Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጭስ የመተንፈስ መዘዝ

ጭስ የመተንፈስ መዘዝ

ቀን:

በኢትዮጵያ አልኮል፣ ሲጋራ፣ ጫት፣ ሐሺሽና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በእነዚህም ሱሶች የተጠመዱ አብዛኛዎቹ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ ሲሆኑ ይታያል፡፡ በተለይም ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ አጉልቶታል፡፡

በአንድ ጥናት እንደገለጸው በኢትዮጵያ በትምባሆ ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡት ከ16,800 በላይ ናቸው፡፡

ቶባኮ ፍሪ ፎር ኪድ ኢትዮጵያ በድረ ገጹ ባሠራጨው መረጃ እንደተጠቀሰው በኢትዮጵያ ካሉ ጎልማሶች መካከል ትምባሆን የሚጠቀሙ ቁጥራቸው አምስት ከመቶ ይሆናል፡፡ ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 15 ከሚሆኑት መካከልም 7.9 በመቶ የሚሆኑት የትምባሆ ምርቶችን ይጠቀማሉ፡፡

ለሲጋራ ጢስ የሚጋለጡ ብሎ ባተተው መረጃው በቤት ውስጥ ሥራ ከሚሠሩት አዋቂዎች መካከል 29.3 በመቶ የሚሆኑን፣ በምግብ ቤቶች ከሚሠሩት 31.1 በመቶ፣ በቡና ቤቶች ወይም በምሽት ክለቦች 60.4 በመቶ እና በሕዝብ ማመላለሻ ውስጥ ደግሞ 11.4 በመቶው ይጋለጣሉ ብሏል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት ‹‹አፍሪካ ታብር! ጭስ መተንፈስ ይብቃ›› በሚል መሪ ቃል፣ በዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን ሲታሰብ የተዘጋጀው ሰነድ ላይ የትምባሆን አስከፊነት እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡

የትምባሆ ጭስ አምስት ሰዓት ለሚሆን ጊዜ በአየር ላይ የሚቆይ ሲሆን፣ በውስጡ የያዛቸው ለካንሰር የሚያጋልጡ ቅንጣቶች ለሳንባ ነቀርሳና ለከፍተኛ ሥር የሰደደ የመተንፈሻ አካላት በሽታ የመጋለጥ አደጋ ይጨምራሉ፡፡

በሲጋራ ሱስ የተጠመዱ ሰዎች የአዕምሮ እክል ተጠቂ ከመሆናቸው ባለፈ፣ የመተንፈሻ አካላቸው ላይ ጉዳት ሲደርስባቸው ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በዚህም የተነሳ አብዛኛውን ተጠቃሚዎች ሕይወታቸው በአጭሩ ሲቀጠፍ አሊያም ደግሞ የአልጋ ቁራኛ ሆነው ሲማቅቁ ማየት ተለምዷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ችግር ለመታደግ መንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በጋራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ‹‹ካምፔን ፎር ቶባኮ ፍሪ ኪድስ›› የተሰኘ ድርጅት ይጠቀሳል፡፡

ድርጅቱም ወጣቶች ራሳቸውን ከሲጋራም ሆነ ከተለያዩ አደንዛዥ ዕፆች እንዲያፀዱ እንዲሁም በቂ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ከመቋሚያ የማኅበረሰብ ልማት ድርጅት፣ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋሞች ጋር ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ውይይት አካሂዷል፡፡

የካምፔን ፎር ቶባኮ ፍሪ ኪድስ የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ደረጀ ሽመልስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከአራት ዓመታት በፊት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ከ6.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች አጫሽ ባይሆኑም እንኳን ለትምባሆ ጭስ ተጋላጭ ናቸው፡፡

ለዚህ ችግር ተጋላጭ የሚሆኑ አብዛኞቹ ሰዎች ለሳምባ ካንሰርና ለሌሎች መሰል በሽታዎች ተጠቂ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ደረጀ፣ እነዚህንም ሰዎች ለመታደግ ተቋሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተለይም በሬስቶራንት፣ በሆቴሎችና በመሸታ ቤቶች ላይ የሚሠሩ  ሠራተኞች የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደሆኑ፣ በዚህም የተነሳ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የተለያዩ የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ ትምባሆ ማጨስን የሚከለክል መመርያ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን፣ ነገር ግን በቸልተኝነት ብዛት የተነሳ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሲጋራ ማጨስ እንደ ልማድ መወሰዱን አክለው ገልጸዋል፡፡

ትምባሆ ማጨስን የሚከለክለው ሕግ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከምግብና ከመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በመሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ በተወሰኑ ክፍለ ከተሞች ላይ በመዘዋወር ለሆቴል ባለቤቶችም ሆነ ለሌሎች ተቋማት ሥልጠናና ማስገንዘቢያ መሠራቱን አቶ ደረጀ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የደንብ አስከባሪዎችና የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ማታ ማታ በሕገወጥ መልኩ ሺሻና ሌሎች መሰል ነገሮችን የሚያስጨሱ የሆቴል ባለቤቶችንም ሆነ ተቋሞችን በመፈተሽ የሕግ ማስከበር ሥራ እንደተሠራ አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የትምባሆም ሆነ የተለያዩ አደንዛዥ ዕፆችን የሚጠቀሙ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ተቋሙ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን ወጥ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመናበብ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሲጋራ ማጨስ እንደ ነውር እየታየ መሆኑን፣ በተለይም ደግሞ በባር እና ሆቴሎች ላይ ጠበቅ ያለ ሥራ በመሥራቱ የአጫሾች ቁጥር ሊቀንስ እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በገሀድ ወጥቶ ሺሻና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን የሚጠቀሙ ሰዎች አለመኖሩን ያስታወሱት አቶ ደረጄ፣ ይህንን የትምባሆ ጭስ ላይ ይኼንን አሠራር ተግባራዊ በማድረግ የአጫሾችን ቁጥር መቀነስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ እንኳ በሕገወጥ መንገድ አደንዛዥ ዕፆችን የሚያስጠቅሙ ተቋሞች መኖራቸውን፣ ይሁን እንጂ እንደ አገር ይህንን ችግር ለመፍታት መንግሥትም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ወጣቶች በሱስ ውስጥ ተዘፍቀው የሚገኙት መንግሥት ለወጣቶች የሚሆኑ የመዝናኛ ቦታዎችን ባለማዘጋጀቱ ነው፤›› የሚሉት፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ሰብዕና ልማት ዴስክ ኃላፊ አቶ አብዱላጢፍ መሐመድ ናቸው፡፡ 

አብዛኛዎቹን ወጣቶች ከተለያዩ ሱሶች ፀድተው እንዲያድጉ ለማድረግ መንግሥት የበኩሉን ሚና መጫወት እንዳለበት ኃላፊው አስምረውበታል፡፡

እንደ አቶ አብዱላጢፍ ገለጻ በየትምህርት ቤቶች፣ በየዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎችም ቦታዎች በመሄድና ክበባትን በማቋቋም የሰብዕና እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል፡፡

በአገሪቱ ከሱስ የፀዳ ትውልድን ለመፍጠር ሚኒስቴሩ የሃይማኖት አባቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ የተለያዩ የሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተሳተፉበት ግብረ ኃይል ማቋቋሙን፣ የተቋቋመው ግብረ ኃይልም በተለያዩ ክልሎች ላይ በመሄድ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ችግሩ የሚየታው የመሸታ ቤቶችና ሆቴሎች ላይ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፣ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰዎች አደንዛዥ ዕፆችን በሕገወጥ መልኩ ሲጠቀሙ ይታያል ብለዋል፡፡  

በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን ሕግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተግባራዊ ቢያደርጉት በሱስ የተዘፈቁ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ይቻላል የሚሉት ኃላፊው፣ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ የሕግ አካላት፣ መንግሥትም ሆነ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የፍትሕም ሆኑ የፀጥታ አካላት ሕጉን ያወጣው ተቋምም የወጣውን ሕግ ተፈጻሚ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት፣ ነገር ግን ተፈጻሚ ከማድረግ አኳያ ችግሩ በተጠቀሱት አካላት ላይ ጭምር እንደሚታይ አቶ አብዱላጢፍ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ወጣቶች በተለያዩ አደንዛዥ ዕፆች ውስጥ ተዘፍቀው እንዳይገኙ እንደ ሚኒስቴር በተለያዩ ቦታዎች ላይ የወጣቶች ማዕከሎችን መገንባቱን፣ ነገር ግን የተገነቡትም ማዕከሎች በቂ አለመሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ 11ዱ ክፍለ ከተሞች በቂ የሆኑ የወጣት ማዕከሎች አለመኖራቸውን፣ ለዚህም መንግሥት ትኩረት አለመስጠቱ አንድ ማሳያ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ይህም ከፍተኛ የሆነ ችግር ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ሚኒስቴሩም በአገር አቀፍ ደረጃ ከሁለት ሺሕ በላይ የወጣት ማዕከሎችን ማስገንባቱን፣ እነዚህም የወጣት ማዕከሎች የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሆነ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከሱስ የፀዳና በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ወጣቶች ላይ መሥራት ያስፈልጋል የሚሉት አቶ አብዱላጢፍ፣ ይህንን ማድረግ ከተቻለ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም ሆነ ማኅበራዊ ዕድገት አንድ ዕርምጃ ከፍ እንዲል ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ከተለያዩ ሱስ የፀዳ ትውልድ ለመፍጠር የቅድመ መከላከል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቦታዎችን መገንባት፣ ከቤተሰብ አባላት ጋር ስለጉዳዩ ውይይት ማድረግና ማገገሚያ ማዕከሎችን ማቋቋም፣ የወጣውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ ትልቅ አማራጭ መሆኑን በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢሰመኮ በዩኒቨርሲቲዎች የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ጉዳይ የሚመራበት የጽሑፍ ፖሊሲ አለመኖሩን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች...

ንግድ ባንኮች በከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ

‹‹የገንዘብ እጥረት የሚገጥመው ያለውን ሀብት የማስተዳደር ችግር ስላለ ነው›› የኢትዮጵያ...

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2,700 በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተገለጸ

ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ የንብረት ጉዳት ደርሷል በአበበ ፍቅር ባለፉት ዘጠኝ...