Friday, June 2, 2023

ፖለቲካዊ ጫና ያስከተለው የኢትዮጵያ ዕዳ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እንደ የዓለም ገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የዓለም ባንክ ያሉ ዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች የሚሰጡት ብድርና ዕርዳታ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ ታዳጊ አገሮች ትልቅ የበጀት መሸፈኛ ነው፡፡ ከውጭ የሚገኘው ብድርና ዕርዳታ የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከ25 እስከ 30 በመቶ ይሸፍናል ይባላል፡፡ ይህ እንደ ኢትዮጵያ ላለ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እጥረት ላለበት አገር ትልቅ ጉድለት የሚሸፍን እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡ በቅርብ ዓመታት በተለያዩ መንገዶች ከለጋሾችና ከአበዳሪዎች የሚመጣው የውጭ ምንዛሪ መቀነሱ፣ ችግሩን በጣም አባብሶታል እየተባለ ነው፡፡  

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የገንዘብና የኢኮኖሚ ባለሥልጣናት ከዓለም ባንክና ከዓለም ገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተሮች ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ምክክር ወቅት ለድርቅ ተጎጂዎች፣ ለተፈናቃዮችና የኑሮ ሁኔታቸው አደጋ ላይ ለወደቀ ዜጎች ፈጥኖ ለመድረስ የሚያስችል የአይኤምኤፍን የመሠረታዊ አቅርቦት ድጋፍ ለማግኘት ጥያቄ ማቅረቧ ተነግሯል፡፡ አገሪቱ ባልተቋረጠ ግጭት፣ የዋጋ ንረት፣ የሸቀጦች ገበያ አለመረጋጋትና በማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ክፉኛ የተጎዳች መሆኗን በመግለጽ አይኤምኤፍ ፈጥኖ ድጋፍ እንዲያደርግላት፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጥያቄ ማቅረባቸውም ተሰምቷል፡፡ ኢትዮጵያ በብዙ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ችግሮች እየተፈተነችም ቢሆንም፣ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጓን እንዳላቋረጠች ለአይኤምኤፍ አመራሮች ያብራሩት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት፣ ተቋሙ ይህን የሚያግዝና ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ እንዲለቅ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡

ይህ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጥያቄና ውትወታ ግን በተጨባጭ አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘቱ ነው የተዘገበው፡፡ ለአይኤምኤፍ በቀላሉ እሺ አለማለት ምክንያት ከሆኑ ነገሮች መካከል ደግሞ አገሪቱ የምትገኝበት ጦርነት አለመቆሙ አንዱ እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡ የአይኤምኤፍ ሰዎች የአገሪቱን የኢኮኖሚ ጥንካሬ፣ የዕድገት ሁኔታም ሆነ የዕዳ አከፋፈል ጉዳዮች ምክንያት አድርገው ማቅረባቸው፣ ነገር ግን ከሁሉ በላይ የተቋሙ ፈንድ የደረቀው በዋናነት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ምክንያት እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡ 

ይህን የሚጋራ አስተያየት የሰጡት መቀመጫቸውን በለንደን ያደረጉት የፋይናንስ ባለሙያው አብዱልመናን መሀመድ (ዶ/ር)፣ የብድር ዕዳ የማራዘሙ ጥያቄ ከጀመረ ዓመት ከዘጠኝ ወራት ገደማ እንደሆነው ነው የሚናገሩት፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ችግር ግጭቶችና የኮሮና ወረርሽኝ በጣም አባብሰውታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የዕዳ ሽግሽግ (ሪስትራክቸር) እንዲደረግ ነው የፈለገው፡፡ የዕዳ ሽግሽግ ደግሞ በብዙ መንገዶች ሊሆን ይችላል፡፡ የአከፋፈል ሒደቱን መለወጥ ሊሆን ይችላል፣ ወይም የተወሰነ ዕዳ መሰረዝ ሊሆን ይችላል፡፡ ሽግሽግ ከተደረገ የብድር ዕዳው ቀለል ይላል፤›› በማለት የኢትዮጵያን ጥያቄ ምንነት ያስረዳሉ፡፡  

