Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገት‹‹ዳኛውም ዝንጀሮ ፍርድ ቤቱም ገደል እምን ላይ ተቁሞ ይነገራል በደል››!

‹‹ዳኛውም ዝንጀሮ ፍርድ ቤቱም ገደል እምን ላይ ተቁሞ ይነገራል በደል››!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ይህ ዓለም ዳኛም፣ የሚዳኝበትም ሕግ የሌለው የጉልበተኞች ዓለም ሆኖ አርፏል፡፡ በዚህ በጉልበተኞችና በጡንቸኞች ዓለም ውስጥ ደሃና አቅመ ቢስ ሆኖ በክብር መኖር አይቻልም፡፡ የሉዓላዊነት መከበርና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የሚሠራው ለፈርጣሞች፣ እንዲሁም ቀዳዳ የሚያስገባ የውስጥ ሰላም ላጎለበቱ፣ ማጎልበት ለቻሉ ወይም ለተሳካላቸው አገሮች ብቻ ነው፡፡ ለዚያውም በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥ፡፡ ይህ እውነት ለኢትዮጵያ እንግዳ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ እውነት እንግዳ አይደለችም ማለት ያው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ በውጭ አፈና፣ በጣልቃ ገብነትና ወረራ የተሞላ ነው፡፡

የትናንትም ሆነ የዛሬ ጣልቃ ገብነቶች፣ ወረራዎችና አፈናዎች ዓላማቸው በመሠረቱ ያው ነው፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጥቅም ማሳና ሎሌ ማድረግ ነው፡፡ በቀድሞ ጊዜ ጣልቃ ለመግባት ቀርቶ መውጪያና መግቢያ በርን ለመያዝም ሆነ፣ አገርን ወርሮ ለመጋጥ ሰበብ መደርደር አስፈላጊ አልነበረም፡፡ የቀጥታ የቅኝ ገዥነት ዘመን አልፎ የአገሮችን ሉዓላዊነት ‹‹የማክበርና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለ መግባት›› ወግ ከመጣ ወዲህ ግን የመግቢያ ሰበቦቹ ዝርዝር ብዙ ናቸው፡፡ የጋራ ደኅንነት ቃል ኪዳን አለን፣ ሕጋዊው መንግሥት ዕርዳታ ጠየቀኝ፣ ሕገ መንግሥታዊው መንግሥት በሕገወጥ መንገድ ተገለበጠ፣ የዜጎች ደኅንነት አሳሰበኝና የመሳሰሉት ተራና ቀላሎቹ ማሳሰቢያዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ከፍ ያሉና ከበድ ያሉ በርኅራኄና በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረቱ የሚመስሉ ማመካኛ ሰበቦች አሉ፡፡ የአካባቢና የዓለም ሰላም፣ የሰው ልጅ ደኅንነት መብት አሳስቦኛል ማለትን የመሰለ ሰበብና ማመካኛም አለ፡፡ በሰው ልጆች ላይ መፈጸም የማይገባ ግፍ ተፈጸመ፣ ረሃብ የፖለቲካ መሣሪያ ሆነ፣ ንፁኃን የጦርነት ጋሻ ተደረጉ፣ የዘር ጭፍጨፋ ተካሄደ፣ የጦር ወንጀሎች ተፈጸሙ ባይ ኡኡታዎች ዝነኞቹ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከዋና ባለጉዳዮቹ መጠቀሚያ ሰበቦችና ማመካኛዎች ጋር እነዚህን ‹‹የሚደርሱ››፣ የሚፈጥሩ ከግለሰብ እስከ ኤንጂኦ፣ እስከ ዩኒቨርሲቲ፣ እስከ ቲንክ ታንክ ድረስ በመጠንና እንደ የደንበኛው ልክ በአቅም በአቅም የተዘጋጁ ‹‹አዝማሪ›› እና ‹‹አልቃሽ›› ቢጤ ሚና ጭምር የሚጫወቱ ቅጥር ጉዳይ አስፈጻሚዎች አሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1990 ኦክቶበር ወር ውስጥ ናይራ የተባለች የ15 ዓመት ታዳጊ የውሸት፣ የሐሰት ምስክርነት ፕሬዚዳንት ጆርጅ ኤች ደብሊው ቡሽን ከአናት ጨምሮ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የአሜሪካ የታወቁ የሕዝብ ግንኙነት ተቋማት፣ የኩዌት መንግሥትና አምባሳደሮቿ በመጠኑም ቢሆን የተዋረዱበት ‹‹የአትሮሲቲ ፕሮፓጋንዳ›› ምሳሌ ሆኖ በሰፊው የተወራ ቅሌት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. 2023 ሲገባ 20 ዓመት የሚሞላው ዋናው የኢራቅ ወረራም ከእነ ሙሉ ቅጥፈቱ፣ ውርደቱና ቅሌቱ ገና ያልተጋለጡ ብዙ ሸሮች፣ ቅጥፈቶችና በሕይወት ያሉ ወንጀለኞች ያሉበት ያልተዘጋ ፋይል ነው፡፡

በአንድ ጊዜ በአንድ ትውልድ ውስጥ የከፉና በገፍ ሕዝብ ያረገፉ ሁለት የዓለም ጦርነቶች የመሰከረው የ20ኛው ምዕተ ዓመት ፖለቲከኞች፣ ‹‹ተከታታይ ትውልዶችን ከዚህ ዓይነት የጦርነት መቅሰፍት ለማዳን…›› ብለው ቻርተር ጽፈውና አፅድቀው ያቋቋሙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሰብዓዊ መብቶች ዩኒቨርሳል ዲክላሬሽን ጋር ማለፊያ በሚባሉ መተዳደሪያዎች ቢጀምርም፣ እዚያም ተቋም ውስጥ ጦርነት መከላከል እንደተሳናቸው የየአገሮቹ ፍጥርጥር የሰው አገዛዝ በሕግ አገዛዝ ባለመተካቱ ተመድም የአምባገነኖች የአድራጊ ፈጣሪዎች መጫወቻ ከመሆን፣ የእነሱን ጥቅም ከማስጠበቅ አላመጠለም፡፡ አሜሪካ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ አሸናፊ ሆና የወጣችው በዓለም ከየትኛውም አገር፣ በታሪክም ከየትኛውም ጊዜ ጋር የማይወዳደር ግዙፍ ጥንካሬ፣ ጉልበትና ሀብት ይዛ በመሆኑ፣ በተመድ መቋቋም አማካይነት የተመሠረተው የዓለም ሥርዓት አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ከመሆን የሚያመልጥ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በተለይም የቀዝቃዛው ጦርነት ፍፃሜ ማግኘት፣ የሁለቱ ጀርመኖች መዋሀድ ‹‹Unipolar Era›› የሚባለውን የአንድ ወገን ብቻ የጉልበተኛነት ዘመን ‹‹መረቀ››፡፡ የሶቪየት ኅብረት መፍረስ በዚህም ምክንያት የምዕራቡ ዓለም የቀዝቃዛውን ጦርነት አሸንፎ ወጣ ማለት፣ አሸናፊው የዕድገትና የራዕይ አቅጣጫውንና ሞዴሉን በሌላው የተቀረው ዓለም ላይ የመጫን ልዩ ‹‹ፀጋ››፣ ልዩ መብትና ጉልበት አጎናፀፈው ተባለ፡፡ አሜሪካ ውስጥም በቃ፣ ከዚህ ከሊበራል ዴሞክራሲ ውጪ ሌላ ዓለም የለም ተባለ፣ ‹‹The End of History›› ታወጀ፡፡

የአሜሪካን ጉልበትና ኃይል ከዚህ በላይ ጠቁመናል፡፡ ምዕራባዊውን ንፍቀ ክበብ እንዳለ የምትቆጣጠር፣ ሁለቱንም ውቅያኖሶች ማለትም አትላንቲክና ፓስፊክ ውቅያኖሶችን፣ ከእነዚህ ውቅያኖሶች ግራና ቀኝ ያሉትን ቦታዎች ሁሉ የምትቆጣጠር፣ በመላው ዓለም ከአንድ ሺሕ በላይ የጦር ሠፈሮች ያሏት፣ የመከላከያ ወጪዋና አቅሟ ከእሷ ቀጥሎ ያሉትን አገሮች ድምር የሚያስከነዳ ነው፡፡ ከዚህ ማዕዘን የአውሮፓን ቦታ መገመት አያዳግትም፡፡ ከአሜሪካ ጋር ኔቶን የመሠረቱት አውሮፓውያን ግን ለምንነጋገርበት የሥርዓት፣ የሕግ ገዥነት ሥርዓትን በማቋቋምና ተመድ ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያ ማገዝ ወይም የአሜሪካን አድራጊ ፈጣሪነት መቋቋም የቻለ ሆነው አልወጡም፡፡ በዚህ ምክንያት አንዳንዴም በጠቅላላ ጉባዔው ከሚሰጡት ድምፅ ጋር በማይጣጣም ሁኔታ፣ ከአሜሪካ ጋር አብረው ሲጓዙ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ የኩባንና የኢራንን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ከሚሰጥ ድምፅ አኳያ አውሮፓውያን በኩባ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ አይደግፉም፡፡ የኢራን ኑክሌር ስምምነት የሚባለውና በኢራን፣ እንዲሁም በአምስቱ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላትና በጀርመን ጭምር የተፈረመው እ.ኤ.አ. የ2015 ስምምነት ዋጋ ያጣውና ኢራንን ለዚህ ሁሉ የዳረገው፣ አሜሪካ ብቻዋን/ራሷ ብቻዋን ስምምነቱን ትታ በመውጣቷ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ሌሎች የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላትም፣ ጀርመንም በአሜሪካ ‹‹እፍርታምነት›› ላይ ለውጥ ማምጣት ያልቻሉ ምስኪንና ብኩን ዋጋ ቢስ ሆነዋል፡፡

ከአሜሪካ አንፃር አውሮፓ ይህን ያህል ከአሜሪካ ኃይልና ጉልበት የራቀች ምስኪን ብትሆንም፣ እሷም እንደ አቅሚቲ በጆሴፕ ቦሬል አማካይነት እንዴት እንደምትደነፋ ባለፈው የኦክቶበር 10 የሰውየው ዕብሪት አማካይነት ዓይተናል፣ ሰምተናል፡፡ አውሮፓ ጋርደን ሆና መገንባቷን የሰው ልጅ የፖለቲካ ነፃነትን፣ የኢኮኖሚ ብልፅግናንና ማኅበራዊ ትስስርን አዋህዶና አዋድዶ ሊደርስበት ይቻለዋል የሚባል የዕድገት ደረጃ ላይ ደርሶ አውሮፓን ጋርደን አድርጎ መፍጠሩን፣ የተቀረው ዓለም ‹‹አብዛኛው የተቀረው ዓለም›› ግን ጋርደን አለመሆኑን፣ ይልቁንም የተቀረው ዓለም፣ አብዛኛው የተቀረው ዓለም ጃንግል መሆኑን፣ ይህ የተቀረው ጃንግል የተባለው፣ እልም ያለው ጫካና ዱር የወረሰው፣ ደንቆሮው፣ ኋላቀሩ፣ አረመኔያዊው ዓለም ደግሞ  የአውሮፓን ጋርደን ሊወር እንደሚችል፣ የዚህ መከላከያውም አጥርና ግንብ መሥራት አለመሆኑን፣ የአትክልት ቦታ ባለቤቶች፣ አትክልተኞች ወደ እዚህ ጫካና ዱር መግባት፣ በትጋትና በንቃት መግባት ያለባቸው እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ይህ ከሌሎች መካከል፣ ከአሜሪካ አንፃር በጣም በረዥም ርቀት ወደኋላ የቀረችው፣ አሜሪካን ግን ኋልኋላ የምትከተለው የአውሮፓ ‹‹ጥጋብ›› መገለጫ ነው፡፡ በደራሲና ገጣሚ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን ቋንቋ ዛሬም በፋሽስታዊ ነቀርሳ የታረሰችው፣ የተማሰችው፣ የበሰበሰችው፣ አሁንም ሒትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን እንደ ኮረብታ የተጫናት የአውሮፓ ዕብሪት ማሳያ ነው፡፡

ጆሴፕ ቦሬል ይህንን ባሉ በሳምንቱ ቆበራቸውን የደፈቁበትን፣ ውስጣቸውና አውሮፓ ውስጥ ጭምር የሚተናነቃቸውን ሁሉ የለፈለፉበትን ያረሙ መስሏቸው ባለፈው ማክሰኞ ባደረጉት ትዊት፣ ‹‹ባለፈው ሳምንት በአውሮፓ ኮሌጅ ባደረጉት ንግግር የተጠቀምኩበት ሜታፎር ቅያሜ አምጥቷል፣ የዚህ ምክንያት ያላግባብ ተተርጉሜያለሁ፣ (ሚስአንደርስቱድ ሆኛለሁ)›› ብለው በቀጥታ፣ ‹‹Should the international order be based on rules, or ‹‹the law of the Jungle››? የሚለውን ‹‹ማረሚያ››ቸውን አስመዝግበዋል፡፡ ‹‹አልሸሹም ዞር አሉ›› ዓይነት እንኳን መሸፋፈኛና ማታለያ የለውም፡፡ የቱ ነው ‹‹Rules›› (ሕግና ደንብ)? የቱስ ነው ‹‹ሕገ አራዊት?››፡፡

ዓለም ብዙ ዕልቂት፣ ታይቶ የማይታወቅ ክፋት፣ ጥፋትና ፍዳ፣ እንዲሁም ከሁለት የዓለም ጦርነቶች በኋላ ለዚያውም ፋይዳ ቢስ የሆነውን፣ ከእጅ አይሻል ዶማ ሆኖ ያረፈውን፣ ማፈሪያም የሆነውን የሊግ ኦፍ ኔሽንስ ክስረትና ውርደት እያውለበለበ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን መሠረተ፡፡ ‹‹Rules›› ማለት ሕግና ደንብ ማለት፣ ‹‹የዓለም ማኅበር፣ የዓለም ማኅበር ለዘለዓለም ይኑር፣ ለሰላም ለፍቅር›› ብለን የዘመርንለት ድርጅት ሕግ ማለት ከሆነ፣ የዚህ ማኅበር ዋና ዋልታና ማገር የሚባሉ ሕጎች፣ ቻርተሩና የሰብዓዊ መብቶች ዩኒቨርሳል ዲክላሬሽን ናቸው፡፡ ሌላው ሁሉ ከእነሱ የተቀዳና የተወለደ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ በየፊናቸው የተመድን የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ሥርዓት ያቋቁማሉ፡፡ ለምሳሌ የተመድ ቻርተር የሚያቋቁመው ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ሥርዓት አንድና አንድ ብቻ መርህ አለው፡፡ አንድ መቶ አሥራ አንድ አንቀጾች ያሉት የዚህ ቻርተር ዋና ፍሬ ነገርና ቁምነገር ‹‹The threat or use of force›› (ማስፈራራትና ኃይል) መጠቀም ይከለክላል፣ ሕገወጥ ነው፡፡፡ ከሁለት ጠባብ ቀዳዳዎች በስተቀር ኃይል መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡ ሕገወጥ ነው ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ሥርዓት ባቋቋመው ሕግ፣ ፍትሕ፣ እንዲሁም የፍርድ ቤቱ ፍርድ መሠረት ከማንኛውም ወንጀል ሁሉ የከፋ (Supreme Crime) ወንጀል ነው፡፡ በኃይል ማስፈራራት ወይም ኃይል መጠቀም፣ በዚህ ሥርዓት ሕግ መሠረት የሚፈቅደው ሁሉም ሰላማዊ ዘዴዎች ተሟጠው አልቀው፣ የፀጥታው ምክር ቤት በውሳኔ ሲፈቅድና ሁለተኛው የቻርተሩ አንቀጽ 51 በሚፈቅደው መሠረት የፀጥታው ምክር ቤት እስኪገባ ድረስ ራስን መከላከል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሲሆን ነው፡፡

