትና ለሕዝባዊ ክብር የሚሰጠውን ዋጋ አደንቃለሁ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቱ መገለጫ እነዚህን ኃይሎች በመጥላት፣ በማበሳጨት ወይም በበቀል ስሜት በሚወሰዱ ዕርምጃዎች መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ የምዕራባውያንን ጫና ለመቃወም ተብሎ ከእነሱ ጋር ቁርሾ ከገቡ አገሮች (ለምሳሌ እንደ ኢራን፣ ሩሲያ፣ ሰሜን ኮሪያ የመሳሰሉት) መርህ አልባ ግንኙነት መፍጠር ለኢትዮጵያ አይበጃትም፡፡  ይህ ሲባል ግን ከእነዚህ አገሮች ጋር ግንኙነታችንን ማሳደግ አይገባም ማለቴ አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ የግንኙነታችንን መስመር ሁሉ አገራዊ ራዕያችንን በማያጨናግፍበት አግባብ መሆን አለበት ነው፡፡ ይህም እንደ አገርና ሕዝብ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ከመክፈል ይታደገናል፣ ከወጥንነው አገራዊ ግብ እንድንደርስ ያደርገናል፡፡ አሁን ባለንበት ቁመናና ተጨባጭ ውስጣዊና ውጫዊ ሁነቶች ከምዕራቡ ዓለም ጋር አተካሮ ውስጥ መግባት ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ በመሆኑም የውጭ ጉዳይ አመራሩ በከፍተኛ ጥንቃቄና ብስለት ሊመራ ይገባዋል፡፡ እንዲያውም ምዕራባውያኑንን ጫና ለመቋቋም ከሚወሰዱ የዲፕሎማሲ ዕርምጃዎች አንዱ መሆን ያለበት፣ ኢትዮጵያ በትብብር የምትሠራባቸውን ማዕቀፎች ማስፋት ነው፡፡

በመጨረሻም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት እየተከተለ ያለው የውጭ ጉዳይ ፖለሲ ማዕዘናት አንዱ ‹‹ቋሚ ወዳጅም ሆነ ቋሚ ጠላት የለም›› የሚለውን የቀደመውን የኢሕአዴግ መንግሥት መርህ፣ ‹‹ወዳጅና ጠላት ብሎ ነገር የለም›› በሚለው ተክቷል፡፡ የዚህ አዲሱ ውጭ ጉዳይ መርህ ታሳቢ ያደረገው፣ ሁሉም አገር እንደ ኢትዮጵያ በጋራ ጥቅም ላይ ያምናል ብሎ ነው፡፡ ነገር ግን በተጨባጩ ዓለም አገሮች የፈለገ ጥብቅ እውነተኛ ወዳጅነት ቢኖራቸውም፣ ግንኙነታቸው እርስ በርስ ከመጠራጠር የፀዳ አይደለም፡፡ በቅርቡ እንደተሰማው ከ2012 ዓ.ም. እስከ 2014 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት አሜሪካ ዴንማርክ በሚገኝ የግንኙነት ኬብል (የስለላ ጣቢያ) የጀርመን፣ የፈረንሣይና የብሪታንያን ጨምሮ የሌሎች አገሮች ባለሥልጣናትን የስልክ ግንኙነት በመጥለፍ ትሰልል እንደነበር ተረጋግጣል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ የፈለገውን ያህል ጥብቅ ቁርኝት ቢኖራት፣ በአገሮች ላይ የሚኖራትን ግንኙነት በፍፁም እምነት ጥላ የትብብር መንገድን ብቻ መከተል የለባትም፡፡ ይህን ስል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን መርህ በሴራ ዲፕሎማሲ ይተካ ሳይሆን፣ እንደ አስፈላጊነቱ የትብብርንና የጥርጣሬን መንፈስ ሚዛን ውስጥ ገብቶ መሆን አለበት ለማለት ነው፡፡

  1. አገሪቱን የመደራደር አቅም መገንባት

ዓለም እንደ መረብ በተሳሰረበት በዛሬው ዘመን ሁሉም አገር ለሁሉም አገር አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን የአገሮች አስፈላጊነት እኩል አይደለም፡፡ ከምዕራባውያኑ አንፃር የአንድ አገር አስፈላጊነት ደረጃ በኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃና ርዕዮተ ዓለማዊ አጋርነት፣ በተፈጥሮ ሀብት ፀጋ (በተለይም በነዳጅና በማዕድን ሀብት) በደኅንነት አጋርነትና ጂኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥ ይወሰናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሰው ልጅ ፍልሰት (Human Migration) ሌላው ቁልፍ የግንኙነት አጀንዳ ሆኖ ብቅ ብላል፡፡ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ አጋርነትም እንዲሁ ደረጃው ዝቅ ቢልም፣ የምዕራቡ ዓለም ከአገሮች ጋር ለሚኖራቸው ግንኙነት የአጋርነት ማዕቀፍ ውስጥ ይመደባል፡፡ እንግዲህ የአገሮች የመደራደር አቅም በዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ ባላቸው ተሳትፎና ወይም አስፈላጊነት ደረጃ ይወሰናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩት ጫና ልክ የሚወስነው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ዙሪያ ባላት (በምትፈጥረው) የመደራደሪያ አቅም (Leverage) ነው፡፡ በዚህ ክፍል ከምዕራቡ ዓለም የሚመጣን ተፅዕኖ ከመመከት አካያ፣ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሊጨምሩ የሚችሉ የዲፕሎማሲ መፍትሔዎች ለመጠቆም ተሞክሯል፡፡

  1. በጂኦ ፖለቲካዊ ሰላምና ደኅንነት ሚናን በማሳደግ የመደራደር አቅምን ማጎልበት

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎች በተለይም ለዓለም ሰላም ያላሳለሰ ድጋፍ ስታደርግ እንደቆየች ይታወቃል፡፡ ይህ ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎዋን ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ትፈጥር ዘንድ ተጠቅማበታለች የሚለው ጉዳይ ጥያቄ የሚያስነሳ ቢሆንም፣ ቢያንስ በታሪክ ማኅደር በመልካም የምትነሳ አገር እንድትሆን የሚያደርጋት እንደሆነ ግን ያለ ጥርጥር መናገር ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድና የቀይ ባህር ከባቢ ሰላም፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ላይ እያደረገችው ካለው ተግባራት በተጨማሪ፣ ብርቱ ተሳትፎ በማድረግ ከጠላቶች የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ ራሷን መከላከል ትችላለች፡፡

ከኢትዮጵያ አንፃር ምዕራባውያን አገሮች የሚፈጥሩት ጂኦ ፖለቲካዊ አጋርነት መሠረቱ በምሥራቅ አፍሪካ (በተለይም በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር አካባቢ) ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነነት ለማረጋገጥ ባላት ቁልፍ ሚና ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተለይም በአፍሪካ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ የማይተካ ሚና እንዳላት ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት አስመስክራለች፡፡ የሽብርተኝነት ድርጅቶች እንቅስቃሴ በአፍሪካ እስካልከሰመ ድረስ፣ የኢትዮጵያ ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የሚኖራት አጋርነት የሚቀጥል ነው የሚሆነው፡፡

አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ በአፍሪካ ከምዕራቡ ክፍል እስከ ምሥራቁ ጫፍ ያለው የአኅጉሪቱ ወገብ ምንም ሰላም የሌለው ነው፡፡ ይህ አለመረጋጋት ከምዕራቡ ክፍል ጫፍ ወደ ምሥራቁ ጫፍ ላይ ከምትገኘው ሶማሊያ ጋር እንዳይገናኝ የሆነው፣ ኢትዮጵያ በአንፃራዊነት የተረጋጋች አገር መሆኗ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓት ለጎረቤት የአፍሪካ አገሮች ሰላም ጭምር ዋስትና ሆኖ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት ከማረጋገጥ አኳያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ከምታበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ፣ የእርስ በርስ ግጭት በተነሳባቸው የአፍሪካ አገሮች ሠራዊቷን ልካ ሰላም በማስከበር፣ እንዲሁም በግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን መጠለያ በመሆን የላቀ ሚና ያላት አገር ናት፡፡ በተለይም በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ሒደት ላይ ቁልፍ የምዕራቡ ዓለም አጋር ሆና ቆይታለች፡፡ እ.ኤ.አ. በሴፕቴምበር 2020 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የተሰማሩ 6,662 በሰላም አስከባሪነት በተለያዩ ዓለም ክፍል ተሰማርተው ቁልፍ ግልጋሎት እየሰጡ ነበር፡፡ ይህም አገሪቱን ከባንግላዴሽ ቀጥላ በዓለም ሁለተኛዋ የሰላም አስከባሪ ጦር የምታዋጣ አገር አድርጓታል፡፡ በተጨማሪም 4,300 የኢትዮጵያ ወታደሮች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ባለው የሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ ሆነው በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በሰላም ማስከበር ሒደቶች ዋነኛ ተዋናይ በመሆን፣ ለአኅጉሪቱ ሰላም ትልቅ አበርክቶት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የሚኖራት ጂኦ ፖለቲካዊ አጋርነት ሌላው መልክ በቀጣናዊ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በሚኖራት አስተዋጽኦ ነው፡፡

