በተሾመ ብርሃኑ ከማል
ውድ ልጆቼና ወዳጆቼ ስለመርከብ መካከለኛ መጠን ያለው መጽሐፍ የዛሬ 20 ዓመት አዘጋጅቼ ነበር፡፡ ሆኖም ማሳተም አልቻልኩም፡፡ ለማንኛውም መኖር ብቻ ሳይሆን አለመኖርም አለና በትንሹም ቢሆን ጨልፌ ላውጋችሁ፡፡ ከወዲሁ ግን ይህ ጽሑፍ በአጭሩም ቢሆን በእንግሊዝኛ አዘጋጅቴ የሰጠሁት ድረ ገጽ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተመራማሪዎች እንዳነበቡት በየቀኑ የሚገልጽልኝ መሆኑን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡ ለማንኛውም ወደ ጽሑፉ እንግባ፡፡
- አጠቃላይ
መርከቦች ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ እንደ ሰማይ በጠለቁ፣ ከከርሰ ምድር በላይ በሰፉ ውቅያኖሶችና በባህሮች ተለያይተው የነበሩ የዓለም ሕዝቦችን ያገናኙ፣ ባህልን ከባህል፣ ማኅበራዊ ኑሮን ከማኅበራዊ ኑሮ፣ ፍልስፍናን ከፍልስፍና ያገናኙና ያዋሀዱ፣ የሰው ልጅ አካባቢውን ለመቆጣጠር ወይም የሚገጥመውን ፈተና ድል ለማድረግ ታጥቆ የሚሠራ መሆኑን የሚያስገነዝቡ የዘመኑ ቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ውጤቶች ናቸው፡፡
መርከቦች መጠናቸው ባደገ፣ ፍጥነታቸው በጨመረ፣ አገልግሎታቸው በሰፋ ቁጥር የሰውን ልጅ ጥበብ የበለጠ እንድናደንቀው፣ የበለጠ እንድናከብረው፣ የበለጠ እንድንጠይቀው ያደርጉናል፡፡ ለመሆኑ የመርከብ ውስጡ ምን ይመስላል? በሥዕል ላይ እንደምንመለከተው ይሆን? በእርግጥ በዚህ አጭር ጽሑፍ ስለእሱ መግለጽ ያስችግራል፡፡ ነገር ግን ወደ ባህር መሄድ ሳያስፈልን የደንበልን ወይም ሌላ አምስትና ስድስት ፎቅ የሚያህል ሕንፃ እናስብ፡፡ በዚያ ሕንፃ ውስጥ እጅግ የተዋበ፣ ወለሉ በፐርሺያ ምንጣፍ ከዳር ዳር የተሞላ፣ ዙፋን አከል ወንበሮች ሲቀመጡባቸው በምቾት ይዘው ወደታች የሚወርዱ ሶፋዎች፣ እጅግ ውብና ድንቅ ሥዕሎች፣ ዓይንን የሚማርኩ አበቦች፣ ምናልባት በቀላሉ መግለጽ ይቻል እንደሆን የአንድ ‹ንጉሥ እልፍኝ› የመሳሰሉ ሳሎኖች፣ ከዝሆን ቀንድ የተሠሩ የሚመስሉ ውብ ምሰሶዎች፣ የመዋኛና የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ የመረብና የመሳሰሉት ኳሶች መጫወቻ ሥፍራ ያሉት እንደሆነ እንገምት፡፡ ወይም የእኛን ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በዓይነ ህሊናችን እንቃኝ፡፡ በዚህ የደንበልን ሕንፃ በሚያህል፣ እንደ ቤተ መንግሥት ባማረ መርከብ በባህር ላይ አንድ ወይም ከአንድ የበለጡ ኦርኬስትራዎች ሲጨፍሩና ሲያስጨፍሩ ለአፍታ እናስብ፡፡ ብዙ የባህር ተጓዦች በጥልቅ ውቅያኖስ የሚሄዱ መሆናቸውን ረስተው በመሬት ላይ ያሉ ቢመስላቸው ያስደንቅ ይሆን? በእርግጥም በዚህ ላይ ሆኖ የባህሩን ውኃ እየቀዘፉና እያሸተቱ መጓዝ ምንኛ ግሩምና ድንቅ ነው?
