መንግሥት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በፖሊሲ ደረጃ ውሳኔ ማሳለፉ ትክክል ቢሆንም፣ ይገቡበታል ተብሎ እየተገለጸ ያለው አካሄድ ሥጋት ያሳደረባቸው ስለመሆኑ የፋይናንስ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ አሉ የሚባሉ ክፍተቶችን ለመድፈን የሚያስችሉ አሠራሮችን እከተላለሁ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱን አስመልክቶ ከፋይናንስ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ትናንት ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ውይይት፣ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የተፈቀደበት መንገድ ላይ አለ የሚሉትን ሥጋቶቻቸውን የገለጹ ሲሆን፣ መፍትሔ ያሉትንም በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በዕለቱ አስተያየታቸውን የሰጡት አብዛኛዎቹ የሥራ መሪዎች የውጭ ባንኮች መግባትና መፈቀዱ አግባብ ስለመሆኑ ገልጸው፣ አገባባቸው ግን ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን እንደሚገባው ከማመልከታቸውም በላይ፣ ምርጫቸው ከኢትዮጵያ ባንኮች ድርሻ ገዝተው እንዲገቡ ማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመንግሥት ዕቅድ መሠረት የውጭ ባንኮች በአራት መንገዶች እንዲገቡ የሚፈልግ ቢሆንም፣ ብዙዎቹ የፋይናንስ ባለሙያዎች ግን አገባባቸው በጆይንት ቬንቸር ወይም ካሉት ባንኮች ላይ አክሲዮን በመግዛት ይሁን የሚለው ሐሳብ የብዙዎች ስለመሆኑ በዕለቱ ከተሰጡ አስተያየቶች መረዳት ተችሏል፡፡ የውጭ ባንኮች እንዴት ይግቡ? በሚለው ጉዳይ ላይ በመንግሥት በቀረበው ዋነኛ ሐሳብ መሠረት፣ ከቀረቡ አማራጮች ውስጥ ብዙዎች የደገፉት ከአገር ውስጥ ባንኮች ላይ አክሲዮን በመግዛት ይግቡ የሚለው ቢሆንም፣ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው 40 በመቶ ድረስ የሚሆን ድርሻ ገዝተው መሆኑ ጥያቄ አስነስቷል፡፡
በፖሊሲው የተቀመጠው ለውጭዎቹ ተላልፏል ተብሎ ከሚጠበቀው ከ40 በመቶ ውስጥ 30 በመቶ የውጭ ባንኮች፣ አምስት በመቶ የውጭ ዜጎችና አምስት በመቶ በኢኪውቲ (Equity) መግዛት የሚል ነው፡፡ ይህ ምጣኔ ግን በጣም የበዛ ስለመሆኑ ያመለከቱት የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ፣ 30 በመቶ የውጭ ባንኮች ገዝተው ግቡ መባሉ በባንኮች ውስጥ ወሳኝ እንዲሆኑ (ዶሚናንት) እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል በሚል ሞግተዋል፡፡ ‹‹በእኛ አገር ሕግ በባንክ ውስጥ አምስት በመቶ የያዘ ባለአክሲዮን ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኑ በግልጽ እየታወቀ፣ አሁን ባለው ዕሳቤ 30 በመቶ የሚሆነውን ለውጭ ባንክ መስጠት በጣም ተፅዕኖ ፈጣሪ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ አሁን በግልጽ እንደሚታየውም ባንኮች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የሚገኙ ባለአክሲዮኖች ቢበዛ 70 በመቶ ነው፡፡ ስለዚህ ለውጪዎቹ 30 በመቶ ድርሻ ይዘው እንዲገቡ ከተፈቀደላቸው ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው ጎልቷል በማለት የገለጹት አቶ በቃሉ፣ በኢትዮጵያ በአንድ ፋይናንስ ተቋም ውስጥ መያዝ ያለበት ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ መጠኑ አምስት በመቶ መሆኑ፣ ይህ ሕግ ቀርቶ ሌላ 30 በመቶ ሊይዝ የሚችል ከሌለ የውጭዎቹ የበላይነቱ እንዲይዙ ያደርጋል በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በረቂቁ ላይ ግን 30 በመቶ የውጭ ባንኮች ሌሎች ደግሞ 10 በመቶ ገዝተው እንዲገቡ የተፈቀደበት ምክንያት ተብሎ የተገለጸው፣ የአገር ውስጥ ባንኮች 60 በመቶ ወይም አብላጫውን እንዲይዙ ታስቦ ነው መባሉ፣ መሬት ላይ ካለው እውነት ጋር አያስኬድም ይላሉ፡፡ አሁን እየተሠራበት ካለው የኢትዮጵያ ሁኔታ አንፃር ተቃርኖ ያለው በአምስት በመቶ እንኳን ተፅዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ፣ ይህ አመለካከት ሊጤንበት ይገባል በማለት ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ይህንኑ የአቶ በቃሉ ሐሳብ ሌሎችም የተጋሩት ሲሆን፣ ጉዳዩ እንዲታሰብበትም አመልክተዋል፡፡
ሌላው በዚህ መድረክ አነጋጋሪ የሆነው ጉዳይ ብሔራዊ ባንክ የአገር ውስጥ ባንኮች በውጭ ባንኮች መግባት ችግር የሚገጥማቸው ከሆነ፣ እንዲዋሀዱ ውሳኔ ሊያሳልፍ ይችላል ተብሎ በረቂቅ ደንቡ ላይ የተቀመጠው ሐሳብ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች ከመግባታቸው በፊት ነው የኢትዮጵያ ባንኮች መዋሃድ ያለባቸው ወይስ ከገቡ በኋላ ነው? የሚል ጥያቄ በማንሳት ሐሳባቸውን የሰጡት አቶ በቃሉ፣ ባንኮቹ ችግር ውስጥ ከገቡ በኋላ ነው ወይ ተዋሃዱ የሚባለው የሚለው ጉዳይም ብዥታ የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህ ዘርፍ ለረዥም ጊዜ ተዘግቶ የቆየ ገበያ ስለሆነ መከፈቱ በጣም ተገቢ ነው ብለው እንደሚምኑ የገለጹት የፀደይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መኮንን የለውምወሰን፣ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መወሰኑ መልካም ዕድሎችን የሚያመጣ ስለሆነ ፖሊሲው የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ይህንን የውጭ ባንኮች ለመተግበር የኢትዮጵያ የፖሊሲ ሪፎርም አብሮ ካልሄደ ይህንን ዕድልና ይህንን ኢኮኖሚ እንዴት ሊጠቀም ይችላል የሚለው ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል፡፡
ፋይናንስ ዘርፉ የኢኮኖሚ ዋና አንቀሳቃሽ ነው ከተባለ፣ ኢኮኖሚው ያንን መሳብ ካልቻለና የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ አብሮ እኩል የሚያድግ ካልሆነ ገባ የተባለው ገንዘብ ባልታሰበ መንገድ ወጥቶ የበለጠ ችግር እንዳይፈጥር ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ የውጭ ባንኮች በውጭ የሚገጥማቸውን ቀውስ እዚህ ይዘው ሊገቡ ስለሚችሉም ይህን መቋቋም የሚያስችል ኢኮኖሚ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡ አሁን ባለው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት፣ የውጭ ባንኮችን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት ጊዜው አይደለም የሚለውም ጥያቄ ከፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎችና ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች ሳይፈቱ ባንኮቹን ማስገባት ችግሩን ማባባስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለዚህ ጥያቄ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ቺፍ ኢኮኖሚስት አቶ ፈቃዱ ገድፌ፣ ‹‹አሁን ባለው የፋይናንስ ዘርፉ እነዚህን ነገሮች እንዴት አፌክት አድርጓቸዋል የሚለው ነገር ሊታወቅ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ አሁን ባለው የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ተጨማሪ ነገር መጨመር አሁን ያለውን ችግር ያባብሳል ማለት እንደማይቻል ገልጸው፣ የውጭ ባንኮች መግባታቸው ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡ የበጀት ፋይናንስ የማግኘት ዕድል ሊያስገኝ የሚችል በመሆኑ፣ በዚህ ደረጃ መሠጋት እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡ በዚህ መድረክ ባንኮቹን ለመቆጣጠር አሁን ባለው ሁኔታ የውጭ ባንኮች ሊመጡ ይችላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄም ከብዙዎች የተነሳ ሲሆን አቶ ፈቃዱ፣ ‹‹ይህ የእኔም ጥያቄ ነው፤›› ይላሉ፡፡ አሁን ሊመጡም ላይመጡም ይችላሉ፡፡ አሁን አይመጡም ብለን መደምደም ግን አይቻልም ብለው፣ ‹‹ቴሌኮሙዩኒኬሽንን ስንከፍት በዚህ ዘርፍ ለመሰማራት የመጡ እንዳሉ ሁሉ፣ ያልመጡም ስላሉ በባንክም ዘርፉ ኃላፊነት ወስደው ወደፊት የተሻለ ነገር ይኖራል ብለው የሚያስቡ ሊመጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ዕቅድ በሚቀመጠው መሥፈርት እንዲገቡ ይፈልጋል ያሉት ምክትል ገዥው፣ አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ ላይመጡ ይችላሉ ከሚለው ሥጋት ይልቅ ባንኮቹ እንዲገቡ በምንሠራው ሥራ ላይ የሚመሠረት ይሆናል ብለዋል፡፡ ‹‹እኛ እንዲገቡ በሩን ክፍት እናደርጋለን፤›› በማለትም እንዲገቡ በፖለሲው የተቀመጡትን አራት አማራጮች በማቅረብ በተሻለው መንገድ እንዲገቡ የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የውጭ ባንኮችን ለማስገባት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአቅም ጉዳይም በመድረኩ ተነስቷል፡፡ በተለይ በፖሊሲው ባንኩ እየተፈተነ፣ እየጠነከረ ይሄዳል የሚለው አመለካከት ትርጉም ያልሰጣቸው መሆኑን የገለጹት የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ፣ ከመግባታቸው በፊት አቅም አሳድጎ መጠበቁ አይሻልም ወይ? የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንሻል ተቋማት ሱፐር ቪዥን ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ፣ እንደተቆጣጣሪ ራሳቸውን እንደሚያበቁና እንደ ወርቅ ተፈትነው ይህንን ኃላፊነታቸውን እንዲያውቁ እየተነሱም ቢሆን እንደሚወጡት አስረድተዋል፡፡ የባንኮች ውህደትን በተመለከተም ብዙ የሚያሠጋ ጉዳይ አለመሆኑንና ያሉን ባንኮች ጥቂት በመሆናቸው፣ የውጭ ባንኮች ከገቡ በኋላም ሆነ በፊት ውህደቱ ቢደረግ የሚያመጣው ችግር የሌለ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ መድረክ ላይ በርካታ ሥጋቶችንና መሆን አለባቸው የተባሉ ሐሳቦችን የፋይናንስ ተቋማቱ ኃላፊዎች ያቀረቡ ሲሆን፣ ከመድረክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ እያንዳንዱን ሐሳብ በመውሰድ በመመርያ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ካሉ በዚያ እንዲካተቱ የሚያደርጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ ማዕዘኖች የቀረቡትን ሥጋቶች ለመቅረፍም አስቻይ ሁኔታዎች ስላሉ፣ እሱን የተከተሉ የሚሠሩ እንደሚሆንም አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡ ይህ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሚፈቅደው መመርያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለመተግበር የታቀደ ሲሆን፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ፖሊሲውን ለማስፈጸም ገና ዝርዝር ጉዳዮች የሚቀርቡ ስለሆነም ብዙዎች ሐሳባቸውን በጋራ እያዳበሩ የሚሄዱ መሆኑንም ኃላፊዎቹ አመልክተዋል፡፡