Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያ ከረዥም ዓመታት በኋላ ስንዴን ሊያገበያዩ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴንና በቆሎን በ2000 ዓ.ም. ለአጭር ጊዜ አገበያይቶ ያቆመው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት፣ ስንዴን እንደ አዲስ ወደ ግብይት መስኮቱ ለማስገባት ዝግጅት ጀመረ፡፡

የግብይት ውል በማዘጋጀትም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ሲገኝ፣ የምርት ገበያው ቦርድ ውሉን ሲያፀድቀው፣ ለንግድና ቀጣናዎች ትስስር ሚኒስቴር እንዲያፀድቅ ይቀርብለታል፡፡

ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ አምርታ ከመተካት አልፋ በዚህ ዓመት ለውጭ ገበያ ዝግጁ እንደምታደርግ መነገሩን ተከትሎም፣ ምርት ገበያው ለዚህ እንደተነሳሳ የምርት ገበያው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ነፃነት ተስፋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ነፃነት ገለጻ የድርጅቱ ውሳኔ የመንግሥትን በርካታ የስንዴ ምርት የማምረት ዕርምጃ ተከትሎ እንደሆነና የምርት መብዛቱም ለውጭ ገበያ የማቅረቡና በአገር ውስጥ እሴት ጨምረው የሚሠሩ ፋብሪካዎች ፍላጎት እንደሚመጣ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡

የገዢው ፓርቲ ብልፅግና ከፍተኛ ኃላፊዎች በሶማሌ ክልል ባደረጉት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በክልሉ የተጀመረውን የስንዴ እርሻ በጎበኙበት ወቅት፣ አገሪቱ እያመረተችው ያለው የስንዴ ምርት ከአጠቃላይ የአገሪቱ ፍላጎት አልፎ በዚህ ዓመት በውጭ ገበያ እንደሚቀርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ገልጸው ነበር፡፡

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅትም አገሮቹ ካረደጉት ስምምነቶች አንደኛው በዚህ ዓመት ስንዴን ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ መላክ እንደሆነ ተገልጾ ነበር፡፡

የምርት ገበያም በበኩሉ ከንግድና ቀጣናዎች ትስስር ሚኒስቴር ውሳኔን እንዳገኘ ስንዴን ማገበያየት እንደሚጀምርና በዚህ ዓመትም ለመጀመር እንደሚያስቡ አቶ ነፃነት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ምርት ገበያው ባዘጋጀው ረቂቅ የግብይ ውል ላይ ከግብርና ምርምር ባለሙያዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ በቀጣይም ከላኪዎች፣ አምራቾች፣ ማኅበራትና ከሚመለከታቸው የክልል ኃላፊዎች ጋር ውይይቱ እንደሚቀጥል አቶ ነፃነት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፈው የክረምት እርሻ ወቅት ካመረተችው 60 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ምርት በ40 ሚሊዮን ኩንታል በመጨመር፣ የዚህኛው ክረምት ምርት ሲሰበሰብ ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ብዙም ምርታማ ባልነበረው የበጋ ወቅትም በቀጣይ ከ52 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱም ተገልጿል፡፡ ዓመታዊ የኢትዮጵያ የስንዴ ፍላጎት 107 ሚሊዮን ኩንታል መሆኑ ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች