የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በመጋዘኖች ባደረገው ቆጠራ ወደ ውጭ መላክ የነበረበትን 944,023 ኩንታል ጥራጥሬና የቅባት እህል አከማችተው የተገኙ ላኪዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምርቱን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው፡፡
ሚኒስቴሩ ትናንት ሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ከላኪዎች ጋር ባደረገው ውይይት ምርቱን በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ወደ ውጭ የማይልኩ አምራቾች ላይ እስከ የሕግ ተጠያቂነት የሚያደርስ ዕርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ተወካይ ዳይሬክተር ወ/ሮ ቁምነገር እውነቱ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር እህል አከማችተው የነበሩ 26 ላኪዎች መጋዘናቸው ታሽጎ እንደነበር አስታውሰው አሁን ማስጠንቀቂያው የተሰጠው ተመሳሳይ ዕርምጃ ከመወሰዱ በፊት ለማሳሰብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተወካይ ዳይሬክተሯ፣ ‹‹የሚላከው ምርት በጣም እያነሰ፣ እየወረደ ስለመጣ ከዕቅዳችን በታች እንዳይሆን ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነው ይህ ስብሰባ የተካሄደው፤›› ሲሉ ላኪዎች እንዲሰበሰቡ የተደረገበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡
ከላኪዎች ጋር በነበረው ውይይት ላይ 944,023 ኩንታል ጥራጥሬና የቅባት እህል የተገኘው ሚኒስቴሩ ሦስት ቡድኖችን በማሰማራት ከመስከረም 13 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ቆጠራ ካከናወነ በኋላ ነው፡፡ የመጀመርያው ቡድን በአማራ ክልል አምስት ከተሞች ውስጥ ያሉ መጋዘኖች ላይ ቆጠራ ሲያካሂድ ሁለተኛ ቡድን አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ሐዋሳና ወላይታ ሶዶ ከተሞችን ዳሷል፡፡ በሦስተኛ ምድብ የተሰማራው ቡድን ቆጠራውን ያካሄደው አዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ አምስት ከተሞች ውስጥ ነው፡፡
ሪፖርተር በስብሰባው ላይ ከተሳተፉ ሦስት ላኪዎች ያገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ሚኒስቴሩ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመጥቀስ ላኪዎቹ እህል በማከማቸት የውጭ ምንዛሪ እዳይገኝ ማድረጋቸውን አንስቶ ወቅሷል፡፡ በመጋዘን ውስጥ የተገኘው ምርት እየተጠናቀቀ ባለው የ2014/15 ምርት ዘመን ወደ ውጭ መላክ የነበረበት እንደሆነና ከዚህ በላይ በመጋዘን ውስጥ የሚቆይ ከሆነ የምርቱ ዋጋ እየቀነሰ እንደሚመጣና ይህም መገኘት የነበረበትን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያሳጣ ገለጻ መደረጉን ላኪዎቹ አስረድተዋል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ላኪ፣ በስብሰባው ላይ የተገኙት የሚኒስቴሩ ባለሥልጣናት የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ የአገር እንጂ የላኪዎች ጉዳይ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹መንግሥት ለላኪው የሚሰጠውን የውጭ ምንዛሪ ድርሻ ያሻሽላል ብላችሁ ምርት ማከማቸት አቁሙና ወደ ውጭ ላኩ፤›› የሚል ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡
ላኪዎች በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ወደ ውጭ ለሚላኩ ምርቶች ያስቀመጠው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ከዓለም አቀፍ ገበያው ጋር የሚጣጣም አለመሆኑ ምርታቸውን ለመላክ እንዳላስቻለው መግለጻቸው በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የነጋድራስ ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ አምሐ ገብረ ሚካኤል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ዓለም ላይ ያለው ገበያ ሚኒቴሩ ካወጣው ተመን ያነሰ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አምሐ፣ ነጋዴዎች ከገዥ ጋር ተስማምተው ምርቱን መላኪያ ፈቃድ ለማግኘት ወደ ሚኒስቴሩ ሲሄዱ ዋጋው ከተመኑ ያነሰ ነው የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል፡፡
ከዝቅተኛው የመሸጫ ዋጋ ተመን በተጨማሪም በዓለም ላይ ያለው የገበያ ፍላጎት መቀዛቀዝም ምርቱ ለመከማቸቱ ምክንያት ነው የሚል ሐሳብ መነሳቱን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የስብሰባው ተሳታፊና የጀማል ሰይድ አስመጪና ላኪ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀማል ሰይድ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ መጨረሻ ላኪዎቹ አዲሱ የምርት ዘመን መጥቶ ሌላ ምርት ከመሰብሰቡ በፊት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምርቱን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ መጽናቱን ላኪዎቹ ገልጸዋል፡፡