በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በማዕከል ተወስኖ የቆየው የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በክልሎች ከተጀመረ በኋላ የተገልጋዮች ቁጥር በአሥር እጥፍ መጨመሩ ተገለጸ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ እንደተናገሩት፣ የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ሲስተሙ በማዕከል ብቻ አገልግሎት ይቀርብበት በነበረበት ወቅት (እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም.) ተመዘግቦ አገልግሎት ያገኝ የነበረው ተገልጋይ 27 ሺሕ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን ከተያዘው የበጀት ዓመት አንስቶ አገልግሎቱ በመላ ኢትዮጵያ ተግባራዊ በመደረጉ እስከ ተያዘው ሳምንት ድረስ 270 ሺሕ የሚደርሱ ደንበኞች በኦንላይን መመዝገባቸውን አስታውቀዋል፡፡
የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ነጋዴዎች ወደ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም ሆነ የክልል ንግድ ቢሮዎች መሄድ ሳያስፈልጋቸው ካሉበት ቦታ በኮምፒዩተርና በእጅ ስልካቸው ኢንተርኔትን በመጠቀም የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶችን የሚያገኙበት ዘመናዊ አሠራር መሆኑ ይታወቃል፡፡
ሚኒስቴሩ አገልግሎቱን ካሁን ቀደም ከነበረው የንግድ ባንክ የክፍያ ሥርዓት በተጨማሪ፣ በቴሌ ብር መተግበሪያ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲሆን ማድረጉ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ተገልጋዮች (ነጋዴዎች) ቶሎ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ከማድረጉ ውጪ ፈጣን አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል ይሆናል ተብሏል፡፡
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀጋው በለጠ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ከዚህ ቀደም በንግድ ጽሕፈት ቤት በግንባር ቀርቦ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት በፌዴራል መንግሥት በኦንላይን መሰጠት የጀመረ ቢሆንም፣ ሲስተሙ ላይ የሚገኙና በክልሎች ላይ የማይሰጡ አገልግሎቶች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
ይህ በማዕከል ብቻ ሲሰጥ የነበረው አገልግሎት በክልሎች እንደሚሰጡት የፈቃድ ዓይነት እንዲሠራበት በመተላለፉ፣ የአገልግሎቱ ተገልጋዮች ቁጥር ማደጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ 2.6 ሚሊዮን የንግድ ማኅበረሰብ እንደሚገኝ ያስታወቀው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ነባርም ሆኑ ክልሎች በቀጣይ እንይዘዋለን የሚሉት አዲስ የንግድ ፈቃድም ሆነ የንግድ ምዝገባ አገልግሎት በኦንላይን ሥርዓት መቅረቡ ከዚህ ቀደም በተገልጋዮች ዘንድ ሲስተዋሉ ለነበሩ እንግልቶችና አላስፈላጊ ወጪዎች ሁነኛ መፍትሔ መሆኑንም ገልጿል፡፡
በተያያዘም ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም ኢትዮ ቴሌኮምና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፣ በስምምነቱ መሠረት በሚኒስቴሩ ለአዲስ ንግድ ምዝገባ፣ ማሻሻያ፣ ምትክና የውል ማቋረጥ አገልግሎት ክፍያዎችን፣ እንዲሁም አዲስ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት፣ ለማሳደስ፣ ምትክ ለመውስድ፣ ውል ለማቋረጥ፣ ለመሰረዝ፣ ለአዲስ የንግድ ስም፣ የንግድ ስም ለማሻሻል፣ ለመቀየርና ለመሰረዝ የሚጠየቁ የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌ ብር የክፍያ አማራጭ እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደገለጹት፣ ስምምነቱ ነጋዴዎች በኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ሥርዓት ለሚያገኟቸው 13 ዓይነት አገልግሎቶች የሚፈጽሙትን ክፍያ በቴሌ ብር በመክፈል አገልግሎቱን ቀላል፣ ፈጣንና ምቹ እንዲሆን ስለሚያደርግ፣ ከዚህ በፊት ይነሳ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሚቀርፍ አስታውቀዋል፡፡
የቴሌ ብር አገልግሎት እስከተያዘው ሳምንት ድረስ 24.9 ሚሊዮን ደንበኞችን ያፈራ ሲሆን፣ ከ101.1 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት በአማራጩ መስተናገዱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ገልጸዋል፡፡