Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መንግሥት በተቻለ መጠን የፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ ያለውን እጅ መሰብሰብ አለበት›› ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር)፣ የኢንተርናሽናል ግሮውዝ ሴንተር ካንትሪ ኢኮኖሚስት

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት ይነገራል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባት እንዳለበትም ይታመናል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቱን ለማከም በመንግሥት መወሰድ አለባቸው የተባሉ ዕርምጃዎች ውጤት ያመጣሉ ተብሎ ቢታሰብም፣ የተፈለገውን ያህል ውጤት አላመጡም፡፡ ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች እንቅፋቶች ተደራርበው መምጣታቸው ነው፡፡ እንዲህ ያለውን አመለካከት ከሚጋሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች መካከል ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንና በመፍትሔዎቻቸው ላይ ቴዎድሮስ (ዶ/ር) አሁን አገራዊ የኢኮኖሚ ችግሮች መነሻ ናቸው ያሉዋቸውን የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቅሳሉ፡፡ በወቅታዊ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈን መንግሥት እየወሰዳቸው ባሉት ዕርምጃዎች፣ በተለይ ከውጭ ምንዛሪ ግብይት አንፃር ችግሩ እንዴት መፈታት አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ የተለየ ምልከታ አላቸው፡፡ በአጠቃላይ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አገር የገጠማትን ችግር ለመፍታትና ኢኮኖሚውን ወደ ጤናማ ጎዳና ለማስገባት ግን ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ ለፖለቲካ ችግሮች መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ ኢኮኖሚውን ለማሳካት ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ማናቸውንም ዓይነት ችግሮች መፍታት ቀዳሚው ጉዳይ መሆን እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ቴዎድሮስ (ዶ/ር) በኢኮኖሚክስ ሪሰርች ከሌስተር ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፣ በሙያው ከ18 ዓመታት በላይ ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢንተርናሽናል ግሮውዝ ሴንተር ካንትሪ ኢኮኖሚስት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙዎች ማኅበር አባልና ማኅበሩ የሚታተመው የኢትዮጵያን ጆርናል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ዋና አዘጋጅ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አማካሪ በመሆን የሠሩ ሲሆን፣ በተለያዩ ተቋማት ውስጥም በአማካሪነትና በተመራማሪነት አገልግለዋል፡፡ ወቅታዊው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት መንስዔ ምንድነው? የሚለውን የመንደርደሪያ ጥያቄ በማቅረብ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ ከቴዎድሮስ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ኢኮኖሚያዊ ችግር ከማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ጋር የተያያዘ መሆኑ ይታመናል፡፡ ይህ ችግር ስለመኖሩ መንግሥት ከሚሰጣቸው የተለያዩ መረጃዎችም መገንዘብ ይቻላል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ መባባስ መንስዔው ምንድነው ይላሉ?

አቶ ቴዎድሮስ፡- ከሁለትና ከሦስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዛባት አጋጥሞታል ተብሎ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ይህንን መዛባት ለማስተካከል መንግሥት አገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ አውጆ ሲንቀሳቀስ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ በእኔ እምነት እዚያ ላይ የተቀመጡ ማሻሻያዎች በሚገባ የተዛባውን ማክሮ ኢኮኖሚ ያስተካክላሉ ብዬ የምጠብቃቸው ውጥኖች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ከሚዛን ያፈነገጠውን ነገር ወደ ሚዛን እንዲመለስ ማድረግ ይገባል፡፡ ሪፎርሙ ከሚሄድበት ሞገድ በተቃራኒው ወደ ቦታው ሊመልሰው ይችላል ተብሎ የሚታሰብ ውጥን ነው፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው እንቅስቃሴ መንግሥት በሚመራው ኢኮኖሚው ውስጥ ብዙ ችግሮች ይታዩ ነበር፡፡ በተለይም በኮንስትራክሽን በመሠረተ ልማት ላይ የሚያደርገው ኢንቨስትመንት ጥሩና ለዕድገት የሚበረታታ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የፋይናንስ ምንጭ ቀጣይነትን የሚያረጋግጥ አለመሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ለምሳሌ ከ60 በመቶ በተለይ የሚሰበሰበውን ተቀማጭ ገንዘብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 85 በመቶውን ለመንግሥት ይሰጥ የነበረ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ስለዚህ በአገር ደረጃ የሚሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ለመንግሥት የሚሄድ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት አብዛኛውን የፋይናንስ ሀብት መንግሥት ወስዶት ለመሠረተ ልማቶች የሚያውለው ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለባቡር፣ ለስኳርና ለመሳሰሉት ፕሮጀክቶች ይህንን ገንዘብ ይረጭ ነበር፡፡ መንግሥት እነዚህን የልማት ሥራዎች ማከናወን ቢችልም ብክነትና ሙስና አለበት፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ሀብት ይባክናል፡፡ ይህ የሚባክን ሀብት እንዲስተካከል ወይም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማግኘት አለበት፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ይህ ሁሉ ሀብት ከሲስተሙ ወጥቶ ወደ መንግሥት ሲሄድ የግሉ ዘርፍ በፋይናንስ ይራባል ማለት ነው፡፡ እኔ በ2004 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ባንክ ውስጥ በምሠራበት ወቅት ባንኮች እርስ በርሳቸው የውጭ ምንዛሪ ይገበያዩ ነበር፡፡ ያኔ የውጭ ምንዛሪ እንደ ልባችን ነበር ባይባልም የተወሰነ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን መንግሥት ኢንቨስት የሚያደርግባቸው ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ያለባቸው ስለነበሩ፣ የውጭ ምንዛሪውም ወደ እዚያ እየዞረ መጣ፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የብረት፣ የማሽንና ሌሎች የገቢ ዕቃዎች የሚፈልጉ ስለነበር ነው፡፡ መንግሥት የውጭ ምንዛሪውን ይወስዳል፡፡ እነዚህ ነገሮች ተደማምረው የፋይናንስ ሀብት በጣም ወደ መንግሥት እንዲያተኩር አድርጎ የነበረ የዕድገት አካሄድ እንደነበረው ያሳያል፡፡ ይህንን ለማስተካከል የረዥም ጊዜ ፋይናንስ ሊያገኝ የሚቻልባቸውን መንገዶች መዘርጋት አለባቸው ተብሎ በሪፎርሙ የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦች ተቀመጡ፡፡ የካፒታል ገበያ እንቅስቃሴ እንዲጀመር የተደረገው ለዚህ ነው፡፡ የዋጋ ንረትን በጣም ያባብሳል ተብሎ የሚጠብቀውንና መንግሥት ቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደውን ብድር ይቀንስ የሚለውም በሪፎርሙ ውስጥ ተቀምጧል፡፡ መንግሥት ራሱ የሚያወጣውን ወጪ ደግሞ በሚገባ እንዲመረምር ወጪውን መቀነስ እንደሚኖርበት ሁሉ ታምኖ ይህም ተካተተ፡፡ በጥቅሉ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ የተጠቀሱት የሪፎርም ሥራዎች ውጤት አምጥተዋል ማለት ይቻላል? በትክክልስ ተተግብረዋል? አሁንም የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባት እንዳለ ነው፣ ለምን?