እንደሚታወቀው የአፍሪካ ቀንድ ጫፍ የሆነው የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ መገናኛ የሆነው ክፍል ዋነኛው የዓለም ኢኮኖሚ መናኸሪያ መገኛ ነው፡፡ በዓለም ኢኮኖሚ የሎጂስቲክስ ዝውውር 70 በመቶ የሚሆነው ዕቃ በመርከብ ከአንዱ ዓለም ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ የሚሸጋገረው፣ የአፍሪካ ቀንድን አስታክኮ በሚያልፈው ስዊዝ ካናል ተብሎ በሚጠራው ሰው ሠራሽ ቦይ ነው፡፡ እናም የኢትዮጵያ የተረጋጋች አገር መሆና ይህን የዓለም ኦኮኖሚ ዓይን የሆነውን ክፍል እንዳይታወክ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ዓለም ይህንን ተገንዝቦ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት በሚያውኩ የውጭ ኃይሎች ሴራዎችን እንዲኮንን የሚያስችሉ የደኅንነት ዲፕሎማሲ ሥራዎች በሰፊው ሊከናወኑ ይገባል፡፡

  • ስደተኝነትና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አጀንዳ

ኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው ሕገወጥ የሰዎች ፍልሰት ማቋረጫ ማዕከል ናት፡፡ ምዕራቡ ዓለም ከአፍሪካ ደቡባዊ ክፍልና ማዕከላዊ ክፍል ወደ አውሮፓ የሚደረግ ፍልሰትን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጥረት የኢትዮጵያ ድጋፍ የማይተካ እንደሆነ ያውቁታል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራቸው ቁርሾ ፍልሰቱን ለመቆጣጠር በማይችሉበት መጠን ያንሰራፋዋል፣ ቢያንስ በሁለት መልኩ፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አለመረጋጋት 120 ሚሊዮን ያላትን አገር ሕዝብ የሚበትን፣ አብዛኛው ፍልሰት ወደ አውሮፓ ማነጣጠሩም አይቀሬ ነው፡፡ እናም እንደ አገር ህልውናዋን አስጠብቃ ለምትቀጥል ኢትዮጵያ ይህንን ከመግታት አንፃር መሠረታዊ ነው፡፡

ከምዕራባውያን ጋር ሌላው የግንኙነት አጀንዳ የሰዎች ስደተኝነት ጉዳይ ነው፡፡ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ከኢትዮጵያ ጋር ባለው ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት በሚገልጸው የበይነ መረብ ጽሑፉ ዋነኛ ጉዳዮች ብሎ ካስቀመጣቸው አንዱ፣ ኢትዮጵያ ስደተኞችን መጠለያ በመስጠት የምታደርገው አስተዋጽኦ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 መጨረሻ ኢትዮጵያ 720,000 ስደተኞችን መጠለያ በመስጠት ታኖራለች፡፡

ኢትዮጵያ የፍልሰት በር የመሆኗ ጉዳይ ሌላው የመደራደሪያ አቅሟ ነው፡፡ በቅርቡ የተከሰተ አንድ ጉዳይ እንደ ማሳያ መጠቀም ይቻላል፡፡ ጉዳዩ የሞሮኮና የስፔን ጉዳይ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ሞሮኮ ሰሃራዊ ዓረብ ሪፐብሊክ የአገሪቱ አንድ አካል አድርጋ ትወስዳለች፡፡ ከሰሃራዊ ዓረብ ሪፐብሊክ ጋር ግንኙነት ባላቸው አገሮች ላይ ድርድር አታውቅም (በመሠረቱ ሞሮኮ ከአፍሪካ ኅብረት አባልነት የወጣችውም ኅብረቱ ለሰሃራዊ ዓረብ ሪፑብሊክ ዕውቅና መስጠቱ እንደሆነ ይታወቃል)፡፡ በቅርቡ ስፔን ለሰሃራዊ ዓረብ ሪፐብሊክ ጋር ባደረገችው ግንኙነት ሞሮኮ ወደ አውሮፓ የሚወስደውን በሯን ለስደተኞች ክፍት በማድረጓ ታይቶ በማይታወቅ የሰዎች ፍልሰት ተሞልቷል፡፡ ሞሮኮ ይህንን ያደረገችው ሆን ብላ አቅሟን ለማሳየት እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ተሳክቶላታል፡፡

ኢትዮጵያም እንደ ሞሮኮ እንኳን ቀጥተኛና አሁናዊ የስደተኞች ጎርፍ መልቀቅ እንኳን ባትችል፣ በርካታ የውጭ አገሮች ስደተኞች መጠለያ በመሆን በዓለም ቀዳሚ አገር ናት፡፡ ይህ የኢትዮጵያ መልካም ስም በስደተኝነት ጉዳይ ላይ ከምዕባውያን አገሮች ጋር ቁልፍ አጋር እንድትሆን አድርጓታል፡፡ እ.ኤ.አ. ጁን 3 ቀን 2021 የፈረንሣይ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ፍራንስ 24 (France 24) እንደዘገበው፣ የዴንማርክ የሕግ አውጪ ምክር ቤት በስደተኞች ጉዳይ ላይ አንድ ሕግ አፅድቋል፡፡ ይህም ጥገኝነት የጠየቁና የተፈቀደላቸው የተለያዩ አገር ዜጎችን ከአገሮች ውጭ ባሉ ሦስት አፍሪካ አገሮች ስለማስፈር ነው፡፡ ሦስቱ የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ቱኒዝያ ናቸው፡፡ ሕጉን ተፈጻሚ ለማድረግ የዴንማርክ መንግሥት ከሦስቱ አገሮች ጋር ድርድር ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ ይህን መሰል የስደተኞች ፖሊሲ ሌሎች የአውሮፓ አገሮችም ይከተሉታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፍራንስ 24 ዘገባ አመልክቷል፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያና አውሮፓ በመጪው ጊዜ በሚኖራቸው ግንኙነት የስደተኝነት ጉዳይ ቁልፍ አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

  • የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ አቀማመጧ በራሱ የበረሃማነት መስፋፋትን ለመግታት የተፈጠረ ነው፡፡ ‹‹ግሪን ቤልት›› ተብሎ የሚጠራው የሰሃራ በረሃ ወደ አፍሪካ ቀንድ መስፋፋትን ተከላክሎ በጥቅጥቅ ደኖች የተሸፈነ መሬት የሚገኘው፣ በኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራብ ግዛት ነው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት አገሪቱን የአስተዳደሩ መሪዎችም (በዋናነት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ) የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ ላይ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ ናቸው፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የሚመሩት መንግሥት በአካባቢ ጥበቃ ላይ ሰፋ ያለ አገራዊ ንቅናቄ በማድረግ፣ አገሪቱን በደን ለማልበስና የሰሃራ በረሃ መስፋፋትን ለመግታት፣ የካርቦን ልቀት መቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት ላይ አተኩሮ እየሠራ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ባለፉት ሦስት ዓመታት አመርቂ ሥራዎች እንደተሠሩ ይታመናል፡፡ እንዲህ ዓይነት አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ የመቀነስ ዓላማ ያነገቡ መንግሥታዊ እንቅስቃሴዎችን መቀጠሉ፣ አንድም ከአገራዊ ጥቅሙ ባሻገር፣ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ከሚኖረን ዲፕሎማሲ አንፃር ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የምዕራቡ ዓለም የትኩረት ማዕከል እየሆነ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ ጠንካራ አጋር ሆና በመቅረብ፣ ከዚሁ አንፃር ዓለም አቀፍ ተሰሚነቷንና ወሳኝ አጋርነቷን በማሳየት ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖዋን በማሳደግ፣ ከፖለቲካ ፍላጎት አኳያ በውጭ ኃይሎች ሊቃጣባት የሚችልን የዲፕሎማሲ ጫና መቀነስ (ማካካስ) ትችላለች፡፡

