ብርሃን ባንክ በአዲስ አበባ ሠንጋ ተራ አካባቢ ያስገነባልና 40 ወለሎች ያሉት ይሆናል ተብሎ ለሚጠበቀው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠ፡፡
ባንኩ ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በተረከበው 5400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ፣ የሚያስገነባውን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ መሠረት ድንጋይ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ከባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን አስቀምጧል፡፡
በዚህ ዙሪያ አርባ ወለል የሚደርስ ሕንፃ ለመገንባት መታቀዱን የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ በአሁኑ ጊዜ የሕንፃውን የዲዛይንና የግንባታ ሥራ የሚሠራ ኮንትራክተር ለመምረጥ ጨረታው በሒደት ላይ ነው፡፡ የጨረታ ውጤቱም በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ ከጨረታ ውጤት በኋላ በፍጥነት ወደ ግንባታ የሚገባ መሆኑን ነው፡፡
ባንካችን ያጋጠመውን ተግዳሮቶችና አስቸጋሪ ጊዜያት በመቋቋም ወደፊት ለሚያደርገው የዕድገት ሩጫ መሠረት የሆነውን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ለመጀመር የመሠረት ድንጋይ መቀመጡ፣ ለባንኩ ትልቅ አቅም የሚሰጠው መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ግሩም ፀጋዬ ገልጸዋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ሕንፃ መገንባት ከባድና ፈታኝ መሆኑን ብንረዳም ጊዜ በሄደ ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ሊሄድ ስለማይችል ከወዲሁ ያለውን ሁኔታ ተቋሙ መጀመር የተሻለ እንደሚሆን በማመን ግንባታውን በቅርቡ ለመጀመር ማቀዳቸውንም ገልጸዋል፡፡
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጉማቸው ጉሴ በበኩላቸው ባንኩን የሚመጥንና ለከተማው ውበት የሚሆን ሕንፃ የሚገነባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ በመሆን የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ሕንፃው በፍጥነት አልቆ ለአገልግሎት የሚበቃ ስለመሆኑ ያለውን ተስፋ ገልጿል፡፡