ከባህር ባሻገር የሚኖሩ ሰዎች መርከብን እንደ መኪና እያዩ ለማድነቅ ባይታደሉም ከ10 እስከ 10 ሺሕ ሰው ወይም 70 እና 80 ሺሕ ቶን ዕቃ ተሸክመው፣ የየአገራቸው አምባሳደሮች መሆናቸውን ለማመልከት ሰንደቅ ዓላማውን ከፍ አድርገው ባህሩን እየሰነጠቁ በኩራት ሲሄዱ፣ የሕዝብ ዓርማና የአገር ምልክት መሆናቸውን እየመሰከሩ ይጓዛሉ፡፡ ግሩም የሰው ልጅ ፍጡር መሆኑን ሲያስቡት ግን ማድነቃቸው አይቀርም፡፡
ይህን ግሩም ድንቅ የሰው ልጅ ጥበብ ወደ ራሳችን ሕይወት መንዝረን እንመለከተው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት የተሠሩትና የአክሱምን መንግሥት የሚያወሱት፣ በግሪክና በሳብኛ የተጻፉት የቋጥኝ ቅርሶች፣ የሐረር ግንብና አድባራት/መቃብሮች፣ የሶፍ ኦማር መስጊዶች፣ የፋሲል ሕንፃና ድልድዮች፣ የላሊበላ ፍልፍል ቤተ መቅደስ፣ በተለይም በኖኅ መርከብ ቅርፅ የተሠራው ቤተ መቅደስ፣ እንዲሁም ሌሎች ከኢትዮጵያና ከውጭ ግንኙነቷ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ከመርከብ በተለይም ከንግድ መርከቦች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን መለስ ብለን ስናጤነው፣ ይህ የባህር መጓጓዣ የየዘመኑን ቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ እየገዘፈ መሄድን ብቻ ሳይሆን፣ የሰውን የአዕምሮ ምጥቀት እያጎላው መጣ፡፡ ሕይወታችንን በከፍተኛ ደረጃ የሚለውጥ መሣሪያ መሆኑንም አስገንዛቢ መሣሪያ ሆነ፡፡
በሌላ አገላለጽ፣ ምናልባት ልብ አንለው ይሆናል እንጂ፣ በዘመናችን ሱቆችንና ሌሎች መደብሮችን ያጥለቀለቁት ሸቀጣ ሸቀጦች ከ90 በመቶ በላይ በንግድ ከመርከብ ጋር የመጣ ነውና አሻራው በእያንዳንዳችን ገላ ላይ አርፏል ማለት ይቻላል፡፡ ከምግብ፣ ከመጠጥና ከልብስ ሌላ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች በዓለም ያለውን እንቅስቃሴ ቤታችን ድረስ አምጥተው ሲያቀርቡልን፣ ከጥቃቅን ጎጆ ኢንዱስትሪ እስከ ግዙፉ ፋብሪካዎች፣ ሁሉም በንግድ መርከብ ሆድ ዕቃ ባህርና ውቅያኖስ አቋርጠው መድረሳቸውን በዓይነ ህሊናችን ውል ማለቱ የግድ ነውና የንግድ መርከብ ሕይወታችንን ከፍተኛ ምዕራፍ የያዘ ብቻ ሳይሆን፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወታችንን በመለወጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ጥርጥር የለውም፡፡
- የመርከብ አመጣጥ ታሪክ
‹‹ሰው በውኃ ላይ መጓዝ የጀመረው መቼ ነው?›› የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልሱን ‹‹በዚህ ጊዜ ነበር›› ብሎ መስጠት ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን ከትልልቅ የውኃ አካላት ማለትም ከትልልቅ ሐይቆች፣ ባህሮችና ውቅያኖሶች በፊት በትልልቅ ወንዞች ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ተቀብረው ከተገኙ ጀልባዎች ቅሪት ለመረዳት የሚቻለው ግን፣ በልዩ ልዩ መሣሪያዎች ወይም በእሳት ትልልቅ ግንድ እየቦረቦሩ ይጠቀሙባቸው ነበር፡፡
በጥንት ዘመን በወንዝ ዳር ይኖሩ የነበሩ፣ በተለይም ወንዞች በበዛባቸው በአፍሪካና በአሜሪካ ያሉ አገሮች ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ ራሳቸውንና አነስተኛ ዕቃዎቻቸውን ከግንድ ጀምሮ በልዩ ልዩ መንገዶች ጀልባ በመሥራት ይጠቀሙ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ጥንታውያን ግብፃውያን በዓባይ ወንዝ፣ ሞሶፖታሚያውያን በኤፍራጥስና በጤግሮስ፣ ህንዳውያን በጋንጀሰና በኤንዲስ፣ ቻይናውያን፣ አውሮፓውያን በያሎ ወንዝ፣ በራይን ወንዝ፣ ወዘተ. በጀልባ ይጠቀሙ ነበር፡፡ ይሁንና ያልታሰበ ጎርፍ እየመጣ አደጋ ያስከትልባቸው ስለነበር በወንዝ ዳርቻዎች (በአሁኑ ጊዜ የውኃ ፍሰታቸው መቆጣጠሪያ እንዳላቸው መስኖዎች) ባለመቆጣጠሪያ ትልልቅ ቦዮችን በመሥራት ይጠቀሙ ነበር፡፡ በቦይ መጠቀም ሲጀምር በወንዞች ውኃቸውን በሚቀንስበት ጊዜ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ የክረምት ውኃ ማጠራቀሚያ እየሠሩ ክረምት ከበጋ ይጠቀሙ ነበር፡፡ የሚቀዘፉ አነስተኛ ጀልባዎች ጥቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ ሲሄድ፣ የጀልባዎቹ መጠንና ዓይነትም እየሰፋ ሄዶ አነስተኛ መርከቦችን መሥራት ሁኔታው አስገደዳቸው፡፡
በ1920 በዴንማርክ የተገኘው ቅሪተ-ጀልባ በ300 ዓመተ ዓለም አካባቢ የተሠራ እንደነበረና በወቅቱ የነበሩት ሰዎች በመርከብ አሠራር ጥበብ የተካኑ እንደነበሩ ያመለክታሉ፡፡ ሮማውያን ወደ የአሁኒቱን ብሪታንያን ሲወሩም የመጡባቸው መርከቦች ብዙ ሰዎችን የሚይዙ እንደነበሩ ተቀብረው ከተገኙ ቅሪቶቻቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ እስካሁን ከተገኙት መረጃዎች እ.ኤ.አ. በ1863 በደቡብ ዴንማርክ የተገኘውን ከ200 ዓመተ ዓለም በፊት የተሠራው ከሁሉም የላቀ ዘመናዊ እንደነበረ ይነገራል፡፡ ይሁንና የሸራ መወጠሪያ ምሰሶ ይኑራቸው አይኑራቸው አይታወቅም፡፡
