ከሦስት ዓመት በፊት ትግበራው በተጀመረው የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ መሠረት ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገቡ ተማሪዎች በሙሉ ከሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪከ (History of Ethiopia and the Horn) ኮርስ በ2015 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ለተመራቂ ተማሪዎች ሊሰጥ ነው፡፡
በ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሊሰጡ ከታሰቡ 19 የጋራ ኮርሶች ውስጥ እስካሁን ሳይጀመር የቆየው የታሪክ ትምህርት (ኮርስ) የተዘጋጀለት ሞጁል ፀድቆ ለሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መላኩን ትምህርት ሚኒቴር አስታውቋል፡፡ ተቋማቱ ያላቸውን የታሪክ መምህራን ቁጥር ከግንዛቤ በማስገባት የታሪክ ትምህርቱን ከተመራቂ ተማሪዎች በመጀመር እንዲሰጡ ትዕዛዝ መተላለፉን በሚኒስቴሩ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በአዲሱ ትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትንሹ የትምህርት ቆይታ አራት ዓመት ሲሆን፣ ተማሪዎቹ የመጀመሪያውን ዓመት የሚመረቁበትን የትምህርት ዘርፍ ሳይለይ ተመሳሳይ ትምህርቶችን እየወሰዱ ነው፡፡ ብዙዎቹ የጋራ ትምህርቶች በዚህ ዓመት ላይ እንደሚሰጥ ያስታወሱት ኤባ (ዶ/ር)፣ የታሪክ ትምህርት ግን በመዘግየቱ ምክንያት የዚህ ፍኖተ ካርታ የመጀመሪያ ተመራቂ ተማሪዎች በዚህ ዓመት ትምህርቱ ካልተሰጣቸው የታሪክ ትምህርትን ሳይወስዱ ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው የሚወጡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹ተመራቂዎች በዚህ ዓመት ስለሚጨርሱ ኮርሱን ሳይወስዱ እንዳይወጡ በማሰብ ነው፤›› ሲሉ ትምህርቱ ከተመራቂ ተማሪዎች እንዲጀመር የተወሰነበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡ ኮርሱን የሚሰጡ በቂ መምህራን ያሏቸው ዩኒቨረሲቲዎች በዚህ ዓመት ከተመራቂ ተማሪዎች በተጨማሪ በሌላ ዓመት ተማሪዎችም መስጠት እንደሚችሉ አክለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን ውሳኔውን በአካዳሚክ ጉዳዮች ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኤባ (ዶ/ር) የተፈረመ ደብዳቤ ረዕቡ ጥቅምት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመላክ አሳውቋል፡፡ ከደብዳቤው ጋር 184 ገጽ ብዛት ያለው የታሪክ ትምህርት መስጫ ሞጁል አብሮ መላኩን ሪፖርተር ሚኒስቴሩ በላከው ደብዳቤው ላይ ተመልክቷል፡፡
እንደ ኤባ (ዶ/ር) ገለጻ የታሪክ ኮርስ ትግበራ ከሌሎች የጋራ ኮርሶች በሦስት ዓመት የዘገየው በታሪክ ትምህርት ሞጁል ላይ የሚደረገው ግምገማና ውይይት በኮቪድ-19 መከሰት ምክንያት በመጓተቱ ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም. መጋቢት ወር አካባቢ ወርክሾፕ ለማዘጋጀት ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ስብሰባ ማድረግ መከልከሉን አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ሞጁሉን የመገምገምና ሐሳብ የማቅረብ ሥራ ተሰጥቶት ግምገማ ማካሄዱን ገልጸዋል፡፡ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደብዳቤም ማኅበሩ ሞጁሉን በመገምገም ግብዓት መስጠቱን ያስረዳል፡፡
ፈርሶ የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር በድጋሚ የተቋቋመው 60 የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራንና የታሪክ ጸሐፊያን በ2013 ዓ.ም. ታኅሳስ ወር ላይ ለአራት ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ ስብሰባ አካሂደው ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ነው፡፡ ይኼ ስምምነት ‹‹የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች የኩሪፍቱ ስምምነት-2013›› በመባል ይታወቃል፡፡
ማኅበሩ በድጋሚ ሲቋቋም ከወሰዳቸው ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ የተሳሳቱ የታሪክ ትርክቶችን ለማረምና በተጨባጭና በአሳማኝ የታሪክ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ ሳይንሳዊ የታሪክ አጻጻፍ ሥልትን የተከተሉ የታሪክ ኅትመቶችን ለማውጣት ነው፡፡
ሌላኛው ደግሞ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ ትምህርት በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠት እንዲጀምር ማድረግ ነበር፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ ማኅበሩ ከሚኒስቴሩ ባለሥልጣናት ጋር ውይይቶች ማካሄዱንና በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ሦስት ባለሙያዎችን በመመደብ ግምገማ አካሂዶ ስምምነት ላይ መደረሱን የማኅበሩ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ባህሩ ዘውዴ (ኤመረተስ ፕሮፌሰር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በየዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የታሪክ ትምህርት ክፍሎች በሞጁሉ ላይ ግምገማ አድርገው የተስማሙበትን ሐሳብ በቃለ-ጉባዔ በማስፈር እንዳቀረቡም አክለዋል፡፡
ሞጅሉ ከታሪክ ምንነት፣ አጠናን፣ የምንጭ አጠቃቀም አንስቶ የሚዳስስ ሰፊ ሰነድ መሆኑን የጠቀሱት ባህሩ (ኤመረተስ ፕሮፌሰር)፣ እስከ 1983 ዓ.ም. ያለውን የኢትዮጵያ ታሪክን እንደሚሸፍን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ከጎረቤት አገሮች ጋር የተሳሰረ መሆኑን በመጥቀስም ‹‹በተቻለ መጠን›› የአፍሪካ ቀንድ ታሪክንም እንዳካተተ አስረድተዋል፡፡
‹‹በታሪክ ዙሪያ ያለውን ውዥንብር ለአንዴም ለሁሌም ማቆም አለብን›› ያሉት ጊዜያዊ ፕሬዚዳንቱ፣ ኮርሱ ለሁሉም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መሰጠቱ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ይረዳል የሚል ዕምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የታሪክ ኮርስ መሰጠቱ የተማሪዎችን ፍላጎት በመቀስቀስ በተማሪ ቅበላ ማነስ ምክንያት በየዩኒቨርስቲው እየተዘጉ ያሉትን የታሪክ ትምህርት ክፍሎች ለማነቃቃት እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በጻፈው ደብዳቤ ማኅበሩ ለሞጁሉ ትግበራ፣ ሥልጠና በመስጠት ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን በመጥቀስ ዩኒቨርሲቲዎቹ የማኅበሩን ድጋፍ በመጠየቅ ኮርሱን ለሚያስተምሩ መምህራን ሥልጠና ማሰጠት እንዳለባቸው ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ አክሎም፣ ‹‹ኮርሱ አካዳሚያዊና ሙያዊ ሥነ ምግባርን በማክበር እንዲሰጥ ክትትልና ድጋፍ እንዲደረግ፤›› አሳስቧል፡፡