‹የቡድን 20 ኮመን ፍሬምወርክ› በሚባለው የዕዳ ማቅለያ ዕቅድ የኢትዮጵያ መንግሥት የብድር ሽግሽግ ጠይቆ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሌሎች የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ አገሮችም በተመሳሳይ መጠየቃቸውን የጠቀሱት የፋይናንስ ባለሙያው፣ አበዳሪዎቹ ዕዳውን ለማሸጋሸግ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን መጠየቃቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹ከእነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ደግሞ ኢኮኖሚው መሻሻል አለበት የሚለው ይገኝበታል፡፡ እንዲሁም ዕዳ አከፋፈላችን የተስተካከለ መሆንም ይገባዋል፡፡ ሌላው ችግር የፈጠረ ጉዳይ ደግሞ ግጭቱ ነው፡፡ አይኤምኤፍ፣ የዓለም ባንክም ሆነ ሌሎች አበዳሪዎች በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት እንዲያቆም ይፈልጋሉ፤›› በማለት ኢትዮጵያ እንድታሟላ የተጠየቀቻቸውን ነጥቦች ያስረዳሉ፡፡

የገንዘብና ሚኒስትር ደኤታ እዮብ ተካልኝን (ዶ/ር) አነጋገርኩ ብሎ ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ፣ አገሪቱ ለዓለም አቀፍ አበዳሪዎች አቅርባው የነበረው የዕዳ ይራዘምልኝ ጥያቄም ቢሆን መዘግየት ገጥሞታል፡፡ ጥያቄው መጓተት የገጠመው ደግሞ በዋናነት በጦርነቱ ምክንያት እንደሆነ የተናገሩት ባለሥልጣኑ፣ ጥያቄው ፈቅ አለማለቱን የሚያበሳጭ ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

በቻይናና በፈረንሣይ በኩል ጥያቄው ይሁንታን ቢያገኝም ሆነ ከቡድን 20 አባል አገሮች እንቅፋት ይገጥመዋል ተብሎ ባይታመንም፣ ነገር ግን ጉዳዩ የአይኤምኤፍን ይሁንታ ለማግኘት መጓተት እንደገጠመው ነበር ሚኒስትር ደኤታው የተናገሩት፡፡

በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ለሚካሄደው የሰላም ንግግር መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት፣ እንዲሁም ለኢኮኖሚ ሪፎርሞች ያለውን ዝግጁነት ተመልክቶ ድርጅቱ ውሳኔ ላይ ይደርሳል የሚል እምነታቸውን እዮብ (ዶ/ር) መግለጻቸው ተነግሯል፡፡ አይኤምኤፍ የብድር አከፋፈል ዋስትና ጉዳይን የማጥናቱ ሒደት ጊዜ እንደፈጀበት ቢነገርም፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ ዕዳ አከፋፈል ላይ መስተጓጎል እንዳልገጠማት ድርጅቱ በሚገባ እንደሚያውቅ ነው ያስረዱት፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ይህ ቢባልም በአንዳንድ መረጃዎች ግን የኢትዮጵያ ዋነኛ አበዳሪ የሆነችው ቻይናም ብትሆን፣ የኢትዮጵያን ዕዳ ለማቅለል ማመንታት እንደሚታይባት ተነግሯል፡፡ በቅርቡ ከሪፖርተር እንግሊዘኛ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአሜሪካ ኤስ ኤንድ ፒ ግሎባል ማርኬት ኢንተለጀንስ (S & P Global Market Intelligence) ተቋም ከሰሃራ በታች አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛ ኢኮኖሚ ባለሙያ አሊሳ ስትሮቤል ይህን የሚደግፍ አስተያየት ነው የሚሰጡት፡፡

‹‹ከቻይና የተገኙ ብድሮችን በሚመለከት የተብራራ መረጃ አልቀረበም፡፡ የቻይና አበዳሪዎች በተለይ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባቀረቡት ብድር ላይ ኢትዮጵያ ግልጽነት የተሞላበት የብድር መግለጫ አላቀረበችም፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ግጭት እየተባባሰ መሄዱ ሌላው ችግር ሲሆን፣ ከአይኤምኤፍ ጋር የሚደረገው ንግግር መጓተቱም ራሱን የቻለ እንቅፋት ነው፡፡ ለቡድን 20 ኮመን ፍሬምወርክ ኢትዮጵያ የተሟላ የዕዳ መግለጫ መረጃ ይዛ መቅረቧ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪም ከአይኤምኤፍ ጋር የሚደረገው ንግግር ሒደትም ለዕዳ ጫናው ማቃለል ጥያቄ ወሳኝ ነው፤›› በማለት የተናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዋ፣ ጦርነቱ በዋናነት አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን በሰፊው አውስተዋል፡፡  

ከዚህ ጋር የሚቀራረብ አስተያየት የሰጡት የፋይናንስ ባለሙያው አብዱልመናን (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ ጋር ያላት ግንኙነት የተስተካከለ እንዲሆን እንደሚፈለግ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የዛሬ ሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር ግድም ከአይኤምኤፍ ጋር ተስማምተን ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ልታደርግ ቃል በመግባት አይኤምኤፍም ወደ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ሊሰጠን ተስማምተን ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ ሪፎርሙን በሚፈለገው ፍጥነት ባለማስኬዱ ስምምነቱ አበቃ፡፡ ይህ ጉዳይ አሁን ለቀረበውም የብድር ዕዳ ሽግሽግ ትልቅ እንቅፋት ሆኖብናል፤›› ሲሉ ስለጉዳዩ አብራርተዋል፡፡  

የራሱ የዓለም ገንዘብ ድርጅት የቅርብ ጊዜ ትንበያ የዓለም ኢኮኖሚ ከዓምናውም ሆነ ከዘንድሮው የቀጣይ ዓመት ዕድገቱ የበለጠ እንደሚያዘግም ያሳያል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2022 የነበረው የ3.2 በመቶ የዕድገት ትንበያ በቀጣዩ ዓመት ግን ወደ 2.7 በመቶ እንደሚወርድ ነው ድርጅቱ የዓለም ዕድገት ማሽቆልቆልን የተነበየው፡፡ ይህ የዕድገት ማዝገም የሚፈጥረው የኢኮኖሚ ቀውስ ደግሞ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ላይ የበለጠ እንደሚፀና ድርጅቱ ያትታል፡፡

ድርጅቱ በዚህ ቀጣና ያሉ የአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚያቸው ከዘንድሮው 3.6 በመቶ ወደ 3.7 በመቶ ከፍ በማለት አንፃራዊ ዕድገት ያሳያል ቢልም፣ ነገር ግን የቀጣናው አገሮች ኢኮኖሚያዊ ችግር ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ እንደሚሆን ነው የተነበየው፡፡ ለዚህ ችግር አባባሽ ከተባሉ ምክንያቶች ደግሞ የዕዳ ጫና አንዱና አሳሳቢው መሆኑን ድርጅቱ ይናገራል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ. 2021 ወደ 6.3 በመቶ ማደጉን የሚናገረው የአይኤምኤፍ ትንበያ፣ በ2022 ግን በግማሽ አሽቆልቁሎ 3.8 በመቶ እንደሚሆን ያመለክታል፡፡ ዕድገቱ ግን በቀጣይ ዓመታት እየተሻሻለ እንደሚሄድ ያመለከተው ድርጅቱ፣ በ2023 አገሪቱ በ5.3 በመቶ ታድጋለች ይላል፡፡ ድርጅቱ በቅርብ ጊዜ ትንበያው የዓለም ኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ይታይበታል ያለ ሲሆን፣ የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ እንዲሁም የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ሁኔታውን እንዳባባሱት ነው የገለጸው፡፡

የአይኤምኤፍ ኃላፊ ክሪስታሊና ጊዮርጊቫ ግን በቅርቡ ባደረጉት ንግግር፣ ከዩክሬንና ከሩሲያ ጦርነት መጀመር ወዲህ ብቻ ለ16 አገሮች 90 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር አቅርበናል ይላሉ፡፡ ኃላፊዋ አክለውም የ28 አገሮችን የብድር ጥያቄ እየመረመርን ነው ብለው፣ ድርጅታቸው በብድር ማቅረብ የሚችለው 700 ቢሊዮን ዶላር እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡ ኃላፊዋ በዚሁ ጊዜ ነበር እንደ ግብፅና ቱኒዝያ ያሉ አገሮች የብድር ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋቸውን የተናገሩት፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የአይኤምኤፍ ሰዎች ለመስማማት ዝግጁ ይሆናሉ ወይ? የሚለው ደግሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በተስፋ የሚጠበቅ ጉዳይ ይመስላል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአይኤምኤፍ ጋር እየተነጋገረ ነው የሚሉት አብዱልመናን (ዶ/ር)፣ መንግሥት የኢኮኖሚ ሪፎርሙን በማፋጠን ከአይኤምኤፍ ድጋፍ ለማግኘት ድርድር በማድረግ ላይ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹የውጭ ምንዛሪ ግብይቱን ከጥቁር ገበያው ጋር ለማጣጣም ጥረት አድርጓል፡፡ የብር ዶላር የመግዛት አቅምን ከማውረድ በተጨማሪ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፍቀዱን፣ የቴሌኮም ዘርፉን መክፈቱን፣ የስኳር ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዘዋወርንና ሌሎች ሪፎርሞችን አከናውኗል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በተቻለው አቅም ጥረት ቢያደርግም፣ የሄደበት ፍጥነት ግን እነሱ ባስቀመጡት የጊዜ ሰሌዳ ባለመሆኑ ድጋፉን አቋርጠውታል፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡ 

አዲስ ስምምነት እንደገና ለማግኘት የኢትዮጵያ መንግሥት ድርድር ጀምሯል የሚሉት አብዱልመናን ‹‹በእኔ ግምት ግን ይህ ድርድር በሦስት ዓመት ካለቀ ፈጣን  ነው የምለው፡፡ ዳግም እሺ ቢሉን እንኳን እንደበፊቱ ሳይሆን አዲስ ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎችን ሊያስቀምጡ ይችላሉ፡፡ ከተሳካ ግን ገንዘቡን እናገኛለን፡፡ ይህ ደግሞ በቡድን 20 ፍሬምወርክ ውስጥ ያቀረብነውን የብድር ዕዳ ጫና ማቅለል ጥያቄም ለመፍታት ያግዘናል፤›› ብለዋል፡፡

እያደጉ ካሉ አገሮች 25 በመቶ፣ እንዲሁም ከታዳጊ አገሮች 60 በመቶ፣ በዕዳ ሸክም የተነሳ እየተንገዳገዱ መሆኑን በቅርቡ የተናገሩት የአይኤምኤፍ ኃላፊ ክሪስታሊና ጊዮርጊቫ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ (Prevention is Better than Cure) በሚል ብሂል ነበር መፍትሔ ያሉትን ሐሳብ ሲናገሩ የተደመጠው፡፡ ድርጅታቸው ከዚህ ይልቅ የዕዳ ማራዘምን ለደሃ አገሮች እንደ አንድ የማገገሚያ መፍትሔ አድርጎ ይተገብራል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ነገር ግን በብዙ መንገዶች ይህን ለማድረግ ዳተኛ ሲሆን መታየቱ ይተቻል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ማሳያ እንደሆነች ነው ብዙዎች የሚጠቁሙት፡፡ 

ቻይናም ሆነች ፈረንሣይና ሌሎቹ አበዳሪዎች በቀላሉ ምላሽ ሰጥተው አይኤምኤፍ ጋ ሲደርስ ኢትዮጵያ ችግር የገጠማት በሁለት ማነቆዎች የተነሳ እንደሆነ፣ የፋይናንስ ባለሙያው አብዱልመናን (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ ‹‹አንዱ የብድር ዕዳ ማስተካከያ ጥያቄያችንን እንዲመልሱልን እንፈልጋለን፡፡ ሌላው ደግሞ በኢኮኖሚ ማሻሻያ ስም የሚሰጡን ድጋፍ ጥያቄም አለን፡፡ አይኤምኤፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን በሚፈለገው ፍጥነት ስላላስኬዳችሁ ብሎ ድጋፉን ከልክሎናል፡፡ ይህ ደግሞ የዕዳ ማራዘም ጥያቄያችን ላይ ተንከባሎ የመጣ ችግር ሆኖብናል፤›› ሲሉ ነው የችግሩን ውስብስብነት የሚያስረዱት፡፡ 