ከጥንታዊ ጀልባዎች ቀጥሎ የመጡት ‹ክላሲካል› የተባሉ መርከቦች ሲሆኑ፣ እነዚህም አነስተኛ መርከቦች ከጥንታዊ መርከቦች በአመዛኙ የሚለዩት በርካታ መቅዘፊያ የነበራቸውና በመጠናቸውም አንፃራዊ በሆነ መንገድ ከፍተኛ መሆናቸው ነው፡፡ ጥንታዊ ግሪካውያን፣ ፊንቃውያንና ግሪካውያን በሜዲትራኒያን ባህር ይጠቀሙባቸው የነበሩት የነጋዴ መርከቦችም በርካታ ዕቃ እየተጫኑ ያጓጉዙ ጀመር፡፡ ከእነዚህ የመርከብ ዓይነቶች ቀጥሎ የመጡት ‹ቪኪንግ› የተባሉት ሲሆን፣ ከዚያም በንፋስ ኃይል የሚንቀሳቀሱ መርከቦች ናቸው፡፡
በንፋስ ኃይል የሚንቀሳቀሱት መርከቦች መሠራት ከሚቀዘፉት መርከቦች አንፃር ሲታዩ ሰዎችን ከድካም ገላግለዋል፡፡ በንፋስ ኃይል የሚንቀሳቀሱት መርከቦች ከክላሲካልም ሆነ ከቪኪን የሚበልጡ ሲሆን፣ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ1120 ኖርማንዲ ባህር ወደብ ላይ መልህቋን የጣለችው መርከብ 300 የሚሆኑ ሰዎችን እንዳጓጓዘች ከቅሪቷ መረዳት ተችሏል፡፡ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በምሥራቅ ህንድ ኩባንያ የተሠራችው 1,000 ቶን ሸቀጥ ለማጓጓዝ ትችል ነበር፡፡ ከንፋስ መርከብ ቀጥሎ የእንፋሎት መርከብ ተከተለ፡፡
በእንፋሎት የሚሠራ መርከብ መሠራት እንደሚችል ጽንሰ ሐሳቡ በ1690 የተጻፈ ቢሆንም፣ ጽንሰ ሐሳቡ በሥራ ላይ የዋለው በቶማስ ኒውከመን አማካይነት በ1712 ነው፡፡ በ1736 ደግሞ ‹‹ጆናታን ኸልስ ግሎወሴስቴርን ሻየር የታግቦት የፈጠራ መብቱን በሕግ አረጋገጠ፣ ምንም እንኳ የፈጠራ መብቱን ቢያረጋግጥም መርከቧ በሥራ ላይ አልዋለችም፡፡ የእንፋሎት መርከብ በሥራ ላይ መዋል የጀመረው 1775 በጄይ ሲ ፔሪ የሠራችው ጀልባ ፈረንሣይ ሴይን በተባለው ወንዝ ስትሞክር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ መጠኑም፣ ፍጥነቱም አገልግሎቱም እያደገ ሄደ፡፡ አትላንቲክ ውቅያኖስን የሚያቋርጠው መርከብ በ1818 በኒው ዮርክ ከእንጨት ተሠራ፡፡ ከኒው ዮርክ መርከብ በኋላ በሌሎች አገሮች መርከቦች በንግድ አገልግሎት ውለዋል፡፡ ከዚያም ወዲህ በመጀመሪያው በብረት፣ ቀጥሎም በዓረብ ብረት (ስቲል) ትልቅ መርከቦች መሠራት ጀመሩ፡፡ በ1881 ሙሉ በሙሉ ከዓረብ ብረት የተሠራችው መርከብ በአገልግሎት ላይ ዋለች፡፡ ይህችም መርከብ 7,392 ቶን ነበረች፡፡ በ1892 የተሠራችውና ‹‹ካምፓኒው›› የተባለችው የእንፋሎት መርከብ ደግሞ 12,950፣ የፈረስ ጉልበት በ1904 የተሠራችው 19,524፣ ከ1906 -1929 የተሠሩት እስከ 130,000 የፈረስ ጉልበት ነበራቸው፡፡
ዛሬ ከእንፋሎት ወደ ነዳጅ፣ ከነዳጅ ወደ ኑክሌር ኃይል የመጠቀም ሽግግር ተደርጓል፡፡ ፍጥነታቸውም በሰዓት ከአምስት እስከ ስድስት ኪሎ ሜትር የነበረው ወደ 100 ኪሎ ሜትር በሰዓት አድጓል፡፡ እስከ 10,000 ሰው ይጭናሉ፡፡ ብዙ ሺሕ ቶን ዕቃ ይሸከማሉ፡፡ የመንገደኞች ብቻ ሳይሆኑ የቱሪስቶች መጓጓዣ ሆነዋል፡፡ በአንድ የእንጨት ግንድ የተጀመረው የባህር ላይ ጉጤ አውሮፕላኖች የሚያርፉበትና የሚበሩበት ሆኗል፡፡ ከዚህም በላይ እንደ መርከብ ባህር የሚቀዝፉና እንደ አውሮፕላን በአየር የሚንሳፈፉ ተሠርተዋል፡፡ ይህም የሚያመለክተው ወደፊት የባህር ማዕበል ድል እንደሚሆን የሚተነብይ ነው፡፡
- ጥንታዊ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ታሪክ
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ታሪክን ስንመለከተው ከጥንት ፊንቃውያን፣ ግሪካውያን፣ ሮማውያን፣ ግብፃውያንና ሩቅ ምሥራቃውያን ጋር የተያያዘ በመሆኑ ተመሳሳይ የሥልጣኔ አቅጣጫን እንደሚከተል አያጠያይቅም፡፡ የታሪክ መረጃዎቹ የሚያረጋግጡትም ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ ከብዙ በጥቂት የሚከተሉትን መረጃዎች እንመልከት፡፡
ሪቻርድ ፓንክረስት (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ቦርደር ላንድስ (1997 ገጽ 3 -21)›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ እንደሚገልጹት፣ የጥንት ግብፃውያን በመርከብ በሰዓት 30 ማይልስ ያህል ለሦስት ወራት እየተጓዙ ኢትዮጵያ ይደርሱ ነበር፡፡ የግብፅና የፑንት (የዚያኔዋ ሐበሻ) ግንኙነት መቼ እንደተጀመረ ባይታወቅም፣ በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኘው ከ3407 እስከ 2888 ዓመተ ዓለም የነበረው ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ግብፆች ከኢትዮጵያ ሸቀጦች የበለጠ የሚፈልጉት መልካም መዓዛ ያለው ዕጣንና ከርቤ ነበር፡፡ ከ2708 እስከ 2697 ዓመተ ዓለም በሥልጣን ላይ የነበረው ግብፃዊ ንጉሥ ሳሁር ወደ ኢትዮጵያ በመርከብ በመምጣት መለኪያው ምን እንደሆነ ባይገለጽም፣ 80 ሺሕ (ስልቻ) ከርቤ፣ 2,600 ያህል ውድ መልካም ሽታ ያላቸው (ምናልባት ቡከቡባ) አጣናዎችና 6,000 ወርቅ ይዞ ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡ ከ2271 እስከ 2112 ዓመተ ዓለም የነገሠው ሜንቱሆተፕ ዳግማዊ ሄኑ የተባለውን ዓቃቤ ንዋዩን ያኔ «የእግዚአብሔር አገር» ትባል ወደ ነበረችው ኢትዮጵያ በመርከብ በመላክ ጊዜ ያላለፈበትን ከርቤ ከዚያው ከምንጩ እንዲያመጣለት አድርጓል፡፡ ከ1501 እስከ 1479 ዓመተ ዓለም የነበረችው የግብፅ ንግሥት ሐትሸበፐስት በ1495 ኢትዮጵያን ስትጎበኝ የከርቤ ዛፍ፣ ብዙ ከረጢት ከርቤ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ትልልቅ ጦጣዎችና ወርቅ ይዛ ወደ አገሯ ተመልሳለች፡፡ በመሠረቱ የንግድ መርከብ ይዘው የሚመጡና የሚፈልጉትን ሸቀጥ ይዘው የሚመለሱት ግብፃውያን ብቻ አልነበሩም፡፡ ኢትዮጵያውያንም ወደ ግብፅ በመሄድ በወቅቱ የነበረውን ሸቀጣ ሸቀጥ ይዘው ይመለሱ ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል በአፄ አሜን ሆቴፕ ዳግማዊ ዘመነ መንግሥት (1447 እስከ 1420 ዓመተ ዓለም) ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ወደ ግብፅ ሄደዋል፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩት የኢትዮጵያ መርከቦች ከኋላና ከፊት ክብ፣ ቀለማቸው ሐምራዊና ምሰሷቸው ትልቅ ነበሩ፡፡ የጥንት ግብፃውያን ታሪክ እንደሚነግረን የንጉሥ ሰለሞን (973 እስከ 930) መርከቦች ከርቤ፣ ዕጣን፣ የከርቤ ዛፍና የከበረ ድንጋይ ለመግዛት ወደ ኢትዮጵያ (አፋር) መጥተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሣልሳዊ ፕቲለሚ (305 እስከ 285 ዓመተ ዓለም)፣ በቀዳማዊ ኢርገተስ (246 እስከ 221 ዓመተ ዓለም) ግብፃውያን ከኢትዮጵያውያን ጋር ይነግዱ ነበር፡፡
ዴቪድ ሐሚልተን የተባሉት የታሪክ ተመራማራ በጁላይ 1967፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መጽሔት ቅጽ 5 ቁጥር 2 ላይ ‹‹ኢምፔሪያሊዝም ኢንሸት ኤንድ ሞደርን›› በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቁት ጽሑፍ ‹‹በሦስተኛውና በአራተኛው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የአክሱም አፄያዊ መንግሥት ግዛቱን እስከ ደቡባዊ ምዕራብ ድረስ አስፋፍቶ ነበር፡፡›› ያወሳል፡፡ በዚህም ዘመን አይላ ወይም አዩላስት የተባሉት ግዛቶች በዚያኔው የአክሱም መንግሥት ሥር እንደነበሩ ሪቻርድ በርተን ‹‹ፈረስት ፉት ስቴኘ ኢን ዘ ኢስት አፍሪካ፣ (ለንደን 1856)›› በተሰኘ መጽሐፉ በገጽ 66 ላይ አሥፍሯል፡፡ በዚህ ጊዜ የአክሱም መንግሥት ሥልጣኑን እስከተጠቀሰው ግዛት ሲያስፋፋ በመርከብ እየተጓጓዘና የንግድ ሥራ እያካሄደ እንደነበረ አያጠያይቅም፡፡ ኤም ፐርሐም የተባለ ታሪክ ጸሐፊ ‹‹ዘ ገቨርንመንት ኦፍ ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1948 ባሳተመው መጽሐፍ እንደገለጸው ከስድስተኛው ምዕት ዓመት አጋማሽ በኋላም የአክሱም መንግሥት ሠራዊት ደቡብ ዓረቢያን በመያዝ፣ ክርስትናን እንዳስፋፋና ለመንግሥቱ ተጠሪ የሆነ አካል አስቀምጦ ነበር፡፡ ሆኖም በስምንተኛው ክፍለ ዘመን እስልምና እየገነነ ሲመጣ፣ የደቡብ ዓረቢያ ግዛት ብቻ ሳይሆን አዱሊስም የዓረቦችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በመርከቦች ንግድ ልውውጥ ማድረግ መቀጠላቸው አልቀረም፡፡
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ቦርደር ላንድስ ገጽ 168 እስከ 169›› ዓረብ ፈቂን (ሺሃበዲን) የተባለውን የመናዊው የአህመድ ግራኝ ዜና መዋዕል ጸሐፊን ጠቅሰው እንደሚገልጹት፣ አፄ ልብነ ድንግል ወርቅ፣ ወርሲ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ዝባድና ባሪያ ወደ ዓረብ አገር ለሚሄዱ ነጋዴዎች ይልኩ ነበር፡፡ ሙስሊሞች ቀይ ባህርንና በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ የነበሩትን ድንበሮች ከስምንተኛው ክፍለ ዘመን አንስተው ለሌላ አንድ ክፍለ ዘመን ያህል ሲቆጣጠሩ የአካባቢው ኅብረተሰብ የእስልምናን ሃይማኖት ተቀብሎ ከመካከለኛውና ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች ጋር የንግድ ልውውጥ ያደርግ እንደነበር፣ ስለሐረር ሡልጣኖች የተጻፉት በርካታ ታሪኮች ያረጋግጣሉ፡፡ ከ1468 እስከ 1480 የአዳል ሡልጣኔትን ይመራ የነበረው አሚር ማሕፉዝ በሸዋው አፄያዊ መንግሥት ላይ ተከታታይ ጦርነት እንዳደረገና እስከ ምሥራቅ ሸዋ ድረስ እንደዘለቀ ስናስታውስ፣ ከጦርነቱ ባሻገር በዘይላና በበርበራ በኩል ሸቀጥ ይገባና ይወጣ እንደነበረም መዘንጋት የለበትም፡፡ የአሚር ማሕፉዝን ልጅ ያገባውና ግዛቱን ከዘይላ እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ አስፋፍቶ የነበረው ኢማም አህመድ ኢብራሂም አል ቓዚ ግራኝም (1506 እስከ 1543) በ15 ዓመት የሥልጣን ዘመኑ ዘይላንም፣ ጂቡቲንም፣ ምፅዋንም አጠቃሎ ይገዛ ስለነበር በሩቅ ምሥራቅና ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር ይደረግ የነበረው የንግድ ልውጥ እንደቀጠለ ነበር፡፡
በእርግጥም የሐረር ሡልጣኔቶች እንደወረሲ፣ ቡና፣ ጥራጥሬ ዝባድና የመሳሰሉትን ሸቀጦች በዘይላ በኩል አድርገው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የመንና ወደ ሩቅ ምሥራቅ አገሮች ሲልኩ፣ በምትኩም የጨርቃ ጨርቅና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመርከብ ያስመጡ እንደነበር በወቅቱ ሐረርን ከየመን ከነጋዴዎች ጋር ገብቶ የጎበኘው ሪቻርድ በርተን በሰፊው ያስረዳል፡፡ ዕውቁ የታሪክ ምሁር ስፔንሰር ‹‹ኢስላም ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. 1965 ለንደን ባሳተመው መጽሐፉም በመርከብ በኩል ነበረውን ግንኙነት ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡
እ.ኤ.አ. ከ1874 ጀምሮ ቱርክ ሐረርን ስትይዝም የመርከብ ንግዱ ከዚህ አንፃር ቀጥሎ ነበር፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን ቱርኮች፣ እንግሊዞችና ፈረንሣዮች ኃያል የነበሩ ሲሆን፣ ሁሉም ይዞታቸውን በቀይ ባህር አካባቢ አስፋፍተው የንግድ መርከብ ልውውጥ ለማድረግ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ በዲሴምበር ወር 1859 ‹‹ለየመን›› የተባለች መርከብ ዘይላንና ምፅዋን የጎበኘች ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ልውውጥ ለማድረግ ፍላጎት እንደነበረ የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
‹‹ሩባቲኖ ስቲም ፓኬት›› የተባለ የጣሊያን ኩባንያ አ.ኤ.አ. በ1870 መርከቡን በአሰብ ወደብ ለማሳረፍና ራሂታ የተባለውን ግዛት በ8,200 ዶላር ለመግዛት ችለው ነበር፡፡ ከዚያም ከ10 ዓመታት በኋላ ማለትም በ1880 ላይ ግን የሩባቲኖ ኩባንያ የንግድ መርከብ በአሰብ ላይ ነበረች፡፡ ሆኖም በዚህ ጊዜ ግብፃውያን የጦር አበጋዞች ተቃውሞ አልነበራቸውም፡፡ ሰርኤፔድ የተባለው እንግሊዛዊ እ.ኤ.አ. ኖቨምበር 20 ቀን 1879 ለሎርድ ሳሊስበር በላከው ማስታወሻ እንደጠቀሰውም፣ ሲኞር ሩባቲኖ በተደጋጋሚ የእሱ የንግድ መርከብ በአሰብ ወደብ ላይ መገኘት ከንግድ ጋር እንጂ ከመንግሥት ጋር በፍፁም የተገናኘ አይደለም ሲል ገልጿል፡፡ ሜይ 19 ቀን 1881 የጣሊያን መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ምንም እንኳን የሲኞር ሩባቲኖቲኖ ዓላማ በንግድ ላይ የተመሠረት ቢሆንም፣ የግዛቷ የበላይ ግን የጣሊያን መንግሥት ነው ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡ ይህም ከማርች 10 ቀን 1882 ጀምሮ የፀና ሆኗል፡፡ ስለዚህም የሲኞር ረባቲኖ ኩባንያ አሰብ ላይ በማረፍ የመርከብ ንግድ ሥራውን በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ አስፋፍቶ ሲሠራ መቆየቱ አንድ ሀቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የዚህ ንግድ ዋና ተቋዳሽ መሆኗ የግድ ነው፡፡
ዴቪድ ሐሚልተን ወደ ጽሑፋቸው ማጠቃለያ ላይ ሲደርሱ (ከጥንት ሳባውያን አንስቶ እስከ ዘመናችን ድረስ የተካሄደው የግዛት መስፋፋት ከንግድ ጋር የተያያዘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ ሎርድ ሳሊስበሪ የኤደን ወደብን ለመጠበቅ የፈለጉበትን ምክንያት ሲገልጹ፣ ‹‹ወደ እዚህች ግዛት የምግብ አቅርቦት ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ነበር፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በክርስትናና በእስልምና እምነት ስም የተካሄዱት እንቅስቃሴዎች ሳይቀሩ ከንግድ ትርፉ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳላቸው አጠያያቂ አልሆነም፡፡
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 1974 ላይ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርመራ መጽሔት ቅጽ 12 ቁጥር አንድ ‹‹ባንያን ኦር ኢንዲያን ፕረዘንስ አት ማሳዋ፣ ዘ ዳህላክ አይላንድስ ኤንድ ሆርን ኦፍ አፍሪካ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፣ ‹‹ፐሪፕለስ ኦፍ ዘ ኤርትሪያን ሲ›› በተሰኘው የመጀመርያው የክርስትና ምዕተ ዓመት የታሪክ መረጃ ተተንትኖ እንደምናገኘው ህንዳውያን በንግድ መርከቦች ልዩ ልዩ ሸቀጦችን ጭነው በመምጣት ከኢትዮጵያ ጋር ይነግዱ ነበረ፡፡ በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ ይገቡ ከነበሩት ሸቀጦች መካከል ተራ ብረት፣ ዓረብ ብረት፣ ሞቻ እየተባለ የሚጠራው የህንድ ልብስና ሌሎች በልዩ ልዩ ቀለም የተነከሩ ነዶ ጨርቆች ይገኙባቸዋል፡፡ በደብረ ዳሞ በተደረገው የመሬት ከርሰ ቁፋሮም የብራህማን ቋንቋ የተጻፈባቸው ቀለበቶችና በ203 ዓ.ም. የተሠሩ 103 ያህል ከወርቅ የተሠሩ ሳንቲሞች ተገኝተዋል፡፡
በ300 ዓመተ ዓለም አካባቢም የቴብስ ምሁራን ያኔ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ወደነበረችው አክሱም መጥተው ይማሩ ነበር፡፡ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢም አፄ ካሌብ ዘጠኝ ጀልባዎችን ከህንድ ገዝተው ቀይ ባህርን ተሻግረው ደቡብ ዓረቢያን እንዳጠቁ ይጠቅሳል፡፡ ፍራንስ አልቫሬዝ የተባለው የፖርቱጋል ቄስም በደቡባዊ ትግራይ ማናደለይ በተባለች የገበያ ሥፍራ የሁሉም አገሮች ነጋዴዎች በተለይም ጥቁር ህንዶች በብዛት ይገኙ እንደነበረ ‹‹በኪንግሃምና ጂ ደብሊው ቢ ሐንቲንግተን›› የተባለ የታሪክ ምሁራን ‹‹ዘ ፕሪስተር ጆን ኦቭ ዘ ኢንዲስ›› በተባለው ሥራቸው ምዕራፍ አንድ ገጽ 5 ላይ አሥፍረዋል፡፡ ባንያውያን ከአዱሊስ እስከ ዘይላና በርበራ ተንሰራፍተው ይነግዱ የነበሩ ሲሆን፣ በምሥራቅ ኢትዮጵያም ሐረር ድረስ በመግባት ልዩ ልዩ ሸቀጦችን ያመጡ እንደነበር ሮበቺ ብሪቸሪ የተባለው ጣሊያናዊ ተጓዥ «ኔል ሐሪር» በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1896 ሚላን ባሳተመው መጽሐፉ ይጠቅሳል፡፡ ፒ. ፖሊቲስኪ የተባለው ጀርመናዊ የታሪክ ተመራማሪም «ሐረር» በሚል ርዕስ በ1888 ‹ላየኘዚግ› ባሳተመው መጽሐፉ «ህንዳውያን በሐረር ከፍተኛ ንግድ ያንቀሳቅሱና ሸቀጣቸውን ሸጠው ከኦጋዴንና ከሸዋ በርካታ የዝሆን ጥርስ በመግዛት በንግድ መርከቦቻቸው ወደሌላ ገበያ ይወስዱ ነበር» ብሏል፡፡
ብዙ የታሪክ ምሁራን እንደ መረጃ የሚጠቅሱት ኮስማስ ኢንዲኮኘሌይትስ የተባለው ግብፃዊ መነኩሴ እ.ኤ.አ. በ525 አዶሊስን ከጎበኘ በኋላ ኢትዮጵያና ኑቢያ ከህንድ፣ ከሲሎንና ሌሎች ጋር አገሮች ጋር ይነግዱ እንደነበረ በያዘው ማስታወሻ ላይ አሥፍሯል፡፡ ኮስማስ በዚያን ጊዜ የነበሩት አክሱማውያን በግዛታቸው አድርገው ያልፉ የነበሩት መርከቦች በሙሉ ግብር እንዲከፍሉ ያስገድዱ እንደነበረና ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ ይካሄድ እንደነበረ ይገለጻል (ለተጨማሪ መረጃ ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ዘ ኢትዮጵያን ቦርደር ላንድስ፣ 1997 ገጽ 24 – 25 ይመልከቱ)፡፡
ብዙዎቻችን የኢትዮጵያ የመርከብ ንግድ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባህር ብቻ የተወሰን ይመስለናል፡፡ ነገር ግን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች በህንድ ውቅያኖስ በኩል እስከ ዛንዚባር በመርከብ ይነግዱ ነበር፡፡ ሪቻርድ ፓንክረስት፣ የተለያዩ የታሪክ ጸሐፊዎችን እየጠቀሱ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ጆርናል ቅጽ 3 ቁጥር 2 እ.ኤ.አ 1965 ከገጽ 37 እስከ 74 እንደሚያስገነዝቡን፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ጫፍ ሕዝቦች በኪሲማዮ፣ በበርበራ፣ በሞቃዲሾ፣ በበናዲር፣ በመርካ፣ በበርቫ፣… በኩል ከብት፣ ቡና፣ የዝሆን ጥርስ፣ ቆዳ፣ በቅሎ፣ ፈረስ፣ አህያ፣ ከርቤ፣ ሙጫ፣ የጎሽ ቀንድ፣ ለገበያ እያቀረቡ በምትኩ ጨርቃ ጨርቅ፣ ብረት፣ ቴምር፣ ስኳር፣ ጌጣጌጥ፣ ዛጎል፣ ወዘተ. በ1980ዎቹ ውስጥ ያስገቡ ነበር፡፡ ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ሮቤቺ-ብሪቸቲን በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ጆርናል (ቅጽ 2 ቁጥር 2 እ.ኤ.አ 1965 ከገጽ 74 እስከ 88) ጠቅሰው እንደሚያስረዱን፣ በሐረር በኩል በትንሹ አንድ ሚሊዮን ኪሎ የዝሆን ጥርስ፣ 200 ሺሕ ቆዳ ገበያው ከፍ ሲል ደግሞ ከ15 ሚሊዮን እስከ 22 ሚሊዮን፤ 500 ኪሎ ቡና ለገበያ ይቀርብ ነበር፡፡
በአጭሩ ቀደም ሲል ለአብነት ያህል ብቻ የተጠቀሱት የታሪክ ማስረጃዎች ይፋ እንደሚያደርጉልን፣ የዛሬው የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ የጥንቱ ንግድ መርከብ የቀጠለ መሆኑን ነው፡፡
- ዘመናዊ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን የሚያውለበልቡ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎቶች (ጀልባና መርከብ) ሥራቸውን የጀመሩት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በተዋሀደች በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በዚህ ጥናት ወደፊት ሰፋ ብሎ እንደሚቀርበው ድሮውንም በምፅዋ አንባቢ ይሠሩ የነበሩ ግሪኮች በሁለት አነስተኛ ጀልባዎች በቀይ ባህር፣ በሜዲትራኒያን ባህርና በዓረብ ባህረ ሰላጤ አካባቢ ይሠሩ ነበር፡፡ እነዚህም ነጋዴዎች በወቅቱ በኤርትራ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ዕውቅና የነበራቸው ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር መዋሀድ ሰፊ የንግድ በር ይከፍታል ብለው ያመኑ የባህር ንግድ ማኅበረሰብ አባላት፣ የባህር ትራንስፖርትና ከባህር ንግድ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚያዋጣ አምነው አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን ማከናወን ጀመሩ፡፡ በእርግጥም ከ1945 ጀምሮ እስከ 1955 ያለውን እንቅስቃሴን ስንመለከት የተጣራ ክብደት ያለው ዕቃ ተጓጉዟል፡፡
በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ቁጥራቸው በርከት ያሉ መርከቦችን በማንቀሳቀስ፣ በተለይም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለብን ባህር ንግድ ለማንቀሳቀስ የተነሱት የቀይ ባህር የልማት ማኅበር የተባለው ኩባንያ ባለቤቶች ናቸው፡፡
በወቅቱ ስለነበረውም ሁኔታ የኢትዮጵያ ድምፅ/አዲስ ዘመን፣ መጋቢት 15 ቀን 1956 ዓ.ም. እንደሚከተለው ዘግቦታል፡፡
መጋቢት 8 ቀን 1956 ዓ.ም. የቀይ ባህር የልማት ማኅበር ንብረት የሆኑ አራት የንግድ መርከቦች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ባለፈው ሳምንት አገልግሎት ጀመሩ፡፡ እነዚህም መርከቦች ኤርትራ፣ ጎንደር፣ አክሱምና ሐረር ተብለው የሚጠሩ ሲሆን፣ እነሱም እንደ ቅደም ተከተላቸው 3,410 ቶን፣ 700 ቶን፣ እና 2,200 ቶን ክብደት ያለውን ዕቃ መጫን እንደሚችሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በወቅቱ ከማኅበረኞቹ አንዱ የሆኑት አቶ ኃይሉ መከታ እንደገለጹት፣ አራቱም መርከቦች ባለፈው ሳምንት (መጋቢት 8 ቀን 1956 ዓ.ም.) የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት ባለሥልጣናትና በአዲስ አበባ ተቀማጭ የሆኑት የቡልጋሪያ አምባሳደር፣ እንዲሁም የማኅበሩ አባሎች በተገኙበት በምፅዋ ወደብ ተመርቀዋል፡፡ መርከቦቹ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት የሚያውለበልቡት የቡልጋሪያን ሰንደቅ ዓላማ እንደነበር ሲታወቅ፣ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ ግን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ የቀይ ባህር ልማት ማኅበር ካፒታል አራት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ሲሆን፣ ወደ ፊት እስከ አሥር ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ በማኅበሩ ይታመናል፡፡ ማኅበርተኞቹም አምስት ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ውስጥ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሦስቱ ቡልጋሪያውያን ናቸው፡፡ ይኼው ማኅበር ከንግድ መርከብ በተጨማሪ የዓሳ ዱቄትና የዓሳ ዘይት፣ እንዲሁም ትኩስ ሥጋ በፋብሪካ መልክ እየሠራና እያከማቸ ወደ ውጭ አገር ይልካል፡፡ ወደ ፊት በቆርቆሮ እያሸገ ለመላክ ያቀደ ሲሆን ለጊዜው በበጌ ምድር፣ በኤርትራና በትግራይ የከብት ማረጃ ቄራ ያቋቁማል፡፡ በተጨማሪም ቆዳ እያለፋ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ነጋዴዎች ያቀርባል፡፡ ዋናው መሥሪያ ቤት አሥመራ ሲሆን፣ በአዲስ አበባና በምፅዋ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ያቋቁማል፡፡ ከአቶ ኃይሌ መከታ በተገኘው መረጃ መሠረት እስከ ሁለት ዓመት 75 በመቶ ያህሉ ሠራተኞች ኢትዮጵያውያን ይሆናሉ፡፡ እስካሁን ድረስ የአገራችን ነጋዴዎች ዕቃቸውን የሚያስጭኑት በተላላፊ መርከቦች ሲሆን፣ አሁን ግን እነዚህ መርከቦች አነስተኛ መጠን ስላላቸው በተጠሩበት ጊዜ ከፍ በማለቱ የነጋዴዎችን ችግር ለማቃለል ይችላሉ፡፡ የልማት ማኅበሩ በመርከቦቹ፣ በፋብሪካው ሥራ በአስመጪነትና በላኪነት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የውጭ ምንዛሪ ለአገሪቱ በማስገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
አቶ ጌታቸው በቀለ «ዘ ኢምፐረርስ ክሎዝ» በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው እንደሚገልጹት፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንደተዋሀደች በምፅዋና በአሰብ አንድና ሁለት መናኛ ጀልባዎች ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት (ኢንነመ) የባህር ክፍል መሣሪያ ቤት እንዳቋቋመ ግን ሁኔታዎች መለወጥ ጀመሩ፡፡ ወደቦችንና መርከቦችን እንዴት ማንቀሳቀስ እንደሚቻል በጎረቤት አገሮችና በአውሮፓ አገሮች ከትምህርት ጋር የተያያዘ የሥራ ጉብኝት መደረግ ተጀመረ፡፡
በኤደንና በሌሎች ሥፍራዎች የነበሩና በባህር ትራንስፖርት ዕውቀት የነበራቸው ባለሙያዎች ከየቦታው ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ከእነዚህም መካከል አቶ አበበ ወልደ ሥላሴ፣ አቶ አድማስ ተሰማ፣ አቶ ደምሴ አበበ፣ አቶ ነጋሽ ጋረደው፣ አቶ ወልዴ አረጋይ፣ አቶ ተክኤ ገብረ ኢየሱስ፣ አቶ መሃሪ ተወልደ ማርያም፣ አቶ በረከት ምሕረት፣ አቶ አፈወርቅ ይስሐቅ፣ አቶ ተስፋ እግዚ ወልደሐዋርያ፣ አቶ መላኩና ዮሐንስ ኪዳነ ማርያም (አቶ ብርሃኑ ሀብተ ማርያም?) የሚባሉ ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህ የባህር ትራንስፖርት ባለሙያዎች ምንም እንኳን በሙያው ቢሠለጠኑም አዲስ አበባ ውስጥ በልዩ ልዩ የግል ድርጅቶች ተበታትነው ይሠሩ ነበር፡፡ ከዚያም እነሱ ካሉበት ቦታ እንዲሰበሰቡ በተደረገው ጥረት ስምንት ያህሉ ተገኙና በባህር ክፍል መሥሪያ ቤት ተመድበው እንዲሠሩ ተደረገ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኤደን ወደብ በመርከብ ጥገና ቺፍ መካኒክ ሆኖ ይሠራ የነበረው የ28 ዓመት ወጣት ወደ አገሩ ተመልሶ እንዲሠራ ሲጋበዝ ፈቃደኛ ሆኖ መጣና ሥራው ተጀመረ፡፡ ይህም በ1945 ዓ.ም. መሆኑ ነው፡፡
በ1948 ዓ.ም. ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ የባህር መሥሪያ ቤት ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው ተሾሙ፡፡ የደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ መሾምም እንቅስቃሴውን የበለጠ ከፍ አደረገው፡፡ ይልቁንም በራስ አንዳርጋቸው መሳይ ሥር አስመራ ላይ የነበረው የባህር ክፍል ከዋናው መሥሪያ ቤት ሥር እንዲሆን በር ከፈተ፡፡
በ1950 ዓ.ም. ደጃዝማች ዘውዴ በልጅ ሚካኤል እምሩ ተተኩ፡፡ ልጅ ሚካኤልም እንደ ደጃዝማች ዘውዴ ሁሉ በእንግሊዝ አገር ትምህርታቸውን የተከታተሉ ከመሆናቸውም በላይ አገራቸውን ለማሳደግ ብርቱ ፍላጎት የነበራቸው በመሆናቸው ኢትዮጵያ የራሷ መርከብ ኖሯት ኢኮኖሚዋን እንድታሳድግ ጠንክረው ይሠሩ ነበር፡፡ በዚህም የሰው ኃይል የማሠልጠኑ፣ የባህር መሥሪያ ቤትን የማጠናከሩ ሥራ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ከተግባረ ዕድ ተማሪዎች መካከል በትምህርታቸው ጎበዝ የሆኑትን ስምንት ተማሪዎችን በመምረጥም ሆላንድ ሄደው የመርከብ ቴክኒክ እንዲሠለጥኑ ተደረገ፡፡ እነዚህም ተማሪዎች ተሰማ ግዛው፣ ዓለማየሁ በትሩ፣ ጽጌ አብርሃ፣ ከበደ ጥላሁን፣ ሡልጣን ኃይሉ፣ ብርሃኑ ወልደሰማያት፣ ማንበግሮህ አደራና ከበደ ይባላሉ፡፡ ምልምል ወጣቶቹ ሆላንድ ሄደው ከሠለጠኑ በኋላ እዚያው ይሠሩ የነበሩትንና መርከቦችን የሚገፉና የሚጎትቱ አራት ታግቦቶችን እየነዱ መጡ፡፡ እርግጥ ነው ስምንቱ ወጣቶች ታግቦቶቹን አትላንቲክ ውቅያኖስን፣ ሜዲትራንያን ባህርንና ቀይ ባህርን አቋርጠው እንዲመጡ ለማድረግ የተከፈለውን 2.5 ሚሊዮን ዶላር ውኃ ውስጥ የመክተት ያህል ስለሚሆን በፍፁም መደረግ እንደሌለበት፣ በምትኩም ፈረንጆች ሊያመጧቸው እንደሚገባ የሚያሳስብ ተቃውሞ ነበር፡፡ ነገር ግን መልምሎ የላካቸው አካል በተለይም ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ ኢትዮጵያውያኑ ሊያመጧቸው እንደሚችሉ በማሳመናቸው ስምንቱ ኢትዮጵያውያን ከታግ ቦታቸው ጋር ከስድስት ወራት በኋላ ምፅዋ ከተፍ አሉ፡፡
በ1952 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት በመደበው ሦስት ሚሊዮን ብር 1,000 ቶን ክብደት ያላት መርከብ «ዲ ዳብሊው ክሬመርና ሶህን» በተባለ የጀርመን መርከብ ሠሪ ኩባንያ እንድትሠራ የኮንትራት ውል ተፈጸመ፡፡ በኮንትራቱም መሠረት መርከቧ ተሠርታ ሜይ 31 ቀን 1961 ርክክብ እንዲፈጸም ነበር፡፡ ይህችም «አጥቢያ ኮከብ» የተባለችው የመጀመሪያ ዘመናዊ መርከብ መሆኗ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ዘመናዊ የንግድ መርከብ ህልውና ታሪክ ንጉሠ ነገሥቱና ባለሥልጣኖቻቸው ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡ ለመሆኑ የተጫወቱት ሚና ምን ነበር? ይህን በክፍል ሁለት እንመለከታለን፡፡ ይቀጥላል
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