Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከባንኮች ጋር ለሚደረገው የጥሬ ገንዘብ ርክክብ የክፍያ ተመን ወጣ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች ጋር ለሚያደርገው የብር ኖት ርክክብ ባንኮች የሚከፍሉትን የክፍያ ተመን አወጣ፡፡ በዚህም መሠረት ባንኮች ለብሔራዊ ባንክ አመልክተው ከሚወስዱትና ከሚያስገቡት ገንዘብ፣ እንደ መጠኑ ከሰባት ብር እስከ 50 ብር የሚደርስ መጠን ያለው ክፍያ እንዲከፍሉ ይደረግበታል ተብሏል፡፡

ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ለመውሰድ ሲያመለክቱ ለአንድ ገንዘብ መያዣ ሳጥን 50 ብር መክፈል እንዳለባቸው፣ በዚህ ዓመት በመስከረም ወር መጨረሻ የወጣው አዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመርያ ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም ከአንድ ሳንቲም መያዣ ሳጥን ሰባት ብር መክፈል የሚኖርባቸው ሲሆን፣ ከአንድ ከረጢት ደግሞ 30 ብር መክፈል ይኖርባቸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ባንኮች ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚያስገቡት ገንዘብ በሥርዓቱ ያልተዘጋጀ ከሆነ፣ አሥር የገንዘብ እስር በሚይዝ የመያዣ መጠን ለማስተካከያ 50 ብር መክፈል ይኖርባቸዋል፡፡ የተበላሹ የገንዘብ ኖቶችን ይዘው የሚሄዱ ከሆነ ደግሞ፣ በድጋሚ አሥር የገንዘብ እስር በሚይዝ መያዣ ልክ የመቁጠሪያ 50 ብር እንዲከፍሉ መመርያው ያዛል፡፡

ለገንዘብ ዝውውር የሚከፈለውን ገንዘብ የሚወስነው መመርያ ከዚህ በተጨማሪም፣ በወርቅና በብር ሽያጮች ላይ ብሔራዊ ባንክ የሚያገኘውን የክፍያ መጠን ከዚህ በፊት ወጥተው የነበሩትን ሁለት የመሸጫ መመርያዎች (ማንዋሎች) ላይ ያሉ ሁለት አንቀጾችን በመሻር አካቶ አውጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት መመርያው ብሔራዊ ባንክ ከማናቸውም የከበሩ ድንጋዮችንና ማዕድናትን ለማዘጋጀትና ለመሸጥ ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ካገኙ ግለሰቦችም ሆነ ማኅበራት ክፍያ እንደሚሰበስብ ይደነግጋል፡፡

ባንኩ በማሪያ ቴሬዛና በምኒልክ የብር ሳንቲሞች ላይ ለሚደረጉ ሽያጮች ሁለት በመቶ የአገልግሎት ክፍያ የሚያገኝ ሲሆን፣ በተያያዘም በአገር ውስጥ ከሚደረጉ የወርቅ ሽያጮች ላይም ሁለት በመቶ ክፍያ እንደሚያገኝ በመመርያው ተመልክቷል፡፡

መመርያው ከዚህ በፊት በ2002 ዓ.ም. እና በ2003 ዓ.ም. ወጥተው የነበሩ ሁለት የአገር ውስጥ የወርቅ ሽያጭና የማርያ ቴሬዛ ብር ሳንቲም ሽያጭ ሒደት ማንዋሎች ላይ ያሉ ሁለት አንቀጾችን፣ እንዲሁም በ2004 ዓ.ም. ወጥቶ የነበረ አንድ መመርያ ሁለት ንዑስ አንቀጾችን የሚሰርዝ ነው፡፡

የሚመለከታቸው የብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎችን አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች