Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበጉምሩክ ኮሚሽን የሙስና ተጋላጭነት የሚታይባቸው አሠራሮች መኖራቸው ይፋ ተደረገ

በጉምሩክ ኮሚሽን የሙስና ተጋላጭነት የሚታይባቸው አሠራሮች መኖራቸው ይፋ ተደረገ

ቀን:

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለፉት ጥቂት ወራት በጉምሩክ ኮሚሽን የሙስና ተጋላጭነት ሥጋት ላይ አካሄድኩት ባለው ጥናት፣ በርካታ ለሙስና ተጋላጭ የሚያደርጉ አሠራሮች መኖራቸውን ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡

ሪፖርተር ያገኘው የጥናት ውጤት ሰነድ እንደሚያሳየው፣ በጥናቱ ውስጥ ለሙስና ሥጋት ተብለው ከቀረቡት ጉዳዮች መካከል የዋጋ አተማመን መመርያን መሠረት ያላደረገ የዋጋ አወሳሰን ይገኝበታል፡፡

ለሙስና ሥጋት ተጋላጭነት እንደ ምክንያት የተቀመጠው የመነሻ ዋጋ ያልተቀመጠላቸው በርካታ ዕቃዎች መኖር፣ የቁጥጥርና የክትትል መላላት፣ የሥነ ምግባር ጉድለትና በአጥፊዎች ላይ የሚወሰድ ዕርምጃ ከጥፋቱ ጋር ተመጣጣኝ አለመሆን የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ በጥናቱ ሙስና ተጋላጭነት ሥጋት ውስጥ ተቋሙን የከተተው በዕቃዎች ላይ መመርያን ያላማከለ ታሪፍ መመደብ ነው፡፡ በዚህ የተጋላጭነት ሥጋት ውስጥ የታየው ችግር ወደ አገር ውስጥ የገቡ ዕቃዎችን ትክክለኛ ብዛት፣ ክብደት፣ ዓይነትና የሥሪት አገር መረጃዎችን ሳይጠቀሙ ቀረጥና ታክስ መጣልና በተሳሳተ ሲስተም ቁጥር መዝገብ ገቢ ማድረግ ይገኝበታል፡፡

በጥናቱ ለችግሩ መከሰት እንደ ዋነኛ ምክንያት የተነሱት የታሪፍ በየጊዜው መቀያየር፣ በገቢዎች ሚኒስቴርና በገንዘብ ሚኒስቴር የቅንጅት ክፍተት መኖር፣ እንዲሁም የሥነ ምግባር ጉድለት ይገኙበታል፡፡

ኮሚሽኑ ከጥናቱ ጠቅላላ ተሳታፊዎች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት የቃለ መጠይቅ መላሾች ነገሩኝ እንዳለው፣ ከፍተኛ ታክስ ወይም ቀረጥ ሊጣልባቸው የሚገቡ ዕቃዎች በዝቅተኛ ምድቦች የመተመን ሥራ ይከናወናል፡፡ በዚህም የተነሳ መንግሥት በየቀኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያጣ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የኢንሹራንስ፣ የባህር ትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎችን በተመኑ መሠረት ያለማስላት ችግር እንዳለ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በኢንሹራንስ ተቋማት በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ደረሰኝ ዝቅ አድርጎ መተመን (Under Invoicing) እየተለመደ መምጣቱ ተመላክቷል፡፡ ጉምሩክ ኮሚሽን የኢንሹራንስ ደረሰኝ ማቅረብ አስገዳጅ ቢያደርግም፣ ዝቅ ተደርጎ የተቆረጠ ደረሰኝ ቢሆንም ተያይዞ ለቀረጥና ለታክስ ሥሌት እንደሚውል፣ ደረሰኝ ዝቅ አድርጎ መቁረጥ በሕግ የማይከለከል በመሆኑ የተጭበረበረ ደረሰኝ ካልሆነ በስተቀር እንደሚስተናገድ ተገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ በጥናት ሪፖርቱ መንግሥት ደረሰኝ ዝቅ አድርገው የሚቆርጡ አካላትን በተመለከተ የሚቆጣጠር ሕግ ሊያወጣ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

በጥናቱ እንደተገለጸው የውጭ ንግድ ማበረታቻ ሥርዓትን በአግባቡ አለመጠቀም የሙስና ሥጋት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው፣ አንዳንድ ምርቶች በውድ የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው ወደ አገር ከገቡ በኋላ ወደ ምርት ሳይቀየሩ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያልፍባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል የቀረጥ ነፃ መብት በተለያዩ አካላት የሚሰጥ በመሆኑ በአግባቡ መተግበራቸውን የሚከታተል፣ የሚደግፍና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚያስተባብር የረባ ቁመና ያለው አደረጃጀት አለመኖሩን ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ኮሚሽኑ ሕገወጥ ሥራ ላይ በተሰማሩ ሠራተኞች ላይ አስተማሪ የሆነ ዕርምጃ እንዲወስድባቸው፣ ዕቃዎች በጊዜያዊነት ሲገቡና ሲወጡ በመግቢያ በሮች እንዴት መስተናገድ እንዳለባቸው የሚገልጽ ግልጽ መመርያና ደንብ ነድፎ ሥራ ላይ እንዲያውል ተጠይቋል፡፡

ሰነድና ገደብ ወይም ክልከላ የተደረገባቸውን ዕቃዎች በተመለከተ በመመሳጠር በኬላ የማሳለፍ ተግባር መኖሩ ተገልጿል፡፡ በዚህ አሠራር ውስጥ ሰነድ አልባ ዕቃዎችን በመመሳጠር በኬላ ማሳለፍ፣ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ የተከለከለን ወይም ገደብ የተደረገበትን ዕቃ በአግባቡ ሳይፈተሹ በኬላ ማሳለፍ፣ ዕቃ የማጉደል፣ የመቀነስና ቅሸባ በከፍኛ ደረጃ መኖሩ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

በመጠይቁ ውጤቱ እንደተገለጸው 48 በመቶ ተሳታፊዎች የኮንትሮባንድ ተግባራትን ዓይቶ እንዳላዩ ማለፍ ተግባር መኖሩን መናገራቸውን፣ እንዲሁም ወደ 40 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የሸቀጦችን ለኮንትሮባንድ የማመቻቸት ወይም የማደራጀት ተግባር እንደሚፈጸም መግለጻቸው ተመላክቷል፡፡

የጥናቱን ውጤት በተመለከተ ከጉምሩክ ኮሚሽን የበላይ ኃላፊዎች ማብራሪያ ለማግኘት ሙከራ የተደረገ ሲሆን፣ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የተቋሙ ኃላፊ የተባለው የጥናት ውጤት ከኮሚሽኑ እንዳልደረሳቸውና ባልደረሳቸው ጉዳይ መልስ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...