  • አፍቃ ኢትዮጵያ (Pan Ethiopian) አፍቃ አፍሪካ (Pan African) ዓለም አቀፍ የዲጂታልትመት ሚዲያዎችን ማቋቋም

ሌላው በዲፕሎማሲው መስክ መሠራት የሚገባው የአገሪቱን ዓለም አቀፋዊነት ማጉላት የሚያስችሉ መንገዶችን መጠቀም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሁለት ጉዳዮች እጠቅሳለሁ፡፡ አንደኛው የአገሪቱን ስምና ግርማ በዓለም መድረክ የሚወክሉ ተቋማት የመኖሩ ነገር ነው፡፡ ሁለተኛው የኢትዮጵያዊያን ሥነ ልቦናዊና ባህላዊ መሠረቶች አገሪቱን ዓለም አቀፋዊ ከማድረግ አንፃር ያላቸው አስተዋጽኦ ሌላው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ጉዳዮችና አጀንዳዎች ትናንትም፣ ዛሬም ቁርጠኛ መሆኗን በተደጋጋሚ አሳይታለች፡፡ በተለያየ ዘመን ኢትዮጵያ የአስተዳደሩ መሪዎች ምንም እንኳን በርዕዮተ ዓለም፣ በአገር ውስጥ የፖለቲካ ፍልስፍና ወይም የአመራር ዘይቤ የተለያየ መልክ የነበራቸው ቢሆንም፣ ለዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ ግን አንድ ዓይነት አመለካከት ነበራቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከአፍሪካ ኅብረት ጀምሮ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሥራች አባል አገር ናት፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ፣ እንዲሁም ቀጣናዊ ተቋማት ዋና መቀመጫ ናት፡፡ የመከላከያ ኃይሏ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ግዳጆች በግንባር ቀደምትነት ያገለገለና እያገለገለ ያለ፣ በወታደራዊ ዲሲፕሊኑ የተመሰከረለት ነው፡፡ በአፍሪካ ስደተኞችን ተቀብላ መጠለያ በመሆን ሦስተኛ ናት፡፡ እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ በ2020 በአገሪቱ 720,000 ስደተኞች ነበሩ፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም፣ ልማትና ትብበር እጅግ የጎላ ሚና ብትጫወትም፣ ዓለም ይህን በሚገባ የተረዳ ስለመሆኑ በእጅጉ እጠራጠራለሁ፡፡ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ፖሊሲ (መስመር)፣ ይህን አገሪቱ ለዓለም ያበረከተችውንና እያበረከተች ያለችውን አስተዋጽኦ በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ተፅዕኖ ፈጣሪ ትሆን ዘንድ ምን ያህል ተጠቅሞበታል? የሚለው ጉዳይ መልስ የሚሻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሁሉም መስኩ ለዓለም ብታበረክትም ዓለም አቀፋዊ መሆን አልቻለችም፡፡

ታዲያ ይህን የኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊነት የሚያጎላ ገጽታ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ለማስረፅ ይቻላል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ጠንካራ ዓለም አቀፍ ሚዲያ መገንባት ነው፡፡ ይህ ሚዲያ የአገሪቱን አጀንዳዎች ለዓለም በዋና ዋና ዓለም አቀፍ ቋንቋንዎች ከማሠራጨት ባለፈ፣ በሚዲያ ፕሮፌሽናሊዝምና በተዓማኒ መረጃ ምንጭ ሆኖ የአገሪቱ ምልክትና ግርማ ሞገስ መሆን ይችላል፡፡ እንደ ኳታር ያሉ በሕዝብ ብዛትም ሆነ በቆዳ ስፋት አነስተኛ የሆኑ አገሮች በዓለም መድረክ ገዝፈው እንዲታዩ በማድረግ ረገድ፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቃሞቻቸው ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ኢትዮጵያም እንዲህ ያለ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ቢኖራት፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም መድረክ ግርማዋን ከፍ የሚያደርግ፣ አጀንዳዎቿን ለዓለም ለመሸጥ ትልቅ ዕድል የሚፈጥርና በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ተሰሚነቷን ማሳደግ ትችላለች፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎቿ ኢትዮጵያን በዓለም ከማስተዋወቅ ከሚኖራቸው ሚና አኅጉራዊ አጀንዳዎች የሚቀርቡበት አፍቃሪ – አፍሪካዊ (Pan – African) ጉዳዮች ላይ አተኩረው የአፍሪካን ዓለም አቀፋዊነት ጭምር የሚያጎሉ ይሆናሉ፡፡ ሚዲያዎቹ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊነት በማጉላት አገሪቱ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ የሚኖራትን ተፅዕኖ ከማሳደጉ ባለፈ፣ የአገሪቱን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ መስህቦችን ለዓለም በማድረስ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል፡፡

