በኢትዮጵያ የሚገኙ የሰሚንቶ ፋብሪካዎች በዘንድሮው ሩብ የበጀት ዓመት ወይም ከሐምሌ እስከ መስከረም 2015 ዓ.ም. ድረስ ያመረቱት ሲሚንቶ ከዕቅዳቸው በ47 በመቶ ያነሰ ነው ተባለ።
በአገሪቱ የሚገኙት አሥር ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዘንድሮው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት በተናጥል ለማምረት ያቀዱት የሲሚንቶ ምርት መጠን ድምር መጠን 2.64 ሚሊዮን ቶን ነበር።
ይሁን እንጂ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በተግባር ማምረት የቻሉት የሲሚንቶ ምርት መጠን 1.4 ሚሊዮን ቶን ብቻ እንደሆነ ሪፖርተር ከማዕድን ሚኒስቴር ምንጮቹ ያገኘው የሰነድ መረጃ ያመለክታል።
ፋብሪካዎቹ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት በተናጥል ለማምረት ያቀዱትና በተግባር ያመረቱት የሲሚንቶ መጠን የተለያየ ቢሆንም ፋብሪካዎቹ በአጠቃላይ በተግባር ያመረቱት የሲሚንቶ ምርት ከድምር ዕቅዳቸው አንፃር የ47 በመቶ ጉድለት እንዳለው ከሰነዱ ለመረዳት ተችሏል።
ሰነዱ በአገሪቱ የሚገኙትን አሥር ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በማምረት አቅም ደረጃቸው ከፍተኛ ደረጃ አምራቾችና ሁለተኛ ደረጃ አምራቾች በማለት ለሁለት ይከፍላቸዋል። ከፍተኛ ደረጃ አምራቾች ምድብ ውስጥ አምስት ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የተቀመጡ ሲሆን፣ እነዚህም ዳንጎቴ፣ ብሔራዊ፣ ሙገር፣ ሐበሻና ደርባ የተባሉት ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ናቸው። እነዚህ ፋብሪካዎች በተጠቀሱት ሦስት ወራት በተናጥል ለማምረት ያቀዱት የሲሚንቶ ምርት መጠን ድምር 1.65 ሚሊዮን ቶን ሲሆን፣ በተግባር ማምረት የቻሉት ግን 1.16 ሚሊዮን ቶን ወይም የዕቅዳቸውን 70.4 በመቶ እንደሆነ ሰነዱ ይገልጻል።
በሁለተኛ ደረጃ አምራችነት ምድብ ውስጥም በተመሳሳይ አምስት ፋብሪካዎች የሚገኙ ሲሆን እነዚህም፣ ኢስት፣ ኢትዮ፣ ካፒታል፣ ኩዩ እና ፓዮነር የተባሉ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ናቸው። እነዚህም በተጠቀሱት ሦስት ወራት በተናጥል ለማምረት ያቀዱት የሲሚንቶ ምርት መጠን ድምር 994.6 ሺሕ ቶን ሲሆን፣ በተግባር ማምረት የቻሉት ግን 243.6 ሺሕ ቶን ሲሚንቶ ወይም የዕቅዳቸውን 24.5 በመቶ እንደሆነ መረጃው ያመለክታል።
ከፍተኛ ደረጃ አምራቾች ምድብ ውስጥ ከተቀመጡት ሲሚንቶ ፋብሪካዎች መካከል ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በተጠቀሩት ሦስት ወራት ለማምረት ካቀደው በላይ በማምረት አፈጻጸሙን 103 በመቶ ያደረገ ብቸኛው ፋብሪካ ነው።
ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ 623,423 ለማምረት አቅዶ ያመረተው 645, 282 ቶን ሲሆን፣ ከዳንጎቴ በመቀጠል ብሔራዊ ሲሚንቶ የዕቅዱን 71 በመቶ ማምረት ችሏል። ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ የዕቅዱን 37.6 በመቶ ፣ ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ የዕቅዱን 46.9 በመቶ፣ ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ደግሞ የዕቅዱን 54.7 በመቶ እንዳመሩቱ ለመረዳት ተችሏል።
በሁለተኛ ደረጃ አምራችነት ምድብ ከተመደቡት ፋብሪካዎች መካከል ኢስት የተባለው ፋብሪካ የዕቅዱን 101.9 በመቶ ያመረተ ሲሆን የተቀሩት ግን ከዕቅዳቸው ከ38 በመቶ እስከ 12.9 በመቶ ባለው መካከል እንዳመረቱ መረጃው ያመለክታል።