ቻይና እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የአፍሪካ አገሮች ወሳኝ አበዳሪ ናት፡፡ ቻይና ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለእነ አሜሪካና አውሮፓ አገሮችም ዋናዋ አበዳሪ ናት፡፡ አገሪቱ ለመላው ዓለም 1.5 ትሪሊዮን ዶላር ብድር አቅርባለች ነው የሚባለው፡፡ ከሰሃራ በታች ላሉ አገሮች ደግሞ ቻይና 305 ቢሊዮን ዶላር አበድራለች፡፡ አንጎላ 25 ቢሊዮን ዶላር፣ ኢትዮጵያ 13 ቢሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ዛምቢያ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ከቻይና በመበደር ቀዳሚዎቹ ናቸው ይባላል፡፡

በነሐሴ አጋማሽ ላይ እንደተሰማው ከሆነ ደግሞ ቻይና ለ17 የአፍሪካ አገሮች የዕዳ ምሕረት ልታደርግ መዘጋጀቷ ተነግሯል፡፡ አገሪቱ ለእነዚህ 17 አገሮች የሰጠቻቸውን ወለድ አልባ ብድሮቿን ለመሰረዝ ተዘጋጅታለች ነው የተባለው፡፡ የእነዚህ አገሮች  ማንነት እስካሁንም አልተነገረም፡፡ ኢትዮጵያ የዕድሉ ተጠቃሚ ትሁን አትሁንም የተባለ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ቻይና የዕዳ ጫና የበዛባቸው የአፍሪካ አገሮችን በመለየት የዕዳ ምሕረቱን ታደርጋለች ነው ሲባል የቆየው፡፡

የኢትዮጵያ የዕዳ ሸክም 57 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ይነገራል፡፡ የአገሪቱ ዕዳ ከጥቅል ኢኮኖሚ ገቢዋ (ጂዲፒ) ጋር ሲነፃፀር ከ50 በመቶ እንደማይበልጥ ይነገራል፡፡ አገሪቱ የውጭ ዕዳ ጫናዋ ከ27 ቢሊዮን ዶላር ያልተሻገረ መሆኑም ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብድር ጫና ከጎረቤት አገሮች ጋር ሲነፃፀርም የሚጋነን አለመሆኑን ነው ብዙዎች የሚጠቅሱት፡፡ ሩዋንዳ ከጂዲፒዋ በተነፃፃሪ 78 በመቶ ዕዳ እንደተሸከመች መረጃዎች ይጠቅሳሉ፡፡ አገሪቱ በዚህ የተነሳ 14 በመቶ የወጪ ንግድ ገቢዋን ለዕዳ መክፈያነት ታውላለችም ይባላል፡፡ የኬንያ ብድር 71 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ የሚነገር ሲሆን፣ ይህም የጂዲፒዋን 68 በመቶ ነው ይባላል፡፡ ከዚህ በመነሳት ኢትዮጵያ ያለባት ዕዳ ብዙም መጋነን እንደማይኖርበት የሚናገሩ አሉ፡፡ ኢትዮጵያ የብድር መክፈል ችግር የለባትም የሚል መረጃም ይቀርባል፡፡  

