ሰላም! ሰላም! ወገኖቼ እንደምን ከረማችሁ? ‹ዶላር አነፍናፊዎች ኑሯችንን ምድረ በዳ እያስመሰሉብን ምን ሰላም አለ…› ብትሉኝም፣ እነሱንም ቢሆን እስከ ወዲያኛው ለመገላገል ከትግል ውጪ ሌላ መፍትሔ የለም ነው መልሴ፡፡ አንዱ በቀደም ዕለት፣ ‹‹አንበርብር ከአልኮል መጠጦች መደብር እስከ መኪና መሸጫ ሠፈሮች ያየሁትን ጉድ ብነግርህ፣ የኑሮ ውድነቱ አንደኛው ምክንያት ምን እንደሆነ በቀላሉ ይገባሃል፡፡ በዚህ ንግድ ውስጥ የተሰማሩ ሰዎች ሰብዓዊነት የራቃቸው፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው፣ ከራሳቸው ጥቅም ውጪ ሌላ ነገር የማይታያቸው፣ ፈጣሪ መኖሩን ዘንግተው ገንዘብን የሚያመልኩ፣ በአጠቃላይ ለአገርም ሆነ ለወገናቸው ምንም ደንታ የሌላቸው መሆናቸውን በተጨባጭ ከተገነዘብኩ በኋላ፣ መንግሥት ገበያው ውስጥ ያለውን የተቆጣጣሪነት ሚና በሰፊው መጫወት ይኖርበታል ብዬ ደምድሜያለሁ…›› ሲለኝ፣ ድንቄም ነፃ ገበያ ከማለት ውጪ የምለው አልነበረኝም፡፡ ‹‹ነፃ ገበያ ብሎ ምስኪኑን ሕዝብ የአልጠግብ ባዮች መጫወቻ ማድረግ ካልቆመ፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው ነጋዴ ተብዬዎች አገር ከማፍረስ አይመለሱም…›› ያለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ትዝ አለኝ፡፡ እሱ የዘመናት ችግራችንን በተመለከተ መናገር ከጀመረ የቆየ ቢሆንም፣ ሰሚ በመጥፋቱ ግን መፍትሔው መራቁን ዘወትር ይነግረኛል፡፡ መንግሥት ሆይ ልበ ብርሃን ልሂቃኖቻችንን ስማ፡፡ ያዋጣሃልና!
ወገኖቼ ለመሆኑ የኑሮ ውድነቱ እንዴት አርድጓችሁ ሰነበተ ይሆን? ‹‹ዘንድሮ በጥቁር ገበያ ‘ሳይለንሰር’ ማለቃችን ነው…›› ያለኝ አንድ አብሮ አደግ ወዳጄ ነው። ድምፁን አጥፍቶ የሚጠፋውና የሚያጠፋን በዝቷል ለማለት ፈልጎ እኮ ነው። ቅኔውም ሳይቀር እንግሊዝኛ ጣል ይደረግበት መጀመሩን ንገረን ባላላችሁኝ፡፡ ታዲያ እኛ ደግሞ ሰበብ አይጥፋ እንጂ ሰበብ ከተገኘ፣ ነገር ዓለሙን ለመተው የሚቀድመን የለም አይደል? የሚቀድመንን ተውት የሚደርስብን ሲኖር እኮ ነው፡፡ ወደን አይደለም በክፉም በደጉም አንደኛ የምንወጣው ለካ? ቢያንስ በትንሹ ለ48 ሰዓት ‘አይገርምህም? አይገርምሽም?’ ስንባባል ኑሯችን ሲዖል ይሆናል። ድሮስ ከስንፍና የገዘፈ ምን ሲዖል አለ አትሉም? እውነቴን ነው። ከዋጋ ጭማሪው እኮ እየባሰ የመጣው በጭምርማሪ ወሬ የታገዘ ሥራ ፈትነት ነው። ‹‹ወይ አንሠራ ወይ አናሠራ በቃ ጠቅላላችን በመሸ በከንቱነት ልንጠቃለል ምን ቀረን?›› ስትል ማንጠግቦሽን የሚሰሟት ጎረቤት ያሉ እናት፣ ‹‹እኛ ምን እናድርግ ምኑንስ አጠፋን፣ ተኙ ተኙ እያሉን ሳያንቀላፋን…›› ይሏታል። ጉድ እኮ ነው ዘንድሮ እናንተ፡፡ ነጋ ጠባ ስለሥራ ክቡርነት ብዙ ይባላል ሰው ስለእንቅልፍ ያወራል። አልጨበጥ ያለ ነገር!
ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደግሞ ሰሞኑን የድለላው ሠፈር እንደ ውርጭ አዘሉ የአየር ንብረት ሥራችን ጭር ብሎ ቢመለከት ተገርሞ፣ ‹‹መንግሥት በጥርጣሬ የባንክ አካውንቱን ከዘጋው ይልቅ፣ ራሱን በስንፍና የዘጋው ብዛቱ…›› ሲለኝ ሰነበተ። እኔም እንደ ነገርኳችሁ ምሬቱና ሁካታው አልጣጣም ብሎኝ ስለነበር ለባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሰበብ ይገኝ እንጂ ደግሞ ለመቀመጥ…›› ብዬው እጥፍ አልኩ። ‹‹ይታያችሁ ‘ዳገቱ ላይ መቆምም ሆነ መቀመጥ አይፈቀድም’ በተባለበት በዚህ ዘመን ምንም ላይፈይድለት ሰው የወሬ ችግኝ መንከባከቡን አልተወው አለ…›› ስል ቢሰማኝ ደግሞ አንዱ፣ ‹‹ከዘንድሮ ልማት የአዛውንቶች ልማድ አትራፊ ሆኗል አንበርብር። ዝም ብለህ ነው አንተ…›› አይለኝ መሰላችሁ? ኧረ እንዲያው በሞቴ እንዲህ ያለውን ጨዋታ ባወጋው ያለ እናንተ ማን ያምነኛል? ያውም እምነት ተረት በሆነበት ዘመን? ኧረ ተውኝ በኋላ እንዲህ የሚሉኝን ዝም ብዬ ባስተውላቸው አንዱ ያለ አቅሙ ገብር ተብሎ የተማረረ፣ ሌላው የክፍለ ከተማ ጣጣ ያበገነው፣ በአጠቃላይ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ያንገበገበው ተሰብስቦ እንደሚወርድብኝ ተረዳሁ። ሰው ቅሬታ ሰሚው ሳይቀር ቅር እያሰኘው ቢቸገር፣ ሲያገኛችሁ እናንተው ላይ ማራገፉን ሥራ አድርጎታል። ከመሥራት እጅን አጣጥፎ መቀመጥ እንደ አማራጭ እየወሰደም መጥቷል። ‹‹በዚህ ከቀጠለ መጨረሻው ምን ይሆን?›› እያልኩ ወዳጆቼን ባዋያቸው፣ ‘ስንቱን እንተንብይ?’ ነበር መልሳቸው። ‘አንዳንዴ እያሰብኩት የዚያችን ልጅ ነገር፣ ካልመሸ አይታወቅ ካልነጋ አይነገር’ ያለው አዝማሪ ለካስ ወዶ አልነበረም? ማን ወዶ ነበር ታዲያ!
እናላችሁ በዚህ አካሄዳችን እንኳን ሌላ ሌላው ውጥንና የተጀመረው ለውጥ ሊሳካ፣ ያንን ሁሉ ቢሊዮን ችግኝ ተክለን መፅደቁን መጠራጠር መጀመር አለብን። እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ላይ ተስፋ መቁረጥ ተጨመረበት የሚለውን አስባችሁታል? ‘መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንሠለፋለን ብለው፣ ስንዴ አምርተን ከተረጂነት እንላቀቃለን ብለው…’ እያለ አቤት ስንቱ ይሆን የሚሳለቅብን? ‹‹እንዴ ምንድነው እንዲህ ማለቃቀስ? ከአገርህ ሌላ አገር እንደሌለህ እያወቅህ፣ የሰውን አገር የራስ ማስመሰል ምን የሚሉት በሽታ ነው?›› እያሉ አዛውንቱ ባሻዬ፣ አንድ አይቼው የማላውቅ እንግዳ ሰው ሲገስፁ ሰማሁ። ‹‹ለመሸነፍም እኮ ጥሩ ምክንያት ያስፈልጋል…›› ያሉት አባባል ግን ውስጤ ቀረ። ከሐዲዱ ያፈነገጠውን በማስተካከል እኮ ባሻዬን የሚደርስባቸው የለም። ድሮም የአዛውንት ክብሩ መካሪነቱና አስታራቂነቱም አይደል? በዚያው ልክ ወስላቹና ሂያጁ ‘ኧረ ማን ነው የሚታመነው ዘንድሮ?!’ እያሰኘን ግራ አጋባን እንጂ፡፡ ምን ልላችሁ ነው ይህንን ጉዳይ ያመጣሁት መሰላችሁ? ለመቆምም ለመውደቅም ጥሩ ምክንያት ማለፊያ ነው። በሌላ በሌላው ይሁን ግድ የለም። አገር በብሔርተኞች ታመሰ፣ በሐሰተኛ ወሬ መተማመን ጠፋ፣ አሉባልታ የምሁራን መለያ ሆነ፣ ወዘተ. እያሉ መጉበጥ ግን ለማን ተብሎ? ኧረ ለማን!
‹‹ሳይንቀሳቀሱ ረብጣው እንደ ቅጠል የሚረግፍላቸው የባለ ጊዜ ልጆች ብቻ ናቸው…›› ብሎ አንድ የመንደሬ ጎረምሳ የነገረኝ ትዝ ቢለኝ፣ ተወዝፌ መቅረቴ ትውስ አለኝና መሯሯጥ ጀመርኩ። በከባዱ በሺዎች ለሚከራይ ቪላ ቤት የሚመጥነውን ተከራይ ስፈልግ ውዬ ተቀጣጠርኩና ጫማ ላስጠርግ አረፍ አልኩ። አጠገቤ ሁለት ወጣቶች እንደ እኔው ጫማ እያስቦረሹ ሙግት ገጥመዋል። መስማት ጀመርኩ። ‹‹ኮምፒዩተር ኢትዮጵያ ውስጥ ቢፈለሰፍ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ያህል አይደንቀኝም…›› ይላል አንደኛው። ይህን የሚለው ኋላ ላይ እንደተረዳሁት ላሊበላን እኛ አልሠራነውም ለማለት ነው። ‹‹እንዴት እንደዚያ ትላለህ?›› ይለዋል ጓደኛው፣ ምሬት የገባው ይመስላል። እኔም፣ ‹‹ለምን?›› ብዬ ጣልቃ ገባሁ። ‹‹መረጃውና ዕውቀቱ በአግቦ፣ በሽሙጥና በሐሜት ላይ የተመሠረተ አገር እንዴት ብሎ ነው በምክንያታዊ አስተሳሰብ ላይ የተንጠለጠለ ያንን የመሰለ ረቂቅ የሥነ ሕንፃ ‘ቴክኒክ’ ሊያሳይ የሚችለው?›› ሲል መልሶ ጠየቀን። ማናችንም ልንመልስለት አልሞከርንም። የዛሬው እኛነታችን ዝብርቅርቅ ቢሆንበት ነው ያ ወጣት ይህን መሰል ሙግት ማንሳቱ፡፡ ለነገሩ ልክ መስሎ ታይቶኛል። የቀጠሩኝ ደንበኞቼ ደርሰናል ብለው ሲደውሉልኝ ተነስቼ ስሮጥ፣ ኑሮ ቀልባችንን ነጥቆን መጠያየቅ ያለብንን ጥያቄዎች እንደረሳናቸው ታወቀኝ። የትናንቱን የመንፈስ ከፍታ ተረስቶ ዛሬ በቁሳቁስ የበላይነት፣ በስመ ማንነት በደል ትርክትና በከንቱ ነገሮች ላይ ተጥደን ውለን ማደራችንን በትዝብት የሚመለከት ግራ እንደሚጋባ በስሱ ገባኝ። በስሜት መነዳቱ እስከ መቼ እንደሚያዛልቀን እንጃ!
ታዲያ እውነት የማትጥመን እዚህ እዚህ ላይ ነው። ከኅብረተሰባዊነት ግለኝነት፣ ከጋራ ጥቅም የግል ፍላጎት ስለተቆጣጠሩን ችግሮቻችን አልተቀየሩም። ‹‹ፎርማታቸው›› ቢቀየር አሁንም የለቅሷችን ዜማዎች አልተቀየሩም። ለቅሶ ብል ይልቅ በቀደም ለታ ባሻዬ ከአልጋቸው ሳይወርዱ መርዶ ሰምተው፣ ‹‹ታሞ እያለ ምናለበት ሄጄ ብጠይቀው ኖሮ…›› በማለት በራሳቸው በጣም አዘኑ። ታዲያ ልጃቸው ልብ ብሏቸው ኖሮ፣ ‹‹አሁን ይህን ያህል ራስህን መውቀሱ ፋይዳ የለውም። ባሻዬ አውቀው ያጠፋሉ የሚል ማን አለ? ደግሞም ራስን እየወቀሱ ሆድን በቂም ከመወጠር ይቅርታ የማድረግን ባህል ብናዳብር ኖሮ፣ እርስ በርስ እየተፋጀን የማንም መሳቂያ ባልሆንን ነበር…›› አይላቸው መሰላችሁ? ደፋር እኮ ነው፡፡ ባሻዬ ምሁሩ ልጃቸው ያላቸውን ሲነግሩኝ፣ ‹‹ይቅርታ ማለት ውርደት አከናናቢነቱ ጎልቶ ይሆን እንዴ ሰላም ማውረድ ከሰው በላይ ከባድ የሆነው?›› ስል ራሴን ጠየቅኩ። ወይስ ውስጡ ለቄስ ነው? ለእናንተው ብተው ይሻላል መሰለኝ፡፡ በጥቂት ጥጋበኞች ምክንያት የገባንበት ጦርነት የት እንዳደረሰን ከእናንተ በላይ ማን ምስክር ይጠራል፡፡ ይቅር መባባልን በጥላቻና በቂም ለውሰውት አገርን እሳት ውስጥ የከተቱት ነውረኞች መጨረሻቸው የቀረበ ቢመስልም፣ ጦሳቸው ግን እንዲህ በቀላሉ የሚላቀቀን አይመስልም፡፡ ምድረ ጦሰኛ!
የነገርኳችሁ ቪላ ቤት ደለብ ባለ ረብጣ ሲከራይልኝ ‘ኮሚሽኔን’ ተቀብዬ ወደ ሌላው የድለላ ሥራዬ ሮጥኩ። ታክሲ ተሳፍሬ በጉዞ ላይ ሳለሁ ታዲያ የሰማኋትን ቀልድ ጣል ላድርግላችሁ። ሁለት እጅግ የሚበሻሸቁ ጓደኛሞች ናቸው። አንደኛው አባቱ በቅርብ በሞት የተለዩ ሲሆን፣ አብሮ አደግ ጓደኛው ደግሞ በጠና ታሞበታል። ሊጠይቀው ቤቱ ሲሄድ ሳቅ የራቀውን ታማሚ ወዳጁን ፈገግ ሊያሰኝ ያዘጋጀውን ደብዳቤ እየሰጠው፣ ‹‹በል እንግዲህ ለአባቴ የምታደርሰው ነው…›› ቢለው፣ ‹‹ወዳጄ፣ እኔ እኮ ወደ ገሃነም አይደለሁም…›› አለው በማለት አንዱ የሴት ጓደኛውን ሲያስቅ እኔንም ፈገግ አሰኘኝ። በውጥረት ቀኑን አሳልፌ ስለነበር ከልቤ ሳቅኩ። ከሳቄ ጀርባ አንድ ተሳፋሪ፣ ‹‹አይ የሰው ልጅ፣ ገሃነም መውረድ ፈርቶ፣ ከሥልጣን በሰላም መውረድ ፈርቶ፣ ስንቱን ፈርቶ ይሆንለታል?›› ሲል ይሰማ ነበር። ለአምባገነኖች ከሥልጣናቸው መውረድ በቁም ከመሞት በላይ ሲዖል እንደ መውረድ እንደሚቆጥሩት ታሪክ አላነበበም መሰል? ከንባብ የተጣላ ትውልድ፡፡ ለነገሩ ሲዖል ድረስ እንወርዳለን ያሉት ሰዎች የት ደረሱ ይሆን? እንጃ ነው እንዴ መልሱ!
በሉ እንሰነባበት። የቀረኝን ሥራ አጠናቅቄ ወደ ቤቴ ስመለስ አመል ነውና ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ብቅ አልኩ። በጂን፣ በቢራና በድራፍት ቸበርቻቻ ያለው የግሮሰሪዋ ታዳሚ ወሬው ሁሉ ስለነፃነት፣ ስለሰሞኑ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውሎ ነበር። የባሻዬ ልጅም በወሬው ዋና ተሳታፊ ስለነበር በቅጡ ሰላም አላለኝም። እየቆየሁ የሚያወሩትን ሳዳምጥ ውይይት ሳይሆን ክርክር ይዘው ነበር። ምን መሰላችሁ? የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ የመንግሥት ተቋማትንና ትልልቅ መሠረተ ልማቶችን በመቆጣጠር ኃላፊነቱን እንደሚወጣ የሰጠው መግለጫ ዋናው መነሻ ነው፡፡ አንድ ልሂቅ መሳይ ጎልማሳ፣ ‹‹እኔ የማይገባኝ እኮ መንግሥት ምን ማድረግ እንዳለበት ለማንም የማስረዳት ኃላፊነት እንደሌለበት አለመታወቁ ነው…›› ሲል ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዳይፈጥር መግለጫ ማውጣት አስፈላጊ ነው…›› ብሎ መለሰ፡፡ ‹‹እኔ የሚያበሳጨኝ ይህ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ብላችሁ የዳቦ ስም የሰጣችሁት የኢምፔሪያሊስት ኃይል የሚባለው ነው፡፡ ወያኔዎች ድል ቀንቷቸው አማራና አፋር ክልል ውስጥ ሕዝብ እየጨፈጨፉ አገር ሲያወድሙ ምንም አይናገርም፡፡ ወያኔ እንደ እባብ እየተቀጠቀጠ ምሱን ሲያገኝ ግን ከያለበት ወጥቶ ይንጫጫል፡፡ ይህ የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው፡፡ ማንም አገር በውስጥ ጉዳዩ በሰብዓዊነት ስም ማንም ጣልቃ ሊገባበት አይችልም፡፡ እኛ ቅኝ ያልተገዛን ኩሩ ሕዝቦች ስለሆንን በማንም ጫና መንበርከክ የለብንም፡፡ ወያኔ በዘረፈው የአገር ሀብት አብረው ይነግዱ የነበሩ ምዕራባውያን ሌቦች በውስጥ ጉዳያችን ሲገቡ፣ እዚያው በጠበላችሁ ብለን ተባብረን መመከት አለብን…›› እያለ ጎልማሳው በንዴት ሲናገር በአድናቆት ነበር ያዳመጥነው፡፡ አንዳንዱ ችግራችንን እንዲህ ኩልል አድርጎ ሲያስረዳ፣ ሌላው ከማዳመጥ በዘለለ አንዳች ነገር ለማበርከት አለመሞከሩ ያናድዳል፡፡ ከዚያ በተጫማሪ አገሩን እየዘረፈ ከመክበር ውጪ ዓላማ የሌለው አልጠግብ ባይ የነጋዴ ሠራዊት ደግሞ ያበሳጫል፡፡ ችግርን ታቅፎ እሹሩሩ ከማለት አፈንድቶ አገርን ነፃ ማድረግ የግድ መሆን አለበት፡፡ መልካም ሰንበት!