ፋብሪካዎቹ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት ለማምረት ያቀዱትን ሲሚንቶ ለማምረት ያልቻሉባቸው ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች በሰነዱ ላይ የተጠቀሱ ሲሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታና አለመረጋጋት ችግሮች ቀዳሚው ነው። ፋብሪካዎቹ የሲሚንቶ ምርት ግብዓቶችን በወቅቱ ማግኘት አለመቻላቸውና ከአቅም በታች ማምረት ሌሎቹ ምክንያቶች ናቸው።
ከላይ የተጠቀሱት አስር ፋብሪካዎች ለበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት ዕቅዳቸውን ለማሳካት የድንጋይ ከሰልና የማምረቻ ማሽነሪዎች መለዋወጫ ግዥ ያስፈልጋቸው እንደነበር የሚገልጸው ሪፖርቱ ይህንን ግዥ ለመፈጸምም 116.9 ሚሊዮን ዶላር መጠየቃቸውን ጠቁሟል። ከተጠየቀው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው የደንጋይ ከሰል ግዥ የሚውል ሲሆን የተቀረው ደግሞ ለማሽነሪዎች መለዋወጫ ግዥ እንደነሆነ አመልክቷል። ከተጠየቀው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ የተወሰነው መፈቀዱንም ለማወቅ ተችሏል።
የምርት ሥራ ተግባራቸው የሚሆን የድንጋይ ከሰልና ለማስገባትና ለማምረቻ ማሽነሪዎች መለዋወጫ ግዥ በድምሩ 116.9 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የጠየቁ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው ወጪ ለድንጋይ ከሰል ግዥ እንደሆነ መረጃው ያመለክታል።
መንግሥት የሰሚንቶ ምርት ዋጋ ንረትን ለማስተካከል በገበያው ሥርዓት ውስጥ ጣልቃ በመግባት ምርቱ በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች የሚሸጥበትን ዋጋ መተመኑ ይታወቃል። በአዲስ አበባና በተለተለያዩ ከተሞች የሚሸጡበትን ዋጋ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች ከገበያው ያላቸውን ርቅትና የማምረቻ ወጪ መሠረት በማድረግ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ በአዲስ አበባ ላይ የሚሸጥበት ትንሹ ዋጋ ከ510 ብር፣ የመጨረሻው ዋጋ ደግሞ 683 ብር እንዲሆን ወስኗል።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሲሚንቶ ምርት እጥረትና የዋጋ ንረት በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች ተከስቷል። በአዲስ አበባ የሚገኙ ቸርቻሪዎች አንድ ኩንታል ሲሚንቶን የሚሸጡቀት አማካይ ዋጋ 1,800 ብር እንደሆነ ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት ለማወቅ ችሏል። በዚህ ዋጋም ቢሆን ምርቱን በበቂ ሁኔታ ለማግኘት አዳጋች እንደሆነ ለመታዘብ ተችሏል። መንግሥት የሲሚንቶ ገበያ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ዋጋ መተመኑ አምራቾቹን ቅር ያሰኘ ሲሆን፣ አንዳንዶችም ይህንን ምክንያት ከምርት እጥረቱ መከሰት ጋር ያገናኙታል።
የሲሚንቶ ምርትን ለአዲስ አበባ ከተማ እንዲያቀርቡ ከተፈቀደላቸው ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ሲሆን፣ ድርጅቱ ከፋብሪካዎቹ በቂ ምርት እየቀረበለት እንዳልሆነ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ሰለሞን ግርሻ እንደተናገሩት ስለተከሰተው የሲሚንቶ እጥረት ሲገልጹ፣ ‹‹ሆን ተብሎ ሰው ሠራሽ የሲሚንቶ እጥረት የመፍጠርና መንግሥት ገበያውን ማረጋጋት አይችልም የሚል መልዕክት የማስተላለፍ ፍላጎት ይስተዋላል፤›› ብለዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በበኩሉ ዋጋው የተተመነው ፋብሪካዎቹ ራሳቸው ባቀረቡት የወጪ ሁኔታ ላይ ተመሥርቶ አንደሆነ ይጠቅሳል። ፋብሪካዎቹ ከጥቂት ወራት በፊትም ማለተም በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. ይሸጡበት የነበረው ዋጋ 500 ብር እንደሆነ የሚገልጸው ሚኒስቴሩ፣ መንግሥት የተመነው አዲስ ዋጋ ፋብሪካዎቹ ባለፈው በመጋቢት ወር ሲሸጡበት ከነበረው ዋጋ በላይ እንጂ ያነሰ እንዳልሆነ ይገልጻል።