እና የዚህን ዓለም ‹‹The law of the Jungle›› ሕገ አራዊት ምንነት መነጋገር የሚቻልበት፣ የሚፈቀድበት ቦታና ሰሚ ቢገኝ በመንግሥታቱ ድርጅት ማኅበርነት ላይ የተመሠረተው ሕግ የሚለው፣ ማንኛውም አገር ብቻውንም ሆነ ከሌላው ጋር አብሮ በየትኛውም የሰብዓዊነትም ሆነ በሌላ ምክንያት ከ‹‹ሴኪዩሪቲ ካውንስሉ›› ፈቃድ ውጪ ኃይል የመጠቀም መብትም፣ ሥልጣንም የለውም፡፡

ሕጉ ይህ ነው፡፡ አተገባበሩም ግን የተለየ ነው፡፡ የሕጉ አስፈጻሚዎች ደግሞ ኃያላን አገሮች ናቸው፣ በተለይም አሜሪካ፡፡ ታላላቅና ኃያላን አገሮች ግን ያልነውንና የገለጽነውን ዋነኛ መርህ አያከብሩም፡፡ እንዲያውም ይጠቅሙናል ባሉ ጊዜ ሁሉ ውድቅ ያደርጉታል፡፡ በተለይ ዩኤስ አሜሪካ ይህን የቻርተሩን ዋነኛና አውራ መርህ የምትቃወመው፣ ውድቅ የምታደርገው በተግባርና ‹‹ይጠቅመኛል›› ስትል ብቻ ሳይሆን በመርህ ደረጃ ጭምር ነው፡፡ እና በዓለም ውስጥ፣ በተመድ ውስጥ፣ በፀጥታው ምክር ቤት ድምፅ መስጫ አዳራሽ ውስጥና ድምፅ በተሰጠበት፣ በተለይም የአሜሪካ የቬቶ ድምፅ በተመዘገበበት ታሪክ ውስጥ፣ የዓለም ማኅበር ሕግን አፈጻጸም የ‹‹ጤንነት›› ሁኔታ ማየት ይቻላል፡፡ ዓለም አቀፋዊው የፖለቲካ ሥርዓት በተግባር ብቻ አይደለም፣ የለም ሞቷል፡፡ ተመድ ለአንደበት ወግ ያህል፣ ለጌጥ ሲባል አለ የሚባለው የአሜሪካን ጥቅም እስካስጠበቀ ድረስ ብቻ ነው፡፡ እውነቱን እንናገር ከተባለና እውነት የሚነገርበትና የሚሰማበት ሁኔታ ካለ አሜሪካ እኮ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ጦርነት ላይ ነች፡፡ ከ1960ዎች ወዲህ ያሉትን የ‹‹ሴኪዩሪቲ ካውንስል›› ውስጥ የቬቶ ድምፅ ታሪክና ስታትስቲክስ የሚያሳየው አሜሪካ በቀዳሚነት እንደምትመራ፣ አጃቢና ተከታዮቿ በርቀት እንደሚከተሏት ነው፡፡ እና የቱ ነው ሕገ አራዊት? የቱ ነው ለሰው ልጆች ሰላም፣ ለሰው ልጆች ክብር የቆመው የመንግሥታቱ ድርጅት ሕግ? በየትኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ሕግና ፈቃድ መሠረት ነው የትኛውን ጦርነት የተዋጋችሁት ሲኞር ቦሌር?

ይህንን በመሰለ ብልሸት በገጠመው፣ ‹‹To save succeeding generation from the scourge of war, which twice in over life time has brought untold sorrow to mankind.›› ተብሎ ተቋቁሞ አሁን አሜሪካ የምትባል አድራጊ ፈጣሪ አገር፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ሆኖ ባረፈው ድርጅትና ሥርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን ነው የጆሴፕ ቦሬልንም፣ የአንቶንዮ ጉተሬስንም ቃል የምንሰማው? ከትንሽ እስከ ትልቅ ቆበሩን ሲደፍቅ የምንሰማው?

አንቶንዮ ጉተሬስ ዩኤስ አሜሪካ በሚፈቅደውና በሚያላውሰው ልክ እንኳን እውነት እውነቱን፣ እውነትን ሁሉ፣ እውነቱን ብቻ መናገር አልፈለጉም፡፡ ጥቅምት 7 ቀን ሰኞ ዕለት የሰጡት መግለጫ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊነት ሚና ራሱ በአሜሪካ ተላላኪነት ሥር እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ እየተምዘገዘገና ከቁጥጥር ውጪ እየወጣ ነው፡፡ ደመ ነውጠኛነትና ውድመት የሚያስደነግጥ ደረጃ ላይ ደርሷል፣ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ድርና ማግ ብጥስጥሱ እየወጣ ነው፣ ወዘተ የሚሉት መግለጫዎች ከእውነትና ከውሸትነታቸው ውጪ የተሰጡበት ጊዜ፣ የ‹‹አድራጊ ፈጣሪ››ዎችን የልብ ትርታ የደረሰበትንና የሚገኝበትን ሁኔታ የሚያረጋግጥ ጭምር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ፣ ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት ጉዳይ በአጠቃላይ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ አሁን ዛሬ (የጉተሬስ መግለጫ በሚሰጥበት ወቅት) መግለጫው የያዘውን መልክ፣ ይዘትና ‹‹ፍላጎት›› ያህል ለምን እንደተብሰለሰለ የሚያጠያይቅ ነው፡፡ ጉተሬስ በዚህ መግለጫቸው በጥያቄና መልስ ጊዜ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያው ግጭት ዓለም አቀፋዊ ገጽታም እንዳለው፣ ኤርትራውያን ኃይሎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ፣ ከሱዳን ጋር ባለው ድንበር በኩል አሳሳቢ ሁኔታ እንዳለ፣ ይህ ሁሉ ግን የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ በሁሉም አካላት ሊታይ ይገባዋል ይላሉ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ፣ ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ኤክስፐርቶች ኮሚሽን (ኢትዮጵያ) የሚባለው አካል አባላት፣ እንዲሁም ለምሳሌ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መደበኛ ሥራቸው ላይ ሆነው፣ መቀመጫቸውን ይዘው፣ ኤፊሴላዊ ሥራቸውን ሲሠሩም ሆነ በዚያው ሥራ ላይ እያሉ የግል ኑሯቸውን ሲኖሩ፣ ከማንም ተራ ዜጋ በላይ እጅግ በጣም የከበደ ለሙያው መታመንና የሙያው ኃላፊነት የሚጠይቀውን ባህርይ ሥነ ምግባርና ጨዋነት ማሟላትና ለዚህም መታመን አለባቸው፡፡ የግል ኑሮ የተከለከለ ያህል ጥብቅና እንደ ብረት የጠነከረ ዲሲፕሊን እንደሚጠይቅ በየአቅማችን፣ እንደ አቅሚቲ በምንከፍለው ‹‹መስዋዕትነት›› እንረዳለን፡፡ በተለይ በመደበኛው ሥራ ውስጥ የገለጽኳችው ዓይነት ሙያ፣ ቦታና ኃላፊነት ውስጥ ያሉ ኃላፊዎች ‹‹‹ሥርዓቱ›› ያበጀላቸው ውኃና ገንዳ ውስጥ ሲንቦጫረቁ፣ ክልላዊና የጎጥ ጉድጓድን ተሻግሮ ማሰብ እያቃታቸው እዚያ ውስጥ ሲፈራገጡና ሲንደባለሉ ማየት የዚህ ‹‹በሕግ ላይ የተመሠረተ›› ዓለም አሳፋሪና ማፈሪያ ትዕይንት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚነጋገሩበትን ጉዳይ፣ ይመለከተናል የሚሉትን ነገር የቀረቡትና የሚያውቁት ክፍት በሆነ አዕምሮ፣ ገለልተኛ በሆነ ስሜት ነው ወይ? ለሙያና ለኃላፊነት መታመን መጀመርያ የሚጠይቀው ሥነ ምግባር ይህ ነው፡፡ የምልከታና የማሰብ ሚዛናቸውን እየታገለ ከሚያስቸግራቸው ‹‹የግል›› ችግር ጋር ራሳቸው ውጊያና ጦርነት ውስጥ ሆነው በሌላ ችግር ላይ መፍትሔ ሊያመጡ አይችሉም፡፡

በተለይ በተለይማ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ‹‹ባሉ ጉዳይ›› ነው፡፡ የራሱ የዓለም የጤና ድርጅት በሚያውቀውና ይፋ አድርጎ በመዘገበው ሲቪ (CV) መሠረት ብቻ የአንዱ ተፋላሚ ወገን አባል ነው፡፡ ወይም በአንድ ወቅት ነበር፡፡ ብዙ ከዚህ ውጪ ያሉ ተመጋጋቢ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩትም የሕወሓት ጉዳይ ጉዳዩ ነው፡፡ ኦፊሺያል ንግግሮቹ፣ የትዊተርና የፌስቡክ ገጾቹ ሁሉ ይህንኑ ያስረዳሉ፡፡ በአጠቃላይ የአንዱ ወዳጅ/ደጋፊ፣ የሌላው ባላጋራ ነው፡፡ ይህን የመሰለ ባላጋራነትና የተጣመደ ግንኙነት ውስጥ ደግሞ አድሏዊ ያልሆነ፣ ሚዛዊና ትክክኛ አተያይና አመለካከት አያገኝም፡፡ የባላጋራነት ፈርጅ የያዙ ሰዎች፣ እዚያ ፈርጅ ውስጥ የገቡና ገብተው የተቀረቀሩ ሰዎች በሚዲያም፣ በዓለም አቀፋዊ ሲቪል ሰርቪስ የሚሠሩ ሰዎችን ጨምሮ ሌለው ቢቀር ባላጋራዬ ነው የሚሉትን ወገን የሚጠቅም፣ ወገኔ ያሉትን ደግሞ የሚጎዳ እውነትና መረጃ ከመሸፈጥ አይመለሱም፡፡ የእነዚህ ዓይነት ሰዎች ጉዳይ የሚከነክነን በዚህ ምክንያት ጭምር ነው፡፡

የአውሮፓው ጆሴፕ ቦሬል የሚናገርለት የአውሮፓ (አትክልት ቦታ) ጋርደንነትና የተቀረው አብዛኛው ዓለም ጃንግልነት ምሳሌ ማስተካከያ ዕርምት ከተደረገበት ጉዳይ ጋር ግንኙነትም አንድነትም ባይኖረውም፣ ሊያሳምኑን እንደሚሹት ‹‹ኢንተርናሽናል ኦርደሩ›› በሕግ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋልታና ማገር የሆኑት ስምምነቶችና ሕጎች (ቻርተሩና UDHR) አሜሪካ በፈቀደችውና በወደደችው ልክ ብቻ የሚተገበር፣ አለበዚያም የሚረጋጥ (ተረግጦ የሚጣል) ሆኗል፡፡ ይህንን ዕውን ያደረገው ደግሞ የአሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነትና የአውሮፓ አጎብዳጅነት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...