የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን በሰላም ለመፍታት የሚሠራ በታዋቂ አፍሪካዊያን የተዋቀረ ከፍተኛ ደረጃ የሰላም መማክርት መቋቋሙን የአፍሪካ ኅብረት አስታወቀ።
የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የፀጥታው ምክር ቤት ዓርብ ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. የሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም ሒደትንና የግጭቱን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ውይይት በማካሄደው መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በመግለጫውም የሰላም ሒደቱ ሰኞ ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ እንደሚጀመር ጠቁሟል።
በታዋቂ አፍሪካዊያን የተቋቋመውን ከፍተኛ የሰላም መማክርትና የሰላም ሒደቱን የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ኅብረት የጠቢባን መማክርት አባል ከሆኑት ከቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕምዚሌ ምላምቦ-ንጉካ ጋር በመሆን እንደሚመሩና እንደሚያስተባብሩ አስታወቋል።
በታዋቂ አፍሪካዊያን የተዋቀረው ከፍተኛ የሰላም መማክርት አባላት ማንነትን በይፋ ከመግለጽ የተቆጠበው መግለጫው፣ የሰላም መማክርት አባላቱም ሆነ የሰላም ሒደቱንና እንዲመሩና እንዲያስተባብሩ የተወከሉት ግለሰቦች የተሰየሙት በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት መሆኑንና ሹመቱንም የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የፀጥታው ምክር ቤት በደስታ የተቀበለው መሆኑን አስታውቋል።
ምክር ቤቱ በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን እያደረጉ ያለውን ጥረት በማመስገን፣ ሁሉም አካላት አዲስ ከተቋቋመው የአፍሪካ ኅብረት የከፍተኛ ደረጃ የሰላም መማክርት ጋር የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስቧል።
መግለጫው አክሎም የደቡብ አፍሪካ መንግስት በአፍሪካ ኅብረት የሚመራውን የሰላም ድርድር ለማስተናገድ በመስማማቱ አድናቆቱን በመግለጽ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሰላም ሒደቱን ለመደገፍ አስፈላጊውን የበጀት ድጋፍና ግብዓት እንዲያዘጋጅም ጠይቋል።
ምክር ቤቱ የአፍሪካ ኅብረት አጋሮች ለዚህ የሰላም ጥረት የሚሰጡትን ድጋፍ በማድነቅ፣ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም እንዲሰፍን ከአፍሪካ ኅብረት ጋር የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስቧል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ምክር ቤቱ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮችና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለተጎጂው ሕዝብ በተለይም ለሴቶችና ሕፃናት ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
ምክር ቤቱ በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ ዳግም መቀስቀሱና የሰው ሕይወት መጥፋቱ እንዳሳሰበው ገልጾ አፋጣኝ፣ ሁሉን አቀፍና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲደረግና በትግራይ የተቋረጡ የሰብዓዊ አገልግሎቶች ዳግም እንዲጀመሩ ጠይቋል። በተጨማሪም ሁሉም የታጠቁ የግጭቱ ተዋናዮች ዓለም አቀፍ ሕግጋትንና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩ እንዲሁም ለሲቪሎች በተለይም የሴቶችና ሕፃናት ጥበቃን እንዲያረጋግጡ በማሳሰብ፣ ግጭቱን በፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲቆም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ መክሯል።
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ነፃነትና የግዛት አንድነት ለመጠበቅ ጠንካራ ቁርጠኝነት እንዳለውና ለሁሉም ኢትዮጵያ ሕዝቦች አጋርነቱን ማረጋገጥ እንደሚፈልግ አስታውቋል።
የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካና ሌሎች አገሮች በዚህ የሰላም ሒደት ለመሳተፍና ቁልፍ ሚና ለመያዝ ሲጥሩ የነበሩ ቢሆንም፣ ኅብረቱ ግን ለሰላም ደቱ ድጋፍ የማድረግ ሚና ብቻ እንዲኖራቸው አድርጓል።