ለዓመታት በዕድሳት ላይ ቆይቶ ሥራው የተጠናቀቀው የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት፣ ከዓርብ ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚዘልቅ ጥበባዊ መሰናዶ በይፋ ይመረቃል፡፡ በሦስቱ የምረቃ ቀናት የሚቀርቡት ጥበባዊ መሰናዶዎች የቴአትር ቤቱን የዘጠኝ አሠርታት ግድም ታሪክ የሚያሳይ ዓውደ ርዕይ፣ ኮንሰርትና ዓውደ ጥናት መሆናቸውን የገለጸው ሀገር ፍቅር በማርሽ ባንድ የታጀበ የእግር ጉዞም ይኖራል ብሏል፡፡
በዕድሳቱ የትልቁ አዳራሽ ዘመናዊ የወንበር መግጠም፣ የመጋረጃና የዓውደ ጥበብ ማሳያ (ጋላሪ)፣ የሠራተኞች መዝናኛ ክበብ፣ የግቢውን ወለል በአዲስ አስፓልት የማንጠፍ፣ የመድረክ ጀርባ፣ የቢሮና የአትክልት ሥፍራዎች የማስተካከል ሥራዎች መሠራታቸውን ቴአትር ቤቱ አስታውቋል፣
ሀገር ፍቅር ቴአትር ‹‹የኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ማኅበር›› በሚል መጠሪያ ሐምሌ 11 ቀን 1927 ዓ.ም. መቋቋሙ ይታወሳል፡፡