የጤና ሚኒስቴር 24ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ ጥር 10 እና 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በሃዋሳ ከተማ አካሂዷል፡፡
‹‹ፍትሐዊነትና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለሁሉም›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ጉባዔ፣ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ መሥርያ ቤታቸው ጥራትና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ለማዳረስ፣ የጤና መረጃ አብዮት፣ የጤናው ዘርፍ አመራር ብቃትን ማጎልበት፣ የተነቃቃ፣ ብቁና ሩህሩህ የጤና ባለሙያ ለመፍጠር በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
የየክልሉ የጤና ቢሮ እና የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮችና በጤናው ዘርፍ የሚሠሩ አጋር አካላት በተገኙበት መድረክ በጤናው ዘርፍ የላቀ የሙያ አፈጻጸም፣ የረዥም ጊዜ የላቀ አገልግሎት ያላቸው፣ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የዕውቅና ሽልማት ተበርክቷል።
ከእነዚህም መካከል አራት ባለሙያዎች የሕይወት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት ተሸላሚ ሲሆኑ ሌሎች ሦስት ባለሙያዎች ደግሞ በዕውቅና ዘርፍ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡
ከሕይወት ዘመን ተሸላሚዎቹ መካከል የአለርት ሆስፒታል የሕክምና ክፍል ኃላፊ ሰለሞን ቡሣ (ዶ/ር)፣ በተለያዩ የመንግሥት ጤና ተቋማት ከ43 ዓመት ላይ ያገለገሉ አቶ ባይሳ ገመዳ፣ የአርማወር ሀንሰን ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ውዴ ምሕረት (ዶ/ር)፣ የኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት አቶ ዳዊት መንግሥቱ ይገኙበታል፡፡
እነማን ናቸው?
የሕይወት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት ቀዳሚ ተሸላሚ የሆኑት ሰለሞን ቡሣ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በዓይን ሕክምና በስፔሻሊስት ደረጃ ሠልጥነው ማኅበረሰቡን ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት ሰለሞን (ዶ/ር) ከ1958 ዓ.ም. አንስቶ ለ46 ዓመታት በተለያዩ ተቋማት አገልግለዋል፡፡ በተለይ በ1970 ዓ.ም.፣ በባሌ ክፍለ ሀገር ገናሌ አውራጃ የጤና አገልግሎት ኃላፊ በነበሩበት ወቅት አርሶ አደሮች በዘመናዊ የሰፈራ አኗኗር እንዲደራጁና ከ2000 በላይ ቤቶች እንዲገነቡና እያንዳንዳቸው የየራሳቸው መፀዳጃ ቤት እንዲኖራቸው በማድረግ ከተላላፊ በሽታዎች የሚጠበቁበትን ስልት ቀይሰዋል፡፡
ወ/ሮ ሣሮ አብደላ የሕይወት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት ተሸላሚ ከሆኑት አንዷ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመሪ ተመራማሪነትና በኤችአይቪና በቲቢ ምርምር ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ ሲሆን ባለፉት አሥር ዓመታት ባከናወኗቸው ችግር ፈቺ ምርምሮችና ባመነጯቸው አዳዲስ የጥናት የምርምር ሥራዎችና ኘሮጀክቶች ይታወቃሉ፡፡
ሌላኛው የሕይወት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት ተሸላሚ አቶ ባይሳ ገመዳ ናቸው፡፡ ከጤና ረዳትነት እስከ ጤና መኰንንነት በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ጭምር ከ43 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡
በጤና ሙያ መስክ የላቀ ልዩ ሥራና አገልግሎት ተሸላሚ የሆኑት ፀሐይነሽ ለማ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በጋምቦ (ሌፒስ) ካቶሊክ ሚሲዮን ሆስፒታል ቆይታቸው በተለይ ከሥጋ ደዌ ሕሙማን ጋር በነበራቸው ቀረቤታ ወደ አዲስ አበባ አለርት ሆስፒታል ከተዛወሩ በኋላ በአርማወር ሃንሰን የጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ድጋፍ ለሥጋ ደዌ ሕክምና በሚያገለግሉ መድኃኒቶች ላይ ውጤታማ ምርምር ማድረግ ችለዋል፡፡ በአህሪ የባክቴሪዮሎጂ ላብራቶሪ በማጅራት ገትር ተህዋስያን በሚከናወነው ጥናት በሰባት ሀገሮች የኢትዮጵያ ላብራቶሪ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ የሦስተኛ ዲግሪ ጥናታቸው የሥጋ ደዌ በሽታ በታማሚዎችና በቤተሰቦቻቸው ላይ ጉዳት ሳያደርስ መከላከል የሚቻልበትን መንገድ ያመላከተ በመሆኑ ጥናቱ ታትሞ ለዓለም ተሰራጭቷል፡፡
ከእዚህም ሌላ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የላቀ አገልግሎት ያበረከቱ አራት ባለሙያዎች ዕውቅና፣ ‹‹ሒውማን ብሪጅ›› የተባለና መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ ሠናይ ድርጅት ደግሞ ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በጤና አገልግሎት የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱና ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ 12 የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችም ዕውቅና ተችሯቸዋል፡፡