(ዶ/ር) ቴዎድሮስ፡- የአንዳንዶቹ ውጤት ታይቷል፡፡ ለምሳሌ የግምጃ ቤት ሰነድን የጡረታ ድርጅቶች ገንዘብ ስላላቸው ተገደው ይግዙ ይባል ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ገበያ ስለተለወጠ ከፍ ባለ ዋጋ ባንኮችም ይሳተፉበታል፡፡ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብር ከሚያትም ይልቅ ከግምጃ ቤት እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ ባለፉት ዓመታት መንግሥት ያገኘው ወደ 200 ቢሊዮን ብር ከዚህ ከግምጃ ቤት ጨረታ የተገኘ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ ከሕዝብ መበደር ተቻለ ማለት ነው፡፡ ብር አትሞ የዋጋ ንረትን ከማባስ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ እንዲህ ያሉ የሚበረታቱ ነገሮች ተጀምረው ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይርቅ ነገሮች ተለዋወጡ፡፡ ረፎርሙ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 2019 ከተጀመረ ዓመት ሳይሞላው መጋቢት እ.ኤ.አ. 2020 ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከሰተ፡፡ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ብዙ የሪፎርሙ ሥራዎች እንዲዘገዩ አደረገ፡፡ ለምሳሌ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን ገንዘብ እንዲቀጥል መደረጉ አንዱ ነው፡፡ ከውጭ የሚመጣው ገቢ እንደሚቀንስ ስለተገመተ ወደ እዚህ ዕርምጃ መልሶ እንዲገባ ሆነ፡፡ ይህም በሪፎርሙ የተጀማመሩ ሥራዎች ላይ ጫና አሳደረ፡፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ሰንሰለቱ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ አገሮች ሲጎዱ፣ ኢትዮጵያውያን ከውጭ ይልኩ የነበረውን ገንዘብ ቀነሰው፡፡ የተወሰኑ የወጪ ንግድ ምርቶችን ላይ ቅናሽ ታየ፡፡ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቡናና የመሳሰሉት ምርቶች ቀንሰው ነበር፡፡ በዋናነት ግን በጉዞና በቱሪዝም ላይ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ትልቅ ጉዳት አድርሷል፡፡ በወቅቱ የጉዞና ቱሪዝም 77 በመቶ ነው የቀነሰው፡፡ ይህ ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ ሪፎርሙ በታሰበው ደረጃ እንዳይሄድ እንዲህ ያሉ ተፅዕኖዎች ስላጋጠሙት የተፈለገውን ማድረግ አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ሪፎርሙ አተገባበር ላይ የራሱ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዓመታት በፊት በውጭ ብድር ጭምር የተገነቡ አሁን እንደጠቀሱልኝ ያሉ መሠረተ ልማቶች ያስከተሉት ችግር፣ አሁን ላለው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት እንደሆኑ ይጠቀሳልና እርስዎ በዚህ ላይ ያለዎት ምልከታ ምንድነው?

(ዶ/ር) ቴዎድሮስ፡- ቀደም ብዬ የጠቀስኩልህ መንግሥት ዕሳቤው የነበረው፣ ለምሳሌ የስኳር ፋብሪካዎቹ ተገንብተው ማምረት ቢጀምሩ ኢትዮጵያ ከምትፈልገው በላይ ስኳር ወደ ውጭ በመላክ ገቢ ይገኛል የሚል ነው፡፡ ራሳቸው ስኳር ፋብሪካዎቹ ዕዳቸውን ይከፍላሉ የሚል እምነት ነበር፡፡ የኃይል ማመንጫዎችም እንዲሁ ተገንብተው ኃይል ለውጭ ተሸጦ ገቢ ይገኛል በሚል ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን የሚያመርቱ ኩባንያዎች የሚገቡበት ይሆናል ተብሎ የተገነቡ ናቸው፡፡ በተግባር ግን አልሆነም፡፡ መንግሥት ውጤት አልባ ነው፡፡ ሥራውን በተሳለጠ መንገድ ስለማይሠራ ብዙ ይመዘበራል፡፡ ብዙ የሚጠፋ ነገር አለ፡፡ ይህ የታወቀ ነው፡፡ ሙስና በጣም አለ፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክቶቹ በታቀደላቸው ጊዜ እንዳያልቁ ተደርጓል፡፡ በተያዘላቸው ጊዜ እንዳያልቁ ብቻ ሳይሆን፣ በተያዘላቸው የጥራት ደረጃ ተገንብተው ማለቅ አልቻሉም፡፡ ይህ በሚሆንት ጊዜ ደግሞ የታሰበውን ዓይነት ምርት አምርተው ወደ ውጭ ልከው ማግኘት የሚገባቸውን ገቢ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ሲባልና በወቅቱም ኢኮኖሚስቶች ሲተቹት የነበረ ነገር ነው፡፡ መንግሥት አቅም የለውም፡፡ ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ስለዚህ እነዚህ ፕሮጀክቶች ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያሉ ውስብሰብ ችግሮች የነበሩባቸው ፕሮጀክቶች ብዙ ዋጋ በማስከፈላቸው፣ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ጋር ተያይዘው ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የተወሰዱት ዕርምጃዎች ምን ውጤት አስገኝተዋል ብለው ያምናሉ? እንደ አገር አሁን ያለውን አገራዊ የኢኮኖሚ ችግር ለመፍታትስ ቅድሚያ ተሰጥቶት መሠራት ያለበት ምንድነው ይላሉ?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- ሪፎርሙ ላይ ተቀምጧል፡፡ ለምሳሌ ሌላ ፕሮጀክት ላለመጀመር የሚለው አንዱ ነው፡፡ ያሉትን ለመጨረስ የተወሰደው ውሳኔ ጥሩ ነበር፡፡ የህዳሴ ግድብ ከተያዘለት ጊዜ በምን ያህል እንደዘገየና ምን ያህል የባከነ ገንዘብ እንዳለ ተለይቶ ለመጨረስ የተደረገው ጥረት በግሌ ጥሩ ዕርምጃ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህንን ፕሮጀክት ማስቀጠል ቀላል ነገር አልተደረገም፡፡ አሁንም ከታሰበበት ጊዜ በላይ ዘግይቷል፡፡ ግን ጥሩ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ሙስና ጠፍቷል፣ ምዝበራ የለም፣ ምንም ችግር የለም እያልኩ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ለማክሮ ኢኮኖሚው መዛባትና ኢኮኖሚው የበለጠ ችግር ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ውስጥ የሰሜኑ ጦርነት ይጠቀሳል፡፡

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- አዎ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከስድስት ወራት በኋላ የሰሜኑ ጦርነት ተነሳ፡፡ የጦርነቱ መነሳት የምናገኘውን ብድርና ዕርዳታ በጣም ቀነሰው፡፡ ስለዚህ ከኮቪድ ሳናገግም ጦርነቱ መጣ፡፡ ይህም በተለይ የውጭ ክፍያ ሚዛናችንን መታው፡፡ እንደገና ደግሞ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት መጣና የዓለም አቀፍ ዋጋን አስወደደ፣ ገቢም ቀነሰ፣ ዋጋውም ተወድደብን፣ እንደ አገር ሲታይ እንዲህ ያሉ ችግሮች ተደራርበው ችግሩን አባብሰውታል፡፡ መንግሥት የጀመረውን የሪፎርም ሥራ እንዳይቀጥል ማነቆ እንዲሆንበት አድርገዋል፡፡ ለምሳሌ በሪፎርሙ መነሻነት የውጭ ምንዛሪ ተመኑ እየጨመረ እንዲሄድ ተደርጎ ነበር፡፡ የውጭ ምንዛሪ ዋጋው በፍጥነት እየጨመረ መሄዱ እኔ ተገቢ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ በእርግጥ ብዙ ኢኮኖሚስቶች ይህንን ሐሳብ አይስማሙበትም፡፡ እኔ ግን ተገቢ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመኑ እንዲፈጥን መደረጉን ያምኑበታል ማለት ነው? ለምን?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- አዎ መፍጠኑ ተገቢ ነበር፡፡ የውጭ ምንዛሪ ገበያውን ከማረጋጋትና ወደ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ለመሄድ ታቅዶ ስለነበረ፣ በባንኮች በኩል የምንዛሪ ዋጋ ከፍ እያለ እንዲመጣ ተደርጓል፡፡ ይህንን ዕቅድ ለማሳካት ከፍተኛ የሆነ ጥረት ተደርጓል፡፡ ምክንያቱም የውጭ ምንዛሪ ዋጋን መገደብ የውጭ ምንዛሪ የሚያመጡ ሰዎችን የሚቀጣ፣ የውጭ ምንዛሪ የሚወስዱትን ሰዎች የሚጠቅም ሥርዓት በመሆኑ አልደግፈውም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ያላግባብ ገድቦ መያዝ አግባብ አይደለም፡፡ ዋጋን ገድቦ መያዝ አንደኛ ወደ ውጭ የሚልኩ ሰዎችን መቅጣት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እነሱ ዋጋውን ወደ ገበሬው ነው የሚያስተላለፉት፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እየሰጡ ያሉትን ገበሬዎች እየቀጣን ነው ማለት ነው፡፡ 50 ወይም 80 ብር የሚያወጣ ነገር በ20 ብር ለመንግሥት ስንሸጥ ወይም ለብልጥ ነጋዴ ስንሸጥ፣ ተጠቃሚ የሚሆነው መንግሥትና ብልጥ ነጋዴ ነው፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ከፍ እያለ መምጣት አለበት፡፡ ወደ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ግብይት መግባት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በፍጥነት እያደገ መሄዱ ግን ለዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት አይሆንም? አሁንም እኮ የዋጋ ንረቱን ያባባሰው ይህ እየተለወጠ የመጣው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ነው፡፡

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- አዎ ከፍ እያለ መምጣቱ የዋጋ ንረት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ የኢኮኖሚ ውጤት ነው፡፡ እኛ አምርተን ለዓለም የምናቀርበው እያነሰ በመጣ ቁጥር፣ ከእነሱ የምንፈልገው እየበዛ ሲመጣ ከውጭ የምናመጣው ነገር እየተወደደ መምጣቱ ግልጽ ነው፡፡ አሁን እኛ ማድረግ ያለብን ምርታማነታችንን የሚያበረታታ ነገር መፍጠር ነው፡፡ ለዚህም አንዱ ኤክስፖርተሮችን ማበረታታት ነው ያለብን፡፡ አንድ ጥሩ ምሳሌ ልንገርህ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2019 በፊት ከወርቅ የወጪ ንግድ በዓመት 30 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነበር የሚገኘው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወርቁን ዋጋ ከጥቁር ገበያ ጋር አቀራርቦ ከዕለታዊ ከዓለም የወርቅ ዋጋ በላይ ከፍሎ መቀበል ሲጀምር፣ በኮንትሮባንድ ይወጣ የነበረ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መጣ፡፡ ይህም በመሆኑ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጣም በጠነከረበት ወቅት እንኳን አንዳንድ ወሮች ላይ ከቡና የበለጠ የውጭ ምንዛሪ ያስገኝ የነበረው ወርቅ ነበር፡፡ በወቅቱ ተጎድቶ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ገበያችንን የታደገ ነው፡፡ ከዚያ በዓመት 600 ሚሊዮን ዶላር ከወርቅ የወጪ ንግድ ተገኘ፡፡ ይህ የሚያሳየን ዋጋውን አሳንሰን ብንይዘው ወደ ኮንትሮባንድ ያላግባብ የሚወጣው የአገር ሀብት ይበዛል እንጂ፣ የተለየ የምንጠቀመው ነገር ያለመኖሩን ነው፡፡ ዋጋን አለመገደቡ የዋጋ ንረት ያመጣል፡፡ የዋጋ ንረት አለ፡፡ በነገራችን ላይ እኛ አገር በዋናነት የዋጋ ንረትን የሚያሽከረክረው የምግብ ዋጋ እንጂ፣ ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች አይደሉም፡፡ ዳታውን ስንመለከት ሁሌ በዋናነት ለዋጋ ንረቱ መንስዔ የሚሆነው የምግብ ዋጋ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዋጋ ንረት መንስዔዎች ጋር በተያያዘ በብዙዎች የሚታመንበት የብር አቅም እየተዳከመ መምጣት ነው፡፡ ትልቁን ቦታ የሚይዘውም እሱ ነው የሚል መከራከሪያ ይቀርባል እኮ?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- አስተዋጽኦ አለው እንጂ ትልቁን ቦታ የሚይዘው የምግብ ዋጋ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የብር አቅም እየተዳከመ መሄድና ኤክስፖርቱን ለማገዝ እየተባለ ሲወሰድ የነበረው ዕርምጃ ከጥቅሙ ጉደቱ ማመዘኑ ይገለጻል፡፡ መንግሥት ብርን እያዳከመ መሄዱ ተፅዕኖ አላሳደረም?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- አዎ ተፅዕኖ አለው፡፡ ግን ምርጫ የለንም፡፡ ትክክለኛ ኢኮኖሚ እንዲኖር ከተፈለገ ግን ምርጫ ያለው ነገር አይደለም፡፡ እንዲሁ ዋጋውን አሳንሰን ልንይዘው አንችልም፣ ተገቢም አይደለም፡፡ የፍትሕ ጥያቄ አለው፡፡ ገበሬው መንግሥትንና ብልጥ ነጋዴውን እንዲደጉም እያደረግን ነው፡፡ ዋጋውን 20 ብር አድርገን ይዘነው ኤክስፖርተሩ በ50 ብር ማግኘት ሲገባው በ20 ብር እያገኘ፣ መንግሥት ደግሞ 50 ብር መክፈል ሲገባው 20 ብር እየከፈለ መሄዱ በምንም ሁኔታ መደገፍ የለበትም፡፡ ይህ ማለት ገበሬው መንግሥትና ብልጣ ብልጥ ነጋዴን እየደጎመ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ በጣም የምንፈልገው ዶላር ሆኖ ሳለ፣ ዶላር የሚያመጡልንን ሰዎች መቅጣት ተገቢ አይሆንም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ሰዎች የምንዛሪ ተመኑን ብንጨምረውም ኤክስፖርቱን አያበረታታልንም ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ችግራችን ምርታማነት ነውና የውጭ ምንዛሪ ዋጋውን ከፍ ብናደርገው የወጪ ንግዱ አይበረታታም የሚል እምነት አላቸው፡፡ እኔ ደግሞ የምለው የማምረት ችግር አለብን፣ ግን ከማምረት ችግር በተጨማሪ የኮንትሮባንድም ችግር አለብን፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ዋጋውን ከፍ ብናደርገው ቢያንስ ኮንትሮባንዱን ያስቀርልናል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የገጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ፣ እንዲሁም ሕገወጥነትን ለመከላከል ያግዙኛል ብሎ ከወሰናቸው ውሳኔዎች መካከል በፍራንኮ ቫሉታ እንደ ዘይት ያሉ ምርቶች ከውጭ እንዲገቡ መፍቀዱ ነው፡፡ ይህ የዋጋ ንረቱን አላባሰም ይላሉ?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- በመሠረቱ እንዲህ ያለው ፖሊሲ ግቡ የት እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ያላቸው ሰዎች ከባንኮች የውጭ ምንዛሪ ሳይጠይቁ በራሳቸው ነው የውጭ ምንዛሪ አግኝተው፣ ዕቃ ገዝተው የሚያስመጡበት መንገድ ነው፡፡ አዎ የዋጋ ንረቱን አባብሷል፡፡ ምክንያቱም በእኔ እምነት በጣም ግራ ከመጋባትና ከመጨነቅ የመጣ ፖሊሲ እንጂ፣ ያን ያህል ውጤት አምጥቶ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ነጋዴ የውጭ ምንዛሪ የሚያገኘው ከጥቁር ገበያ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ የሚያገኘው ከጥቁር ገበያ ነው፡፡ ከጥቁር ገበያ የሚያገኘው ከሆነ ደግሞ ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ የማድረግ መንገድ ነው የሚሆነው ፍራንኮ ቫሉታ፡፡ ምክንያቱም ከጥቁር ገበያ የተገኘን የውጭ ምንዛሪ ዕቃ ለማስመጣት ከተጠቀምክበትና ያንን ደግሞ መንግሥት ከተቀበለህ፣ ዕቃው ሕጋዊ ይሆንና ገንዘቡ ሕገወጥ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ፍራንኮ ቫሉታ የታሰበለትን ግብ የመታ አይመስለኝም፡፡ የፍራንኮ ቫሉታ መፈቀድ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችንና ዕቃዎችን ዋጋ ያረጋጋል ቢባልም ያረጋጋ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ትክክለኛና ተገቢ የሆነ ፖሊሲ ነው ብዬ አላስብም፡፡ አሠራሩም መቀጠል አለበት ብዬ አላምንም፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥቁር ገበያው ውስጥ ያለውን የምንዛሪ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ፍራንኮ ቫሉታ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ምንጩ እስካልተገለጸ ድረስ በፍራንኮ ቫሉታ ዕቃ ማስገባት እንደማይቻል ማስታወቁ አግባብ ነው ማለት ነው?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- አዎ፣ በፍራንኮ ቫሉታ ለምታስመጣው ዕቃ የውጭ ምንዛሪ ምንጩ መታወቅ አለበት፡፡ ሕገወጥ እንዳይሆን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነጋዴዎች ሌላ ምንጭ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ቢኖራቸው ኖሮ ያስታውቁ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት አሁን እየታየ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንፃር ወደ 38 የሚሆኑ ምርቶች ወደ አገር እንዳይገቡና ሌተር ኦፍ ክሬዲት እንዳይከፈትላቸው ወስኗል፡፡ ይህ ውሳኔ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው አንፃር እንዴት ይታያል? አሉታዊ ተፅዕኖዎቹስ? እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች በትክክል የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በመቅረፍ መፍትሔ ያመጣሉ?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- ከፖሊሲ ግፊት አንፃር ብዙ የሚገርም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ድሮም ቢሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚገቡ ዕቃዎችን ቅድሚያ የሚሰጣቸው ብሎ ይወስናል፡፡ ባንኮች ለየትኛው ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸውና ለየትኛው መጀመርያ መፍቀድ እንዳለባቸው፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተዘጋጀና የተላከ ሊስት አላቸው፡፡ በዚህ ሊስት መሠረት መጀመርያ ለማዳበሪያና ለመድኃኒት ቅድሚያ እንዲሰጡ ያስገድዳል፡፡ ከዚያ የአምራቹ ኢንዱስትሪዎች ግብዓትና የመሳሰሉት እንደ አስፈላጊነታቸው ደረጃ ወጥቶላቸው እየተሠራበት ነው፡፡ ይህ ሊስት ግን በደንብ እየተተገበረ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የላቸውም፡፡ የብዙ ሰዎችን ጉሮሮ የሚሸፍኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት አጥተው ተሠልፈው ባሉበት ሁኔታ፣ ብዙ የቤት መኪኖች ይገባሉ፡፡ ሌሎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የማይገቡ ምርቶችንም ገበያ ውስጥ እናያለን፡፡ እነዚህ ነገሮች ኢትዮጵያ ያላትን በጣም ውስን የሆነ ሀብት በአግባቡ እየተጠቀመችበት እንዳልሆነ ያሳያሉ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ፣ ‹‹ይህንን ሁሉ ዕቃ እንዴት አድርገው ነው ያስገቡ ያሉት?›› የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህ በጉምሩክ ፕራይሲንግ ሲስተም ላይ ክፍተት እንዳለበት አንድ ማሳያ ነው፡፡ አንድ ነጋዴ ዕቃ ለማምጣት ኤልሲ ለሚከፍትለት ዕቃ የዋጋውን ያህል ከባንክ መጠየቅ አለበት የሚል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ አለ፡፡ ሰዎች ወደ ጥቁር ገበያ እንዳይሄዱ ለማድረግና በባንክ መሸፈን እንዲችሉ ነው፡፡ ኤልሲ የሚከፈትለት ዕቃ ደግሞ ጉምሩክ በሚያወጣው ዋጋ መሆን አለበት የሚል ሕግም አለ፡፡ ዕቃቸውን ከባንክ ጠይቀው እንዲያስመጡ የሚያስገድድ ሕግ ነው፡፡ ግን የጉምሩክ ዋጋዎች ውስጥ የሌሉ ዕቃዎች ከሆኑ፣ ይህ ሕግ አይሠራም፡፡ በዚህ ክፍተት ብዙ መኪናዎች ይገባሉ፡፡ የጉምሩክ ዳታ ቤዙን ቶሎ ቶሎ ‹‹አፕዴት›› ስለማይደረግ እነዚያ መኪኖች እዚያ ላይ ስለሌሉ በትንሽ ዋጋ ኤልሲ ይከፍትላቸውና ዕቃው እንዲመጣ ይደረጋል፡፡ የቀረው ከየት ነው የሚመጣው? ሲባል ደግሞ የሚሸፍነው ከጥቁር ገበያ ነው፡፡ በዚህ ከፍተት አማካይነት በትንሽ የውጭ ምንዛሪ በባንክ በኩል መጣ ተብሎ ዕቃው ከጥቁር ገበያ በተገኘ የውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ ብዙ የማይፈለጉ ነገሮች ይገባሉ ማለት ነው፡፡ እነዚህም ዕቃዎች እንደምናውቀው ዋጋቸው በጣም ከፍተኛ ሆኖ ለገበያ ይቀርባሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ቢያንስ የጥቁር ገበያውን ፍላጎት ጋብ ለማድረግ እነዚህ ቅድሚያ ሊሰጣቸው አይገባም ተብለው የታሰቡ ዕቃዎች እንዳይገቡ የማድረግ ውሳኔ ተወስኗል፡፡ እንዳይገቡ የተከለከሉ ዕቃዎች ግን ገበያ ውስጥ ዋጋቸው ከፍ ሊል ይችላል፡፡ እነዚህን ዕቃዎች የሚጠቀም የኅብረተሰብ ክፍል ምን ያህል ነው ስንል ግን እጅግ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሁለትና ሦስት ዓመት በባለሙያዎች በተደረገ ጥናት፣ ከአዲስ አበባ ሕዝብ የግል መኪና ያለው ከ15 በመቶ በታች ነው፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ ገቢ አለው የሚባለውን የኅብረተሰብ ክፍል ይህ ውሳኔ ሊጫን ይችላል፡፡ ለአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ግን ትንሽ የውጭ ምንዛሪ ያድንለታል፡፡ ሌሎችም ከ38ቱ ምርቶች ውስጥ የተዘረዘሩትም ቢሆን ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው ተብለው የማይታሰቡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህ ዕርምጃ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- ከብዙ ሰዎች ከተሰባሰቡ መረጃዎች መረዳት እንደተቻለው አንገብጋቢ ያልሆኑና በቀላሉ እዚህ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶችን መርጦ ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን እንዳይገቡ መከልከሉ አግባብ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ያን ያህል አንገብጋቢ ሳይሆኑ ዶላር የሚወጣባቸው ዕቃዎች እነዚህ ብቻ ናቸው ወይ የሚል ጥያቄ የሚያነሱ አሉ፡፡ ይህ ከሆነ ሌሎች ምርቶችስ መካተት የለባቸውም? ከዚሁ ጋር ተያይዞ መከልከል ይገባቸዋል የተባሉ ምርቶችን አጥንቶ የሚያቀርብ ተቋምስ ሊኖር አይገባም?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- በኢትዮጵያ የሚመረቱ ምርቶች ይታወቃሉ፡፡ የተለየ ግብረ ኃይል አያስፈልገውም፣ ትንሽ ዕቃ ነው የምናመርተው፡፡ ሌሎች ዕቃዎች መጨመር አለባቸው የሚለው ነገር ያስማማል፡፡ እንደ ሁኔታው እየታየ መከልከል ሊኖርበት ይችላል፡፡ በእኔ እምነት ግን ከገቡት ውስጥ የደሃውን ኅብረተሰብ ክፍል የሚነካ አለ ወይ? ያልተመጣጠነ የሆነ ጥቅም የሚሰጥ አለ ወይ? የሚለው ነው ዋናው ነገር፡፡ ለእኔ በዚህ ሊስት ውስጥ የለም፡፡  

ሪፖርተር፡- ካለው ወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ ችግርና ጫና አንፃር በተለይ የውጭ ምንዛሪ እጥረትንና ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው የተለያዩ ውሳኔዎችን እያሳለፈ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ውሳኔዎች የት ድረስ ይሄዳሉ? ኢኮኖሚውን ከፍ ለማድረግ ሊወሰዱ የሚችሉ ሌሎች ዕርምጃዎች የሉም?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- በክልከላና በፖሊሲ ነገሮችን ማከናወን አያስኬድም፡፡ ከዚህም በፊት የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ መንግሥት በትይዩ ገበያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሱቆችን ሲዘጋ ዋጋው ትንሽ ይወርዳል፡፡ ከዚያ ትንሽ ቆይቶ ወደ ቦታው ይመለሳል፡፡ መንግሥት አንዳንዴ ቁጥጥር ተኮር ውሳኔ ይወስናል፡፡ ከዚህ ይልቅ ዘላቂ የሆነ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ማምጣት ነው የሚያስፈልገው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ ምን ዓይነት የፖሊሲ ውሳኔዎች?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- ቅድም የገለጽኳቸውን የሪፎርም ሥራዎች መቀጠል ማለት ነው፡፡ በገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ሲስተም የምንሄድበትን መንገድ መከተል ማለት ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ማስፈጸም ከቻለ እጁንም ማስገባት አይጠበቅበትም፡፡ በገበያ ዋጋ መሥራት ነው፡፡ ይህንን ካደረገ የመንግሥት እጅ ይወጣል፡፡ ሁልጊዜ ከእሳት ማጥፋት ሥራ ወጥቶ በገበያ የሚመራ አሠራር ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ውስጥ መሆኗ፣ በተለይም ጦርነት ውስጥ ሆነን ይህንን ፖሊሲ ለማስፈጸም የሚቻልበት ሁኔታ ባለመኖሩ ያለው አማራጭ ፖሊሲውን ትቶ በፖሊስ ይቆጣጠረዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ነገሮች ሲረጋጉ ወይም አሁን አገር ካለችበት ችግር የምትወጣ ከሆነ፣ የውጭ ምንዛሪ ዋጋን በገበያ ዋጋ ለመወሰን የሚያስችል አቅም አለ? አሁንስ የውጭ ምንዛሪ ዋጋን በገበያ ዋጋ እንዲወሰን ማድረግ ይቻላል?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- አሁን ኢኮኖሚያችንን በገበያ እንዲመራ አቅም መፍጠር እንችላለን ወይ ለሚለው፣ የተቋማትና የቁጥጥር ሥርዓት መገንባት ሒደት አሁን ደርሰናል ወይም አልደረስንም የሚባልበት አይደለም፡፡ ያን ሲስተም እያስተካከሉ፣ እያሻሻሉ፣ ለአገር በሚጠቅም መንገድ እየለወጡና እያዳበሩ መምጣት ነው እንጂ፣ የሆነ ቦታ እስክንደርስ ምንም ነገር ማድረግ የለብንም በሚለው አላምንም፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ዋጋን በገበያ እንዲመራ አሁን መጀመሩ ያዋጣል እያሉኝ ነው?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- አዎ ስንጀምረው ዝቅ አድርገን እንጀምራለን፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የሚመጡትን ችግሮች እያየን፣ እያስተካከልን፣ ተቋሞቻችንን እየገነባን፣ የቁጥጥር አቅማችንን እያሳደግን፣ ተጨማሪ እየከፈትን በሒደት ወደ የሚፈለገው ግብ መድረስ ይቻላል፡፡ ይህንን ሥራ እኮ ጀምረነው ነበር፣ አቆምነው እንጂ፡፡ ብዙ ነገሮችን በገበያ ዋጋ እንዲጓዙ የማድረግ ሥራ ጀምረን ነበር፡፡ ነገር ግን ጦርነት፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝና የመሳሰሉት ችግሮች መጥተውብን ነው የቆሙት፡፡ ስለዚህ ሥራውን እየሠራ በሒደት ራሱን እያሻሻለ፣ እያሻሻለ መሄድ ይቻላል፡፡ ፍፁም ሆኖ የሚጀመር ነገር አይኖርም፡፡ የትም አገር ኖሮ አያውቅም፡፡ ሁሉም አገር የፖሊሲ ክፍተቶችን በጥናት እየሞላ፣ እያስተካከለ፣ ለግብረ መልስ መንገድ ፈጥሮ፣ በእነዚያ ግብረ መልሶች መሠረት ቶሎ ቶሎ የሚስተካከሉበትን ነገር እየፈጠረ መሄድ እንጂ ፍፁም ሆኖ የሚጀምር ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ባለው አቅም መጀመር ተገቢ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለኢኮኖሚው ሲወሳ በዚህ ወቅት ትልቁ የአገር ችግር እየሆነ የመጣው የዋጋ ንረት ነው፡፡ የዋጋ ንረቱን ለማስተካከል ተብሎ በርካታ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ቢባልም፣ ተደጋጋሚ ሙከራዎቹ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም፡፡ ምክንያቱ ምንድነው? ከዚህ በኋላስ ምንድነው መደረግ ያለበት?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- የዋጋ ንረት ብዙ የተባለበት ጉዳይ ነው፣ ጥናትም አካሂደናል፡፡ ሁለቱንም ገጽ የሚያይ ጥናት ተደርጓል፡፡ የዋጋ ንረቱን የሚያመጡ የኢኮኖሚ መነሻቸው ምንድናቸው? ለዋጋ ንረቱ ዋነኛ መንስዔው የምግብ ዋጋ ስለሆነ፣ በዚህ ላይ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጀምሮ የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ እኔ የምሠራበት ድርጅት ሁሉ የዋጋ ንረቱ ላይ ጥናት አድርጓል፡፡ ስለዚህ የጥናትና የመረጃ ችግር የለም፡፡ መረጃው የሚለው የገንዘብ ልቀት የዋጋ ንረትን በዋነኝነት የሚያመጣ ነው፡፡ የምግብ ዋጋዎችን ስንመለከት ደግሞ፣ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ከሚመረትበት ቦታ ገበያ እስኪደርስ ድረስ ካለው ሒደት ጋር የሚያያዝ ነገርም አለው፡፡ እስካሁን ከ17 እስከ 20 በመቶ የሚሆነው ነው ወደ ገበያ የሚመጣው፡፡ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው እዚያው ገበሬው ራሱ ነው የሚጠቀምበት፡፡ ስለዚህ ምርቱ ቢጨምርም አብዛኛው ወደ ገበያ እየመጣ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ይህ ራሱ ብዙ ጊዜ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው በምትለቅበት ጊዜ ሰው ወደ ከተማ መጥቶ መኖር በሚጀምርበት ጊዜ፣ ምግብ ላይ ያለውን የፍላጎት ጫናን እየጨመረ ነው የሚመጣው፡፡ ይህ ሲሆን ወደ ገበያ የሚመጣው ምርት መጠን ተመሳሳይ ከሆነ፣ መዋቅራዊ የሆነ የዋጋ ንረትን የሚመጣ አካሄድ አለ ማለት ነው፡፡ ይህ በምርታማነት ነው መፍትሔ የሚያገኘው፡፡ በአንድ ምሽት ልትቀርፈው አትችልም፡፡ ሁለተኛው ነገር ድሮ በገንዘብ መንስዔ የሚመጣውን የዋጋ ንረት ሁሉንም ክልል ነው የሚነካው፡፡ ስለዚሀ የሁሉም ክልሎች የምግብ ዋጋን ከፍ ያደርጋል፡፡ አሁን ግን ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ጂኦግራፊውን ስንመለከት ከአንዱ ቦታ ያለው የዋጋ ንረት፣ ከሌላው ቦታ የተለያየ ነው፡፡ ልዩነቱም እየሰፋ መጥቷል፡፡ ይህ የሚያሳየን ጆኦግራፊካዊ ጉዳዮች አሉ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጂኦግራፊያዊ የሆነ የዋጋ ንረት ሲባል ምን ማለት ነው?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- የአቅርቦት (ሰፕላይ) መቆራረጥ ነው፡፡  በዚህ ረገድ ያጠናነው ነገር አለ፡፡ ግጭት በሚኖርበት ጊዜ የሚከሰት ነው፡፡ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የነበሩ ግጭቶችን አጥንተናቸዋል፡፡ ግጭቱ ባሉበት ጊዜ ወደ መሀል የሚመጣው የአቅርቦት መቆራረጥ ሰንሰለቱ ይረበሻል፡፡ ሲረበሽ ዋጋዎች ይጨምራሉ፡፡ ስለዚህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከገንዘብ ልቀት በተጨማሪ አገራችን ውስጥ ያሉ ግጭቶች ራሳቸውን የቻሉ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩህ በአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርሙ መሠረት የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ብዙ ገንዘብ እንዳይለቀቅ ተደርጎ ነበር፡፡ መሻሻልም መጥቶ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በኮቪድና በጦርነቱ ምክንያት የገንዘብ ልቀቱ ጨምሯል፡፡ ይህም አንድ ምክንያት ነው፡፡ መንግሥት አሁን ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረው የገንዘብ መጠን ጨምሯል፡፡ እ.ኤ.ኡ በጁን 2022 ተጠረቃቅሞ ወደ 160 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ ቀላል የሚባል ገንዘብ አይደለም፡፡  

ሪፖርተር፡- የአገራችንን ወቅታዊ ኢኮኖሚ ገጽታ ሲታይ በችግሮች ውስጥ የቆየ፣ አሁንም ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ ሙስና አለ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ፣ ሕገወጥነትና የመሳሰሉ ችግሮች አሉ፡፡ ከዚህ አዙሪት ለመውጣት እንደ አንድ ባለሙያ ምን ዓይነት መፍትሔ ያስፈልጋል ይላሉ? ሥጋትዎስ?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- የኢትዮጵያ ችግር ውስብሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለት ዋና ዋና ነገሮች ይታዩኛል፡፡ አንደኛው የፖለቲካ ችግሮችን መፍታት ነው፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ችግሮች ካልተፈቱ የኢኮኖሚው ችግር አይቀረፍም፡፡ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ የማንነት ጉዳዮችን በሙሉ መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ አንድ ችግር በተፈጠረ ቁጥር ኢኮኖሚውን የሚረብሽ ነገር መምጣቱ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ ነው የመጣው፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ግን እየተለወጠ ያለ ነገር አለ፡፡ ዘመናዊ እየሆነ ነው የመጣው፡፡ ከወለድ ነፃ ባንክ ተጠቃሚ እየጨመረ ነው፡፡ የአገልግሎት፣ የአምራችና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ድርሻቸው እየጨመረ ነው፡፡ ስለዚህ ኢኮኖሚያችንን የሚደናቅፍ ነገር እንዲቀንስ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ መንግሥት ተግቶ መሥራት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ካላደረገ ፖሊሲ አውጪዎች የፈለጉትን ነገር ቢያደርጉ ችግሩ አይቀርም፡፡ ሌላው መፍትሔ ተቋማት መገንባትና በአግባቡ እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡ ይህ የረዥም ጊዜ መፍትሔ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሪፎርሙ ላይ የተቀመጡ ነጥቦች በጣም ጥሩዎች ናቸው፡፡ ገበያዎች በትክክል እንዲሠሩ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ተቋማዊ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ እነዚህ ላይ በደንብ መሥራት መቻል አለብን፡፡ እኛን የሚያስቸግሩንን ማነቆዎች ተቋማት እንዲፈቱ ያደርጓቸዋል፡፡ ተቋማት ሲገነቡ መንግሥት ቢለዋወጥም ሥራውን እየሠራ የሚቀጥልበት ሥርዓት ስለሚጨምር፣ ይህ በዘላቂነት ነገሮችን እንድናስኬድ ያስችለናል፡፡ የተቋም ግንባታ የምንለው የመንግሥትን የማስፈጸም አቅም የተመለከቱ፣ በትምህርትና በብቃት ላይ የተመሠረቱ ሹመቶችን ጭምር ያካትታል፡፡ ሥር ያለውን ቢሮክራሲ በሚገባ እንዲወጣ የማድረግ ነገርም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ስንቀጥል ደግሞ ሪፎርሞቹን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መንግሥት በተቻለ መጠን ፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ ያለውን እጅ መሰብሰብ አለበት፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል፡፡ ነገሮችን ያረጋጋልናል፡፡ ደግሞም ሌላ አማራጭ የለም፡፡ መንግሥት በራሱ በጀት ነው ሊሠራ የሚችለው፡፡ ይህ ታስቦ ሊሠራበት ይገባል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ምሁራንም ሆኑ የሲቪል ማኅበረሰቦች በፖሊሲ ቀረፃና መሰል እንቅስቃሴዎች ለመንግሥት ያስፈልጋሉ›› አድማሱ ገበየሁ (ፕሮፌሰር)፣ የቀድሞ ፖለቲከኛና የውኃ ሀብት ተመራማሪ

በምርጫ 97 ጊዜ በእጅጉ ከሚታውሱት ውስጥ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የነበረው ሚና ሲሆን፣ በጊዜው የታሪክ አሻራ አኑሮ ያለፈ ስብስብ ነበር፡፡ ቅንጅትን ከመሠረቱት አራት የፖለቲካ ድርጅቶች...

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...