 

የዲፕሎማሲ ሥራው በዓለም አቀፋዊነትነ ልቦና የተደገፈ እንዲሆን ማስቻል

ኢትዮጵያ ለዓለም በርካታ ነገር እያበረከተች፣ ዓለም ግን በሚገባት ደረጃ የሚያውቃት አይመስለኝም፡፡ የአንድን አገር ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ሊያመጣ የሚችለው በመንግሥት የዲፕሎማሲ ሥራ ብቻ ሳይሆን በዜግነት ዲፕሎማሲም ጭምር ነው፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት የሕዝብ ሥነ ልቦና ዓለም አቀፋዊነት የሚጠይቀውን የዕሳቤ (ከቦታ አንፃር) አድማስ፣ ከአገር ቤት ውጭ በዓለም መድረክ ጎልቶ ለመውጣት የሚበረታታ አለመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያዊያን በዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መድረኮች ምን ያህል ተሳትፎ አላቸው የሚለው የሚሠራው ለዚህ እንደ አስረጂ ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ለምሳሌ ኢትዮጵያዊያን ምሁራንና ባለሙያዎች በአኅጉራዊና በዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ላይ ተቀጥረው እየሠሩ አናያቸውም፡፡ በአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ዜጎች አንፃር እንኳን በጣም ያነሰ ተሳትፎ ነው ያላቸው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የተማሩና የሠለጠኑ ኢትዮጵዊያን ጠፍተው አይደለም፡፡ ይልቁንም እንደ አንድ ሕዝባዊ የጋራ ሥነ ልቦና መገለጫ ያላቸው ዓለም አቀፋዊ ዕይታ (International Mindset) ከአገራቸው ድንበር ብዙም የማይዘል መሆኑ ነው፡፡ በጣም የተማሩ የሚባሉትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ኢትዮጵያዊያን እንኳን የተሳትፎ አድማሳቸውን ዓለም አቀፍ ለማድረግ ይቸገራሉ፡፡ የመገናኛ አውታሮች በስፋትና በአማራጭ ለመጠቀም በምንችልበት በዛሬው ዘመን እንኳን፣ ኢትዮጵያዊያን እነዚህን የመገናኛ አውታሮች ተጠቅመው በአጀንዳዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ አይስተዋልም፡፡ ተማሩ የምንላቸው ኢትዮጵያዊን ዘመኑ ያፈራቸውን የመገናኛ ቴክኖሎጂ አማራጮች ተጠቅመው፣ ዓለም አቀፍ ዕድሎችን የመፈለግና የመጠቀም ንቃተ ህሊናቸው እምብዛም ነው፡፡

ኢትዮጵያ የምትከተለው የዲፕሎማሲ ፖሊሲና ስትራቴጂ ይህንን ሕዝባዊ ሥነ ልቦና ከግምት ያስገባ መሆን አለበት፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖው በሁሉም መስክ በበረታበት በአሁኑ ወቅት፣ የዲጂታል ዲፕሎማሲን ተጠቅማ አገራዊ አጀንዳዋንና ዓላማዎቿን ለዓለም ለማድረስ፣ ሕዝቡ (በተለይ የልሂቃኑ ክፍል) ዓለም አቀፋዊ ሥነ ልቦናን ሊይዝ ይገባዋል፡፡ በተለመደው የዲፕሎማሲ መስክ (Conventional Diplomacy) የሙሉ ጊዜ ሥራቸው የሆነው ዲፕሎማቶቻችንም አገራዊ ተልዕኮዎቻቸውን በብቃት እንዲወጡ፣ የዓለም አቀፋዊነት ሥነ ልቦና ሊያዳብሩ ግድ ይላቸዋል፡፡

ለአንባቢያን እንደ ማስታወሻ፡- ይህ አጭር ጽሑፍ በታኅሳስ ወር 2014 ዓ.ም. ለኅትመት ከበቃው ‹‹ኢትዮጵያን እንዴት እናሻግራት?›› ከሚለው መጽሐፌ ምዕራፍ አሥራ ስምንትገጽ 221 እስከ 230 ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው ruhe215@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...