Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበደቡብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ የሚሳተፉ አስፈጻሚዎችን በተመለከተ ከሕዝብ አስተያየት ሊሰበሰብ ነው

በደቡብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ የሚሳተፉ አስፈጻሚዎችን በተመለከተ ከሕዝብ አስተያየት ሊሰበሰብ ነው

ቀን:

ለሕዝበ ውሳኔው የምርጫ ክርክር ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሊያካሂድ ባቀደው ሕዝበ ውሳኔ፣ በምርጫ አስፈጻሚነት በሚሳተፉ ግለሰቦች ሥነ ምግባርና ገለልተኝነት ላይ ከሕዝቡ አስተያየት ሊቀበል ነው፡፡

ቦርዱ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የምርጫ አስፈጻሚዎችን አስመልክቶ አስተያየት ሲቀበል የነበረው ከፖለቲካ ፓርቲዎች የነበረ ሲሆን፣ ይህ አሠራሩ ገለልተኝነትን ከማረጋገጥ አንፃር ክፍተት እንዳለበት መገለጹን አስታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቦርዱ በሕዝበ ውሳኔው የሚሳተፉ ምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ገዥው ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአሁኑ ቅሬታቸውን እየገለጹ መሆኑን፣ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ቦርዱ ለሕዝበ ውሳኔው የሚያደርገውን ዝግጅት አስመልክቶ ሐሙስ ጥቅምት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ የሚያስፈልጉ 18,750 የምርጫ አስፈጻሚዎችን በምልመላ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ሕዝበ ውሳኔ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በአስፈጻሚነት ተሳትፈው ከነበሩ አስፈጻሚዎች ውስጥ፣ ዘጠኝ ሺሕ ሰዎች በድጋሚ አስፈጻሚ ለመሆን ፈቃደኝነት ማሳየታቸውን ወ/ሪት ብርቱካን ገልጸዋል፡፡ ተጨማሪ አስፈጻሚዎችን ለማግኘት በኦንላይን ማስታወቂያ እንደሚያወጣና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን ተጨማሪ ምልመላ እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡

በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አፈጻጸም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኝነትን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የተናገሩት ዋና ሰብሳቢዋ፣ ቦርዱ በዚህ መነሻነት ተጫማሪ የማጣሪያ መንገድ ለመተግበር ማሰቡን አስረድተዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. የፀደቀው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ፣ ቦርዱ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላና ምደባ በምርጫ ክልሉ ለሚወዳደሩ የፓርቲና የግል ዕጩዎች ግልጽ እንዲሆን የማድረግና ምልመላውም የፆታ ተዋፅኦን የጠበቀ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

አዋጁ የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች አመዳደብን በተመለከተ መመርያ እንደሚወጣ ከመግለጽ ውጪ፣ በሕዝበ ውሳኔ ወቅት የምርጫ አስፈጻሚዎችን ምልመላና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልቶ ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡ 

ዋና ሰብሳቢዋ ወ/ሪት ብርቱካን፣ ቦርዱ እስካሁን በነበረው አካሄድ በኦንላይን ምርጫ አስመራጮችን ሲመርጥ መቆየቱንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ማስረጃ አቅርበው አስፈጻሚዎች ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ ዕርምጃ ሲወስድ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

‹‹አሁን ግን ማንኛውም ዜጋ ዕጩ አድርገን በቀረብናቸው አስፈጸሚዎች ላይ ችግር አለ ብሎ ካመነ አስተያየት መስጠት የሚችልበትን ሥርዓት ፈጥረናል፤›› ያሉት ዋና ሰብሳቢዋ፣ የአስፈጻሚዎቹ ማንነት ቀርቦ ከሕዝብ አስተያየት እንደሚሰበሰብ ገልጸዋል፡፡ ምርጫ በሚደረግባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች በአስፈጻሚዎች ላይ የሥነ ምግባርና የገለልተኝነት አቤቱታ ካለ በኦንላይን ማቅረብ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ቦርዱ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በክልልነት ለመዋቀር ባሳለፉት ውሳኔ ላይ በሚያካሂደው የሕዝበ ውሳኔ ሒደት ሊተገብረው ያሰበው ሌላው ጉዳይ የምርጫ ክርከር ነው፡፡ 

በ2012 ዓ.ም. በተካሄደው የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ በአማራጮች ሐሳቦች ላይ ክርክር ለማድረግ “ሙከራዎች” የነበሩ ቢሆንም፣ “በተለያዩ ምክንያቶች” መካሄድ እንዳልቻለ የቦርዱ የኮሙዩኒኬሽን ዲፓርትመንት ምክትል ኃላፊ አቶ አንዋር አብራር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ በተካሄደው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ላይም ይህ ክርክር አለመካሄዱን ገልጸዋል፡፡

ቦርዱ ለሦስተኛ ጊዜ በሚያካሂደው ሕዝበ ውሳኔ የምርጫ ክርክሩን ለማድረግ ማቀዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ብርቱካን አስታውቀዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራትና በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች፣ ሕዝበ ውሳኔውን አስመልክቶ የተሻለ የሚሉትን አማራጭ ለመራጩ እንዲያቀርቡ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

ቦርዱ ያዘጋጀው የሕዝበ ውሳኔ አፈጻጸም የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያሳየው የተለያዩ አማራጮችን ለማሳወቅ ለሚደረጉ የመድረክና የቴሌቪዥን ክርክሮችን ለማከናወን የታቀደው፣ ከጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

በአማራጮች ላይ ለሚደረገው ክርከር ትግበራ ከተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በቀናት የዘገየ ሲሆን ምርጫ ቦርድ የክርክሩ አካሄድ፣ ቅደም ተከተል፣ ተሳታፊዎችንና አጠቃላይ ጉዳዮች አስመልክቶ ውሳኔ አሳልፎ ወደ ተግባር እንደሚገባ አቶ አንዋር አስረድተዋል፡፡

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙት ጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶና፣ ደቡብ ኦሞ ዞኖች፣ እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶና የአሌ ልዩ ወረዳዎችን በአንድ ክልልነት ለማደራጀት በሚደረገው ሕዝበ ውሳኔ 3.1 ሚሊዮን መራጮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...