Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትና የውክልና ጦርነት የተወገዘበት የተቃውሞ ሠልፍ

የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትና የውክልና ጦርነት የተወገዘበት የተቃውሞ ሠልፍ

ቀን:

በደቡብ አፍሪካ ሰኞ ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት የሰላም ንግግር ከመጀመሩ በፊት ቅዳሜ ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም በተጠራው አገር አቀፍ የተቃውሞ ሠልፍ፣ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ በሰብዓዊ ዕርዳታ ሰበብ  የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነትና የውክልና ጦርነት በማውገዝ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በበርካታ ከተሞች ተቃውሞአቸውን አሰሙ፡፡

የተቃውሞ ሠልፉ በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በጅማ፣ በአምቦና በተለያዩ ከተሞች ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ሲካሄድ በርካታ ኢትዮጵያውያን ታድመዋል፡፡ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር አባይ፣  ‹‹ፕሮጀክቶችን ደግፉ እንጂ የጦርነት ስፖንሰር አትሁኑብን፤›› በማለት ‹‹አንዳንድ›› ያሏቸውን ምዕራባውያን አገሮች ጣልቃ ገብነት አውግዘዋል፡፡

የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትና የውክልና ጦርነት የተወገዘበት የተቃውሞ ሠልፍ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተርየምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትና የውክልና ጦርነት የተወገዘበት የተቃውሞ ሠልፍ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

- Advertisement -

ምክትል ከንቲባው፣ ‹‹ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፣ ድምፄን አሰማለሁ›› በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹የውክልና ጦርነታችሁን አቁሙልን፣ ስንደፈር ጃስ አትበሉን፣ ስንከላከል አታስቁሙን፣ ስናሸንፍ ደግሞ አስለቃሽ አትሁኑብን…›› በማለት በስም ያልጠቀሷቸውን ምዕራባውያን አገሮች ወቅሰዋል፡፡

በአዲስ አበባው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ ሕወሓት ትጥቁን እንዲፈታ የሚጠይቁ መፈክሮች በብዛት የተስተጋቡ ሲሆን፣ ‹‹ሁለት ሠራዊት በአንድ ሉዓላዊት አገር ውሰጥ አይኖርም፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ ስም ጣልቃ ገብነቱ ይቁም፣ ሕወሓት የችግሩ ምንጭ ነው፣ በድርድር ስም ሰቆቃችንንና የሕወሓትን ዕድሜ ማራዘም ይቁም…›› የሚሉና መሰል መፈክሮችን መስቀል አደባባይ የተገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች ከያዟቸው ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

 አቶ ጃንጥራር በሠልፈኞች የድጋፍ ጩኸት የታጀበውን ንግግራቸውን በመቀጠል፣ ምዕራባውያን አገርች ዕገዛና ድጋፋቸው መሆን ያለበት ‹‹አገር በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ላይ›› እንጂ፣ ‹‹አገር በሚበትን ፀረ ሉዓላዊነት” ተግባር ላይ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

አክለውም፣ ‹‹የሠለጠነ አገርና ሕዝብ አለን እንደምትሉን ሁሉ፣ የሠለጠነ አገርና ሕዝብ እንዲኖረን ፕሮጀክቶችን ደግፉ እንጂ የጦርነት ስፖንሰር አትሁኑብን፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም. ሕወሓት በጀመረው ሦስተኛው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የፌደራል መንግሥት ሽሬ፣ አላማጣና ኮረም ከተሞችን መቆጣጠሩን ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ጥምር ኃይሉ  በተቆጣጠራቸው በእነዚህ አከባቢዎችም የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የሚካሄድባቸው መንገዶችን ክፍት ማድረጉን ከመግለጹም በላይ፣ ለነዋሪዎች ዕርዳታ ማቅረብ መጀመሩ መግለጹ አይዘነጋም፡፡ በሰሜን ጎንደር በኩል ወደ ሽሬ እንዲሁም ከኮምቦልቻ ተነስቶ በደሴ፣ በወልዲያ፣ በቆቦና በአላማጣ የሚያልፈው ዋና መንገድን ለሰብዓዊ እርዳታ ክፍት ማድረጉንም  አስታውቋል፡፡

ይህንኑ የመንግሥት አቋም ዓርብ ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ለሚገኙ ዲፕሎማቶች ያስረዱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ሰኞ ዕለት በደቡብ አፍሪካ እንደሚካሄድ ቀጠሮ በተያዘለት የፌደራል መንግሥትና የሕወሓት የሰላም ንግግር ላይ መንግሥት እንደሚሳተፍ በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ ሁለት ዓመት ሊሞላው ውስን ቀናት የቀሩት ሲሆን በጦርነቱ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በርካቶች ለሞት፣ ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት፣ ለመፈናቀልና ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡ የፌዴራል መንግሥት በዚህ ወቅት በጦርነቱ የበላይነት የያዘ በመሆኑ በደቡብ አፍሪካ ይደረጋል የተባለው የሰላም ንግግር ሒደትና ውጤት የብዙዎችን ትኩረት ስቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...