ይህን የሚቃወሙት አብዱልመናን (ዶ/ር) ግን የማክሮ ኢኮኖሚ ዳታ ብዙ ጊዜ አደናጋሪ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ብድር ከጂዲፒው አንፃር 50 ወይም 55 በመቶ ነው ሲባል ቀላል አኃዝ ይመስላል፡፡ የመክፈያ ጊዜው የማይታወቀውና የብሔራዊ ባንክ ዕዳ የሚባለው የአገር ውስጥ ብድር ራሱ ከዚህ ውስጥ ግማሹን የሚሸፍንና ብዙም የማያሳስብ ነው ይባላል፡፡ በዚህ መንገድ ከታየ የኢትዮጵያ ዕዳ ቀላል ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ ከጂዲፒያቸው እጥፍ የሆነ ዕዳ ኖሮባቸው ችግር ውስጥ የሌሉ አገሮች በመኖራቸው የኢትዮጵያን ቀላል ነው ሊባል ይችላል፡፡ ችግሩ ግን የውጭ ዕዳ የሚከፈለው በዶላር ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ከሌለህ የጂዲፒህን አሥር በመቶም ቢሆን ዕዳውን ለመክፈል ከባድ ነው የሚሆንብህ፡፡ አንድ መለኪያ ብቻ ወስደህ የዕዳ ጫናው ቀላል ነው ወይም ዕዳ አከፋፈል ላይ ቁመናችን ጠንካራ ነው ማለት አትችልም፤›› በማለት ነው ባለሙያው የሚሞግቱት፡፡ 

እ.ኤ.አ. 2020 ሚያዝያ መጀመርያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሰብሳቢነት በመረጃ መረብ የተሰባሰቡት የአፍሪካ አገሮች የገንዘብ ሚኒስትሮች፣ ለመጀመርያ ጊዜ የዕዳ ማራዘም ጥያቄን ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሮቹ የዓለም ገንዘብ ድርጅትን፣ የዓለም ባንክንና የአውሮፓ ኅብረትን በማግባባት አገሮቻቸው የተሸከሙትን የዕዳ ጫና ለተወሰነ ጊዜ አበዳሪዎች እንዲያራዝሙላቸው ጥረት አድርገው ነበር፡፡

በወቅቱ በአፍሪካ 5,300 ሰዎችን ይዞ ወደ 170 ሰዎችን የገደለው የኮሮና ወረርሽኝ ድንጋጤ ፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ ወረርሽኙ በአኅጉሩ ሊያስከትል የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ድቀት ታሳቢ በማድረግ ነበር የአፍሪካ አገሮች ባለሥልጣናት የዓለም አበዳሪዎችን ቢያንስ ዕዳቸውን የሚከፍሉበትን የጊዜ ገደብ በማራዘም እንዲያግዟቸው የጠየቁት፡፡ ይህ የአፍሪካ አገሮች ጥያቄ በወቅቱ በጎ ምላሽ ያገኛል ተብሎ ቢገመትም፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች የተጠበቀውን ምላሽ አግኝተዋል ብሎ ለመናገር ዛሬ ላይ ከባድ ሆኖ ነው የሚገኘው፡፡ የዚህ ዋና ምክንያት ደግሞ በእነ አሜሪካና በምዕራባውያን የሚደረገው ጫና እንደሆነ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡

ይህን የሚደግፍ አስተያየት የሚሰጡት አብዱልመናን (ዶ/ር) ‹‹አይኤምኤፍ እኮ በአገሮች ሼር የተያዘ ነው፡፡ ድርጅቱ ውስጥ ደግሞ የእነ አሜሪካ ሼር ትልቅ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ የአሜሪካንን የውጭ ግንኙነት ፍላጎት አያስፈጽሙም ማለት አይቻልም፡፡ ሙሉ ለሙሉ የኢኮኖሚ ተቋም ብቻ እስካልሆኑ ድረስ ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገቡ ማሰቡ የዋህነት ነው፡፡ የፖለቲካ ተቋምም ናቸው፤›› ይላሉ፡፡  

እንደ አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ አበዳሪዎችና የፋይናንስ ምንጮች የፖለቲካ ተፅዕኖ የማይደረግባቸውና ገለልተኛ ተቋማት ናቸው ቢባሉም፣ በዓለም ላይ የሚታየው እውነታ ግን ይህን መላምት ሲቃረን የታየበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1996 በሩሲያ ምርጫ በተጋጋለበት ወቅት የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረትን መልሰን እንፈጥራለን የሚሉት በጊናዲ ዙካኖቭ የሚመሩት ኮሙኒስቶች ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አግኝተው ነበር፡፡ በዚህ የተደናገጡት የለውጥ ሐዋሪያ ነኝ ይሉ የነበሩትና የምዕራባውያን ሸሪክ የሆኑት ፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሲን ምርጫው ስድስት ወራት በቀረው ወቅት፣ ወደ ወዳጃቸው ቢል ክሊንተን አንዲት የስልክ ጥሪ ማቃጨላቸው ይነገራል፡፡ የልሲን የአይኤምኤፍ ሰዎችን እንዲያግባቡላቸው ክሊንተንን ጠየቁ፡፡ ክሊንተን ለይስሙላ እነዚህን ተቋማት ማግባባት እንደማይችሉ ቢዘገብም፣ ዋል አደር ብሎ የሆነው ግን በተቃራኒው መሆኑን ታሪክ ከትቦ አስቀርቶታል፡፡ ለተጎዳችው ሩሲያ አሥር ቢሊዮን ዶላር ብድር በአይኤምኤፍ በኩል እንዲሰጣት አስደረጉ፡፡ ይህ ክሊንተን ያስፈጸሙት የአይኤምኤፍ ዕርምጃ የሩሲያን የምርጫ ውጤት ለመቀየር ከበቂ በላይ ነበር ይባላል፡፡

እንደ አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ ያሉ የውጭ ፋይናንስ ምንጮች የምዕራባውያን ዋና የፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሣሪያዎች መሆናቸውን፣ ከዚያም በፊትም ሆነ በኋላ ዓለም ደጋግሞ አይቶታል፡፡ የእነሱን አስገዳጅ ፖሊሲና ጫና ከመቀበል ድጋፋቸው ቢቀር እንደሚሻል በምሬት የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡ አንዳንዶች የእነዚህ ተቋማት ድጋፍ ቢመጣም ሆነ ቢቀር ለደሃ አገሮች ትርጉም ያለው ለውጥ እንደማያመጣ ሲናገሩም ይሰማል፡፡

ለአብነት ኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታና ብድር ታገኝ ነበር የሚሉት እነዚህ ወገኖች፣ ነገር ግን ይህም ሆኖ የምንዛሪ እጥረት ችግሩ ከፍተኛ ነበር ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ በ27 ዓመታት ሲደማመር ወደ 94 ቢሊዮን ዶላር ምንዛሪ ከዕርዳታና ከብድር ማግኘቷን የሚጠቅሱት እነዚህ ወገኖች፣ ይህንን ሁሉ ዶላር ባገኘች አገር የምንዛሪ አቅርቦት ችግር እንዴት ሊከሰት ይችላል ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ክርክሮች ቢኖሩም፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ወደ ዋሽንግተን የሚመላለሱትና የዓለም አቀፍ አበዳሪዎችን ደጅ የሚጠኑት ከውጭ በዕርዳታና በብድር የሚመጣው ገንዘብ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ ነው የሚለው ብዙዎችን የሚያግባባ ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አይኤምኤፍ ያሉ የፋይናንስ ምንጮችን እንደምትፈልገው ሁሉ፣ እነሱም ኢትዮጵያን እንዲሚፈልጉ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ይህን የሚደግፍ አስተያየት የሚሰጡት የፋይናንስ ባለሙያው አብዱልመናን (ዶ/ር)፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የሆነ ቦታ ላይ መስማማታቸው አይቀርም ይላሉ፡፡ ‹‹የፖለቲካ ችግሩ መፈታቱ ነገሮችን ለኢትዮጵያ ያፈጥናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚችለውን ያክል የኢኮኖሚ ሪፎርም እያደረገ እንደሆነ አንዳንድ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ መንግሥት በሚፈልገው ፍጥነት ላይሆን ይችላል፡፡ በስድስት ወራትም ሆነ በአጭር ጊዜ ላይሆን ይችላል፡፡ የሆነ ቦታ ላይ ግን የፖለቲካውን ችግር ከተፈታ መመለሳቸው አይቀርም፡፡ ከዚህ ቀደምም እኮ ቢሆን በኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ሳንስማማ ቀርተን ግንኘነታችን ቢሻክርም ተመልሰው መጥተዋል፤›› ሲሉ ኢትዮጵያ ከነዚህ አበዳሪዎች ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ያብራራሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -