Saturday, March 2, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ሥርየትም አልሻ፣ ስኬትም አያምረኝ

ትኩስ ፅሁፎች

ጥንቸል ሁዋላ ቀረች ፤ በኤሊ ተቀድማ-

-በሩጫ በዝላይ

የመስቀል ወፍ መጣች፤ በገና ዋዜማ

አደይ ለመለመች፤ ትኩስ አቧራ ላይ::

አትላስ ትናንትና፤ ሸክሙን ፈጠፈጠው

ሲሲፈስ ሰልችቶት፤ አለቱን ፈለጠው

የኔ አመል ብቻ ነው፤ የማይለወጠው::

ተነሳሁ ከንቅልፌ

ንጋት ከነጣጣው፤ ቁሟል  ከደጃፌ፤

ስፋለም አልታይ

ለሥልጣን ለሜዳይ

ከትጉሀን ጋራ ንብረት አልሻማ

አልሞት ወይ አልገድል፤  ለባንዲራ ላርማ

ደግሞ መተኛት ነው፤ የሕይወቴ ዓላማ::

ላዳም ልጆች ሁሉ፤ ወትሮ ብርቅ አይደለም

በትንሽ አልጋ ላይ፤ በትልቁ ማለም::

እኔ ግን ተኛሁኝ፤

በዳመናዎች ላይ እግሮቼን ሰቅየ

የህልሜን ቡቃያ፤ እንዳረም ነቅየ::

ደሞ አንዳንድ ጊዜ

የሌሊቱ ግርማ፤ ተማላይ ሲያደርገኝ

ይሄ ነው ጸሎቴ፤ የሚሰማ ቢገኝ፤

‘አይቀንስ ደስታየ፤ አይጨምር ስቃየ

‹‹እኔ እንዳለሁ አለሁ›› ይሁን ሙዚቃየ

የጊዜ ሥውር እጅ፤  ዕዳና ስጦታው የተትረፈረፈ

እንዳለሁ ያስቀረኝ

ከዚያ በተረፈ

ሥርየትም አልሻ፤ ስኬትም አያምረኝ::

በገጣሚ በዕውቀቱ ሥዩም

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች