እንግሊዝ ጠንካራ የኢኮኖሚ መናጋት ውስጥ የገባችው አገሮች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተመቱበት ወቅት ቢሆንም፣ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ችግሩ በሌሎች አገሮች ላይ እንደተከሰተው ሁሉ ፈትኗታል፡፡
የኢኮኖሚው መዋዠቅና የፖለቲካው አለመረጋታት ይበልጡኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት የገነኑባት እንግሊዝ፣ እ.ኤ.አ.አ በ2019 ከተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ በኋላ ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮቿን አሰናብታ ትናንት ሦስተኛውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክን ሾማለች፡፡
በእንግሊዝ ምክር ቤት ውስጥ አብላጫ ድምፅ ያለው ወግ አጥባቂ ፓርቲ ከ2019 ወዲህ ቦሪስ ጆንሰንን በኋላም ሊዝ ትረስን የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ቢሾምም፣ ሁለቱም የሥልጣንና የሥራ ጊዜያቸውን ማጠናቀቅ አልቻሉም፡፡
ከሁለት ወራት አስቀድሞ ሥልጣን እንደሚለቁ ባስታወቁት በቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ምትክ ሊዝ ትረስ መንበሩን ተረክበው የነበረ ቢሆንም፣ ከ45 የሥራ ቀናት በኋላ የሥልጣን መልቀቂያቸውን አስገብተዋል፡፡
ቦሪስ ጆንሰን ከሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ በወግ አጥባቂው ውስጥ በተደረገ ምርጫ ሊዝ ትረስና የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ተወዳድረው የነበረ ቢሆንም፣ ትረስ ነበሩ በምርጫው ያሸነፉት፡፡
ሆኖም ትረስ ግብር ለመቀነስና የንግድ አሠራሩን ለማሻሻል የጀመሩት ሥራ የእንግሊዝን ኢኮኖሚ ይበልጡኑ በማዳከሙ፣ ትረስ ከሥልጣን ለመልቀቃቸው ምክንያት ሆኗል፡፡
አዲሱ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የ42 ዓመቱ ሪሺ ሱናክ ይህንን የትረስ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ያልተጠበቀ ብለውታል፡፡ ‹‹የትረስ ስህተት›› ማለታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከፔኒ ሞርዳንት ጋር ተወዳድረው አብላጫውን የምክር ቤት ድምፅ ያገኙት ሱናክ ባደረጉት ንግግር፣ እንግሊዝ ያጋጠማትን መሠረታዊ የኢኮኖሚ ፈተና በአንድነት፣ በሃቀኝነትና በትህትና ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡
የትረስ ያልተደጎመ የግብር ቅነሳ እንቅስቃሴ የብሪታኒያን ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ከቶታል በሚል የምረጡኝ ዘመቻ ሲያካሂዱ የቆዩት ሱናክ፣ ‹‹እኔ የእንግሊዝን ኢኮኖሚ ለማስተካከል ትክክለኛው ሰው ነኝ፤›› ብለዋል፡፡
ፖለቲከኞች ግን ሱናክ ኢኮኖሚውን ለማስተዳደር አይችሉም ይሏቸዋል፡፡ የሌበር ፓርቲ መሪ ኪር ስታርመርንን ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው፣ ከ12 ዓመታት የእንግሊዝ የተወካዮች ምክር ቤት ውድቀት በኋላ፣ እንግሊዛውያን እየተዟዟረ ከሚበጠብጣቸው የኢኮኖሚ ቀውስ የሚያወጣቸው የተሻለ አመራር ያስፈልጋቸዋል፣ ሆኖም አላገኙም ብለዋል፡፡
ሱናክ ይህንን ለማሳካት ተጨባጭ የሆነ ውጤት አሁኑኑ ማሳየት ይገባቸዋልም ሲሉ አክለዋል፡፡ በኖቲንግሃም ትረንት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሁሩ ቶም ኬያጊል በበኩላቸው፣ ሱናክ በጠረጴዛቸው ላይ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቋቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ትረስ ማሻገር ያልቻሉትና ለውድቀት ያበቃቸውን ዝቅተኛ በጀት ያነሱት ኬያጊል፣ የገንዘብ ገበያው መረጋጋትና መተማመን ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ ድጎማዎችን ማንሳት ወይም ግብር መጨመርም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የተከፋፈሉ ፓርቲዎችን አንድ ማድረግም የሱናክ የቤት ሥራ ይሆናል ብለዋል፡፡ የእንግሊዝን ኢኮኖሚ ለመታደግ በርካታ የቤት ሥራዎች ይጠብቋቸዋል የተባሉት የሂንዱ ዝርያ ያላቸው ሱናክ፣ ትረስ የሠሯቸውን ስህተቶች ማረም እንግሊዝንና ፓርቲያቸውን ማስተሳሰር ቅድሚያ የሚሰጧቸው ሥራዎች መሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡
የቢቢሲ የኢኮኖሚ አርታኢ ፈይሰል ኢስላም እንደሚለው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ በፍጥነት እየናረ የመጣውን የዋጋ ውድነት ማረጋጋት ሱናክን የሚጠብቃቸው ፈተና ነው፡፡
የነዋሪዎችንና የነጋዴዎችን የኤሌክትሪክና የጋዝ ክፍያ ለማገዝ የኢነርጂ ዋጋ ዋስትና ድጎማ ለቀጣይ ሁለት ዓመት እንዲዘልቅ የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ትረስ አሳውቀው የነበረ ቢሆንም፣ አዲሱ ቻንስለር ጄርሚ ሃንት እስከ ሚያዝያ 2022 ብቻ የሚቆይ መሆኑን ማሳወቃቸው ሌላው መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡
ሱናክ ጥቅማ ጥቅሞች እንደሚጠበቁ፣ የታክስ ክሬዲትና ጡረታ አሁን በእንግሊዝ ካለው የ10.1 በመቶ የዋጋ ግሽበት ጋር በተጣጣመ መልኩ እንደሚስተካከል ቢናገሩም፣ ይህን ቃል ተግባራዊ ማድረግ ከባድ ይሆናልም የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡
የጤና ኢንሹራንስ፣ የሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ፣ ለዩክሬን የሚደረግ ድጋፍና የእንግሊዝ መከላከያ በጀት፣ የሰሜን አየርላንድ ፕሮቶኮልና ሌሎችም ቀጣዩ የሱናክ ፈተናዎች እንደሚሆኑ ቢቢሲ በትንታኔው አስፍሯል፡፡