Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ፕሮጀክት እንዴት እየሄደ ነው?

የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ፕሮጀክት እንዴት እየሄደ ነው?

ቀን:

የአደጋ ሥጋት የተጋረጠባቸውን የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠበቅ፣ ለማደስና ለማልማት የተዘጋጀውን ፕሮጀክት ለማገዝ ፈረንሣይ የአምስት ሚሊዮን ዩሮ (260 ሚሊዮን ብር) ድጋፍ ልታደርግ ነው፡፡ ድጋፉንም ዕውን ለማድረግ እንዲረዳ የኢትዮጵያና የፈረንሣይና መንግሥታት በተወካዮቻቸው አማካይነት ስምምነት አድርገዋል፡፡

 የአምስት ሚሊዮን ዩሮ የዕርዳታ ስምምነትን በገንዘብ ሚኒስቴር ጥቅምት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. የተፈራረሙት በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋስውና በኢትዮጵያ የፈረንሣይ አምባሳደር ሪሚ ማሪሹ ናቸው፡፡

ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው፣ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረው የሁለቱ ወዳጅ አገሮች መልካም ግንኙነትና ትብብር አሁን ላይ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡትን የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የደረሰባቸውን ጉዳት ለመጠገን ባሳዩት ትብብር ቀጥሏል፡፡

ትብብሩ የቅዱስ ላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በቀጣይ እንዳይበላሹ አስፈላጊውን መከላከል ለማድረግና ለመጠበቅ ያደርጋል ተብሏል፡፡ እንዲሁም ቅርሶች ከከተማው ጋር ተስማሚ መስተጋብር እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣንን አቅም ለመገንባት የሚያስችል ነው፡፡

ባህልና ቅርስን በተመለከተ በትብብር መሥራት ቀዳሚ ጉዳይ ነው ያሉት የፈረንሣይ አምባሳደር፣ ድጋፉ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ለመንከባከብና ለቅርሱ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ያለመ ነው ብለዋል፡፡

አደጋ የተጋረጠባቸውን የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ለመጠገን እንዲያስችል በኢትዮ ፈረንሣይ የቅርስ አድን ፕሮጀክት የተካሄደውን ጥናት መንግሥት በግንቦት 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የፈረንሣይ አምባሳደር በኩል መረከቡ ይታወሳል፡፡

ከጥናት ሰነዱ በተጨማሪ ተብሎ የሚታወቅና አካባቢውንና ተቋሙን በአቅም ግንባታ፣ በማኅበረሰብ ድጋፍ፣ በአርኪዮሎጂ፣ በቅርስና በቱሪዝም ለማጠናከር፣ እንዲሁም የሪሶርስ ማዕከል ለማደራጀት ‹‹ዘላቂነት ለላሊበላ›› ፕሮጀክት ይፋ መደረጉም አይዘነጋም፡፡ አደጋ ለተደቀነባቸው አብያተ ክርስቲያናት የኪነ ሕንፃ መፍትሔ ተቀያሪ የመጠለያ ንድፎች እንደሚዘጋጁም እንዲሁ፡፡የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ፕሮጀክት እንዴት እየሄደ ነው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የዲጂታል ዓውደ ርዕይ በእንጦጦ 

በአገር ውስጥና በውጭ በሦስት አውታር (ስሪዲ) ቴክኖሎጂ የዲጂታል ዓውደ ርዕይ በ2014 ዓ.ም. ለማሳየት ታስቦ የነበረው በወቅቱ ባይፈጸምም፣ ዘንድሮ ግን ዕውን ሆኖ በእንጦጦ ፓርክ በሚገኘው የሥነ ጥበብ ጋለሪ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እየታየ ይገኛል፡፡

በእንጦጦ መታየት የጀመረው የቨርቹዋል ሪያሊቲ ቱር ቴክኖሎጂ የመጪው ጊዜ የቱሪዝም ዕድገት ዋነኛ ማስተዋወቂያና የጎብኝዎች ቀልብ መግዣ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡

አስደናቂዎቹን የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ከኪነ ሕንፃ ዲዛይናቸው (አርክቴክቸራል ዲዛይኖች) ጭምር ባለሦስት አውታር መነፅር ከመጎብኘት ባለፈም፣ የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይም የትርዒቱ አካል ነው፡፡

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ምን አጋጠማቸው?

በ12ኛው ምዕት ዓመት የታነፁትና ‹‹አዲሲቱ ኢየሩሳሌም›› የሚል ስያሜ ያገኙት የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ኪነ ሕንፃ በየክፍለ ዘመኑ የምዕመናንና የብዙዎች ጎብኚዎች ቀልብ መያዝ ችለዋል፡፡ ዩኔስኮም በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ አሠርታት ወዲህ በዘመን ብዛት በደረሰባቸው ተፈጥሯዊ ጫና ምክንያት፣ የተወሰኑት ላይ ከተደቀነባቸው አደጋ ለመታደግ ከተወሰደው ዕርምጃ አንዱ ከባድ የብረት ምሰሶ ከለላ እንዲሆናቸው ጥላ መሠራቱ ነው፡፡ በአሳሳቢ ሁኔታ ፈተና ውስጥ ከወደቁት መካከል ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ አማኑኤልና ቤተ መስቀል ይጠቀሳሉ፡፡

በየቤተ መቅደሶቹ የቆሙት የብረት እግሮች በአካባቢው በየወቅቱ እየተለዋወጠ የሚነፍሰው የነፋስ መጠን በእጥፍ እየጨመረ በመምጣቱ ብረቱን አነቃንቆ እንዳይጥለውና ጉዳት እንዳይደርስ በየጊዜው ሥጋቱን ሲገልጽ የቆየው ኅብረተሰቡ ‹‹ይነሱ›› የሚል ድምፅንም ሲያስተጋባ ቆይቷል፡፡

 ለመፍትሔውም በተለይ ከዓመታት በፊት ጀምሮ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም ተጠሪው ተቋም የቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን ለችግሩ ዓለም አቀፍ መፍትሔ ሲያፈላልጉ ቆይተዋል፡፡

በ1950ዎቹ በኢትዮጵያ የአርኪዮሎጂ ጥናት ተቋም እንዲቋቋም ቀዳሚ አጋር የነበረችው

ፈረንሣይ የቅዱስ ላሊበላ መካነ ቅርስን ለመታደግ የባህል ሚኒስትሯን ብቻ በመላክ አልተወሰነችም፡፡ የአገር ውስጥና የፈረንሣይ ባለሙያዎችን ያካተተ የቴክኒክ ተቋቁሞ ሥራውን ሲሠራ ቢቆይም ጥገናውን ለማካሄድ በባለሙያዎች ሲሠራ የነበረው ጥናት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ ቆይቷል፡፡

ወደ ጥገናው ከመገባቱ በመካነ ቅርሱ ላይ ቀደም ሲል የተሠሩ ሥራዎች ለምን ውጤታማ ሳይሆኑ እንደቀሩ የሚፈትሽ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱም ታውቋል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ ገጽታ

ከስምንት ምዕት ዓመት በፊት ስለታነፁት የላስታ ላሊበላ ውቅር አብያተ  ክርስቲያን የገድለ ላሊበላ ጸሐፊ በአድናቆት የከተበውን እዚህ ላይ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ እንዲህም አለ፣

‹‹ወዳጆቼ ሆይ! ተመልከቱ እንጂ! ይህ ሰው በእጆቹ የተገለጹለት እነዚህ ግንቦች በየትም በሌሎች አገሮች አልተሠሩም፡፡

ስለነዚህ አብያተ ክርስቲያን አሠራር በምን ቃል ልንነግራችሁ እንችላለን? የቅጽራቸውንም ሥራ እንኳ መናገር አንችልም፡፡ የውስጡንስ ተዉት ታይቶ አይጠገብም፣ አድንቆና አወድሶም ለመጨረስ አይቻልም፡፡ በላሊበላ እጅ የተሠራ ይህ ድንቅ ሥራ በሥጋዊ ሰው የሚቻል አይደለም፡፡ የሰማይን ከዋክብት መቁጠርን የቻለ፣ በላሊበላ እጅ የተሠራውን መናገር ይችላል፡፡ እናም ለማየት የሚፈልግ ካለ ይመልከት፡፡ በላሊበላ እጅ የተሠሩትን የአብያተ ክርስቲያኑን ሕንፃዎች ይምጣና በዓይኖቹ ይመልከት፡፡››

በታሪክ እንደሚያወሳው የላሊበላ ከተማዋ የመጀመርያ መጠሪያ ሮሃ ሲሆን፣ በ1170ዎቹ አጋማሽ የነገሠው ንጉሥ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያኑን በማነፁ ከተማዋ በስሙ ተጠርታለች፡፡

አብያተ መቅደሶቹ በሦስት የተለያዩ ሥፍራዎች ሲገኙ፣ ስድስቱ በሰሜን አቅጣጫ፣ አራቱ በሊባ (ደቡባዊ ምሥራቅ) አቅጣጫ ሆነው የሚገናኙበት መስመር አላቸው፡፡

በኖኅ መርከብ አምሳል የተሠራው 11ኛው ቤተ ጊዮርጊስ ግን ተነጥሎ ነው ያለው፡፡ በሰሜናዊ ክበብ የሚገኙት ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ መስቀል፣ ቤተ ደናግል፣ ቤተ ሚካኤል ቤተ ጎልጎታ ሲሆኑ፣ በሊባ በኩል ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ አባ ሊባኖስ፣ ቤተ መርቆርዮስ፣ ቤተ ገብርኤልና ቤተ ሩፋኤል ይገኛሉ፡፡ በምዕራብ አቅጣጫ ከላይ ወደታች ተፈልፍሎ የታነፀው 11ኛው ቤተ ጊዮርጊስ ይገኛል፡፡

 የእነዚህን አብያተ ክርስቲያናት ሥራ አስደናቂነት ለመግለጽ ቃል እንዳነሰው የገለጸው የገድለ ላሊበላ ደራሲ እነዚህ ላሊበላ በአንድ ቋጥኝ ያሠራቸው፣ ሰሎሞን በጢሮስ ንጉሥ በኪራም እየተረዳ በኢየሩሳሌም ካሠራው ቤተ መቅደስ እንደሚበልጥም አመስጥሯል፡፡ የላሊበላም ጥበብ ከሰሎሞን መብለጡን ጭምርም በመግለጽ፣ ሰው ሁሉ እየመጣ በዓይኑ እያየ ሊያደንቃቸው የሚገባ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...