የንግዱ ማኅበረሰብ እስከ ኅዳር 30 በሲስተሙ ካልተመዘገበ በጨረታ መወዳደር አይችልም ተብሏል
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ለአንድ ዓመት ከዘጠኝ የመንግሥት ተቋማት ጋር ብቻ ሲተገብር የቆየውን የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት፣ ከጥር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ 169 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን በኤሌክትሮኒክ ሲስተሙ ግዢ እንዲፈጽሙ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
በግዥ ሒደቱ ላይ የሚፈጸመውን ብልሹ አሠራር በተወሰነ ደረጃ ያስቀራል የተባለው ሥርዓቱ፣ በአሁኑ ወቅት በ73 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ መጀመሩን የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱ ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ የክልል ዩኒቨርሲቲዎችና የክልል የመንግሥታት ተቋማት ማሟላት ያለባቸውን መሠረተ ልማት ካሟሉ በኋላ ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሥርዓቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉ አቶ ሐጂ አስረድተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የንግድ ሒደት ማለትም ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ጨረታዎችን የሚሳተፉ ከ20 ሺሕ በላይ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ብቻ በሲሰተሙ ተጠቃሚ ለመሆን መመዝገብ አለባቸው ብለዋል፡፡
በአገሪቱ ያለው የንግድ ማኅበረሰብ እስከ ኅዳር 30 ቀን ድረስ በአዲሱ የግዥ ሥርዓት የማይመዘገብ ከሆነ፣ የመንግሥት ጨረታዎችን መወዳደርና ማቅረብ እንደማይችል የገለጹት አቶ ሐጂ፣ አሠራሩ አቅራቢዎች እኩል እንዲወዳደሩና ወጪ ሳይኖርባቸው ባሉበት ሆነው መወዳደርና ማቅረብ እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
አሠራሩ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከመንግሥትና ከግል ባንኮች፣ ከመድን ተቋማት፣ እንዲሁም ከቴሌ ብር አገልግሎት ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ከወረቀት ንክኪ የተላቀቀ ነው ብለዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የመንግሥት በጀት ለግዥ የሚውል ሲሆን፣ ከአገሪቱ ጠቅላላ ምርትም እስከ 14 በመቶ ይይዛል። ሁሉም የመንግሥት ተቋማት የሥርዓቱ ተጠቃሚ የሚሆኑ ከሆነ፣ ከሚፀድቀው የአገሪቱ በጀት አሥር በመቶውን ማዳን እንደሚቻል አቶ ሐጂ ገልጸዋል፡፡
በኤሌክትሮኒክ የሚካሄደው ጨረታና ግዥ ወጪን የሚቀንስ፣ ቅልጥፍናንና ግልጽነትንም የሚያሰፍን መሆኑንና ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንደሚያሳየው የመንግሥትን የኤሌክትሮኒክ ግዥ የተጠቀሙ አገሮች ከአምስት እስከ 25 በመቶ ከበጀታቸው መቆጠብ ችለዋል ብለዋል፡፡
ባለሥልጣኑ የግንባታ ተቋራጮች ማኅበርን ጨምሮ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት ላይ፣ ማክሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በኃይሌ ግራንድ ሆቴል ባደረገው የምክክር መድረክ 500 ያህል የንግድ አቅራቢዎች ተገኝተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱ የሚካሄደው በኦንላይን በመሆኑ የግለሰብ ዳታ ጥበቃ፣ የተደራሽነቱ ስፋትና የኔትወርክ ችግርን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም የጨረታ ሒደት በሚከናወንበት ወቅት የሌሎችን ተጫራቾች ዋጋ በመመልከት አቅራቢው ዝቅ ያለ ዋጋ የሚያቀርብ ከሆነ፣ የሚቀርበው ምርት ጥራት ሊቀንስ እንደሚችል አውስተዋል፡፡
አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ በሚሆኑበት ጊዜ የመሠረተ ልማትና የኔትወርክ ችግር መከሰቱ የማይቀር ነገር ነው የሚሉት፣ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ሶፍትዌሩን ያበለፀገው የፔራጎ ኢንፎርሜሽን ሲስተም ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ እውነቱ አበራ ናቸው፡፡
ነገር ግን በአንፃራዊነት የአገር ውስጥ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ተደራሽነት እየተስፋፋ መምጣቱና የውጭ አገሮች እንደ ሳፋሪኮም ያሉ ኔትወርክ የሚያቀርቡ ተቋማት መኖራቸው፣ አገልግሎት አሰጣጡን ቀላል ያደርጉታል ብለዋል፡፡
ተደራሽነትን በተመለከተ ገንዝብ ሚኒስቴር በሚገኝ ዳታ ሴንተር የሚተገበር ስለሆነ እያንዳንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የራሳቸው ዳታ ሴንተር ሳያስፈልጋቸው በጋራ እንደሚጠቀሙ አቶ እውነቱ ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የደኅንነት ጥበቃን በተመለከተ እንደ ማንኛውም የባንክም ሆነ የኢንሹራንስ አገልግሎት ላይ እምነት የሚኖረው በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ጥበቃ መሆኑን፣ ይህንንም ቴክኖሎጂ ኢንሳ የግለሰቦችንም ሆነ የተቋማትን መረጃ በመቆለፍ የደኅንነት ጥበቃ እንደሚያደርግ አቶ እውነቱ ተናግረዋል፡፡